Saturday, 27 September 2014 09:09

“እንደየትውልድህ አስብ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

           ዛሬ ቃለ መጠይቅ ማድረግ አምሮኛል…ልክ ነዋ! በአንድ በኩል ትውልዱ ሁሉ እየተገለማመጠና እየተቻቸ በየራሱ መንገድ እየሄደ ነው፡፡ በሌላ በኩል እነእንትናዬን በተመለከተ የትውልድ ግንብ እንደ በርሊን ግንብ ይፈረካከስና… ህዝቤ በጋራ መግባባት ይሠራል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…. “‘እሱ’ ላይ ቬቴራን ምናምን ብሎ ነገር የለም…” ያልከን ቬቴራን ወዳጃችን… “የማረቆ በርበሬ ጠቃ ያለበት ምግብ ማዘውተር ነው” ያልከውን እስኪ ታወራናለህማ! እናላችሁ ዛሬ ጠያቂ እሆናለሁ፡፡ አስቀድሜ ጊዜያችሁን ሰውታችሁ እዚህ ድረስ በመምጣታችሁ…(‘ብላ’ ‘ብላ’ አይደል የሚሉት የፈረደባቸው ‘ፈረንጆች’!) በጣቢያችን፣ በአድማጮቻችን… (ሌላ ዙር ‘ብላ’ ‘ብላ’…) አመሰግናለሁ፡፡

(ሁሉም ፈገግ ይላሉ፡፡ ከመሀላቸው…“ገና ማታ ተነክሮ ያደረበት ጠጅ አልለቀቀውም…” “ውይ በእናታችሁ ምን አይነት ምስኪን ጋዜጠኛ ነው!… ለዳዲ ነግሬ እኛ ቤት ዘበኛ ቢሆን ይሄኔ እንዴት እንደሚያምርበት…” “ይሄኔ እኮ አናግራቸው የተባለ የለየለት ሰላይ ይሆናል…አሁንማ መኪና በስም ዝርዝር እየታደላቸው ይመስላል…” ምናምን የሚሉ አስተያየቶች እንዳሉ እኔ ‘ጠያቂው’ ጥርጣሬ የለኝም፡፡) ጠያቂ፡— እንደምታውቁት የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ከሠላሳ ዓመት በኋላ… (‘ብላ!’ ‘ብላ!’ እቀጥላለሁ)… ስለ እግር ኳሳችን ምን ታስባላችሁ? የአሁኑ እሱ፡— አቦ…ጠቅላላ የሚመጡ አሰልጣኞች የሚመርጡትን አያውቁም፡፡ አሰላለፍ ነው እንጂ አልጄሪያን እስኪነስረው አሯሩጠን ነበር የምናሸንፈው፡፡ ጠያቂ፡— እዚህ ላይ ይቅርታ ላቋርጥህና በቀደም ዩናይትድ…(አያስጨርሰኝም) የአሁኑ እሱ፡— (ይቆጣል) እሱን ተወው፡፡ የሆነ እየተሠራብን ያለ ተንኮል አለ፡፡ እነኛ ባረኩት ነው ምናምን የተባሉት ሰዎች ደግመውበት…ተወው ብቻ፣ ለቬንገር ደስ አይበለው፡፡ የትናንቱ እሱ፡— ስለ እግር ኳሷችን አልነበረም ያልከው… ስማኝ፣ እኔ ልንገርህ አይደል… እነ ሙሉጌታ ከበደ፣ እነ ገብረመድህን፣ እነ ሚሊዮን ቢኖሩ ኖሮ አይደለም አፍሪካ ምናምን ብራዚልም አታስቸግረንም ነበር፡፡

