Saturday, 27 September 2014 09:50

የኢቦላ ተጠቂዎች ቁጥር በጥቂት ወራት 1.4 ሚ. ሊደርስ ይችላል ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

           ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ለምዕራብ አፍሪካ ቀውስ ፈጣን ምላሽ ካልሰጠ፣ የኢቦላ ወረርሽኝ ተጠቂዎች ቁጥር እስከመጪው ጥር ወር አጋማሽ 1.4 ሚ. ሊደርስ እንደሚችል የአሜሪካ የበሽታ ቁጥጥር ማዕከል ተነበየ፡፡ ሰዎች በከፍተኛ ፍጥነት በኢቦላ እየተጠቁ እንደሆነ የጠቆመው ማዕከሉ፤ እስካሁን በቫይረሱ ተጠቅተዋል ተብሎ ከተነገረው በ2.5 እጅ የሚልቁ ተጠቂዎች እንዳሉ ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት ገልጿል፡፡

በቅርቡ የተጀመረው ዓለምአቀፍ እርዳታ ከቀጠለ ግን ይሄ አስከፊ ሁኔታ ሊቀለብስ ይችላል ብለዋል - የአሜሪካ የበሽታ ቁጥጥር ማዕከል ዳይሬክተር ቶም ፍሪይዴን፤ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው ሪፖርት መሰረት፤ በምዕራብ አፍሪካ 5800 የሚገመቱ ሰዎች በበሽታው የተጠቁ ሲሆን ከ2800 በላይ ሞተዋል፡፡ የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል አዲሱ ሞዴል፤ የገዳዩን ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል የኢቦላ በሽተኞችን ከጤነኞች መነጠል ባለው ፋይዳ ላይ ያተኩራል፡፡

እስካሁን የኢቦላ ተጠቂዎች ቁጥር በሁለቱ አገራት በየ20 ቀኑ በእጥፍ እየጨመረ እንደሆነ የጠቆመው ማዕከሉ፤ ለዚህም ምክንያቱ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ከጤነኞች ጋር ባላቸው ንክኪ በቫይረሱ ስለሚበክሏቸው ነው ብሏል፡፡ ከአስሩ የኢቦላ በሽተኞች ሰባቱ በቤታቸው ወይም በህክምና ማዕከል ውስጥ ተነጥለው እንዲቀመጡ ቢደረጉ፣ በላይቤሪያና በሴራሊዮን ያለው ወረርሽኝ በጥር ወር አጋማሽ ላይ ሊገታ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡

የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል፣ የመከላከያ ኃይል እንዲሁም ዩኤስኤይድ በምዕራብ አፍሪካ ገንዘብና የሰው ሃይላቸውን እያፈሰሱ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎች አገራትም የዚ ጥረት አካል እንደሆኑ የፕሁሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ልዩ ረዳትና የብሔራዊ ደህንነት ም/ቤት ከፍተኛ ዳይሬክተር ጋይሌ ስሚዝ ተናግረዋል፡፡ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ዓለምአቀፍ የእርዳታ ጥረቶች እየጨመሩ ቢመጡም፤ ቫይረሱ ግን ስርጭቱን ቀጥሏል ያለው አሶሼትድ ፕሬስ፤ ከችግሮቹ አንዱ በበሽታው ክፉኛ በተጠቁት ጊኒ፣ ላይቤሪያና ሴራሊዮን በቂ የሆስፒታል አልጋዎች እንዲሁም የጤና ሰራተኞች፣ ወይም ሳሙናና ውሃ ሳይቀር አለመኖሩ ነው ብሏል፡፡

Read 3304 times