Monday, 06 October 2014 07:31

በቦሌ በሰዓት ለ1ሺ ሰዎች የኢቦላ ቫይረስ ምርመራ እየተደረገ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

                   በቦሌ አየር ማረፊያ በሰዓት ለ1ሺ ሰዎች የኢቦላ ቫይረስ ምርመራ ማድረግ የሚያስችል መሳሪያ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በስራ ላይ ማዋሉን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የገለፀ ሲሆን ከምዕራብ አፍሪካ የሚመጡ ሰዎች በያረፉበት ሆቴል ለ21 ቀናት ክትትል ይደረግላቸዋል ተብሏል፡፡በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የኢቦላ መከላከል ኮሚቴ ትናንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ቫይረሱ በአለማቀፍ ተጓዦች አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ በ8 የድንበር ኬላዎች ላይ የሚደረግ ምርመራን ጨምሮ እንግዶች በስፋት ያርፉባቸዋል ከተባሉ 130 ሆቴሎች ጋር በመተባበር በየጊዜው ምርመራ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡
 በቦሌ አየር ማረፊያ ለእንግዶች የሚደረገውን የኢቦላ ቫይረስ ምርመራ የተቀላጠፈ ለማድረግም በሰዓት ለ1ሺህ ሰዎች የኢቦላ ቫይረስ ምርመራ ለማድረግ የሚያስችል ዘመናዊ መሳሪያ ተገዝቶ ሰሞኑን አገልግሎት እንደጀመረ ታውቋል፡፡
የኢቦላ ምልክት የታየባቸውን ሰዎች ለማከም ታስቦ በተዘጋጀው የኮተቤ አዲሱ ሆስፒታል እስከዛሬ ህክምና የተደረገለት ተጠርጣሪ አለመኖሩንም ኮሚቴው አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል በምዕራብ አፍሪካ የኢቦላ ቫይረስ ስርጭት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መሆኑን የጠቆመው የአሜሪካ የበሽታ ቁጥጥር ማዕከል (CDC)፤ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ድጋፍ ካልታከለበት እስከ መጪው ጥር ወር ድረስ በቫይረሱ የሚያዘው ሰው ብዛት 1.4ሚ ሊደርስ እንደሚችል አስታውቋል፡
ከአንድ ወር በፊት ከላይቤሪያ ወደ አሜሪካ ዳላስ የገባ የ45 ዓመት ላይቤሪያዊ፣ ሰሞኑን በኢቦላ ቫይረስ መያዙ የተረጋገጠ ሲሆን ጉዳዩ በአሜሪካ ስጋት ፈጥሯል፡፡ ከግለሰቡ ጋር ንክኪ የነበራቸው 4 ሰዎችም ለብቻቸው ተገልለው ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነ ተዘግቧል፡፡
 ቶማስ ኤሪክ ዱንካን የተባለው ይሄው ላይቤሪያዊ፤ ከወር በፊት በላይቤርያ በቫይረሱ ለተያዘች ነፍሰጡር የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጥ በኢቦላ ሳይያዝ እንዳልቀረ ኒውዮርክ ታይምስ ግለሰቡን ጠቅሶ የዘገበ ሲሆን ነፍሰጡሯ ከጥቂት ቀናት በኋላ ህይወቷ እንዳለፈ ታውቋል፡፡
 ግለሰቡ የበሽታው ምልክት እስኪታይበት ድረስ 5 ህፃናትን ጨምሮ ከ18 ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪ እንደነበረው የዘገበው ኒውዮርክ ታይምስ፤ ልጆቹ ከትምህርት ቤት ቀርተው ምልክቱ እስኪታይባቸው ድረስ ለብቻቸው ተገልለው ክትትል እየተደረገባቸው እንደሆነ ጠቁሟል፡፡
በቫይረሱ የተያዘው ላይቤሪያዊ በአሁኑ ሰዓት በዳላስ ፕሮኪባይቴሪያን ሆስፒታል የህክምና ክትትል እየተደረገለት እንደሆነ ታውቋል፡፡
ዘ ሰን ትናንት እንደዘገበው፣ በዳላስ የኢቦላ ቫይረስ ከተገኘበት ግለሰብ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ንክኪ የነበራቸውን ሌሎች ሰዎች የመፈለግ ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በላይቤሪያ የሚገኘው የኤንቢሲ ቴሌቪዥን ጣቢያ አሜሪካዊ የካሜራ ባለሙያም፣ በኢቦላ መያዙን የጠቆመው ዘገባው፤ ግለሰቡ ለህክምና ወደ አሜሪካ ሊወሰድ እንደሆነና ሌሎች የስራ ባልደረቦቹም በአፋጣኝ ወደ አሜሪካ ሄደው ለ21 ቀናት ያህል በጥብቅ የህክምና ማዕከል እንደሚቆዩ ገልጿል፡፡ የካሜራ ባለሙያውን ጨምሮ በቫይረሱ የተያዙ አሜሪካውያን ቁጥር አምስት እንደደረሰ ዘ ሰን ዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ከኢቦላ ጋር በተያያዘ ከዳላሱ ከንቲባ ማይክ ሮውሊንግስ ጋር ሰሞኑን ውይይት ያደረጉ ሲሆን፣ ቫይረሱ ወደሌሎች ሰዎች እንዳይሰራጭ የአገሪቱ መንግስት ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል፡፡
የኢቦላ ቫይረስ በምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የ3338 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ሲሆን ከ3ሺህ በላይ የሚሆኑ ህፃናትንም ወላጅ አልባ አድርጓል፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት፤ እስካሁን የኢቦላ ቫይረስ ከምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ውጭ ወደ ሌላው የአፍሪካ ክፍል አለመዛመቱን አስታውቋል፡፡   

Read 2106 times