አሰልጣኝ መጣ ሄደ ለውጥ የለውም፡፡ የትናንት ወዲያው እሳቸው፡— ኳስ! የምን ኳስ! ኳስማ ትናንት ቀረ…በእነ መንግሥቱ፣ በእነ ሉቻኖ ዘመን ቀረ፡፡ በእነ ሸዋንግዛው ዘመን ቀረ፡፡ አሁን ለራሳቸው እህል ከቀመሱ ሳምንት የሆናቸው ህጻናት ሰብስባችሁ…ብቻ አታናግረኝ፡፡ ኳሱማ ነበር ሆኖ ቀረ፡፡ የአሁኗ እሷ፡— ኧረ በእናታችሁ ኳስ፣ ኳስ እያላችሁ አትጨቅጭቁን፡፡ በዛ ሰሞን የእርግብ አሞራ ምናምን እያላችሁ ጂምና ስፓ መሄጃ መንገድ አሳጥታችሁን! እማዬ ትሙት… እንደዛ ሰዉ በሌሊት ተሰልፎ ሳየው ምን ትዝ እንዳለኝ ታውቀላችሁ…አሜሪካ አዲሱን አይፓድ ለመግዛት የተሰለፈው ህዝብ ትዝ ብሎኝ…እማዬ ትሙት ለኢትዮዽያ አዘነኩ፡፡ በእናታችሁ ሰው የኢትዮዽያን ኳስ ለማየት…. ጠያቂ፡— እንደምታውቁት ቀላል ባቡር እየተገነባ ነው፡፡ የአሁኑ እሱ፡— አሪፍ ነው…በቃ፣ ፊልም ላይ ኤል.ኤ. ምናምን አይታችሁ የለ… የትናንቱ እሱ፡— እባከህ…ተናግረህ አታናገር፡፡ ድፍን አዲስ አባባን በባቡር ለማገናኘት የታሰበው ገና በፊት ነው፡፡ የነበረ ፕላን እየወሰዳችሁ እንደ አዲስ…(ጣደፍ ብሎ ያቆማል፡፡

አንዳንዴ እኮ በየመንገዱ ካለው የትራፊክ ቀይ መብራት ይልቅ ውስጣችን የሚበራው ‘ቀይ መብራት’ አንድ ሚሊ ሜትር እንኳን ሳያንሸራተተን ነው ‘ቀጥ’ የሚያደርገው!) የትናንት ወዲያው እሳቸው፡— እኔ እኮ የምለው ይሄ ሁሉ ያዙኝ ልቀቁኝ ምንድነው? ባቡር እኮ ከገባ መቶ ዓመት ሆኖታል፡፡ ትሰማኛለህ… ባቡር፣ ባቡር የምትሉት ድፍን አፍሪካ ገና ንጣፍ መንገድ ሳይሆነው እኛ አገር የሚያቋርጥ ሠርተናል፡፡ ዕድሜ ለእምዬ ምንሊክ…(ዘወር፣ ዘወር ብለው ሁላችንንም ይገረምማሉ፡፡) የአሁኗ እሷ፡— በቀደም የአክስቴን ሌከሰስ መኪና ይዤ እዚሀ ነፋስ ስልክ መንገድ በየት በኩል ልለፍ! ገና ለገና ባቡር ይገባል ተብሎ እኛ መሰቃየት አለብን እንዴ! እማዬ ትሙት…ይሄ ከተማ እንዳስጠላኝ! ለክሪስማስ እዚህ ከተቀመጥኩማ ሞቻታለሁ፡፡ ጠያቂ፡— በአሁኑ ጊዜ ያለውን ሰውና የቀድሞውን ሰው ባህሪይ እንዴት ታዩታላችሁ? (መቼም ዘንድሮ ጥያቄው ሁሉ የሚያልቅው …‘እንዴት ታየዋለህ/ታዪዋለሽ በሚል ነው፡፡) የአሁኑ እሱ፡— አሁንማ ሰዉ ገብቶታል፣ ነቄ ህዝብ ነው፡፡

