Saturday, 27 September 2014 09:23

ኢህአዴግ “ወደ አገራችሁ ተመለሱ” ማለት ይልመድበት!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(7 votes)

መንግስት ርዕዮተ ዓለሙን ቀየረ እንዴ?

            በሴቶች ዙሪያ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ከተሳታፊ እንደተሰነዘረ በተነገረኝ አስተያየት ነው የዛሬ ወጌን የምጀምረው፡፡ ሰውየው አዲስ ከተዋወቃት ልጃገረድ ጋር በትዳር የመጣመር ፍላጎት አለው፡፡ ግን አካሄዱን ያወቀበት አይመስልም፡፡ ልጅቱ በነገረ ሥራው ደስተኛ አይደለችም፡፡ በመጀመሪያ ቀጠሮአቸው ሲያጫውታት፣ ሲደባብሳት፣ እንደሚወዳትና ወደፊት አግብቷት በፍቅር ለመኖር እንዳሰበ ሲነግራት ቆይቶ በክብር ሸኛት፡፡ የመጀመሪያ ቀጠሮ ስለነበር ልጅቱ ብዙ አልተከፋችም፡፡ ግዴለም በቀጣዩ ቀጠሮ ከመደባበስ ያለፈ ድፍረት አግኝቶ ዓለሜን እቀጫለሁ … የሚል ተስፋ ሰንቃ ነበር፡፡ በሁለተኛው ቀጠሮ ልጅቱ ከበፊቱ የበለጠ አምራና ተውባ ነበር የመጣችው፡፡ ሰውየውን ማርካ የልቧን እንደምትፈፅምም ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ አልነበራትም፡፡ ወደ ቤቷ የተመለሰችው ግን ተስፋ ቆርጣ ነው፡፡ ሰውየው ልክ እንደመጀመሪያው ቀጠሮ በወጉ አጫውቶ፣ ደባብሶና አሟሙቆ ነው የለቀቃት፡፡

በንዴት እየተንጨረጨረች ቤቷ ገብታ ኩርምት ብላ ተኛች፡፡ በነጋታው ከእንቅልፏ ስትነቃ ግንፍል ግንፍል ይል የነበረው ደሟ ፍሪጅ እንዳደረ ሁሉ ቅዝቅዝ ብሎ ነበር፡፡ (ደም ሲቀዘቅዝ አዕምሮ ሳይነቃ አይቀርም!) እናም በነቃ አዕምሮዋ በቀጣዩ ቀጠሮአቸው ሰውየውን ጉድ እንደምታደርገው ለራሷ ቃል ገባች፡፡ ቃል ገብታም የሰውየውን ስልክ በጉጉት መጠባበቅ ያዘች፡፡ በሳምንቱ ደወለ፡፡ እንደተለመደው ቀጠራት፡፡ ሦስተኛው ቀጠሮአቸው መሆኑ ነው፡፡ ልጅቱ ይበልጥ ተውባና ተሽቀርቅራ ሄደች - ወደ ቀጠሮዋ፡፡ ዛሬም ግን ሰውየው የተለየ ነገር አላደረገም፡፡ መሳም…ማቀፍ… ማሻሸትና መደባበስ ብቻ! እንዲያም ሆኖ ልጅቱ ታግሳዋለች፡፡ ጉዱን አያለሁ ብላ እስከ 11ኛው ሰዓት ድረስ ጠበቀችው፡፡ ግን ጠብ ያለ ነገር የለም፡፡ ይሄኔ የሚያስደነግጥ ጥያቄ አቀረበችለት፤ “ቆይ አንተ… ከወገብ በታች መውረድ አትችልም እንዴ?” አለችው፤ ዓይኗን በጨው አጥባ (“ይሞታል ወይ ታዲያ” አለ ዘፋኙ!) ሰውየው ይሄን ስትለው በድንጋጤ የጨው አምድ መስሎ እንደሚቀር ብትገምቱ አይፈረድባችሁም፡፡ እኔም ብሆን ከእናንተ የተለየ ነገር አልነበረም የጠበቅሁት፡፡

