Saturday, 20 September 2014 11:51

ከኢቦላ ያገገሙ ታማሚዎች ደም በድብቅ እየተሸጠ ነው

Written by 
Rate this item
(5 votes)

የኢቦላ ቫይረስ በተስፋፋባቸው የምዕራብ አፍሪካ አገራት በበሽታው ተይዘው የነበሩና ከህመማቸው ያገገሙ
ሰዎች ደም፣ ታማሚዎችን ለማከም በሚል በድብቅ እየተሸጠ መሆኑን ሲኤንኤን ከትናንት በስቲያ ዘገበ፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በበሽታው ተይዘው ያገገሙ ሰዎች ደም በውስጡ የኢቦላ
ቫይረስን የሚያጠፋ ንጥረ ነገር አለው በሚል እየተናፈሰ ባለው መረጃ የተነሳ፣ በአገራቱ የሚገኙ የኢቦላ
ታማሚዎች ደሙን በድብቅ ከሚሸጥበት ስውር ገበያ እየገዙ ይገኛሉ፡፡
የአለም የጤና ድርጅትን በሽታው በተስፋፋባቸው የምዕራብ አፍሪካ አገራት እየተከናወነ ያለውን ስውር የደም
ሽያጭ ለማስቆም ከአገራቱ መንግስታት ጋር በመተባበር እየሰራ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ ታማሚዎች
በአገራቱ ሆስፒታሎች በሚሰጠው ህክምና ተስፋ በመቁረጥ ፊታቸውን ወደዚህ ህገወጥ ገበያ ማዞራቸውን
ገልጿል፡፡ ዘ ቴሌግራፍ በበኩሉ፤ ምንም እንኳን ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ደም ታማሚዎችን ቶሎ እንዲድኑ
በማድረግ ረገድ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ቢረጋገጥም፣ ደሙ ኤችአይቪ ኤድስን በመሳሰሉ ቫይረሶች የተበከለ
መሆን አለመሆኑ ሳይረጋገጥ በድብቅ የሚሸጥ መሆኑ ሌላ ቀውስ እንዳያስከትል ስጋት መፍጠሩን ዘግቧል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ቃል አቀባይ ማርጋሬት ሃሪስን ጠቅሶ፣ ድርጅቱ ከኢቦላ በሽታ ያገገሙ ሰዎችን ደም
በአግባቡ መርምሮ በመሰብሰብና በማጠራቀም ለተመሳሳይ ህክምና ለማዋል የሚያስችል ደህንነቱ የተጠበቀ
አሰራር እየቀየሰ እንደሚገኝ የዘገበው ዋሽንግተን ፖስት በበኩሉ፣ ድርጅቱ መሰል የደም ህክምናን እንደሚደግፍ
ቃል አቀባይዋ መናገራቸውን አስታውቋል፡፡

Read 2839 times