Saturday, 27 September 2014 09:44

ከቻይና ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የአቪየሽን ስልጠና ለመስጠት የተዘጋጀው ኮሌጅ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

      ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ ለረዥም ዓመታት በመንግስት ብቻ ተይዞ በነበረው የአየር መንገድ ስራ ውስጥ የግል ባለሀብቶች መሳተፍ የጀመሩት በቅርቡ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህን እድል በመጠቀም ወደዘርፉ ከተሰማሩ ጥቂት የግል አየር መንገዶች መካከልም ናሽናል ኤርዌይስ አንዱ ነው፡፡ የዛሬ ስድስት ዓመት የተመሰረተው አየር መንገዱ፤ በዘርፉ የሚታየውን የባለሙያ እጥረት ለማቃለል፣ በ2003 ዓ.ም ናሽናል አቪየሽን ኮሌጅን የከፈተ ሲሆን የመጀመሪያዎቹን ሰልጣኞችም ባለፈው ነሐሴ ወር አስመርቋል፡፡ ናሽናል ኤርዌይስ እንዴትና በእነማን ተቋቋመ፣ ምን ምን አገልግሎቶችን ይሰጣል፣ የኮሌጁ አመሰራረትና የስልጠና ሂደቱ ምን ይመስላል በሚሉትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከናሽናል አቪየሽን ኮሌጅ ዲን ከአቶ ገዛኸኝ ብሩ ጋር ተከታዩን ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡

ስለ ናሽናል ኤርዌይስ አመሰራረት ሊነግሩኝ ይችላሉ? ናሽናል ኤርዌይስ በ2001 ዓ.ም ነው የተመሰረተው፡፡ የመሰረቱትም ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ አየር መንገድና በሌሎች አገራት አየር መንገዶች በአብራሪነት የረጅም ጊዜ ልምድ ያካበቱ ኢትዮጵያዊያን ካፒቴኖች ናቸው፡፡

አየር መንገዱ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ያወጣውን መስፈርትና መመዘኛ በማሟላት ኤር ኦፕሬተር ሰርተፍኬት ሊያገኝ ችሏል፡፡ በዚህ ሰርተፍኬት መሰረት የኤር አምቡላንስ፣ የቪአይፒ እንዲሁም የካርጎና የቻርተር በረራዎች አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፡፡ ይህ ቻርተርድ ኩባንያ አገር በቀል ቢሆንም የሚታገዘው በውጭ አገር ባለሙያዎች ጭምር በመሆኑ በጥሩ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ የግል አየር መንገድ ለማቋቋም የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን የሚያስቀምጣቸው መስፈርቶች ምንድን ናቸው? በርካታ ነገሮች ያስፈልጋሉ፤ ከፍተኛ ውጣ ውረድም አለው፡፡ ከኢንቨስትመንት ጀምሮ ለአየር መንገዱ የሚያስፈልጉ ክራፍቶችን ማሟላት፣ የውስጥ አሰራርና አደረጃጀትን ማጠናከር እንዲሁም በቂ የሰለጠነ የሰው ኃይል ከሚጠየቁት መስፈርቶች አንዱ ነው፡፡

