Saturday, 27 September 2014 09:17

ታላቁ የኩፋ ፒራሚድ

Written by  መሐመድ ኢድሪስ
Rate this item
(3 votes)

አብዛኛው ሰው ስለፒራሚድ ሲነሳ ግብፅን ማሰቡ አይቀሬ ነው፡፡ እነዚህ ድንቅ የምህንድስና ጥበብ የታየባቸው

የግንባታ ውጤቶች ያሉት ግን ግብፅ ውስጥ ብቻ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በአለም ግዙፉ ፒራሚድ ያለው ሜክሲኮ

ውስጥ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1492 ክሪስቶፎር ኮሎምበስ አሜሪካንን

ከማግኘቱ በፊት ጥንታውያን ግብፃውያን አትላንቲክን ተሻግረው፣ የስልጣኔያቸውን አሻራ በሰሜን አሜሪካ

እንዳሰፈሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ለመሆኑ ፒራሚድ ሲነሳ ግብፅም አብራ የምትነሳው ለምንድነው? ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም በግብፅ ውስጥ ከ138

በላይ ፒራሚዶች መኖራቸው አንደኛው ምክንያት ሲሆን ሌላው ደግሞ ከሰባቱ የአለም አስደናቂ ነገሮች ተርታ

በቀዳሚነት የተመዘገበው ታላቁ የኩፋ ፒራሚድ  የሚገኘው እዚያው ግብፅ በመሆኑ ነው፡፡
ጥንታውያን ግብፃውያን ፈርኦኑ የመለኮት ባህሪ አለው ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ሲሞትም ነፍሱ ወደ ሰማይ አርጋ

ከአማልክቱ ጋር ትቀላቀላለች የሚል እሳቤ ነበራቸው፡፡ የፒራሚድ ዋና ጠቃሜታ ለዚሁ አላማ የሚውል ሲሆን

በጂኦሜትሪካዊ ቅርፁና የከዋክብትን አቀማመጥ መሰረት ባደረገው አቅጣጫዊ አቀማመጡ፣ ፒራሚድ ውስጥ

የተቀበረው የፈርኦኑ አስከሬን ነፍስ በቀጥታ ወደሰማይ ታርጋለች የሚል እምነት ነበራቸው፡፡
እንግዲህ ፒራሚድ አሁን ያለው ቅርፁን ከመያዙ በፊት መሰረቱ የአራት ማዕዘን ቅርፅ ኖሮት ጫፉ ሹል ያልሆነ

ግንባታ ነበር፡፡ ይህ የፒራሚድ የመጀመሪያ ደረጃው እርከን እንደሆነ ሲታወቅ ስሙም “መስተባ” በመባል

ይታወቅ ነበር፡፡
ቀደምት እንደሆነ የሚነገርለት ፒራሚድ በሰሜን ምዕራብ ሜሞፈስ ሰካራ ውስጥ የተገኘው የፈርኦን ዲጂሶር

ፒራሚድ ነው፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ2630 ግንባታው ተጀምሮ በ2611 ከክርስቶስ ልደት በፊት

እንደተጠናቀቀ ይገመታል፡፡ ፈርኦን ዲጂሶር ይህንን በዓለም የመጀመሪያውን ፒራሚድ በማስገንባቱ ብቻ

አልነበረም የሚታወቀው፡፡ ይልቁንም በፒራሚዱ ግንባታ ላይ ተሰማርተው ለነበሩት በሺዎች የሚቆጠሩ

ሰራተኞች የምግብ፣ የመጠለያና ሌሎች ለህይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን በማቅረብም ጭምር ነበር፡፡ በዚህ ጥሩ

ምግባሩ እስካሁን ግብጽ ውስጥ ከተነሱት ፈርኦኖች ደጉ ፈርኦን እየተባለ ይታወሳል፡፡ በአጠቃላይ ግብፅ ውስጥ

ከሚገኙት 138 ፒራሚዶች እጅግ ትልቁና ዝነኛው ከካይሮ ወጣ ብላ በምትገኘው ጊዛ ውስጥ ያለው ታላቁ የኩፋ

ፒራሚድ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ ፒራሚዱ ከዓለም ሰባቱ አስደናቂ ነገሮች ተርታ ውስጥ የቀዳሚነት

ደረጃ ይዞ ይገኛል፡፡ ሁሉም ኢጂፕቲሊስቶች እንደሚስማሙበት፤ ፒራሚዱ የተገነባው በአራተኛው ስርወ

መንግስት ግብፅን ይገዛ ለነበረው ለፈርኦን ኩፋ እንደሆነ ነው፡፡ ፒራሚዱ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ2560

ዓመተ አለም እንደተገነባ ይታወቃል፡፡ ሄዋን የተባለ የምህንድስና ሊቅ፣ የዚህ ታላቅ ፒራሚድ አርኪቴክት

እንደነበረ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ይህንን ፒራሚድ ለመስራት 20 ዓመታት እንደፈጀ ሲታወቅ በግንባታው

