Saturday, 27 September 2014 08:49

መሠረት በጎ አድራጎት ድርጅት ከ4ሺ በላይ ደብተሮች እያከፋፈለ ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

• መስራቿ ድጋፋችሁን ፈጣን አድርጉት ብለዋል

መሠረተ በጎ አድራጎት ድርጅት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ቤተሰብ ልጆች ከ4 ሺ በላይ ደብተሮችን አሰባስቢ እያከፋፈለ እንደሆነ የድርጅቱ መስራች ወ/ሮ መሰረት ዘውገ ገለፁ፡፡ ዘንድሮ 10ሺህ ደብተሮችን ከ10ሺህ በጎ አድራጊዎች ለመሰብሰብና የሰበሰቡትን ደብተሮችም በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብና በአዲስ አበባ ለሚገኙ ደብተር መግዛት የማይችሉ ሕፃናት ለመስጠት አቅደው እንደነበር የጠቆሙት መስራቹ፤ እስካሁን ማሰባሰብ የቻሉት ግማሽ ገደማ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ “10ሺህ ደብተር ከ10ሺህ በጎ አድራጊ ያልነው፣ እኛው በእኛ እንድንደጋገፍ በማለት ነው፡፡

ጥያቄውን ለአንድ ባለሀብት ወይም ድርጅት ብናቀርብ፤ የፈለግነውን ያህል ደብተር ማግኘት እንችል ነበር፡፡ የእኛ ዓላማ ግን ብዙዎችን የዚህ በጎ ተግባር ተሳታፊ ማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን ደብተር መሰብሰቡ እንዳሰብነው ቀላል አይደለም - ከባድ ነው፡፡ ዓላማችንን የሰሙ ብዙ ሰዎች ድጋፍ አድርገውልናል፡፡ እስካሁን ከ4ሺህ በላይ እሽግ ደብተሮች ተረክበናል፡፡ ድጋፉ አሁንም ቀጥሏል፡፡ ትናንት 50፤ ዛሬ ደግሞ 62 እሽግ ደብተሮች ተረክበናል፡፡ ወደፊትም ብዙ ሰዎች ስለዓላማችን ሲሰሙና ሲረዱ ድጋፉ እንደሚቀጥል እርግጠኛ ነኝ” ብለዋል መስራቿ፡፡ አሁን ማከፋፈሉን ጀምረናል፡፡ በአዲስ አበባ መሠረት በጎ አድራጎት ድርጅት የሚረዳቸው 480 ሕፃናት አሉ፡፡ በየዓመቱ መስከረም 4 ቀን ዓመታዊ በዓላችንን እናከብራለን፡፡ ዘንድሮም በዓላችንን ስናከብር ዩኒፎርም ላሰፋንላቸው 200 ሕፃናትና ደብተር ላዘጋጀንላቸው 480 ሕፃናት ደብተር ሰጥተናል፡፡ ለአንድ ተማሪ 12 ደብተር (አንድ እሽግ)፣ 2 እስክሪብቶ፣ 2 እርሳስ፣ 2 መቅረጫ፣ 2 ላጲስ ሰጥተናል፡፡

ባለፈው ማክሰኞ፣ በትንሳኤ ብርሃን ት/ቤት ለሚማሩ 290 ሕፃናት፣ በዚህ ሳምንት ረቡዕ ዕለት ደግሞ እኛም ድጋፍ ያስፈልገናል ብሎ ለጠየቀው ሙን ላይት ስትሬት ችልድረን (የጎዳና ተዳዳሪዎች) ት/ቤት ለ90 ልጆች ደብተርና መጻፊያ ሰጥተናል፡፡ እንዲሁም በወልዲያ ለሚገኝ የአካል ጉዳተኞችና ወላጆቻቸውን በሞት ላጡ 500 ተማሪዎች፣ በዋድላ ዳላንታ ከተማ ለተመረጡ 500 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ለመስጠት ነገ ወደ አማራ ክልል እንደሚሄዱም ወ/ሮ መሰረት ተናግረዋል፡፡ ቀጣዩ የክልል ጉዟችን ወደ ኦሮሚያ ነበር፡፡ በመስቀል በዓል ምክንያት እንዲዘገይ ስለተነገረን ደቡብ ክልል ተጉዘን ለኮንሶ ወረዳ 1,400 ሕፃናት የመማሪያ ቁሳቁስ ለመስጠት እንሄዳለን፡፡ በመቀጠል ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ለያቤሎ አርብቶ አደር አካባቢ ሕፃናት ከ1000-1500 ደብተሮች ለመስጠት አቅደናል፡፡

ለጉራጌና በኦሮሚያ ዞን ለወበራ ወረዳ በመቶዎች የሚቆጠሩ እሽግ ደብተሮችን ለማሰራጨት አቅደናል፡፡” ብለዋል መስራቿ፡፡ ይህን የበጎ ተግባር ስራ የጀመርነው የማትሪክ ተፈታኞች የተፈተኑበትን እርሳስ የመግዛት አቅም ለሌላቸው ሕፃናት እንዲሰጡን በመጠየቅ ነበር፡፡ በዚሁ መሰረት ከፈተና ጣቢያው 23,800 እርሳሶች አሰባስበን አከፋፍለናል፡፡ አንድ ሰው 107 ብር በማውጣት አንድ ልጅ ዓመቱን ሙሉ ማስተማር እንደሚችል በተለያዩ ሚዲያዎች ቅስቀሳ አድርገናል፡፡ በዚህም ሀሳብ ብዙ ሰዎች ተስማምተው ባደረጉት ድጋፍ ከፍተኛ ውጤት ተገኝቷል፡፡ ለምሳሌ፣ አትላንታ - አሜሪካ ያሉ ኢትዮጵያውያን በሬዲዮ የተላለፈውን መልዕክት ሰምተው 8፣ 8 ዶላር አሰባስበው 120 ሺህ ብር ልከውልናል፡፡ ወገን ወገኑን ሲረዳ በጣም ደስ ይላል በማለት ስሜታቸውን ገልጸዋል፡፡ በመጨረሻም ወ/ሮ መሠረት፣ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ከሚኖርባት አዲስ አበባ 10ሺህ ደብተር መሰብሰብ ቀላል ነው ብለን ነበር የጀመርነው፡፡ ነገር ግን እንዳሰብነው አይደለም - ከባድ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ሀሳቡን ሲሰሙ ፈቃደኛ ቢሆኑም ወዲያው ሀሳባቸውን ተግባራዊ አያደርጉም፡፡

ክፋት ሳይሆን በቸልተኝነት እንደሆነ ይገባናል፡፡ እርምጃቸው በዘገየ ቁጥር መማር እየቻለ በደብተር ችግር ትምህርቱን የሚያቋርጥ ተማሪ በጣም ብዙ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከማሳዘንም በላይ ወደፊት ፀፀት ስለሚሆን እባካችሁ ድጋፋችሁ ፈጣን አድርጉ በማለት ጠይቀዋል፡፡ መሠረት በጎ አድራጎት ድርጅት፣ በ2004 የተቋቋመና በሕፃናትና ሴቶች ጉዳይ ላይ አተኩሮ የሚሰራ አገር በቀል ድርጅት እንደሆነ ይታወቃል፡፡

Read 3023 times