Saturday, 20 September 2014 11:05

“ግብረ ሰናይ ተግባር”

Written by  ከጉማራ ዙምራ zmtm1229@yahoo.com
Rate this item
(22 votes)

በ“ጆሲ” እና “ሰይፉ” ፕሮግራሞች ሲለካ!

          ኢቢኤስ ቴሌቪዥን፤ በቅርቡ “አወቃቀሬን አሻሽላለሁ” ብሎ “ኢብኮ” በሚል ስያሜ ብቅ ላለው ኢቲቪ፣ እንደ አማራጭ በመሆን የተለያዩ አዝናኝና አስተማሪና ዝግጅቶችን እያቀረበልን ነው፡፡ ተፎካካሪ ሊባሉ የሚችሉ ቶክሾዎችም የይዘትና ቅርጽ ልዩነት ሳይኖራቸው እንግዶቻቸውን እያቀረቡልን፣ ከስኬታቸውም ይሁን ከውድቀታቸው ትምህርት እየቀሰምን ነው፤ በሂደት ተመልካችን እንዳያሰለቹ ስጋት ቢኖረኝም፡፡ በተለይ ጆሲ እና ሰይፉ ሾዎች ፉክክሩ እያየለ ሲመጣ፣ ከተቋቋሙበት አላማ ውጪ በልዩ ልዩ የግብረ ሰናይ ተግባራት ተጠምደው መዋላቸው ሰርክ ተግባራቸው አድርገውታል፡፡ ጆሲ በዚህ በኩል የማንአልሞሽ ዲቦንና የአለባቸው ተካን ቤተሰቦች እንዲሁም ከሜሪ ጆይ የመጡ ሁለት ህጻናትን እንደደገፈና እንደረዳ ሲያበስረን፣ በዚህኛው ጎራ ደግሞ ሰይፉ ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከሰጠው ሱፍ ልብስ ጀምሮ ለአባባ ተስፋዬ መኪና፤ ለአንድ ሀገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት ከ100 ደርዘን በላይ ደብተሮች ወዘተ ከስፖንሰሩ ጋር በመተባበር መለገሱን አሳይቶናል፡፡ ሁለቱ የቲቪ ቶክ ሾው አዘጋጆች፤ የፈጸሙት ተግባር በአርአያነቱ በጎ የሚባልና ሌሎች አቅሙ ያላቸው አርቲስቶች፤ ባለሃብቶች፤ ተራው ዜጋም ቢሆን በአቅሜ ምን ማድረግ አለብኝ ብሎ እንዲያስብ የሚያነሳሳ በመሆኑ እንደ መልካም ጅማሮ ቢወሰድ ክፋት የለውም፡፡

ለዚህ ጽሁፌ መነሻ የሆነኝን ሃሳብ የጫረብኝ ግን ጥድፊያና ሩጫቸው የተቸገሩትን ሰዎች ማገዝና መደገፍ ቢመስልም አላስፈላጊ ፉክክር ውስጥ ተዘፍቀው እየዳከሩ ይመስለኛል፡፡ ነገርዬው ልግስና ሳይሆን በልግስና መነገድ ነው የሚመስለው፡፡ ወደ ዝርዝር ጉዳዬ ከመግባቴ በፊት ግን philanthropist ለሚለው ቃል ፍቺውን ላቅርብና ሃሳቤን በጆሲ እጀምራለሁ፡፡ ታዲያ ይሄ የልግስና አስተሳሰብ (Philanthropic mentality) ድንገት የሆነ ሰአት ላይ የሚከሰት ሳይሆን ከልጅነት ጀምሮ በልቦናችን ውስጥ እያደገ,፣ እየጎለበተ የሚመጣ በጎ ሀሳብ ነው፡፡ ጆሲ ታዲያ እውነት የተቸገሩትን መርዳት የሚል የተሰበረ ልብ ካለው,፣ የቲቪ ዝግጅቱን በኢቢኤስ ማቅረብ እስኪጀምር ድረስ ምን አስጠበቀው? የመጀመሪያ አልበሙን ካወጣ እንኳን ወደ 10 አመት ገደማ አይጠጋም እንዴ? እስከ ዛሬ የት ነበር? ማንኛውም በጎ አድራጎት ተግባር ወይም ፋውንዴሽን ማቋቋም የፈለገ ግለሰብ፣ መነሻው የእርሱና የራሱ ጥሪት ነው፤ከዚያ መልካም ስራው ታይቶ ድጋፍና እርዳታ ሊያገኝ ይችላል፡፡ “ሜቄዶንያ”፤ “አረጋውያንን አንሱ”፤ “አበበች ጎበና”፤ ወዘተ የተባሉ ግብረሰናይ ድርጅቶችን ልብ ይሏል፡፡ ድጋፍ የተደረገላቸው ሰዎች በእርግጥም የተቸገሩ እንደሆኑ ከውስጣቸው ፈንቅሎ የሚወጣው እንባቸው ምስክር ነው፡፡ ምንም እንኳን የአለባቸው እህት ከወንድሟ ሞት በኋላ “የአለባቸው እህት ካሸር ሆና ሰራች እንዳይሉኝ ብዬ፣ ልጄ ትምህርት አቋርጣ እኔን እየረዳችኝ ነው” የሚለው አነጋገሯ ቀሽምና የሚያበሳጭ ቢሆንም፡፡

