Saturday, 20 September 2014 10:56

ከግቢ ‘በሮች’ ወደ መንደር ‘በሮች’…

Written by 
Rate this item
(2 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

         እኔ የምለው…ግድግዳው ላይ ያለው ቀን መቁጠሪያ ተለወጠ? እኛ አገር ዘመን መለወጥ ማለት ግድግዳ ላይ ያለውን ቀን መቁጠሪያ መለወጥ ከሆነ እየሰነበተ ነዋ! የምር እኮ…ዘንድሮ “ሲጋራ አቆማለሁ…” “ቂማ አቆማለሁ…” “መጨለጥ አቆማለሁ…” የሚል አንድም ወዳጅ አልገጠመኝም፡፡ ወዳጆቼ ‘ሲፑ’ና ‘ቂማው’… ይሄን ያህል ተስማምተዋችኋል እንዴ! “ነገር እየሰማሁና እያየሁ ከምቃጠል ሳላይና ሳልሰማ እየቃምኩና እየጠጣሁ ብቃጠል ይሻለኛል!” ያልከን ወዳጃችን ጭራሽ እየወፈርክ ሄድክሳ! እውነትም “አለማየትና አለመስማትን የመሰለ ነገር የለም…” ምናምን የሚል የጥናት ውጤት የሆነ ቦታ ሊኖር ይችላል፡፡ ሀሳብ አለን…እንዲህ መፋጠጥ በተለመደበት ዘመን በየምግብ ቤቱ “ሌላው ተመጋቢ የሚመገበውን እየተንጠራሩ ማየት የተከለከለ ነው…” ምናምን የሚል ማስታወቂያ ይለጠፍልንማ!! ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ሰዎቹ ምን የሚሉ ይመስለኛል መሰላችሁ… “አየሻት ስቴክ እኮ ነው የምትበላው!” “ታዲያ ስቴክ ብትበላ ምን አለበት?” “ምን አለበት! አንድ ብልቃጥ የጥፍር ቀለም ዓመት ተኩል የምታብቃቃ፣ ስቴክ የምትበላበት ከየት አምጥታ ነው! ይሄኔ አንዱን ሼባ ይዛ ይሆናል፡፡”

ሌላው ቡድን ዘንድ ደግሞ ምን ይባላል መሰላችሁ… “ስማ ያንን ችጋራም ምን እንደሚበላ አየኸው!” “ምንድነው የሚበላው?” “በእናትህ በቅዳሜ ምድር ክክ ምናምን ይበላል!” “የፈለገውን ቢበላ ምናለበት!” “የምን መፈለግ ነው! ችጋራም ነው እንጂ! የሚሠራው ቢዝነስ ቀላል መሰለህ! ልጄ ከሰዎቹ ጋር ተለጥፎ…” እናላችሁ…ልንመገብ ገብተን ስለሌሎች ተመጋቢዎች… “ከዕለታት አንድ ቀን…” ምናምን ታሪኮች የምናበዛ ሰዎች በርክተናል፡፡ የምር ግን…ነገሬ ብላችሁ እዩልኝማ…አሥር ጠረጴዛ ዘሎ ያሉ ሰዎች ያለ አጉሊ መነጽር እያሻገሩ አጎራረሳችሁንና አዋዋጣችሁን ‘ሲገመግሙ’ (ቂ…ቂ…ቂ…) እኔ የምለው…አጎራረሳችን የትኛው ካምፕ ውስጥ እንዳለን ያስነቃብናል እንዴ! ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… አዲስ አበባ በራሷ አነሳሽነት ነዋሪዎቿን ‘በመደብ’ እየለየች ነው፡፡

ልክ ነዋ…‘ንጥጥ’ ያሉ ሀብታሞች በተወሰኑ አካባቢዎች፣ ‘ምጥጥ’ ያሉ ቺስታዎች ደግሞ በየስርቻው! ሟርት አያስመስልብኝና እንዲህ አይነት ነገሮች እየበዙ በሄዱ ቁጥር የኋላ፣ ኋላ አሪፍ አይሆንም፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…አሁን ‘የምንፈራው’ የሀብታሞቹን መኮሳተር (ለመኮሳተርስ ሲያዩን አይደል!) የጥበቃዎችን ግልምጫ ነው፡፡ ስሙኝማ…እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው… አንዳንድ ሰዎች ‘መለዮ ሲለብሱና ዱላ ቢጤ መወዝወዝ ሲጀምሩ’ … አለ አይደል…የሚናፍቃቸው ዱላውን የሚያሳርፉበት ጀርባ ነው እንዴ! አሀ…በሰፈር ደረጃ ያሉ አንዳንዶቹን እኮ ስታዩዋቸው…አለ አይደል… በዓይናቸው እናንተን እያዩ በልባቸው… “ይሄ እንዲህ ትከሻውን እያሳየ የሚንጎማለለውን ቀልጥሞ፣ ቀልጥሞ መጣል ነበር!” እያሉ የሚያስቡ ይመስላችኋል፡፡

