Saturday, 27 September 2014 09:20

ሴፕ ብላተር ፤ አምባገነኑ የእግር ኳስ ፕሬዝዳንት

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

 ለ5ኛ ጊዜ መመረጥ ይፈልጋሉ፤ ተቀናቃኛቸው  አንድ ፈረንሳዊ ብቻ ናቸው
    ምርጫው ከ7 ወር በኋላ ነው


በዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር “ፊፋ” ፕሬዝዳንትነት  ያለፉትን ለ16 ዓመታት የቆዩት ስዊዘርላንዳዊው ሴፕ

ብላተር ተጨማሪ 4 ዓመት ልቀጥል ማለታቸው እያነጋገረ ነው፡፡  ለአምስተኛ ጊዜ የመመረጥ ፍላጎት እንዳላቸው

ሲያስታውቁ፤ “የስልጣን ዘመኔ ቢያበቃም ጅምር ስራዎቼን ከዳር ለማድረስ ለመመረጥ  እቀርባለሁ” ብለዋል፡፡

ሰሞኑን የፊፋ ስራ አስኪያጅ ኮሚቴ ይህንን የሴፕ ብላተር ጥያቄ ተቀብሏል፡፡ በዓለም መገናኛ ብዙሐናት

በሙስና እና በመልካም አስተዳደር መጓደል እንደ ፊፋ  የሚታማ ተቋም የለም፡፡ እንደ ሴፕ ብላተር ደግሞ

ለተቋሙ ተዓማኒነት የሚሟገት አልተገኘም፡፡ ሰሞኑን በፊፋ ላይ የቀረበውን ትችት በተመለከተ ሴፕ ብላተር

ሲናገሩ፤ ዓለም አቀፉ ተቋም በስሩ የ209 አገራት ፌደሬሽኖችን በብቃት እንደሚያስተዳድር፤ በመላው ዓለም

ከ300 ሚሊዮን በላይ የእግር ኳስ ተጨዋቾችን በማወዳደርና በመከታተል ትልቅ ኃላፊነት እንደሚወጣ

አስታውሰዋል፡፡ ከ1.2 ቢሊዮን በላይ የዓለም ህዝብን ያቀፈውን ስፖርት በማስተዳደር ፊፋን የሚስተካከለው

የለም በማለት ፕሬዚዳንቱ ይከራከራሉ፡፡
ሴፕ ብላተር በ1998 እኤአ ላይ በ62 ዓመታቸው ለመጀመርያ ጊዜ የፊፋ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡

ዓለምአቀፍ ተቋሙን ለመምራት የቻሉ ስምንተኛው ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡ ላለፉት 16 ዓመታት ለአራት ጊዜ

ተመርጠው እየሰሩ ቆይተዋል፡፡ አሁን 78ኛ ዓመታቸውን የያዙት ሴፕ ብላተር፤ በድጋሚ ተመርጠው ለአምስተኛ

የስራ ዘመን ከቀጠሉ በዓለም የስፖርት ታሪክ በከፍተኛ ዓመራርነት ለ20ኛ ዓመታት የቆዩ ብቸኛው ሰው

ይሆናሉ፡፡ ዓለምአቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ለሴፕ ብላተር  በዓመት 1.4 ሚሊዮን ዶላር ደሞዝ

ይከፍላቸዋል የሃብታቸው ግምት ደግሞ እስከ 58 ሚሊዮን ዶላር ይሆናል፡፡
ከዠሮሜ በቀር ማን ይፎካከራቸው?
ሴፕ ብላተር በፊፋ ፕሬዝዳንትነት ለአምስተኛ ጊዜ በድጋሚ ለመመረጥ ሲፈልጉ፣ በእኩል ደረጃ የሚፎካከራቸው

አለመገኘቱ የሰሞኑ አነጋጋሪ ጉዳይ  ነው፡፡ ያለተቀናቃኝ መወዳደር ቢያቅዱም ብቸኛ ተፎካካሪያቸው ፈረንሳዊው

ዥሮሜ ሻምፔን ሆነዋል፡፡ ከአራት ዓመት በፊት የፕሬዝዳንትነት መንበሩን ከሴፕ ብላተር ለመንጠቅ ምርጫ

ሊገቡ የነበሩት የኳታር እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ማሀመድ ቢን ሃማም ነበሩ፡፡ በሙስና ተጠርጥረው

ከተወዳዳሪነት ውጭ ሆነዋል፡፡
እግር ኳስ የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት ኡሳ ሃያሉ የአህጉሪቱን እግር ኳስ መልቀቅ አይፈልጉም፡፡  