ለጆሲ ግን አንድ ጥያቄ ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ አርቲስት መርዳት ያለበት አርቲስትን ብቻ ነው እንዴ? ሀገራችን ውስጥ ታላላቅ ስራዎችን የሰሩ፣ ነገር ግን ዛሬ ዞር ብሎ የሚያይ ሰው የሌላቸው የቀድሞ ጦር መሪዎች፤ መምህራን፤ የስፖርት ባለሙያዎች ወዘተ የሉም? በየሜዳው ሰብሳቢ ያጡ ህጻናት፤ አረጋውያን የሉም? እውነት የመረዳዳት ሃሳቡ ካለህ፣ እስቲ ያለህን ስምና ዝና ተጠቅመህ፤ የገንዘብ ድጋፍ አፈላልገህ፤ፕሮጀክት ቀርጸህ ወይም አስቀርጸህ የብዙዎች ችግር በዘላቂ ሁኔታ እንዲቀረፍ ለመትጋት ሞክር፡፡ መቼም ወታደርን ወታደር፤አስተማሪን አስተማሪ፤አርቲስትን አርቲስት ወዘተ ብቻ ይርዳ አይባልም፡፡ ሌላው ትዝብት የጫረብኝ ደግሞ የጆሲ አዲሱ አልበም ጉዳይ ነው፡፡ ከአልበሙ ሽያጭ 50 ከመቶ ለበጎ አድራጎት ይውላል ብሎ አወጀ፡፡ አልበም ማውጣትን ከበጎ ስራ ጋር ምን አገናኘው? አልበሙ ምርጥ ስራ ከሆነ (artistically) ስራው በራሱ አይወዳደርም ወይ? ኪነጥበብ ልትለካ የምትችለው በውስጧ የሚገኘው ውበት ያለው ፈጠራ፤ ነፍስን አሸፍቶ ስሙኝ ስሙኝ ስትል እንጂ በበጎ ስራ ካባ ተሸፍና ስትቀርብ አይደለም፡፡ የጥበብ ሥራና የበጎ አድራጎት ተግባር ሲደበላለቅ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ሆደ ቡቡ ወዳጆቼ ያሉት ነገር ጥሩ ማሳያ ይመስለኛል፡፡ “የጆሲን አልበምማ አሪፍ ባይሆንም እገዛዋለሁ” ይሄ ደግሞ በአበሻ ስስ ብልት ገብቶ አልበም መቸብቸብ ሆነብኝ፡፡