እና ‘መረጋጋት’ን የመሰለ ነገር የለም፡፡ ልክ ነዋ…ዱላው ‘እዛኛው እጅ’ ላይ የገባ ዕለት “…ይቅርታ እለምናለሁ፣ ጥፋቴን አውቄያለሁ…” ምናምን አይነት የአድማጮች ዘፈን ምርጫ አይሠራም! እኔ የምለው…ካወራን አይቀር…እዚቹ ከተማ ‘ጌትድ ኮሚዩኒቲስ’ የሚባሉ ግቢዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ሙሉ መንደሮቹ ራሳቸው ግማሽ የእግር ኳስ ሜዳ በሚያካክሉ በሮች እየተከረቸሙ ነው፡፡ (ቀስ ብሎ ደግሞ ሙሉ አውራጃን ዓመት ሙሉ ቀጥ አድርገው ‘መቀለብ’ በሚችል ገንዘብ የሚገዙ መኪኖች በሚያልፉባቸው መንገዶች “ዝር ትሉና!” እንዳንባል መፍራት ነው!) እናላችሁ…ቀደም ሲል የመኖሪያ ግቢ በር ላይ ነው “ማንን ፈልገህ ነበር?” የምንባለው፡፡ አሁን ግን በታጠሩት መንደሮች ዋና በር ላይ ነው “ወዴት ነው!” የምንባለው፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በፊት እኮ የሀብታምና የድሀ መኖሪያ የሚለየው እንዲህ በመንደር ሳይሆን በቤቶቹ ትልቅነት ምናምን ነበር፡፡ እዚህ ጋ ቅልጥ ያለ ቺስታ እንደ ባለቤቷ ጠጅ ያንጋደዳት ጎጆ ውስጥ እየኖረ፣ ከፊት ለፊቱ ደግሞ የፊታውራሪ እከሌ የተንጣለለ ግቢ ይገኛል፡፡

(በነገራችን ላይ ፊትአውራሪ የሚለው መጠሪያ እየጠፋ መሄዱ የፊት አውራሪነት ባህሪይም አብሮ እየጠፋ ነው ማለት አይደለም፡፡ እንደውም ባይብስበት ነው!) እናላችሁ…ፈራንካው ያላቸው ሰዎች መንደሮቻቸውን በትላልቅ የብረት በሮች እንደሚዘጉት ሁሉ፣ ባለፈረንካዎችና ‘ባለድርሻ አካላቱ’ (ቂ…ቂ…ቂ…) በሁሉም በኩል ራሳቸውን በትላልቅ ‘የብረት በር’ እየከለከሉ ነው፡፡ ለምሳሌ…የፈረንካ ሰፈር ትኩስ ሀይሎች ሲገናኙ የሚያወሩት ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… “ፌስቡክ ፍሬንዶቼ አራት ሺ ሰባት መቶ ሆኑ!” “ዋው! የእኔ ገና ሦስት ሺህ ናቸው፡፡ በቀደም ፍሬንድ የሆነችኝ…አንድ ምን የመሰለች ልጅ በፌስቡክ አግኝቻለሁ፡፡“ “ዩ ዶንት ሴይ! ከስቴትስ ነው?” “ኖ እዚሁ ነች…” “ኋት! ዩ ሚን ሺ’ዝ ሎካል!” “ብታያት እንዲህ አትልም ነበር፡፡ ምን የመሰለች ቺክ መሰለችህ! እንደውም ፕሮፋይል ፒክቸሯን ላሳይህ…” ከዛማ ሳምሰንግ ጋላክሲ ኤስ ፋይቭ ምናምን ይወጣል፡፡ ‘እዚህኛው ሰፈር’ ደግሞ ‘ፌስ’ ገና ከ‘ቡክ’ ጋር ሳይያያዝ ከሰው ልጅ አካል አንዱ የሆነበት ቺስታው መንደር ምን የሚባባሉ ይመስለኛል መሰላችሁ… “ስማ ከዚያች ልጅ ጋር እንዴት ናችሁ…” “የቷ!” “የቷ ትላለህ እንዴ! ያቺ ቀበሌ ሸማቾች ምናምን የምትሸጠው…” “ምን ታደርግ አንተ…እኔ ልጄ ስንት ሀሳብ አለብኝ! ሥራ ፍለጋ ስንከራተት ሁለት ዓመት እንዳለፈኝ አታውቅም!” “አትበሳጭ፣ ግዴለህም ለደግ ነው፡፡” “የምበላው እያጣሁ ለደግ…” ይልና መሀል ላይ ያቋርጣል፡፡ ‘ትርፍ’ ሊናገር ነበራ! አንድ ሁለቴ ያማትብና “…ይልቅ የማነበው አሮጌ መጽሐፍ ካለህ…” ምናምን እየተባለ ይቀጥላል፡፡እናላችሁ…እነሱ በ‘ቴክስት ሜሴጅ’ የፈለጉትን ቢባባሉ ያው የለመዱት ነው፡፡

