Print this page
Saturday, 27 September 2014 09:39

ተከሳሹ ስኖውደን የስዊድን አማራጭ ኖቤል ተሸላሚ ሆነ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

            አሜሪካ በድብቅ የያዘቻቸውን 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ያህል የብሄራዊ ደህንነት ሚስጥሮችና የተለያዩ ድብቅ መረጃዎችን በማውጣት ለአለም ይፋ ያደረገውና በአገሪቱ መንግስት ክስ የተመሰረተበት ኤድዋርድ ስኖውደን፣ ለፕሬስ ነጻነት ባበረከተው አስተዋጽኦ፣ አማራጭ የኖቤል ሽልማት በመባል የሚታወቀው ‘የስዊድን ራይት ላይቭሊሁድ ኦኖራሪ አዋርድ’ ተሸላሚ መሆኑን ሮይተርስ ዘገበ፡፡ ‘ራይት ላይቭሊሁድ ኦኖራሪ አዋርድ ፋውንዴሽን’ ስኖውደን የአሜሪካ መንግስት የዲሞክራሲያዊ ስርአት ሂደቶችንና ህገ መንግስታዊ መብቶችን በሚጥስ መልኩ የምታከናውነውን የመረጃ ክትትል ለማጋለጥ ባደረገው ጥረት ለሽልማቱ መመረጡን አስታውቋል፡፡ ተቋሙ ሽልማቱን ለስኖውደን ከማበርከቱ በተጨማሪም፣ በቀጣይ ከአሜሪካ መንግስት ለሚገጥመው የወንጀል ክስ ህጋዊ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

የመንግስት ንብረትን መዝረፍ፣ ብሄራዊ የመከላከያ መረጃዎችን በህገወጥ መንገድ ማሰራጨትና የስለላ መረጃዎችን ለማይገባቸው ሰዎች አሳልፎ መስጠት የሚሉ ክሶች ባለፈው አመት በአሜሪካ መንግስት የተመሰረተበት ስኖውደን፤ በዚያው አመት ከአሜሪካ ወጥቶ ወደ ሆንግ ኮንግ፣ ከዚያም ወደ ሩስያ አቅንቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከሩስያ መንግስት በተሰጠው ለሶስት አመታት የሚቆይ ጊዜያዊ የመኖሪያ ፍቃድ በሞስኮ ይገኛል፡፡ በዘንድሮው ‘የስዊድን ራይት ላይ ቭሊሁድ ኦኖራሪ አዋርድ’፣ስኖውደን ያወጣቸውን መረጃዎች ለህትመት በማብቃት ትብብር ያደረጉት የታዋቂው ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አለን ራስብሪጀርም ተሸላሚ እንደሆኑ ዘገባው አስረድቷል፡፡

Read 1863 times
Administrator

Latest from Administrator