ሰውየው ግን ቅንጣት ታህል ድንጋጤ ሳይታይበት “እኔና ኢህአዴግ የማስፈፀም ችግር አለብን!” አላት - ለልጅቱ!! (በኢህአዴግ ቋንቋ “ሂሱን ዋጠ” ማለት ነው!) በነገራችሁ ላይ ይሄ ታሪክ (ቀልድ) የተፈጠረው የሴቶች፣ የህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮን ለመተቸት ነው፡፡ የተነገረውም ራሱ ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ እንደሆነ ምንጮቼ ጠቁመውኛል፡፡ ህግና ደንብ ቢወጣም፣ ፖሊሲ ቢቀረፅም በተግባር ግን ለኢትዮጵያዊቷ ሴት ጠብ ያለላት ነገር የለም ለማለት ተፈልጐ ነው፡፡ የአገሪቱ ህግ መንግስት እኮ የሴቶችን መብትና ነፃነት ለማስከበር እንዲያስችል ተደርጐ ነው የተቀረፀው፡፡ ግን ማን ይተግብረው? ለዚህ እኮ ነው ኢህአዴግ ገና በማለዳ “የፖሊሲ ችግር የለብኝም፤ የአፈፃፀም እንጂ!” ሲል የተናዘዘው፡፡ (ኢህአዴግ ደስ የሚለው ጥፋቱን ያምናል!) ሁሌ ግን አይደለም፤ ሲለው ሲለው ነው፡፡ ጥፋቱን አመነ ሲባል ደግሞ ሁለተኛ አይደግመውም ማለት አይደለም፡፡ እንዲያ ከመሰላችሁ ተሸውዳችኋል፡፡ ባይገርማችሁ… ያንኑ ተመሳሳይ ጥፋት አንዴ ሳይሆን አስሬ ሊደግመው ይችላል፡፡ (የአፈፃፀም ችግር እንዳለበት ተናግሯላ!) እኔ የምለው… ኢህአዴግ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሲሰጥ የነበረውን ስልጠና እንዴት አያችሁት? (በጐሪጥ እንዳትሉኝ!) አንድ ያልገባኝ ነገር አለ፡፡

ኢህአዴግ የርዕዮተ ዓለም ለውጥ አደረገ እንዴ? እርግጠኛ ነኝ አያደርግም (“ሞቼ ነው ቆሜ” አለ!) ታዲያ ምን መጥቶበት ነው አገሪቱን በስልጠና ያጥለቀለቀው?! (የአብዮታዊ ዲሞክራሲ “ጥምቀት” ይሆን?) አትፍረዱብኝ… ግራ ቢገባኝ እኮ ነው፡፡ መቼም የልማት ስትራቴጂ… ህገ-መንግስት…የኒዮሊበራሊዝም ውድቀት… አብዮታዊ ዲሞክራሲ… ድህነትን ተረት ማድረግ… ፌደራሊዝም… የብሄር ብሄረሰቦች ነፃነት… የሃይማኖት እኩልነት…ወዘተ… ለእኛ ባይተዋር አይደሉም፡፡ ለሁለት አስርት ዓመታት እስክንጠግብ ሰምተናቸዋል፡፡ ታዲያ የስልጠናው ጋጋታ ለምን ተፈለገ? (ኢህአዴግ transparency ይጐድለዋል!) አንዳንዴ እኮ በተቃዋሚዎችም መፍረድ ይቸግራል፡፡ አሁን ለምሳሌ ስልጠናውን ተቃውመውታል - ርዕዮተ ዓለሙን በግዳጅ እየጋተ ነው በማለት፡፡ (ግን ነው እንዴ?) እነሱ ደሞ ያለተቃውሞ ስራ የላቸውም እንዴ ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ ለነገሩ ስራቸውም እኮ ይሄው ነው - መቃወም ነው፡፡