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት የሆኑት ሚሸል ፕላቲኒ በብቃት እንደሚተኳቸው ቢገመትም ከብላተር

ጋር ለመፎካከር ምርጫ አልገባም ብለዋል፡፡  ፕላቲኒ በፊፋ ፕሬዝዳንት ምርጫ ላይ አለመግባታቸው የተጠበቀ

ነበር፡፡ ምክንያቱም የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ራሱን የቻለ ግዙፍ የእግር ኳስ አካል በመሆኑ ነው፡፡ የፕላቲኒ

ማፈግፈግ ለብላተር ምቹ ሁኔታዎችን ቢፈጥርም በርካታ የአውሮፓ እግር ኳስ ፌደሬሽኖች በተለይ የጀርመን፣

ሆላንድ እና እንግሊዝ አመራሮች ለስዊዘርላንዳዊው ድጋፍ መስጠት አይፈልጉም፡፡ የአውሮፓ ትልልቅ የእግር ኳስ

ሊጐች የሚካሄድባቸው እነዚህ አገራት ዓለም አቀፍ ተቋሙ ብላተርን በማሰናበት በአዲስ ፕሬዚዳንት ከፍተኛ

ተሃድሶ እንደሚያስፈልገው መጠየቃቸውን ቀጥለዋል፡፡ በሌላ በኩል የጀርመኑ ፍራንዝ ቤከንባወር ለፊፋ

ፕሬዚዳንትነት ብቁ ልምድ እንዳለው ቢታወቅም ወደ ምርጫው ለመግባት ምንም አይነት ፍላጎት አላሳየም፡፡

ሃያቱ፤ ፕላቲኒና ቤከንባወር ሴፕ ብላተርን በምርጫ ከመፎካከር ይልቅ ማፈግፈጋቸው ለትችት አጋልጧቸዋል፡፡

ስለዚህም ሴፕ ብላተር እንደልማዳቸው አባል ፌደሬሽኖችን በማባበል ለአምስተኛ ጊዜ የመመረጥ እድላቸው

መስፋቱን መረጃዎች ይገልፃሉ፡፡ ሴፕ ብላተርን ለመፎካከር በብቸኝነት የወጡት በአሁኑ ጊዜ የፊፋ ከፍተኛ

አማካሪ  ሆነው የሚያገለግሉት ዥሮሜ ሻምፔን ብቻ ናቸው፡፡ የ56 ዓመቱ ፈረንሳዊ የፊፋ ምክትል ዋና ፀሃፊ

ሆነው ለ3 ዓመታት ሠርተዋል፡፡ ዤሮሜ ሻምፔን ዓለም አቀፉ ተቋም ለሁሉም ፌደሬሽኖች በእኩልነት እንዲሰራ

ይሟገታሉ፡፡ የፊፋ ሃላፊነት ለቀው ከወጡ አራት ዓመት ያለፋቸው ዤሮሜ፤ በፊፋ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች

በዲያሬክተርነት ተሹመው የፕሬዝዳንቱ አማካሪ በመሆን ያገለገሉት ለ11 ዓመታት ነው፡፡ ከአውሮፓ

ህበረት፤ከዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ፤ ከአውሮፓ ክለቦች ህብረት እና ከዓለም አቀፍ የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች

ማህበር ጋር በቅርበት የሰሩበት ልምዳቸው ሰፊ ነው፡፡ ዤሮሜ በፊፋ ውስጥ ባላቸው ሃላፊነቶች በችግር ውስጥ

ያሉ በርካታ ፌደሬሽኖችን በማገዝ እውቅና ያተረፉ ሲሆን በተለይ በኬንያ፤ ኢትዮጵያ ፤ ሴኔጋል እና ፖላንድ

የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ያሉ መናወጦች እንዲረጋጉ በተጫወቱት ሚና ከፍተኛ ድጋፍ አላቸው፡፡
የብላተር ድጋፍ ፤ ውጤትና የስራ ልምድ
ሴፕ ብላተር በ1998 እኤአ ለመጀመርያ ጊዜ ፕሬዝዳንት ሲመረጡ የአባል አገራትን ሙሉ ድጋፍ በማግኘታቸው

ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በ2002 እኤአ ያለአንዳች ተቃውሞ በሙሉ ድምፅ በድጋሚ መመረጥ ሆኖላቸዋል፡፡ በ2007