ላይ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች  (አብዛኛዎቹ ባርያዎች)  እንደተሳተፉ ይነገራል፡፡
ይህ ፒራሚድ 135.5 ሜትር ወይም 481 ጫማ ርዝመት አለው፡፡ ይህ ርዝመት እንደአውሮፓውያን የቀን ቀመር

በ1989 የፓሪሱ ኤፍል ታወር እስኪሰራ ድረስ ለ3800 አመታት ዓለም ሪከርድ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ፒራሚዱ በ230.4 ሜትር መሰረት ላይ ያረፈ ሲሆን ከሁለት ሚሊዮን ሶስት መቶ ሺህ በላይ ግዙፍ ድንጋዮች

ግንባታው ላይ ውለዋል፡፡ የእያንዳንዱ ድንጋይ ክብደት ከ2-30 ቶን የሚመዝን ሲሆነ አንዳንዶቹ እስከ 50 ቶን

ያህል ክብደት  ያላቸው ናቸው፡፡ የዘመናችንን የምህንድስና ሊቃውንት ግራ ካጋባው ነገር አንዱ፣ 50 ቶን

የሚመዝን ድንጋይ 165.5 ሜትር ከፍታ ላይ እንዴት ማስቀመጥ እንደተቻለ ነው፡፡ የፒራሚዱን የውስጠኛውን

ክፍል ለመስራት 144.000 ድንጋዮች ጥቅም ላይ ሲውሉ ሁሉም በደንብ የተጠረቡና የተወለወሉ (Polished)

ወይም ስቶን ድንጋይ ናቸው፡፡ የአሰራር ጥራታቸውም /Accuracy/ የኢንች አንድ መቶኛ ያህል ነው፡፡
እነዚህ ድንጋዮች ካላቸው ንጥረ ነገርና የአሰራር ጥራታቸው ተነሳ የፀሐይን ብርሃን እንደመስተዋት የሚያንፀባርቁ

ሲሆን ይሄም ፒራሚዱን ከጨረቃ ላይ ሳይቀር የሚታይ ሰው ሰራሽ አካል አድርጎታል፡፡
የዚህ ፒራሚድ ጠቅላላ ክብደት 5.955,000 ቶን እንደሆነ ሲገመት ይህም 16 የኒውዮርክ ኢምፓየር ህንፃ

ክብደት ያህል ነው፡፡ የኒውዮርክ ኢምፓየር ህንጻ 102 ፎቆች ያሉት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ፒራሚዱ የተሰራው

ሙቀትንና የመሬት መንቀጥቀጥን እንደሚቋቋም ሆኖ ሲሆን የውስጣዊ ክፍሉ የሙቀት መጠን ሁልጊዜ 20 ዲግሪ

ሴንቲ ግሬድ ወይም 68 ፋራናይት ብቻ መሆኑ ሌላው አስገራሚው ነገር ነው፡፡ ፒራሚዱ የተሰራባቸው የላይም

ስቶን ድንጋዮች ከአስምን ነው ወደ ጊዛ በመርከብ የተጓጓዙት፡፡
ይህ እንግዲህ የ500 ማይልስ ርቀት ያለው መንገድ ሲሆን እያንዳንዳቸው ከ2-30 ቶን የሚመዝኑ ሁለት ሚሊዮን

ሶስት መቶ ሺህ ድንጋዮች ማጓጓዝ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡
ፒራሚዱ በሚገነባበት ወቅት በየቀኑ 800 ቶን ድንጋይ ጥቅም ላይ ይውል እንደነበር ኢጂፕቶሊስቶች

ይናገራሉ፡፡ግንባታውን ሲያከናውኑ እንደ ሲሚንቶ ይጠቀሙበት የነበረው ውህድ የኬሚካል ይዘቱ በተራቀቀ

የኤሌክትሮኒክስ መሳርያ ቢመረመርም ያለው ንጥረ ነገር ምን እንደሆነ አልታወቀም፡፡ ነገር ግን ለ4500 ዓመት

ፒራሚዱን በጥንካሬ ለመያዝ ችሏል፡፡
ጥንታውያን ግብፃውያኑ በዝያን ወቅት 2 ቶን የሚመዝን ድንጋይ መብሳት የሚችል የመከሻ

መሳሪያ/dril/እንደነበራቸው ሲታወቅ ይህም ከከበሩ ድንጋዮች የተሰራ እንደነበር ይገመታል፡፡
ይህ ታላቁ የኩፋ ፒራሚድ የካፍሬና ማንኩዋር ፒራሚዶች ሲገነቡ አቀማመጣቸው የኦርዮን ኮንስታሌሽን

አቅጣጫ መሰረት አድርጐ ሲሆን ጠቀሜታው ለምን እንደሆነ ግን አልታወቀም፡፡
ስለዚህ ታላቅ ፒራሚድ ከሞላ ጐደል ልናወራ የቻልነው ይህን ያህል ብቻ ሲሆን ስለአሰራሩም ሆነ

ስለጠቀሜታው ግብፃውያኑ ምንም ፍንጭ ስላልተውልን ከዚህ በላይ ምንም መናገር አልተቻለም፡፡ 

Read 6514 times