Saturday, 27 September 2014 08:47

‘ንግስተ ሳባ’ እና ‘ባቲ’ በኒውዮርክ ምርጥ 10 የአፍሪካውያን ሬስቶራንቶች ዝርዝር ተካተቱ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

             ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት ከኒውዮርክ አፍሪካን ሬስቶራንት ዊክ ጋር በመተባበር ባወጣው በኒውዮርክ ሲቲ የሚገኙ ምርጥ አስር የአፍሪካውያን ሬስቶራንቶች ዝርዝር ውስጥ፣ የኢትዮጵያውያኑ ሬስቶራንቶች ‘ንግስተ ሳባ’ እና ‘ባቲ’ ተካተቱ፡፡ በኒውዮርክ ሲቲ የአፍሪካውያን ምግቦችን በማቅረብ ከሚታወቁት ከ50 በላይ ሬስቶራንቶች መካከል፣ በሚያዘጋጇቸው ምግቦች ጣዕም፣ በመስተንግዶ፣ በውስጣዊ ድባብና ዘላቂነት በሚሉ መስፈርቶች ከተመረጡት 10 ሬስቶራንቶች መካከል የኤርትራውያኑ ‘ምጽዋ’ም ይገኝበታል፡፡

ከታዋቂው ታይምስ አደባባይ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውና በሼፍ ፊሊጶስ መንግስቱ ባለቤትነትና አስተዳዳሪነት የሚመራው ንግስተ ሳባ፣ የኢትዮጵያውያንን ባህላዊ ምግቦች እያጣጣሙ ከወዳጅ ዘመድ ጓደኛ ጋር ለመጨዋወት ተመራጭ ቦታ እንደሆነ የገለጸው ፎርብስ፤ የሚያቀርበው ጣፋጭ ኬክም ልዩ መገለጫው እንደሆነ ጠቁሟል፡፡ በባህላዊ የቤት ማስጌጫዎች የተዋበው ይሄው የኢትዮጵያውያን ሬስቶራንት፤ በተለያዩ የአሜሪካ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ የዘገባ ሽፋን እንዳገነ ፎርብስ አስታውሷል፡፡ በአዲስ አበባ በተወለደችው ህብስት ለገሰ ባለቤትነት የሚንቀሳቀሰው ባቲም፣ ጣፋጭ የኢትዮጵያውያን ምግቦችን በአስደናቂ መስተንግዶ ለደንበኞቹ በማቅረብ እንደሚታወቅ ፎርብስ ገልጿል፡፡ የሴኔጋሎቹ “ፖንቲ ቢስትሮ”፣ “ካፌ ሪዮ ዲክስ” እና “ሌኖክስ ሳፋየር”፣ የደቡብ አፍሪካዎቹ “ማዲባ” እና “ቶላኒ ኢተሪ ኤንድ ዋይን”፣ የናይጀሪያው “ቡካ” እንዲሁም የአይቬሪኮስቱ “ፋራፊና ካፌና ላውንጅ”ም፣ በኒውዮርክ ሲቲ ምርጥ 10 የአፍሪካውያን ሬስቶራንቶች ዝርዝር እንደተካተቱ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 2874 times