እኤአ ላይ ለሶስተኛ የስራ ዘመን ሲወዳደሩ ግን በአፍሪካ ለሚገኙ አንዳንድ ፌደሬሽኖች መደለያ በማቅረብ

እንደተመረጡ ተወራባቸው፡፡ በ2011 እኤአ ላይ ደግሞ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸው እና እንደልማዳቸው የአባል

አገራት ፌደሬሽኖች አመራሮችን በገንዘብ መደለላቸው በስፋት እየተነገረ ለአራተኛ ጊዜ ፕሬዝዳንት ሆነው

ተመርጠዋል፡፡ የፊፋን ፕሬዝዳንት ለመምረጥ 209 የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ድምፅ ይሰጣሉ፡፡ ለአምስተኛ ጊዜ

በድጋሚ መመረጥ እፈልጋለሁ ያሉት ብላተር የኤስያ እና የአፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽኖችን ሙሉ ድጋፍ

ማግኘታቸው ከ90በላይ ድምፅ የሚያገኙበትን እድል ሰጥቷቸዋል፡፡ ከአራት ዓመታት በፊት በመጨረሻው

የአራተኛ ስራ ዘመን ምርጫቸው ድምፅ ከሰጡት 203 አገራት የ186 ድጋፍ ነበራቸው፡፡ ብላተር በዚሁ ድላቸው

ማግስት ድጋሚ የመመረጥ ፍላጎት የለኝም ብለው ነበር፡፡
ብላተር በፊፋ ሲቀጠሩ ዓለምአቀፍ ተቋሙ 12 ሰራተኞች ነበሩት፡፡ ዛሬ በየዓመቱ 75.64 ሚሊዮን ዶላር

የሚከፈላቸውን 452 ሰራተኞች ቀጥሮ ያስተዳድራል፡፡  የፊፋ ዋና መስርያ ቤት በዙሪክ የሚገኝ ሲሆን በ100

ሚሊዮን ዶላር የተገነባ ዘመናዊ ህንፃ ነው፡፡ በህዝብ ግንኙነት እና ጋዜጠኛነት የሰሩት ሴፕ ብላተር

በወጣትነታቸው እግር ኳስ ተጨዋችነትንም በአማተርነት ሞክረውታል፡፡ በቢዝነስ ኢኮኖሚ ዲግሪ አላቸው፡፡

ሴፕ ብላተር በ1998 የፊፋን የፕሬዝዳንትነት መንበር ከመቆናጠጣቸው በፊት በተቋሙ በተለያዩ የስራ ዘርፎች

ከ1975 እኤአ ጀምሮ አገልግለዋል፡፡ ከ1975 እስከ 1981 እኤአ የቴክኒክ ዲያሬክተር ነበር ከ1981 እስከ 1998

እኤአ ደግሞ በዋና ፀሃፊነት አሠርተዋል፡፡ በአጠቃላይ ሴፕ ብላተር በፊፋ ከቆዩባቸው 23 ዓመታት17ቱን

ያሳለፉት የቀድሞው ፕሬዝዳንት  ብራዚላዊው ጆ ሃቫላንጅ ቀኝ እጅ ሆነው በዋና ፀሃፊነት በማገልገል ነበር፡፡
በሴፕ ብላተር አራት የስራ ዘመናት ፊፋ በጣም አትራፊ አለም አቀፍ ኩባንያ ሆኗል፡፡  በካዝናው ከ1 ቢሊዮን

ዶላር በላይ ያኖረ ተቋም ነው፡፡ በአራት ዓለም ዋንጫዎች ተቋሙ ከ16 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አንቀሳቅሷል፡፡

ዓለም ዋንጫ ለመጀመርያ ጊዜ በኤስያ እና በአፍሪካ አህጉራት ሊዘጋጅ የበቃው በሴፕ ብላተር የግል ጥረት

እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም ውድድሩ በ2022 እኤአ ለመጀመርያ ጊዜ በአረቡ ዓለም የሚዘጋጅበት

ሁኔታም ተመቻችቷል፡፡ በዘመነ ብላተር ሌሎች ለውጦችም ተከስተዋል፡፡ የ “ሲልቨር ጎል” ህግ በ “ጎልደን ጎል”

ተተክቶ ከተሠራበት በኋላ ከዚያም ተሽሯል፡፡ ከ2002 እኤአ ጀምሮ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ አገር በማጣርያ

እንዲሳተፍ ተደርጓል፡፡ ማልያ አውለቆ የጎል ደስታን መግለፅ ከ2004 እኤአ ጀምሮ በካርድ የሚያስቀጣ ሆኗል፤

ከ20011 ጀምሮ እግር ኳስ በጎል ላይን ቴክኖሎጂ፤ እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች ስርነቀል ለውጥ እያመጣም