ስማቸው ተቃዋሚ ግብራቸው መቃወም ነው፡፡ ግን ስንት ዓመት ሲቃወሙ ሊኖሩ ነው? አላለላቸውም እንጂ ለጥቂት ጊዜ ተቃውመው፣ ህዝብን ከጎናቸው አሰልፈው፣ እንደ ኢህአዴግ በ98.5 በመቶ ባይሆንም ከ50 በመቶ በላይ ድምፅ አግኝተው ሥልጣን መያዝ ነበረባቸው እስካሁን፡፡ (ኢህአዴግ በስልጣን፣ እነሱ በተቃውሞ አረጁ እኮ!) በነገራችሁ ላይ … መንግስት ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እየሰጠ በሚገኘው ስልጠና ላይ አንዳንድ ደፋር ተማሪዎች አሰልጣኞችን የሚያፋጥጡ (በደንብ እንዳላጠና ተማሪ ማለት ነው!) ጥያቄዎችን እንደሰነዘሩ ሰምተናል (ዕድሜ ለዲሞክራሲ!) እናላችሁ… አንደኛው ሰልጣኝ እጁን አወጣና “ቆይ ግን እናንተ መቼ ነው ከስልጣን የምትወርዱት? 23 ዓመት እኮ ገዛችሁ!” ሲል በአሰልጣኝነት ተመደበውን “የልማት ታጋይ” አፋጦት ነበር አሉ፡፡ የአንዳንድ ተማሪዎች ድፍረት የተደበላለቀ ስሜት የፈጠረበት ሌላ ተማሪ ደግሞ እንዲህ የሚል በአስተያየት የተሟሸ ጥያቄ ሰነዘረ፡፡ (ምንጮች ናቸው የነገሩኝ!) “በደርግ ዘመን ካድሬዎች ሰውን እንዲህ ይሰበስቡና የተሰማችሁን በነፃነት ተናገሩ ይሉ ነበር፤ ማታ ታዲያ በስብሰባው ላይ ጠንካራ ሂስና ትችት የሰነዘሩትን ከየቤታቸው ለቅመው አረመኔያዊ እርምጃ ይወስዱባቸዋል፡፡ እናንተም አሁን ሳትሸማቀቁ በነፃነት ተናገሩ እያላችሁን ነው፡፡ ከእናንተስ ምን እንጠብቅ?” በወጣትነት ድፍረትና በዩኒቨርሲቲ ተማሪነት ብልጠት የተጠቀለለ ጥያቄ (“አንሸዋወድ” ነው ነገሩ!)፡፡ በዚያው በደርግ ዘመን አንድ ስብሰባ ላይ አንድ ሰው አገዛዙን የሚነቅፍ አስተያየት ሰጥቶ እንደተቀመጠ በደህንነቶች “ትፈለጋለህ” ተብሎ ታጅቦ ይወሰዳል፡፡ ከዚያም ከፊት የተቀመጠ ሌላ ሰው ሃሳቡን እንዲናገር ከመድረኩ መሪዎች ይጋበዛል (የአደጋ ግብዣ በሉት!) ሰውየውም ጉሮሮውን ይጠራርግና “የእኔም ሃሳብ…” ብሎ ድንገት ንግግሩን ያቋርጥና ወደኋላ ሲመለከት አንድ ሰው ያጣል፡፡ ደንግጦ “ከእኔ በፊት የተናገረው የታለ?” በማለት የመድረክ መሪዎቹ ላይ ያፈጥባቸዋል፡፡ “ሃሳብህን ቀጥል!” አሉት የመድረክ መሪዎቹ፡፡