ብዙ ለማለት ባልሻም ከተነሳው ሃሳብ ጋር ተያያዥ ስለሆነው “ሰይፉ በኢቢኤስ ሾው” አንድ ሁለት ነገር ልበል፡፡ ሰይፉ ፣ የጆሲን ጅማሮ ቀድቶ፣ እኔም Philanthropist ሆንኩላችሁ እያለን ነው፡፡ የሱ ማስመሰል ደግሞ ይብሳል! በተለይ በአባባ ተስፋዬ ሽልማት ወቅት፣ በቃለ መጠይቁ ላይ የተስተዋሉ ተቃርኖዎች የሚያስተዛዝቡ ናቸው፡፡ ለምሳሌ “እኔ ወደ አሜሪካ ከመሄዴ በፊት” አለ ሰይፉ፤ “እኔ ወደ አሜሪካ ከመሄዴ በፊት አባባ ተስፋዬን ከኢትዮጵያ ህዝብ ምን እንደሚፈልግ በስልክ ጠይቄው “አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቅልኝ የምፈልገው እግሬን ጉልበቴ ላይ እያመመኝ ስለሆነ፣ እንደ ምንም አዋጥተውም ቢሆን መኪና እንዲገዙልኝ ነው የምጠይቀው” ብሎ ስልኩ ተዘጋ፡፡ መቼም አባባ ተስፋዬን የሚያክል ታላቅ ሰው፣ (በሸገር የጨዋታ እንግዳ ከመዓዛ ጋር የነበራቸውን ቆይታ ጨምሮ በልዩ ልዩ ሚዲያዎች ያደረጉትን ቃለ ምልልስ አዳምጫለሁ) አንድ ህጻን ልጅ ማታ አባቱ ምን ይዞለት እንዲመጣ እንደሚፈልግ ሲጠየቅ፤ “ትልቁን ብሽክሊሊት” እንደሚለው አይነት ጥያቄ፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያቀርባሉ ብዬ አልገምትም፡፡ ታዲያ ነገሩ ከየት መጣ ሊባል ነው? ራሱ ሰይፉ የእርሱንና የስፖንሰር አድራጊዎቹን ስምና ዝና ለማግነን የተጠቀመበት ተራ “እቃቃ ጨዋታ” ነገር ይመስለኛል፡፡ ሰው በድህነት ምክንያት የመደራደርና የመግደርደር አቅሙን ሲያጣ፣ እንደ አሻንጉሊት ልጫወትብህ ማለት እግዝሄሩም ቢሆን አይወደውም፡፡ አስገራሚው ነገር ደግሞ አባባ ተስፋዬ መድረክ ላይ ቀርበው “አሁን መኪናውን ምን ያደርጉበታል?” ሲላቸው “ያ በሽተኛው የልጅ ልጄ ትምህርት ቤት ይመላለስበታል” አሉ፡፡

አዲዮስ! የአባባ ተስፋዬ የእግር ህመምና የሰይፉ አስመሳይ የለጋሽነት ፍላጎት ተጋለጠ!! እናም ጆሲና ሰይፉ ሆይ፤ የቲቪው ፕሮግራም በፈጠረባችሁ ውድድር ምክንያት የተመልካችን ቀልብ ለመሳብ፣ ፕሮግራማችሁ ከተቋቋመበት አላማ ውጪ በሰዎች ማጣትና ድህነት ላይ ተንጠላጥላችሁ ከንቱ ዝናና ገንዘብ መቃረም ቢቀርባችሁ ይሻላል ባይ ነኝ፡፡ እውነት Philanthropist ነን ካላችሁ፣ ሃገራችን ውስጥ ታላላቅ የበጐ አድራጐት ስራዎችን ከፈጸሙት ግብረሰናይ ድርጅቶች ልምድ ውሰዱ፡፡ ሌላው ቢቀር በሙዚቃና ኪነጥበብ ሥራ ውስጥ ከሚገኘው ከታዋቂው የክቡር ዶክተር አሊ ቢራ ፋውንዴሽን ብዙ ተሞክሮ ማግኘት ትችላላችሁ፡፡ የአሊ ቢራ ፋውንዴሽን አርቲስቱ በራሱ ገንዘብ ያቋቋመው፤ የራሱ ቦርድና ስራ አስኪያጅ ያለው ሲሆን ትምህርት ባልተዳረሰባቸው የሀረር ቀበሌዎች ትምህርት ቤትን በማስገንባት ለትውልድ የሚተላለፍ አሻራ እያስቀመጠ ይገኛል፡፡ በተረፈ የራሳችሁን ስም ለማግዘፍ ስትሉ መድረክ ላይ ለይምሰል የምታፈሷትና የምታብሷት እንባ፣ የማስመሰል ነገር አለባትና እባካችሁ ልብ ይስጣችሁ!!

Read 4168 times