Monday, 06 October 2014 07:27

ተቋምና ጊዜያዊ ችግርን እንለይ! ደመነፍሳዊነት ተቋማችንን አይገልፀውም! Featured

Written by  ሠይፈ ደርቤ (ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)
Rate this item
(0 votes)

       ሀሳብን በነፃ የመግለፅ ህገመንግስታዊ መብቴን ተጠቅሜ፣ ይህን የግል አስተያየቴን ለመላክ የተገደድኩት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞችን በሚመለከት ያወጣችሁትን የዜና ዘገባ መነሻ በማድረግ ነው። በዚህ አጋጣሚ ለጋዜጣችሁ የዜና ሽፋን መረጃ የሰጧችሁ ግለሰቦች እንደ ሰው ሀሳብን በነፃ የመግለፅ መብት ያላቸው በመሆኑ የሰጡትን ሀሳብ የማከብር ሲሆን እናንተም ጉዳዩን የጋዜጣችሁ አጀንዳ ማድረጋችሁ የመፃፍ መብታችሁ አንድ አካል አድርጌ እንደምቆጥርና አስተያየቴ የሚያተኩረው ማን ምን አለ የሚለው ላይ እንዳልሆነ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ። ወደ ዜናው ሽፋን ስመጣ፣ የዘገባችሁ ትኩረት እውነታን በገለልተኝነት ከማሳወቅ ይልቅ በተጋነነ ሁኔታ ተቋሙን በማብጠልጠልና አጠቃላይ ገፅታውን በማጠልሸት፣ ሰራተኛው በተቋሙና በመንግስት ላይ ጥርጣሬ እንዲያሳድር የሚያደርግ መሆኑን ልገልፅ እወዳለሁ፡፡
በተቋማችን ከመልካም አስተዳደር ችግር ጋር ተያይዞ ሰራተኛው በሀምሌ ወር 2006 ዓ.ም የመጀመሪያ ሳምንት ላይ ከተቋሙ ማኔጅመንት ጋር በግልፅ መድረክ ተወያይቷል፤ አሉ የተባሉ የአሰራር ችግሮችንም ፊትለፊትና ዴሞክራሲያዊ በሆነ አግባብ ገልጿል፤ ችግሮቹ እንዲፈቱም ጠይቋል። ማኔጅመንቱም ችግሮቹ እንደሚፈቱ ገልፆ፣ ያስተካከላቸው አሰራሮች ያሉ ቢሆንም እስካሁንም ያላስተካከላቸው ነገር ግን መስተካከል ያለባቸው ሌሎች ጉዳዮች እንዳሉ በግሌ አምናለሁ።  በዚህ አጋጣሚ ጋዜጠኛው ሀሳቡን በነፃነትና በግልፅ በማቅረብ፣ ችግር ያለበትንም ችግር አለብህ ብሎ ከመንገር ወደ ኋላ የማይል መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ይህ ሲባል ጋዜጠኛው ኃላፊነት በማይሰማው መልኩ ተቋሙንና ጊዜያዊ ችግሮችን ለይቶ የማያይ የዋህ ነው ማለት አይደለም። በተለይ ሙያዊ ተልዕኮውን በመወጣት፣ በሀገሪቱ የልማትና ዴሞክራሲ እንዲሁም የህዝብ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ጉዳይ ላይ ያለ ምንም ተጽዕኖ ሀሳቡን በድርጅቱ ህትመቶችና መፅሄት እንደሚገልጸው ሁሉ፣ ከራሱም አንፃር በሚፈጠሩ የአሰራር ችግሮች ሀሳቡን በነፃ የመግለፅ መብቱን ለድርድር እንደማያቀርብ ራሱ ጋዜጠኛው ምስክር ነው።
ጋዜጠኛው በራሱ ላይ የሚደርስ የመልካም አስተዳደር ችግርን አሜን ብሎ የማይቀበል፣ በመንግስትና ህዝብ ግንኙነት ባሉ አሰራሮች የሚከሰቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንም ገንቢ በሆነ መልኩ በግልፅ የሚተች እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ጋዜጠኛው የመልካም አስተዳደር ችግርን አሜን ብሎ የተቀበለና የተሸነፈ፣ በራሱ ተስፋ ቆርጦ ከሌላ አካል መፍትሄ የሚፈልግ ጠባቂ፣ በመንግስትም ፈፅሞ የተረሳ በማስመሰል «የፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞች በመልካም አስተዳደር እጦት ተማረናል አሉ» ብሎ በጥቂት የሀሳብ መነሻዎች ሙሉ ሰራተኛውን ወካይ የሚመስል ግርድፍ ዘገባ መቅረቡ፣ የተቋሙን ሰራተኛ አሳንሶ እንደማየትና እንደ መስደብ እንዲሁም በሙያ አጋር ላይ እንደተሰነዘረ ጥቃት አድርጌ እቆጥረዋለሁ። የዘገባው መንፈስ ይሄ ነገር ለእውነት ከመቆርቆር የተሰራ ይሆን? የሚል ጥያቄም አጭሮብኛል።