ዘርፉ ትንሽ ከበድ ያለ እንደመሆኑ ከአገር ደህንነት፣ ከበረራ ደህንነትና ከአጠቃላይ ሴኩሪቲ አንጻር የሚደረጉ ከፍተኛ ጥንቃቄዎች ያሉ ሲሆን ለዚህም በርካታ ነገሮችን ማሟላት የግድ ነው፡፡ በተለይ የገንዘብ አቅም ወሳኝ ነው፡፡ መስፈርቶቹን ለማሟላት የግድ ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ናሽናል ኤርዌይስ እንግዲህ እነዚህን አሟልቶ ነው የተመሰረተው፡፡ የበረራ አገልግሎታችሁ በአገር ውስጥ የተገደበ ነው ወይስ ወደ ውጭም ትበራላችሁ? ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት፤ የቪአይፒ እና የአንቡላንስ አገልግሎቶችን በአብዛኛው በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች ነው የምንሰጠው፡፡ ከዚያ ውጭ ቻርተርድ በረራዎች ይኖራሉ፡፡ ይህ ማለት መንገደኞችን ይዞ መጓዝ ነው፡፡ በብዛት የአገር ውስጥ በረራ እንሰራለን፡፡ ወደ ጎረቤት አገሮች ለምሳሌ ሶማሌላንድ፣ ጁባ፣ ናይሮቢና መካከለኛው አፍሪካ ድረስ የመብረር አቅም አለን፡፡ አየር መንገዱ በተለያዩ ኢትዮጵያዊያን አብራሪዎች መቋቋሙን ነግረውኛል፡፡ በዋናነት የሃሳቡ ጠንሳሽ ማን ነው? ሀሳቡን በመጠንሰስ እውን እስኪሆን ድረስ ተነሳሽነቱን የወሰዱት ካፒቴን አበራ ለሚ ይባላሉ፡፡ እኚህ ኢትዮጵያዊ ለረጅም ጊዜ ኢትዮጵያ አየር መንገድን ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው፡፡ አየር መንገዱን ከሌሎች ሰዎች ጋር ካቋቋሙ በኋላ በዘርፉ ያለውን የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት በማጤን ኮሌጁ እንዲመሰረት ሃሳብ ያፈለቁትም ካፒቴን አበራ ናቸው፡፡

እኚህ ሰው ድርጅቱን በመምራትና በማስተባበርም ከፍተኛ ድርሻ አላቸው፡፡ የመነሻ ካፒታላችሁ ምን ያህል ነው? በአሁኑ ሰዓት አየር መንገዱ ምን ያህል አውሮፕላኖች አሉት? ኢንቨስትመንቱ በጣም ከባድ ነው፤ አሁን እንዲህ ነው እንዲህ ነው ለማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ እንኳንስ አንድ የግል አየር መንገድ ለመክፈት ቀርቶ አንድ አነስተኛ ምግብ ቤት ለመክፈት እንኳ ምን ያህል ፈተና እንዳለው ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን በቁጥር ማስቀመጡ አስፈላጊ መስሎ ባይታየኝም እጅግ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እንደሆነ ልደብቅሽ አልችልም፡፡ ምን ያህል አውሮፕላኖች አላችሁ ለሚለው፣ አንድን አየር መንገድ ለማቋቋም የተቀመጠውን መስፈርት ያሟላንባቸውን ያህል አሉን፡፡ አንዳንዴ ስራ ሲበዛና የእኛ ጥገና ላይ ሲሆኑ የሌሎችን የምንጠቀምበት ሁኔታ አለ፡፡ የካፒታል መጠኑንና የአውሮፕላኖቹን ቁጥር ለመግለፅ ያልፈለጋችሁበት ምክንያት አልገባኝም… ወደፊት ይፋ እናደርጋለን፡፡ አሁን በራሳችን ምክንያት ግልፅ ማድረጉ አስፈላጊ መስሎ ስላልታየን ነው፡፡ እሺ-- ናሽናል አቪየሽን ኮሌጅ እንዴት ነው የተመሰረተው? ኮሌጁን የመሰረተው ናሽናል ኤርዌይስ ነው፡፡ የተመሰረተበት ምክንያት የናሽናል ኤርዌይስ ሰዎች አየር መንገዱን ከመሰረቱ በኋላ፣ በአገር ደረጃ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት እንደነበረ በመረዳታቸው፣ ለምን ኮሌጅ ከፍተን ችግሩን አናቃልልም በማለት ነው የመሰረቱት፡፡ እንደሚታወቀው የአቪየሽን ዘርፍ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ እጅግ እያደገ ያለ ዘርፍ ነው፤ ሆኖም በአገራችን ብዙ ባለሙያዎች የሉም፡፡

