Print this page
Saturday, 20 September 2014 11:14

“ኢህአዴግ ደንግጧል ወይስ ተለውጧል?”

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(5 votes)

ከኢትዮጵያ ቴሌኮም ይልቅ ህልሜን አመንኩት!

    ባለፈው ሳምንት በህልሜ ያየሁት ነገር አስገራሚ ነው፡፡ በአብዛኛው በህልማችን የምናየው ነገር የግል ህይወታችን ላይ የሚያተኩር ይመስለኛል፡፡ መቼም ናላውን ከሚያዞረው የኑሮ ውድነት ሃሳብ ወጥቶ ስለአገሩ ባለ ሁለት ዲጂት የኢኮኖሚ ዕድገት በህልሙ የሚያይ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ (ቢያይማ ከኑሮ ውድነት ይወጣ ነበር!) ስለ አገሪቱ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበት ወይም ስለ ስልጡን የፖለቲካ ባህል መዳበር ተኝቶ የሚያልም አለ ብዬ አልገምትም፡፡ (በህልም ዲሞክራሲ ማየት እንዴት ነው? ) በነገራችሁ ላይ ኢህአዴግ በህልሙ ያየውን ነገር ሁሉ እኛም ብናይለት (“ኮፒ ፔስት” ነው ታዲያ!) እንዴት ጮቤ እንደሚረግጥ አልነግራችሁም፡፡ በቃ ሃሳባችን ከሃሳቡ፣ህልማችን ከህልሙ ቢገጥምለት በእድሜው ላይ 40 ዓመት ይጨምር ነበር (ከ30-40 ዓመት በሥልጣን ላይ ለመቆየት ካሰበው ውጭ!) አንዳንዴ ሳስበው “እኔን ምሰሉ!” ማለት ምን ክፋት አለው እላለሁ፡፡

(በፍቅር ከሆነ የለውም!) ነገር የሚመጣው መቼ መሰላችሁ? በውዴታ ሳይሆን በግዴታ ምሰሉኝ ሲባል ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ሰርክ አፉን “ዲሞክራሲ” በሚል ቃል ለሚያሟሽ ፓርቲ፤ በግድ “እኔን ሁኑ” ማለት ጨርሶ አያስኬድም፡፡ (ጸረ - ዲሞክራሲያዊ ነው!) ለነገሩ እኔን ምሰሉ እኮ ማለት ሌላ አይደለም - በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ጠበል ተጠመቁ ማለት ነው፡፡ (የወደደ ይጠመቃል!) እኔ የምለው---ከአዲስ አበባ ህዝብ ውስጥ ምን ያህሉ “ልማታዊ”፣ ምን ያህሉ ደግሞ “ኪራይ ሰብሳቢ” እንደሆነ በጥናት የተደገፈ መረጃ አለ እንዴ? (ለጠቅላላ እውቀት ነው!) እንደ ኢህአዴግ ልፋት ቢሆንማ፣ ይሄኔ ከጠቅላላው የአገሪቱ ህዝብ 95.8 በመቶ ያህሉ “ልማታዊ” ይሆን ነበር፡፡ (ከምርጫ ውጤት ጋር ተመሳሰለባችሁ አይደል!?) አንድ ጥያቄ አለኝ -----ከኢህአዴግ ጋር ንኪኪ ሳይኖር (የፎረም… የሊግ.. ምናምን!) ልማታዊ መሆን ይቻል ይሆን? (ልማታዊ ባለሃብት፣ ልማታዊ ቲያትረኛ፣ ልማታዊ ዘፋኝ፣ ልማታዊ ሃኪም፣ ልማታዊ ጋዜጠኛ፣ ልማታዊ ሰው … ወዘተ!!) የ2007 እቅዴ በኢህአዴግ ያልታቀፈ ልማታዊ ጋዜጠኛ መሆን ነው፡፡ (“አብዮታዊ ዲሞክራሲ” አልወጣኝም!) አያችሁልኝ የኔን ነገር --- ስለ ኢህአዴግ ህልም ሳወራ የራሴን ህልም ሳልነግራችሁ! እናላችሁ --- ባለፈው ሳምንት በዓይነቱ ለየት ያለ፣ “ውጤት ተኮር” ህልም ነው ያየሁላችሁ፡፡

