Monday, 06 October 2014 07:21

የታሰሩት የፓርቲ አባላት ጠበቃ ፍ/ቤት እንደማይገኙ አስታወቁ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

ሶስት ፓርቲዎች በታሰሩ አባሎቻቸውና በጠበቃው ላይ የሚፈፀመው ህገወጥ ድርጊት አወገዙ

ጠበቃና የህግ አማካሪ ተማም አባቡልጉ ከሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ ክስ ሳይመሰረትባቸው በጊዜ ቀጠሮ ፍ/ቤት ለሚመላለሱት የአንድነት፣ የሰማያዊና የአረና አመራሮች የሆኑ ደንበኞቻቸው ላይ ህገ ወጥ ምርመራ እየተደረገባቸውና በአግባቡ ሊገናኙ ባለመቻላቸው፣ ከዚህ በኋላ ለጊዜ ቀጠሮ ወደ ፍ/ቤትና ወደ ማዕከላዊ ሄደው ደንበኞቻቸውን እንደማያገኙ ለፓርቲው በፃፉት ደብዳቤ አስታወቁ፡፡ ሶስቱ ፓርቲዎች በበኩላቸው፤ በአመራሮቻቸውና በጠበቃው ላይ ፍ/ቤትና ማረሚያ ቤቶች እያደረሱ ነው ያሉትን ኢ-ህገ መንግስታዊ ድርጊት አውግዘዋል፡፡
የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኑነት ኃላፊ አቶ ሃብታሙ አያሌው፣ የአንድነት ምክትል የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ የአረና ትግራይ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አብርሃ ደስታና የሰማያዊ ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ የሺዋስ አሰፋን በጥብቅና ለማገልገል የተስማሙት አቶ ተማም፤ በጊዜ ቀጠሮ ፍ/ቤት እና ማዕከላዊ እስር ቤት መገኘታቸው አስፈላጊ ሆኖ ስላላገኙት ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ በተጠቀሱት ቦታዎች እንደማይገኙ ገልፀዋል፡፡
ደንበኞቻቸው ከተጠረጠሩበት ጉዳይ ውጪ ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን የጠቆሙት ጠበቃው፤ የፓርቲዎች የገንዘብ ምንጭ እንዲሁም ጥንካሬና ድክመት ላይ ያተኮሩ መረጃዎችን እንዲሰጡ እየተደረጉ ነው ብለዋል፡፡ ፖሊስ ያልሆኑ ግለሰቦች በምርመራው ተሳታፊ መሆናቸውን የጠቆሙት ጠበቃው፤ ደንበኞቻቸው እኛን የመመርመር መብት የላችሁም ሲሏቸው፣ ግለሰቦቹ የዘረኝነት ስድብ እየሰደቧቸውና “ለሃገር ጥቅም ሲባል ልንገድላችሁ እንችላለን” በማለት ዛቻና ማስፈራራት እንደፈፀሙባቸው ገልፀዋል፡፡
“ፖሊስ እኔንም ሆነ ሌሎች ጠበቆችን ከደንበኞቻቸው ጋር አላገናኝም በማለቱ የምርመራውን ሂደት ህገ-ወጥነት እና የደንበኞቼን አያያዝ በተመለከተ ማመልከቻ ብናቀርብም፣ ፍ/ቤት ትዕዛዝ የሰጠባቸውን ጨምሮ እርምጃ አልተወሰደም” ብለዋል አቶ ተማም፡፡
የተለያዩ ዛቻዎች እንደሚደርሷቸው የጠቆሙት ጠበቃው፤ “ካላረፍክ አደጋ ያገኝሃል እየተባልኩ የሌላውን መብት ለማስከበር እቆማለሁ ብዬ ብናገር ራሴንም ሆነ ሌላውን ከመዋሸት ለይቼ አላየው” ብለዋል፡፡ አክለውም በተጠቀሱት ሁኔታዎች ውስጥ ባለ ሂደት መሳተፍን ኢትዮጵያዊነታቸው፣ እውቀታቸውና የሙያ ስነ-ምግባራቸው የማይፈቅድላቸውና የማይቀበሉትም ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የአረና ትግራይ ፓርቲ፣ አንድነትና ሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ጉዳዩን አስመልክቶ ባለፈው ረቡዕ  በአንድነት ፅ/ቤት “በህገ-ወጥ ድርጊት መገዛት ያብቃ” በሚል በሰጡት የጋራ መግለጫ፤ በጠበቃው ላይ የደረሰውን ጫና እንዲሁም ታሳሪ አባሎቻቸው ከጠበቃው ጋር መገናኘት እንዳይችሉ መደረጋቸውን በማውገዝ መንግስት በህገ - መንግስቱ የሰፈረውን በህግ ጥበቃ ስር ያሉ ግለሰቦችን መብት እንዲያከብር በአፅንኦት ጠይቀዋል፡፡ በቀጣይም ድርጊቱን የሚያወግዙበት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንደሚጀምሩ ፓርቲዎቹ ጠቁመዋል፡፡

Read 1680 times