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ለራሱ የሚያሰለጥናቸው የአቪየሽን ባለሙያዎች አሉት፡፡ በግል ደረጃ ግን ከዚህ በፊት የለም፡፡ በመሆኑም ካፒቴን አበራ ለሚ ሃሳቡን ካዳበሩ በኋላ፣ ይህን የባለሙያ ችግር ለመቅረፍ ኮሌጁ ተቋቋመ፡፡ የመጀመሪዎቹ 140 ያህል ሰልጣኞችም ነሐሴ 3 ቀን ለምርቃት በቅተዋል፡፡ ኮሌጃችሁ በአቪየሽን ዘርፍ የሚሰጣቸው ስልጠናዎች ምን ምን ናቸው? በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ስልጠና ለመስጠት ፈቃድ ስንጠይቅ፣ዘርፉ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ነው የተመደበው፡፡ ስልጠናው በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆንና ሰልጣኞቹ የትኛውም ዓለም ቢሄዱ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ለማድረግ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቀውና ካናዳ ከሚገኘው ኢንተርናሽናል ኤር ትራንስፖርት አሶሴሽን (IATA) ጋር ለመስራት ከፍተኛ ጥረት ስናደርግ የቆየን ሲሆን አሁን ተሳክቶልናል፡፡ አያታ የራሱ መስፈርትና መመዘኛ አለው፤ ያንን አሟልተን በእነሱ የተፈቀደልን የስልጠና ማዕከል ለመሆን ችለናል፡፡ በዋናነት በበረራ አስተናጋጅነት፣ ትኬቲንግ እና ሪዘርቬሽን፣ በካርጎ፣ በኤርፖርት ኦፕሬሽን ኤርላይን ከስተመር ሰርቪስና ሌሎች ዘርፎች ስልጠና እንሰጣለን፡፡ ሰልጣኞቻችን በአገር ደረጃ መስፈርቱን አሟልተው ከሰለጠኑ በኋላ፣ አያታ በአመት አራት ጊዜ ፈተናዎችን ይሰጣቸዋል፤ ያንን አሟልተው ሲገኙ አለም አቀፍ የምስክር ወረቀትና ዲፕሎማ ያገኛሉ፡፡

የመጀመሪያ ዙር ተመራቂዎቹ በዚህ መልኩ ነው የተመረቁት? አዎ! በዚህ መልኩ ነው የተመረቁት፡፡ እነዚህ ልጆች ሰርተፍኬታቸውንና ዲፕሎማቸውን ይዘው የትኛውም ዓለም ላይ በሰለጠኑበት ዘርፍ መስራት ይችላሉ፡፡ ኮሌጃችሁን ለማሳደግና ወደ ከፍተኛ ትምህርት ለመሸጋገር ከውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማችሁን ሰምቼ ነበር፡፡ እስቲ ስለሱ ይንገሩኝ… እስካሁን በዘርፉ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ስልጠና ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን ስናጠና ቆይተናል፡፡ በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረምነው ከሶስት የቻይና ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ነው፡፡ እነዚህን ዩኒቨርሲቲዎች የመረጥንበት ምክንያት በዘርፉ ደረጃውን የጠበቀ ስልጠና በመስጠት የሚታወቁ በመሆናቸው ነው፡፡ ክፍያቸው ተመጣጣኝና ከሌላው የተሻለ መሆኑ ሌላው ምክንያታችን ነው፡፡ ስለ እነዚህ ዩኒቨርሲቲዎችና ስለሚሰጡት የሙያ ስልጠና ሊነግሩኝ ይችላሉ? አንደኛው ቫንጋይ ኤሮስፔስ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ይህ ተቋም በቻይና በጣም ግዙፍና ታዋቂ ነው፡፡ በኤሮኔቲካል ኢንጂነሪንግ፣ በኤሮክራፍት ማኑፋክቸሪንግና ዲዛይኒንግ፣ በኤሮስፔስ ኢንጂነሪንግ፣ በኤሮክራፍት ቴክኒሺያን፣ በሲቪል ኢንጂነሪንግ… ባችለር ኦፍ አቪየሽን ሳይንስ ስልጠናዎችን ይሰጣል፡፡ ሁለተኛው ሊኒዋንግ ዩኒቨርሲቲ የሚባል ሲሆን ተቋሙ በፔትሮሊየም ኢንጂነሪንግ፣ በጋዝ ኢንጂነሪንግ በኢንቫይሮሜንታል ኢንጂነሪንግ… ስልጠና ይሰጣል፡፡ እኛ ፍላጎት በበዛበት ዘርፍ አብረን ስልጠና ለመስጠት አስበናል፡፡ ሶስተኛው ሊኒዋንግሸዋ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ተቋሙ በቢዝነስና ኢኮኖሚ ዘርፎች ለምሳሌ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን፣ በቢዝነስ ማኔጅመንት፣ በኢንተርናሽናል ትሬድና በመሳሰሉት በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጥናሉ፡፡ ከእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ነው የመግባቢያ ሰነዱን የተፈራረምነው፡፡ ስምምነታችሁ ምን ይመስላል? ወደተግባር ለመግባትስ ምን እየጠበቃችሁ ነው? ስምምነታችን በትብብር ለመስራት ነው፡፡ በአገራችን እነዚህን የስልጠና ማዕከላት ለመገንባት ረጅም ጊዜና ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል፡፡ ይህን ስልጠና ሊሰጡ የሚችሉ መምህራንም የሉንም፡፡