(በአፍሪካ በዓይነቱ የመጀመሪያው ህልም ሳይሆን አይቀርም!) አይዞአችሁ አትጨናነቁ ---የእኔ ህልም cost effective ነው - ቡናና ህልም ፈቺ አይፈልግም፡፡ ወደ ህልሜ ከመግባቴ በፊት አንዳንድ መረጃ ልጠቁማችሁ፡፡ እንግዲህ በቢሮአችን የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ከተቋረጠ ወደ ሁለት ወር ገደማ ሆኖታል፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም ሃላፊ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው፣ “ከእንግዲህ የኢንተርኔትና የኔትዎርክ ችግር አከተመ” ባሉ በሳምንቱ ሁለቱንም አጣን፡፡ ከዚያስ? ከሁለት ወር ገደማ በኋላ ባለፈው እሁድ፣ የተቋረጠው የቢሮአችን ኢንተርኔት በህልሜ ሲሰራ አየሁ፡፡ በህልሜ ነው ያልኩት፡፡ ህልሜ ግን ከሌሎች ህልሞች ለየት ያለ ነበር፡፡ በነጋታው ቢሮ ስገባ ህልሜ እውን ሆኗል፡፡ ኢንተርኔታችን መስራት ጀምሯል!! በህልሜ ያሁትን ኢንተርኔት፣ በነጋታው በእውኔ አየሁት፡ እናም ከአሁን በኋላ የኔትዎርክና የኢንተርኔትን ጉዳይ በተመለከተ፣ ኢትዮ-ቴሌኮምን ሳይሆን ህልሜን ነው የማምነው! ይታያችሁ… ላለፉት 2 ወራት ከቴሌ አካባቢ ዝር ያለ ሰው የለም፤ በዚህ ጊዜ መስራት ይጀምራል ብሎ የነገረንም አልነበረም፡፡ (ቢነገረንስ ስናምን አይደል!) ግን ዕድሜ ለህልሜ! የኢንተርኔት አገልግሎት መጀመሩን በምስል አስደግፎ አሳየኝ፡ ከአሁን በኋላ ኢንተርኔት ብቻ ሳይሆን ሌላውንም የማምነው በህልሜ ሳይ ብቻ ነው፡፡ የትራንስፖርት እጥረት በሉት የመብራት መጥፋት፣ የመልካም አስተዳደር ችግር በሉት የኑሮ ውድነት ወዘተ… በዚህ በዚህ ጊዜ ይቀረፋል ተብሎ በኢቴቪ (EBC) ይሁን በጋዜጣዊ መግለጫ ቢነገር በጄ አልልም (“ካልታዘልኩ አላምንም አለች” አሉ!) በቃ በህልሜ እስከማይ ድረስ እጠብቃለሁ፡፡

(ህልሜ አይዋሽማ!) በነገራችሁ ላይ እነዚህ ችግሮች በእርግጥም ተፈተው ማየት የምትሹ ከሆነ፣ ሌላ ሌላውን ትታችሁ ህልማችሁን ብትጠብቁ ይሻላችኋል፡፡ የእናንተ ህልም እንደኔ ቀጥተኛ ሳይሆን ሰምና ወርቅ የበዛበት ቅኔ ከሆነ ደግሞ ለእኔ ፀልዩልኝ (ቶሎ በህልሜ እንዲታየኝ!) ግን አይገርምም---ከእውኑ ዓለም የህልም ዓለም መሻሉ! እኔ የምላችሁ… የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ከሞቱ በኋላ ኢህአዴግ አካባቢ የተለወጠ ነገር አለ እንዴ? (በህልሜ እስኪታየኝ እኮ ነው!) ባለፈው ሳምንት እዚሁ ጋዜጣ ላይ ቃለመጠይቅ የተደረገላቸው ጉምቱው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፤ በመጪው ምርጫ ዙሪያ ከመንግስት ጋር ለመወያየት ጥያቄ አቅርበው ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ጠቁመው፣“የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ከሞቱ በኋላ በትንሹ የነበረው የመነጋገር ዕድል ተዘግቷል፤ እስካሁን ያየነው ነገር የለም” ብለዋል - በተስፋ መቁረጥ ስሜት (“በአገሬ ጉዳይ ተስፋ አልቆርጥም” ማለታቸውን አልዘነጋሁትም!) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንድ ታዋቂ ምሁር፣ የ2006 የጋዜጠኞችን እስርና ስደት በተመለከተ ሲናገሩ፤ “ኢህአዴግ ከጠ/ሚኒስትሩ ህልፈት በኋላ ደንግጧል” ብለዋል፡፡

የእኛ ነገር እኮ ግርም ይላል፡፡ በህይወት ሳሉ በተቃዋሚዎች ዘንድ አንዴም በበጎ ተነስተው የማያውቁት የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር፤አሁን እየተመሰገኑ ነው (“ሰው ካልሞተና ካልራቀ አይመሰገንም” አሉ!) በነገራችሁ ላይ --- ከእሳቸው ሞት በኋላ የመወያየት ዕድል ይጥበብ ይስፋ የሚያውቀው ኢህአዴግ ነው (የስነ-ምግባር ኮዱ አሁንም እያወዛገበ እኮ ነው?) ከቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ህልፈት በኋላ ኢህአዴጎች ደንግጠዋል የሚለውም ጉዳይ ለእኔ ብዙ አልተዋጠልኝም፡፡ ቆይ ምንድነው የሚያስደነግጣቸው?! (ገዢ ነው ተገዢ የሚደነግጠው?) ህዝቡና አገሩ እኮ አልተለወጡም! እኔ ግን ምን ይመስለኛል መሰላችሁ? ኢህአዴግ ደንግጦ ሳይሆን ተለውጦ ነው፡፡ ለውጡ ለበጎ ይሁን ለክፉ ገና አለየለትም፡፡ እኔ የምለው--- ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ንግግራቸው ቁጣና ኃይለ ቃል ያዘለ አልሆነባችሁም ?(“የማይመቱት ልጅ ሲቆጡት ያለቅሳል” እንዳትሉኝ!) በሉ የቅርብ ጊዜ እቅዴን ልንገራችሁና ልሰናበት፡፡ በመጪው ግንቦት ወር አገራዊ ምርጫ ይካሄዳል፡፡ (የውጭ ታዛቢ አይኖርም ነው የተባለው?) እናም--- በምርጫው ማን እንደሚሳተፍና ማን “ፎርፌ” እንደሚሰጥ፣ ስለምርጫው ፍትሃዊነትና ዲሞክራሲያዊነት ወዘተ-- ለማወቅ የምርጫ ቦርድን መግለጫ አልጠብቅም፡፡ እኔ ያቀድኩት በህልሜ ለማየት ነው - እንደ ኢንተርኔቱ! ዘመኑ የህልም ነው!!

Read 3868 times