በተቋማችን የመልካም አስተዳደር ችግር ያጋጠማቸው አንዳንድ ሰራተኞች እንዳሉ ባውቅም፣ አጠቃላይ ፍረጃው የዘገባውን ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል፡፡ ለመልካም አስተዳደር መስፈን ሌት ተቀን የሚሰሩ ጋዜጠኞችንም ሞራል የሚነካና ጤነኛና ገለልተኛ ያልሆነ ዘገባ ነው ብዬ አምናለሁ። በተለይ ጋዜጠኛውን የሚወክለው ትልቅ ኃላፊነት የተጣለበት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በጋዜጣው እንደተጠቀሰው የሚያሳትማቸው አራት ጋዜጦችና በዘገባው ያልተጠቀሰው አንድ መፅሄትም የየራሳቸው መሪዎች ያሏቸው፣ በስራዎቻቸው የተሰጣቸውን ኃላፊነት ሙያው በሚፈቅደው አግባብ እየተወጡ መሆኑ እየታወቀ፣ ፕሬስ ድርጅት በአንድ ግለሰብ  ብቻ እንደሚመራና አመራሩም ደመነፍሳዊ አካሄድ እንደሚከተል ተደርጎ የቀረበው ጥቅል ፍረጃ ሚዛናዊ ነው ተብሎ ሊታመን የማይችል ነው።
በደመነፍስ ይመራል ሲባል፣ መሪው ብቻ ሳይሆን ተመሪውም የደመነፍስ አመራር ውጤት ነው ብሎ ከመግለፅ የተለየ አይደለም። ሀሳብን በነፃ የመግለፅ መብታቸውን ተጠቅመው አስተያየት የሰጡ የተወሰኑ ሰዎችን ሀሳብ ብቻ ይዞ አጠቃላይ የተቋም ውክልናን በመስጠት፣ ተቋሙ በደመ ነፍስ የሚመራ ነው ተብሏል ብሎ ማቅረብ፣ በደመነፍስ አንመራም የሚል ምላሽንም እንደ ሚዛናዊ አቀራረብ መጠቀም በራሱ ደመነፍሳዊና ሚዛናዊነትን ያልተከተለ፣ ጋዜጠኝነት የሚያስፈልገውን ሙያዊ ጥንቃቄ የዘነጋ ወገንተኛ አሰራር በመሆኑ መታረም ይኖርበታል እላለሁ። ይህ ስያሜ በተቋሙ የሚሰራውን ሰራተኛ (አጠቃላዩንም ጋዜጠኛ ጭምር) ሞራል የሚነካ፣ ጋዜጠኛውን እንደ ተላላኪ የሚቆጥር፣ ተቋሙ የተጣለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት የሚያደርገውን ጥረትም አሳንሶና አንኳሶ የሚያይ፣ ሙያዊ ኃላፊነትን የዘነጋ የዘገባ አሰራር በመሆኑ ጋዜጣው ራቅ አድርጎ ቢያይ የተገባ ነበር ብዬም አምናለሁ።
ተቋሙ መንግስት የዘነጋው ተደርጎ መቅረቡን በተመለከተ በስሜትና ባለመረዳት የተገለፀ ነው ብዬ አስባለሁ። ጋዜጠኛው ከመሰል ተቋማት አንፃር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ በግል ባምንም፣ ተቋሙ በአደረጃጀቱም ሆነ ባህሪያዊ በሆነ መልኩ የራሱ ዓላማ ያለው በመሆኑ፣ በገቢ አቅምና መሰል በሆኑ ጉዳዮች ከሌሎች ጋር አላግባብና በተለጠጠ ሁኔታ እየተነፃፀረ መቅረቡ፣ ከዜናው ማዕከላዊ ነጥብና ፍላጎት ጋር የማይጣጣም፣ ሚዛናዊ አወዳዳሪ ሳይሆን ነጣጣይ፣ በተቋሙም ላይ ጫና የሚፈጥር ነው ብዬ እረዳለሁ። ይልቁንም ይህ አይነቱ አካሄድ ሰራተኛው ራሱን ዝቅ እንዲያደርግ፣ አልፈለግም ተረስቻለሁ ብሎ እንዲያስብ በሚያደርግ አግባብ የቀረበ በመሆኑ፣ የማይገነባና ለማንም የማይጠቅም ይመስለኛል፡፡ በነገራችን ላይ እንደ ሙያ ጓደኛ፣ ጋዜጠኛው በዚህ መሰሉ አተያይ ተስፋ የማይቆርጥ፣ በቀላሉ የሚፈቱ የዛሬ ችግሮችን ከተቋሙ ዓላማና ተልዕኮ እንዲሁም የነገ ራዕይ ጋር ቀይጦ የማያይ በመሆኑ፣ ከሙያዊ ኃላፊነቱ ይዘናጋል ብዬ አላስብም።
ከአዘጋጁ፡- ከላይ የቀረበው ፅሁፍ አንባቢ የፀሃፊውን ሃሳብና ስሜት በቅጡ ያገኘው ዘንድ ያለ ብዙ የአርትኦት ስራ (እንደወረደ በሚባል መልኩ) ማውጣታችንን ልንገልፅ እንወዳለን፡፡ ባለፈው ሳምንት “የፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞች በመልካም አስተዳደር እጦት ተማረናል አሉ” በሚል የወጣው ዘገባ፣ በፕሬስ ድርጅቱ ስር በሚታተሙ የተለያዩ ጋዜጦች ላይ ከሚሰሩ ጋዜጠኞች የተገኘን መረጃ መሰረት ያደረገና ድርጅቱን የሚመሩ ኃላፊዎች በጉዳዩ ላይ የሰጡትን ምላሽ ያካተተ እንደሆነ የሚታወስ ነው፡፡
በዚህ የዜና ዘገባ፣ የፕሬስ ድርጅቱን ጋዜጠኞች ሃሳብ ከማንጸባረቅ ውጭ ወደ ማጠቃለልና አቋም ወደ መያዝ እንዳልገባን  ዜናውን ያነበበ ሁሉ የሚገነዘበው ነው፡፡ በሁሉም ዘገባዎቻችን እንደምናደርገው ሁሉ፣ የዜናውን ሚዛናዊነት በተቻለ መጠን ለመጠበቅም ሞክረናል ብለን እናምናለን፡፡
 ዓላማችን እውነተኛ፣ ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃ ለህብረተሰቡ ማድረስ ነው!!

Read 1466 times