በተጨማሪም ለስልጠናው የሚያስፈልጉ ግብአቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማሟላት ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ በትብብር ነው የምንሰራው፡፡ ትብብር ሲባል ለምሳሌ ስልጠናው አራት ዓመት ከሆነ፣ ተማሪዎች ሁለቱን ዓመት እዚህ ሰልጥነው፣ ቀሪውን ሁለት ዓመት በቻይና ሰልጥነው እንዲመለሱ ይደረጋል፡፡ ከዚያ አቅማችንን በማደራጀት የራሳችንን መምህራን ስናፈራና በቂ የስልጠና ማዕከላት ስንገነባ፣ ስልጠናው እዚሁ ተጀምሮ እዚሁ ይጠናቀቃል፡፡ ወደተግባር ለመግባት የምንጠብቀው የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲን እውቅና ነው፡፡ በአቪየሽን ዘርፍ እየሰራን ቢሆንም ከዘርፉ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው የሆቴል ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ኢንዱስትሪው በአገራችን እየሰፋና እያደገ ቢሄድም የሆቴል ዘርፍ የባለሙያ እጥረት አለ፡፡ እየተሰጠ ያለው ስልጠናም ደረጃውን የጠበቀ አይደለም፤ ስለዚህ በዚህም ዘርፍ በአጭር ጊዜ ስልጠና ለመስጠት ኢንተርናሽናል ኮሜርሺያል ማኔጅመንት (ICM) ከተባለ የለንደን ድርጅት ጋር እየሰራን ነው፡፡ ሰልጣኞቹን እንደ አያታ ሰርቲፋይድ ያደርጋቸዋል፡፡ ከዚያም የትኛውም አገር ሲሄዱ ተቀባይነት አግኝተው ይሰሩበታል ማለት ነው፡፡ የከፈታችሁት ኮሌጅ በቴክኒክና ሙያ ደረጃ ስልጠና ቢሰጥም በአገራችን እምብዛም የተለመደ ዘርፍ ባለመሆኑ የመምህራን ችግር እንደሚያጋጥማችሁ የታወቀ ነው፡፡

እንዴት ተወጣችሁት? እንዳልሽው መምህራን ማግኘት ፈታኝ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ መምህራንን ከኬንያ ማስመጣት ነበረብን፤ ኬንያ በዚህ ዘርፍ የዳበረ ልምድ አላት፡፡ የማሰልጠኛ ተቋማቶቻቸው በመንግስትም በግልም ደረጃ ከኢትዮጵያ በጣም የተሻሉ ናቸው፡፡ ተማሪዎቻችንን ያሰለጠኑልን በአብዛኛው የኬኒያ መምህራን ናቸው፡፡ እነዚህን መምህራን በከፍተኛ ክፍያ ነው ያመጣናቸው፡፡ የኮሚዩኒኬሽንና የስነ-ልቦና ስልጠናዎችን የወሰዱት ግን በአገራችን መምህራን ነው፡፡ እንደስትራቴጂ የያዝነው ከእነዚህ መምህራን ልምድ በመውሰድ፣ከሰልጣኞችም አቅም ያላቸውን በማስቀረት በረጅም ጊዜ ሂደት በአገራችን መምህራን ለመተካት ነው፡፡ ለቀጣዮቹ አራትና አምስት ዓመታት ግን ኢትዮጵያዊ መምህራንን ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ አንዳንዴ እንደውም ናሽናል ኤርዌይስ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎችንም ለመጠቀም እንገደዳለን፡፡ እናም በቀጣይ ላሰብናቸው የከፍተኛ ትምህርት ስልጠናዎች ከቻይና መምህራንን ማስመጣት ይኖርብናል፡፡ አሁን ካስመረቃችኋቸው ተማሪዎች ውስጥ ወደ ስራ የተሰማሩ አሉ? አዎ አሉ! ከተመረቁም በኋላ ሳይመረቁም የተቀጠሩ አሉ፡፡ ለምሳሌ ሶስት ልጆች በበረራ አስተናጋጅ፣ በተለያዩ ዘርፎችም ብዙዎች ተቀጥረዋል፡፡