ቆይቷል፡፡
በዓለም ዋንጫ የፊፋ የገቢ እንቅስቃሴ ለማደጉ ሴፕ ብላተር ጉልህ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ በአንድ ዓለም ዋንጫ

መሰናዶ የፊፋ ወጭ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ቢሆንም፤ በአራት ዓመታት ውስጥ  4 ቢሊዮን ዶላር ማስገባቱ

ሪከርድ ሆኖ የተመዘገበ ነው፡፡ ፊፋ ከዚህ ገቢው ሰባ በመቶውን ለአባል አገራት ፌደሬሽኖች የእግር ኳስ እድገት

እንቅስቃሴዎች ያከፋፍላል፡፡ በየ4 ዓመቱ በየድምሩ 1.5 ቢሊዮን ዶላር የሚከፍሉ አብይ ስፖንሰሮችን እስከ

2030 እኤአ በአጋርነት ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
የኳታር ዓለም ዋንጫ መዘዝ
የሴፕ ብላተርን የፕሬዚዳንትነት ዘመን እንዳይቀጥል የተጋረጠው ዋንኛ ፈተና 22ኛውን የዓለም ዋንጫ በ2022

እ.ኤ.አ እንድታዘጋጅ ኳታር የተመረጠችበት ሁኔታ ነው፡፡
የኳታር ዓለም ዋንጫ መሰናዶ ፊፋ በአረቡ ዓለም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫ እንዲዘጋጅ ካለው

ፍላጐት አንጻር የተሰጠ ውሳኔ እንደነበር ይገልፃል፡፡ ይሁንና ለየአገሪቱ አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ፣ በስታድየሞች እና

ከሌሎች መሠረተ ልማቶች አለመሟላት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ውዝግቦች ያለፉትን ሁለት ዓመታት ዓለም አቀፉን

ተቋም አስተችተዋል፡፡  ኳታር ለ22ኛው ዓለም ዋንጫ መሰናዶ ከ60-100 ቢሊዮን ዶላር በጀት መድባለች በ20

ማይሎች ርቀት የምትገነባቸው 12 ስታድዬሞች እስከ 9 ቢሊዮን ዶላር ወጭ እንደሚኖራቸው ተገምቷል፡፡ ነገር

ግን ኳታር በ2022 እኤአ የሚካሄደውን 22ኛው ዓለም ዋንጫ የማስተናገድ እድል ያሸነፈችው በሙስና የፊፋን

ስራ አስፈፃሚ አባላት ደልላ ነው የሚለው ክስ እስካሁን መቋጫ አላገኘም፡፡ በወቅቱ ኳታር አዘጋጅ ሆና

ስትመረጥ የፊፋ ስራ አስፈፃሚ 22 አበላት ከሰጡት ድምፅ የ14ቱን ይሁንታ አግኝታ ሲሆን 8 የፊፋ ስራ

አስፈፃሚዎች አልደገፏትም ነበር፡፡ የኳታር የአዘጋጅነት ምርጫ መጭበርበሩን ያጋለጠው የእንግሊዙ ሰንደይ

ታይምስ ሲሆን የምርመራ ዘገባውን በባለ11 ገፅ ሪፖርት ይፋ አድርጎታል፡፡
በሙስና የፊፋ አባል አገራት ፌደሬሽን ሃላፊዎን ደልለዋል የተባሉት ቀድሞ የፊፋ ስራ አስፈፃሚ የነበሩት እና

ከዚሁ ሃላፊነት በከፍተኛ ውዝግብ የተሰናበቱት ኳታሯዊው ማሀመድ ቢን ሃማን ናቸው፡፡ መሃመድ ቢን ሃማም

ኳታር የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ እንድትሆን በግል ኩባንያቸው 10 ያህል የገንዘብ ልውውጦች ማድረጋቸውን

ሰንደይ ታይምስ አጋልጧል፡፡
 ለ30 የአፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን ተወካዮች ለእያንዳንዳቸው 200ሺ ዶላር እንደተሰጠ፤ በአፍሪካ እግር ኳስ

ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ድጋፍ 400ሺ ዶላር በተጨማሪ ለመደለያ እንደተለገሰ፤ ለፊፋ ስራ አስፈፃሚ አባላት

በየደረጃው ኪ50 እሰከ 100ሺ ዶላር ጉቦ መከፈሉን ጋዜጣው በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

Read 2474 times