በአይ.ቲ. ዘመን መሮጥ ነው ጌታዬ፡፡ ይሄ እንደ ኮንሰርቫቲቭ…እጅ መንሳት፣ ከወንበር መነሳት…ያን ጊዜ እኮ እነሱ ከመቀመጫ የሚነሱት ጊዜ ስለነበራቸው ነው፡፡ (ይስቃል፡፡ እሷዬዋ ናሳ ላቦራቶሪ ውስጥ ተመጥኖ የተሠራ የሚመስል ሳቅ ትስቃለች፣ እኔ እንደመሳቅ አስቤ ‘ኤዲቶሪያል ፖሊሲ’ ስለማይፈቅድልኝ ጭጭ አልኩ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… የትናንቱ እሱ በንቀት ገላምጦት “የማንም ወጠጤ መጫወቻ እንሁን!” እንደሚል ያስታውቅበታል፡፡ የትናንት ወዲያው እሳቸው ዕቃ ቤት ጭስ የጠገበው ጎራዴያቸው ትዝ እንዳላቸው ግንባራቸው ላይ ያስታውቅባቸዋል፡፡) የትናንት ወዲያው እሳቸው፡— የአሁን ሰው! ምን ሰው አለና ነው…አንቱታውን ተወው አንቺ ሊልህ ምንም አይቀረው፡፡

የማንም ማቲ እየተነሳ ፋዘር ይልሀል፡፡ ማን ቢወልድ ማን! የዘንድሮ ሰው ነገርማ ተዉት፡፡ የዕድሜ እኩዮቼ እንኳንም ይሄን ሳያዩ አለፉ! የአሁኗ እሷ፡— ውይ በእናታችሁ…የድሮ ሰዎች ሲያስጠሉ! አንድ የማሚ አጎት አሉ…በቃ በገቡ በወጡ ቁጥር ካልተነሳህላቸው እንዴት እንደሚገላመጡህ! ማሚ ትሙት… የድሮ ሰው የማላይበት የት እንደምሄድ! ጠያቂ፡— ስለ አገራችን ፖለቲካ ምን ታስባላችሁ? (ስቱዲዮ ላይ የአርከቲከ በረዶ እንዳለ ተዘረገፈበት፡ ሳቅ የለ፣ ምን የከለ…ሁሉም ጭጭ ብሎ ተቀመጠ፡፡ ትንሽ ቆይቶ የትናንት ወዲያ እሳቸው ብዙም ድምጽ ሳያሰሙ ቀስ ብለው ይስቃሉ፡፡ የትናንት ወዲያው እሳቸው፡— የአገራችን ፖለቲካ አልክ…አንተማ ምን ታደርግ… እንጀራህ ነው፡፡ የአገራችን ፖለቲካ አልክ! (ከልባቸው ሳቁ፡፡ እኔም ሳቅሁ…አለቃዬ የሰውዬውን ንግግራቸውን መቁረጥ ብቻ ሳይሆን ንግግራቸውን የቀዳሁበትን ቴፕ በመቀስ ከመቁረጥ እንደማይመለስ ስለማውቅ እኔም ለራሴ ሳቅሁ፡፡) የአሁኗ እሷ፡— ግን በእማዬ ሞት እንዳትስቁብኝ… እንዴ፣ ሰዎቹ ምንድነው በየቴሌቪዥኑ የሚጨቃጨቁት! እማዬ ትሙት… እኔማ አንድ ጊዜ በቴሌቪዥን ፖለቲከኞቹ ሲጨቃጨቁ ለአባዬ ምን አልኩት መሰላችሁ… (ከት ብላ ሳቀች) ምን አልኩት መሰላችሁ… ‘ዳድ ይሄ ሆረር ፊልም መቼ ነው ሲኒማ ቤት የሚመጣው?’ አልለው መሰላችሁ! (እንደገና ሳቀች!) አባዬ ደግሞ ተኮሳተረና…“እንዲህ እንዳሰኘሽ እየተናገርሽ ጦስ እንዳታመጪብን!” ሲለኝ ሜሴጁ ገባኝና በቃ…አይ ፌል ሳይለንት፡፡