ዘርፉ የስራ ችግር የለበትም፡፡ ምክንያቱም ብዙ አየር መንገዶች ኢትዮጵያ ውስጥ እየተከፈቱ ነው፡፡ ወደ መካከለኛው ምስራቅና ሌሎች አገራት ሄደው እየሰሩ ያሉም አሉ፡፡ ለስልጠናው ብዙ ወጪዎች እንደምታወጡ ነግረውኛል፡፡ ለምሳሌ ፋየር ፋይቲንግ ለማሰልጠን ለሲቪል አቪየሽን ትከፍላላችሁ፡፡ በመጀመሪያ የህክምና እርዳታ ለማሰልጠን ወደ ቀይ መስቀል፣ ዋና ለማሰልጠን ደግሞ ወደ ትልልቅ ሆቴሎች ትሄዳላችሁ፡፡ የምታስተምሩባቸው መጻህፍትና ሞጁሎች ከውጭ ሲገቡ ይቀረጣሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ለስልጠናው የምትጠይቁት ክፍያ ውድ ይመስለኛል፡፡ ልክ ነኝ ወይስ ተሳስቻለሁ? አንድ ሰው ወደ ትምህርት ዘርፍ ሲሰማራ፣ኢንቨስት ያደረገውን በአጭር ጊዜ አይመልስም፡፡ እንደ ማንኛውም ንግድ አይደለም፡፡ የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ ለትምህርት የሚከፈለው ክፍያ በጣም ርካሽ ነው፡፡ ድንገት ተነስተሽ የአቪየሽን ት/ቤት ልክፈት ብትይ አትችይም፡፡ ልጆቹ ብቃት እንዲኖራቸው ከውጭ ተቋማት ጋር ስምምነት ስናደርግም እነ አያታና አይሲኤም የሚያስከፍሉን ክፍያ አለ፡፡ ቅድም ከላይ የገለፅሻቸው ፋየር ፋይቲንግ፣ የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ፣ የዋና ስልጠና ወዘተ የምንሰጠው ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ሲሆን የመማሪያ ግብአቶችን የምናስመጣውም ከውጭ ነው፡፡ ይሄን ሁሉ ስታስቢው አሁን የምናስከፍለው በጣም ትንሽ ነው ማለት ይቻላል፡፡

እንደየስልጠናው አይነትና የጊዜ መጠን (ከ6-8 ወር ነው) ትንሹ ክፍያ ዘጠኝ ሺህ ብር ሲሆን ትልቁ ክፍያ 34ሺ ብር ነው፤ ነገር ግን ሰልጣኞች ተመርቀው ሲወጡ የሚቀጠሩት በጥሩ ደሞዝ ነው፤ ተፈላጊም ናቸው፡፡ በዘርፉ ዋና ዋና ፈተናዎች የሚባሉት ምንድን ናቸው? በርካታ ፈተናዎች ነበሩ፡፡ ራሱ በዘርፉ መሰማራት አንድ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ በግል ዘርፍ ኮሌጅ ስትከፍቺ፣ የግንዛቤ እጥረት ስላለ በግል ተምረን ማን ይቀጥረናል የማለት አዝማሚያ ነበር፡፡ ይህን ለመለወጥ ብዙ ፈተናዎችን አልፈናል፡፡ ከውጭ የሚመጡ የስልጠና ግብአቶች ከፍተኛ ቀረጥ ይጣልባቸዋል፡፡ ብቻ በርካታ ችግሮች ነበሩ፤ አሁን በሂደት እየተቀረፉ ነው፡፡

Read 4326 times