Saturday, 27 September 2014 09:42

ኮካኮላ ለ30 የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ድጋፍ ያደርጋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

            ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ አክሲዮን ማህበር (ኮካኮላ) ከመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከፍተኛ ውጤት ያላቸው ተማሪዎች በገንዘብ ችግር ውጤታቸው እንዳይቀንስ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡ ከአዲስ አበባ፣ ከባህርዳርና ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች ለተመረጡ ከ3.0 ነጥብ በላይ ውጤት ላላቸውና ለአነስተኛ ገቢ ቤተሰብ ተማሪዎች፣ለሶስት ዓመት የኪስ ገንዘብ እንደሚሰጥና ለትምህርት አስፈላጊ የሆኑ ቁሶችን ድጋፍ ለማድረግ 1.2 ሚሊዮን ብር መመደቡን የኢትዮጵያ ኮካኮላ የሰው ኃይል ሀብት ማናጀር አቶ አንተነህ ተገኝ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዓመት ድጋፍ የሚደረግላቸው ተማሪዎች 30 ሲሆኑ 11ዱ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የኩባንያው ሰራተኛ ልጆች ሲሆኑ የተቀሩት፣አነስተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ልጆች መሆናቸውን የተመረጡበት ዩኒቨርሲቲዎች እንዳረጋገጡላቸው ጠቁመዋል፡፡በቀጣዩ ዓመት 15 ተማሪዎች እንደሚጨመሩና ገንዘቡም ወደ 1.8 ሚ ብር እንደሚያድግ የጠቀሱት አቶ አንተነህ፣ ለተማሪዎቹ በየወሩ 500 ብር የኪስ ገንዘብ ይሰጣል ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በየዓመቱ አንድ ጊዜ አስፈላጊ የትምህርት ቁሳቁስ እንደሚሟላላቸው፣ትምህርታቸውን እንዴት እየተከታተሉ እንደሆነ በኩባንያው ኃላፊዎች እንደሚጎበኙ፣ ለመመረቂያ ጽሑፍ ድጋፍ እንደሚደረግና በየዓመቱ መጨረሻ ት/ቤት ሲዘጋ ወደ ኩባንያው መጥተው እንደየትምህርታቸው በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን በተግባር እንደሚለማመዱ፣ በዚህ ወቅትም ለምግብና ለትራንስፖርት ወጪ የሚሆን ገንዘብ እንደሚሰጣቸው አስረድተዋል፡፡

ተማሪዎቹ በመንግስት 70/30 የትምህርት ፖሊሲ መሰረት፤ ከሳይንስ ዘርፍ የተመረጡ (በአብዛኛው ከኢንጂነሪንግና ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ) መሆኑን የተናገሩት ማናጀሩ፣ እነዚህ የትምህርት ዘርፎች እነሱም የሚጠቀሙባቸው እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ለ30ዎቹ ተማሪዎች በዓመት ከ400 እስከ 500 ሺህ ብር ወጪ ይደረጋል፡፡ኩባንያው የማህበራዊ አገልግሎት ተሳትፎን ለማጎልበት በጤና፣ በመጠጥ ውሃ፣ በስፖርት… ዘርፎች እየተሳተፈ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ አንተነህ፤አሁን በትምህርት ዘርፍ የጀመሩት ተሳትፎ የአነስተኛ ገቢ ቤተሰብ ተማሪዎች፣ከፍተኛ ውጤት እያላቸው በገንዘብ ችግር ትምህርታቸውን እንዳይደናቀፍና ውጤታቸው እንዳይቀንስ በማለት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ አንተነህ፣ ይህ የኩባንያው እቅድ የሚሳካው በተማሪዎቹ፣ በዩኒቨርሲቲዎቹና በህብረተሰቡ ተሳትፎ እንደሆነ ገልጸው፣ ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ አሳስበዋል፡፡ ባህሪያቸው ያማረና በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ፋብሪካዎች ለሶስት ዓመት በሚያደርጉት የተግባር ልምምድ የሚሰጠውን ፈተና በሚገባ የሚያልፉት በኩባንያው እንደሚቀጠሩ አስታውቀዋል፡፡ ቅድስት ታደለና ቤዛዊት ዚያድ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የኩባንያው ሰራተኞች ልጆች ናቸው፡፡ ቅድስት በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የ2ኛ ዓመት የኮምፒዩተር ሳይንስ፣ ቤዛዊት በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ የ2ኛ ዓመት፣ ማተቡ ወርቁ ደግሞ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የ2ኛ ዓመት ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ ነው፡፡ ተማሪዎቹ ይህን ዕድል በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ ዕድሉን ባያገኙ ኖሮ ለተግባር ልምምድ (አፓረንትሽፕ) የሚወጡት 4ኛ ዓመት ሲደርሱ እንደነበር ጠቅሰው፣ አሁን ግን ሶስት ዓመት የሚያደርጉት ልምምድ፤ ለእውቀታቸው መዳበርና ለውጤታቸው ማማር በእጅጉ እንደሚረዳቸው ተናግረዋል፡፡

Read 1990 times