እኛ ግን… አንዳንዱ የእኔ ቢጤ ‘ፋራ’ እንትናዬውን “ስዊቲ፣ አይ ላቭ ዩ ቬሪ ማች!” በሚል ሁሉም ሰው በሚገባው የፈረንጅ አፍ ግጥም አድርጎ ይጽፋል፡፡ አሀ…በእንግሊዝኛ ጥየቄ ማቅረብ ነገሩን ሁሉ ‘አሪፍ’ ያስመስለዋላ! ለነገሩ…“ስዊቲ!” “ሀኒ!” “ማይ ኤንጅል!” ምናምን ነገሮች በእኛ አፍ አያምሩማ! “ዳቦ ፍርፍር እየበሉ በእንግሊዘኛ ማወራት አያምርም…” የሚል ሰው የሆነ ቦታ ያለ አይመስላችሁም! (ስሙኝማ…አንዳንድ በፈረንጅኛ አፍ እንኳን የሚያነጥሱት ሰበሰቧቸው ቦታዎች ብቅ ማለታችን አይቀርም፡፡ እናላችሁ…በፈረንጅ አፍ ሲያወሩ ቋንቋው ላይ የሚያደርሱበት የኃይል ጥቃት ሶሪያና ኢራቅ አጠገብ ብንሆን ኖሮ ሌላ የዓለም ጦርነት ዋዜማ ሊሆን ይችል ነበር፡፡ አሀ… የአትክልት ተራ “ማዳም ጉድ ኦራንጅ…” አጠገብ እንኳን አይደርሱም! በዚህ ላይ ቅልጥ ያሉ ‘የብልግና’ ቃላት መሸለያ እየመሰላቸው ሲደጋግሙት ፈረንጅ ምን ያህል ይሳቀቅ ይሆን ያሰኛል! ከዓመታት በፊት በዕድሜ ‘ሲክስቲዋን’ ፉት ብለው ወደ ‘ሰቨንቲዋ’ የሚጠጉ እናት በ‘ታይታቸው’ ኋለኛ በኩል ‘ባይት ሚ’ (Bite me!) ተብሎ የተጻፈበት ለብሰው መሃል ከተማ ሲዘንጡ ማየቴ ትዝ ይለኛል፡፡ ብቻ ምን አለፋችሁ…በመንደር ትላልቅ በሮችም፣ በፌስቡክ ‘ፍሬንዶችም፣’ በ“ባይት ሚ” ምናምን አካሄዳችንም እያማረበት አይመስልም፡፡ የ‘ቦተሊካው’ ነገር አልበቃ ብሎ የሚለያዩን ነገሮች እየበዙ ሲሄዱ…አለ አይደል… ነገርዬው የትላልቅ በሮች ጉዳይ መሆኑ እንዳያበቃለት መፍራት ነው፡፡ከግቢ ‘በሮች’ ወደ መንደር ‘በሮች’…ተስፋ የሚሰጥ ‘ዕድገት’ አይደለም፡፡ ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3235 times