Saturday, 20 September 2014 11:55

የመጀመሪያዋ በጐ ፈቃደኛ የኢቦላን የሙከራ ክትባት ወሰደች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

አሜሪካ 300 ወታደሮች ወደ ላይቤሪያ ልትልክ ነው

እንግሊዛዊቷ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ ሩት አትኪንስ ሰሞኑን በኦክስፎርድ ለ60 በጎ ፍቃደኞች ሊሰጥ የታቀደውን
የኢቦላ ቫይረስ የሙከራ ክትባት በመውሰድ የመጀመሪያዋ በጎ ፈቃደኛ እንደሆነች መሆኗን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የሙከራ ክትባቱን የሚወስዱ በጎ ፈቃደኞች እንደሚፈለጉ በቢቢሲ ሬዲዮ መስማቷን የገለፀችው አትኪንስ፣
በምዕራብ አፍሪካ ሁኔታው በጣም አሳዛኝ ስለሆነና የዚህ ክትባት ሂደት አካል መሆን ትልቅ ውጤት ለማምጣት
በሚደረገው ጥረት ማበርከት የምችለው ትንሹ ነገር እንደሆነ በማሰብ፣ ክትባቱን በበጎፈቃደኝነት ለመውሰድ
ወስኛለሁ” ብላለች፡፡
ክትባቱ ከኢቦላ ቫይረስ ትንሽ የዘረመል ንጥረ ነገር ብቻ የያዘ በመሆኑ ተከታቢው በበሽታው እንደማይያዝ
የተገለፀ ሲሆን በኦክስፎርድ የጄነር ኢኒስቲቲዩት ዳይሬክተርና የሙከራ ክትባቱ መሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አድርያን
ሂልም፤ “ይሄ ክትባት ማንንም ኢቦላ ያስይዛል የሚል ቅንጣት ስጋት የለም” ብለዋል፡፡
ክትባቱን ለመወጋት ስታስብ የደህንነቷ ጉዳይ እንዳላስጨነቃት የተናገረችው ሚስ አትኪንስ፤ የ15 ዓመት ታዳጊ
ልጇ የኢቦላ ቫይረስ ተሰጥቷት የምትሞት መስሎት እንደነበርና እንዳረጋጋችውም ገልፃለች፡፡
ብዙ ጊዜ አዲስ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ ከማግኘቱ በፊት ለዓመታት በሰዎች ላይ ሙከራ ሲደረግ
ይቆይ ነበር ያለው ቢቢሲ፤ በምዕራብ አፍሪካ የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ አጣዳፊነት ግን ይሄ የሙከራ ክትባት
በአስደናቂ ፍጥነት ጥቅም ላይ እንዲውል ጥረቱ እንዲጠናከር አድርጓል ብሏል፡፡
በሰዎች ላይ የሚደረገው ሙከራ ውጤታማ ሆኖ ከተገኘ፣ ክትባቱ በፈረንጆች ዓመት መጨረሻ ላይ በቫይረሱ
በተጠቁ አካባቢዎች የሚገኙ የጤና ሰራተኞችን ከበሽታው ለመከላከል ጥቅም ላይ እንደሚውል ታውቋል፡፡
ያን ጊዜ ግን ለ10ሺ ሰዎች ያህል የሚሆን ክትባት እንደሚያስፈልግ የተገለፀ ሲሆን በምዕራብ አፍሪካ ክፉኛ
የተጠቁ አካባቢዎች ላይ የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎችን ከቫይረሱ ለመከላከል ጥቅም ላይ ይውላል ተብሏል፡፡
ክትባቱ እየተሰራ የሚገኘው ግላክሶስሚዝክላይን በተባለ ኩባንያና በአሜሪካ ብሔራዊ የጤና ተቋም ሲሆን፣
የእንግሊዝ ዓለምአቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ የምርምር ተቋማት ለሙከራ ክትባቱ የገንዘብ
ድጋፍ እንዳደረጉ ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የኢቦላ ቫይረስን ለመከላከል እገዛ የሚያደርጉ 3ሺ ወታደሮችን
ወደ ላይቤሪያ የመላክ ዕቅድ እንዳላቸው ባለፈው ማክሰኞ አስታወቁ፡፡ ኦባማ ይሄን ያስታወቁት የላይቤሪያዋ
ፕሬዚዳንት አለን ጆንሰን ሰርሊፍ በሽታውን ለመከላከል እገዛ ያደርጉላቸው ዘንድ ለኦባማ በቀጥታ ያቀረቡትን
ጥያቄ ተከትሎ እንደሆነ ታውቋል፡፡
የአሜሪካ ወታደራዊ ሃይል የህክምና ማዕከሎችን ግንባታ በመቆጣጠርና የጤና ሰራተኞችን በማሰልጠን
ለላይቤሪያ መንግስት እገዛ እንደሚያደርግ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በምዕራብ አፍሪካ ለተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ የዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ፈጣን ያልሆነ ምላሽ ትችት ሲሰነዘርበት
፣ቆየቱ ይታወቃል፡፡
በበሽታው ክፉኛ የተጠቁት የምዕራብ አፍሪካ አገራት ሴራሊዮን፣ ላይቤሪያና ጊኒ ሲሆኑ ወረርሽኙ ከ2400 በላይ
ሰዎችን ለህልፈት እንደዳረገ ተጠቁሟል፡፡ ከእዚህ የሞት አደጋ ውስጥ ግማሹ የተከሰተው በላይቤሪያ ነው፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት፤ አገሪቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ሰዎችን በቫይረሱ ልታጣ እንደምትችል በቅርቡ
አስጠንቅቋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኃላፊዎች፣ በጄኔቫ በሚያካሂዱት ስብሰባ ለወረርሽኙ
በተሰጠው ዓለም አቀፍ ምላሽ ላይ እንደሚወያዩ ቢቢሲ ጠቁሟል፡፡
የጋና ፕሬዚዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ ባለፈው ሰኞ ወረርሽኙን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤
“በምዕራብ አፍሪካ ለተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ከፍተኛና ፈጣን የውጭ እርዳታ ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡

Read 2963 times