ምኑ ሞኝ ነው … “ሃሳቤን ጨርሻለሁ፤ አመሰግናለሁ!” ብሎ ተቀመጠ፡፡ ትረፍ ቢለው እኮ ነው (ተርፎ ከሆነ ማለቴ ነው!) ወደ ሰሞኑ የዩኒቨርሲቲ ስልጠና ልመልሳችሁ፡፡ ስገምት ምን ይመስለኛል መሰላችሁ? በኢህዴግ ውስጥ በተደረገ ግምገማ (በተጨባጭ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ማለት ነው!) እዚህ አገር ላይ የሚፈጠሩ ቀውሶች… ግጭቶች.. አክራሪነቶች.. የሽብር ተግባሮች… ነውጦች ወዘተ መንስኤያቸው የግንዛቤ ማነስ ነው ወደሚል ድምዳሜ ሳይደረስ አልቀረም፡፡ ለዚህ ደሞ መፍትሔው ሥልጠና ነው ተባለ (ግልፅነት እስኪለመድ መገመት መብቴ ነው!) እናም አገሪቱ በስልጠና ተጥለቀለቀች፡፡ ግን እኮ አንዳንዶቹን የስልጠና አጀንዳዎች እንደኮርስ ቀርፀው እዚያው ዩኒቨርሲቲ በወጉ እንዲሰጥ ማድረግ ይችሉ ነበር፡፡ (ኢህአዴግን ከሃሜት አትዳን ቢለው እኮ ነው!) እኔ የምለው ግን… መንግስት ስልጠናውን ለተማሪዎች እየሰጠ ያለው በግዳጅ ነው የሚባለው ነገር እውነት ነው እንዴ? ወይስ ሃሜት ነው? (እንዴት ቻይና ሃሜት አጣሪ ማሽን መስራት አቃታት?) እናላችሁ… ያልሰለጠነ ተማሪ የዩኒቨርሲቲን ደጃፍ አይረግጣትም ተብሎ ነው ሥልጠናው የተካሄደው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ (“አደጋ አለው!” አሉ) እኔ የምለው… መንግስት ሰሞኑን አገር ጥለው ለኮበለሉት ጋዜጠኞች፣ “ወደ አገራች ገብታችሁ በሙያችሁ ሥሩ” የሚል ጥሪ አቀረበ የሚባለው እውነት ነው እንዴ? (ስደቱ መታመኑም አንድ ነገር ነው!) እውነቱን ልንገራችሁ አይደል… ይሄ ለአገሩ ዜጎች ኃላፊነት ከሚሰማው መንግስት ወይም ገዢ ፓርቲ የሚጠበቅ ክቡር ተግባር ነው፡፡ (እንግዳ ነገር ቢመስለንም ይለመዳል!) ይሄውላችሁ ለአገሩ የሚያስብ መንግስት በተቻለ መጠን ዜጎቹን ይሰበስባል እንጂ ዝም ብሎ አይበትንም፡፡

እናላችሁ… የምሰማው የመንግስት ጥሪ እውነት ከሆነ (ያድርገው!) ኢህአዴግን በአደባባይ አደንቀዋለሁ፡፡ (ምርጫ የለኝማ!) በቃ እኮ እቺን ታህል ማሰብ… ማሰላሰል… ሆደ ሰፊ መሆን ብቻ ነው የሚፈለገው፡፡ አሁንም ይሄንን ቀና ጅምር አጠናክሮ፣ የጋዜጠኞች እስርና ክስ በምክክርና በውይይት ቢተካው ብዙ የሚጠቀመው ራሱ ኢህአዴግ ነው፡፡ አንደኛ ወዳጆች ባያፈራበት እንኳን ጠላቶች ይቀንስበታል፡፡ ሁለተኛ ለትውልዱም ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን እንዴት በውይይትና በምክክር መፍታት እንደሚቻል በተግባር ያስተምርበታል (Leading by example - ይሏል ይሄ ነው!) ከእንደኔ ዓይነቱ ዜጋ፤ በግንቦቱ ምርጫ ድምፅ ባያገኝበትም እንኳን አክብሮትና አድናቆትን ማንም አይከለክለውም፡፡ እናላችሁ… በያዝነው አዲስ ዓመት ኢህአዴግ እንዲህ ያለውን “መጀገን” በብዛት እንዲታጠቅ እመኝለታለሁ፡፡ ለሁላችንም የሚበጀን ይሄ ነው፡፡ መልካም የመስቀል በዓል ይሁንላችሁ!!

Read 3666 times