(የትናንቱ እሱ ከንፈሩን ሲነክስ አየሁት፡፡ የማን ዘፈን ትዝ እንዳለውም ጠረጠርኩ!) ጠያቂ፡— እንደምታውቁት ዘፋኞች እየፈሉ ነው፡፡ ስለ ሙዚቃችን ምን ታስባላችሁ? የአሁኑ እሱ፡— አሪፍ ነው፣ ለውጥ አለ፡፡ አየህ ሂፕ ሆፕን ብሉዝን ምናምን ከእኛ ሙዚቃ ጋር ስትቀላቅለው ፈጠራ ማለት አይደል! የአሁኗ እሷ፡— የእኛ ሙዚቃ ኦ ማይ ጋ….ድ! ምን ሙዚቃ አለና! እማዬ ትሙት…እኔ አማርኛ ዘፈን ቤታችን ሲለቀቅ ቤድሩም ገብቼ ኢርፎኔን ነው የማደርገው፡፡ ሪሃናና ሻኪራን በሰማሁበት… እማዬ ትሙት ልክ አይደላችሁም! የትናንቱ እሱ፡— የሙዚቃ ጎልድን ታይም…. የአሁኑ እሱ፡— ይቅርታ በእናንተ ጊዜ በቃ ተጋደል፣ አሳደው ምናምን አይደል እንዴ ሲዘፈን የነበረው! የአሁኗ እሷ፡— እኔ አላምንም! በዘፈን ነው ተጋደል ምናምን የሚባባሉት! የትናንቱ እሱ፡— (ተቆጣ) ተጋደልም ተባለ ምንም የኢትዮዽያ ሙዚቃ ወርቃማ ዘመን ነበር፡፡ የትናንት ወዲያው እሳቸው፡— ስማኝ ሙዚቃችንን አይደል ያልከው…እኔ ልንገርህ፣ ሙዚቃችን ሞቶ፣ ተገንዞ አፈር ከገባ ቆየ፡፡ እነ ጥላሁን በዘፈኑበት መድረክ፣ እነ ብዙነሽ በዘፈኑበት መድረክ አሁን ሱሪውን ጭኑ ድረስ እያወረደ፣ ሲጨፍርበት..ከዚህ የባሰ ምን ስምንተኛው ሺህ አለ! እኔ እንደውም አሁን፣ አሁን እቤት ልጆቹ ለዘፈን ብለው ቴሌቪዥን ሲከፍቱ ወደ መኝታዬ ነው የምሄደው፡፡ ዘፋኝ ነን የሚሉት ሲጨፍሩ ሳያቸው ዛር የሰፈረባቸው፣ ጋኔን ያጠናፈራቸው ነው የሚመስለኝ፡፡ ዳንስ አይሉት፣ እስክስታ አይሉት እንዲሁ መርገፈገፍ! ጠያቂ፡— እንደው ስለወደፊቱ ምን ታስባላችሁ? (መቅለጥ ጀምሮ የነበረው በረዶ እንደገና ይጋገር ጀመር፡፡ ልክ ሳይነጋገሩ ያደሙብኝ ነው የመሰለኝ፡፡ በቃ ጭጭ! “እንደየትውልድህ አስብ” የተባለ ይመስል በምንም ነገር ላይ ሊስማሙ ያልቻሉ ትውልዶች፤ በመጨረሻ ጥያቄዬ ላይ ሳይነጋገሩ ተስማሙብኝ፡፡ ‘ጭጭ’ አሉ! እኔም እንደነሱ ‘ጭጭ’ ከማለቴ በፊት እንደ መክፈቻው ሁሉ የመዝጊያ ‘ብላ’፣ ‘ብላ’ ለፈለፍኩና አጀብኳቸው — ‘ጭጭ!’) ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2904 times