Print this page
Saturday, 31 December 2011 11:21

የሆስተስ አበራሽ ሀይላይን አይን ያጠፋው የ14 ዓመት ፅኑ እስራት ተበየነበት

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(0 votes)

ተከሳሹ በፍርድ ውሳኔው ላይ ቅሬታ የለውም

አቃቤ ህግ ለጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ እጠይቃለሁ አለ

የተጐጂ ቤተሰቦች በሞት መቀጣት ነበረበት ብለዋል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና አስተናጋጅ የነበረችው ሆስተስ አበራሽ ሀይላይን ሁለት ዓይኖች ማጥፋቱ የተረጋገጠበት የቀድሞ ባለቤቷ አቶ ፍሠሃ ታደሠ በ14 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ በትናንትናው ዕለት በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ተበየነበት፡፡ ለሦስት አመት ከማንኛውም ህዝባዊ መብቶች እንዲታገድም ተወስኗል፡፡ አቃቤ ህግ ተከሳሹ በሞት እንዲቀጣ የቅጣት ማክበጃ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ትላንት ከቀኑ 5 ሰዓት ላይ ነበር የተከሳሽ ፍሠሃ ታደሰን የቅጣት ውሳኔ ለመበየን የተሰየመው፡፡

ተከሳሹ የሹራብ ኮፍያ እና ቱታ ጃኬት አድርጎ በፖሊሶች ታጅቦ የገባው ከሌሎች ታራሚዎች ጋር በካቴና ታስሮ ሲሆን እንደወትሮው በችሎቱ ብዙ ታዳሚ አልተገኘም፡፡ አቃቤ ህግ ካቀረበው የቅጣት ማክበጃ ውስጥ ድርጊቱ የተፈፀመው በለሊት በመሆኑና በቀድሞ ባለቤቱ ላይ የተፈፀመ ስለሆነ የሚለውን በቅጣት ማክበጃነት የተቀበለው ፍ/ቤቱ፤ ሌሎቹን የአቃቤ ህግ ማክበጃዎች የክሱ ፍሬ ነገር በመሆናቸው ሳይቀበላቸው እንደቀረ ገልጿል፡፡ ፍ/ቤቱ የተከሳሽ ጠበቆችን የቅጣት ማቅለያ በመቀበልም ቅጣት ማስተላለፉን አመልክቷል፡፡    በዚህም መሠረት የወንጀሉ አፈፃፀም ከባድ እንደሆነ የጠቆመው ፍ/ቤቱ፤ ከባድ  የመግደል ሙከራ ክስ በሚለው ጥፋተኛ ብሎታል፡፡ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት በሚለውም ክስ ተከሳሹ ጥፋተኛ ነው ተብሏል፡፡ እንዲሁም በስለት እና በእጅ አይኗን ጐልጉሎ በማውጣቱ የወንጀሉ አፈፃፀም ከባድ እንዲባል አድርጐታል ሲል ፍ/ገልጿል፡፡የቅጣቱ መነሻ እድሜ ልክ እንደሆነ የጠቆመው ፍ/ቤቱ፤ የተከሳሽ ጠበቆችን የቅጣት ማቅለያዎች መርምሮ ቅጣቱን እንደበየነ በመግለጽ የ14 አመት ከ6 ወር ፅኑ እስርና  ለሦስት አመት ከህዝባዊ መብቶች እንዲታገድ መወሰኑን ያስታወቀ ሲሆን ተከሳሽ በበኩሉ በቅጣቱ ላይ ቅሬታ እንደሌለው ገልጿል፡፡ በክስ ሂደቱ ላይ አስተያየት የሰጡን የተከሳሽ ጠበቃ አቶ አምሀ መኮንን የፍርድ ሒደቱ ላይ አስቸጋሪ ነገሮች እንደገጠሟቸው ያስታውሳሉ፡፡ ከችግሮቹ መካከል በየቀጠሮው በተከሳሹ ፍርድ አሰጣጥ ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር የሚችል ሰላማዊ ሰልፍ መደረጉን ይጠቅሳሉ፡፡ ሚዲያው የአንድ ወገን መረጃ ብቻ ያቀርብ ነበር ያሉት ጠበቃው፤ ይሄም ካሳለፉት ችግር አንዱ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ለፍ/ቤቱ ተጨማሪ ማስረጃዎች ለማቅረብ የተጐጂዋን እና የተከሳሽን የስልክ ልውውጥ ከኢትዮጵያ ቴሌኮም እንድናመጣ ፍ/ቤቱን ጠይቀን ነበር የሚሉት ጠበቃው፤ ፍ/ቤቱ የስነ ስርአት ጥያቄ አንስቶ አልተቀበለውም ብለዋል፡፡ በፍርድ ብያኔው ላይ  ችግር እንደሌለ ጠቁመው ፍ/ቤቱ የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት ተቀብሎ ጥሩ አድርጐ መርምሮታል ብለዋል፡፡ አቃቤ ህግ በበኩሉ ቅጣቱ በቂ ስላልሆነ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ እንደሚጠይቅ ገልጿል፡፡     የተጐጂዋ የሆስተስ አበራሽ አጐት አቶ አስመላሽ ሞላ በበኩላቸው በተከሳሽ ላይ ፍ/ቤቱ የበየነው ቅጣት በቂ አይደለም ይላሉ፡፡ የ14 ዓመት እስር ከወንጀሉ ጋር የሚመጣጠን አይደለም የሚሉት አቶ አስመላሽ፤ ከዚህ ቅጣትስ በነፃ ቢለቀቅ ይሻለኛል ብለዋል፡፡ “ዳኞች የሠጡትን መቀበል ቢኖርብኝም አነሰ ቢባል የዕድሜ ልክ እስራት እጠብቅ ነበር” ያሉት አቶ አስመላሽ፤ የሞት ፍርድ አለመወሰኑ የብዙ እህቶቻችን አይን እንደሚጠፋ ይጠቁመኛል ብለዋል፡፡ ይግባኝ እንደሚጠይቁም ተናግረዋል - አቶ አስመላሽ፡፡ ተጐጂዋ በደረሠባት ጉዳት ሁለቱም ዓይኖቿ የማይሠሩ ሲሆን የነርቭና የወገብ ህመምም እንዳጋጠማት ይታወቃል፡፡ ችሎቱን የተከታተሉ የተጐጂ ቤተሠቦች እና የሴቶች ጉዳይ ቢሮ ሀላፊዎች ቅጣቱ ማነሱን በእንባ ገልፀዋል - ድርጊቱ ዘግናኝ ሆኖ አስተማሪ ያልሆነ ቅጣት መሆኑን  ጠቆም፡፡  አቶ ፍሰሀ ታደሰ “ቃል የእምነት እዳ እንጂ የእናት አባት ውርስ አይደለም፡፡”በሚል ርዕስ ከማረሚያ ቤት የፃፉትን ደብዳቤ በዚሁ ገፅ በስተቀኝ ይመልከቱ

 

 

 

 

 

 

 

Read 16284 times Last modified on Saturday, 31 December 2011 16:09