Saturday, 20 September 2014 10:40

‹‹ከአንድ ብርቱ....››

Written by  ዳንኤል አበበ (Red8)
Rate this item
(4 votes)

           ከእለታት አንድ ቀን አንድ ብልህ አባት የመሞቻው ቀን እንደተቃረበ አዉቆ፣ አለመተባበራቸው የሚያስጨንቀው ሦስት ልጆቹን ይጠራቸዉና በአንድ ላይ የታሰሩ አስር በትሮችን ሰጥቶ እንደሰበሩዋቸው ይጠይቃቸዋል፡፡ የመጀመሪያው ልጁ ለመስበር ሞክሮ ያቅተዋል፡፡ ሁለተኛውም ልጅ ታግሎ አልሰበር ይሉታል፡፡ የመጨረሻው ትንሹ ልጅ በወንድሞቹ አላዋቂነት እየሳቀ በትሮቹን ተቀብሎ በአንድ ላይ የታሰሩበትን ገመድ በመፍታት ከለያያቸዉ በኋላ፣ እያንዳንዳቸዉን ለብቻ በየተራ ሰባብሮ ይጨርሳቸዋል፡፡ ህመምተኛው አባት ፈገግ ብሎ “አያችሁ ልጆቼ በትሮቹ አንድ ላይ በሆኑ ጊዜ ልትሰብሩዋቸው አልቻላችሁም፡፡ እናንተም አንድ ላይ ብትሆኑ ስለምትጠነከሩ ማንም አይጎዳችሁም” አላቸው ይባላል፡፡“ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሃኒቱ”፣ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር”፣ “በአንድ እጅ አይጨበጨብም ” ወዘተ የሚሉትን የሀገራችንን አባባሎች እና ከላይ ያስነበብኩዎትን አይነት የመተባበርን ወይም የህብረትን ጠቀሜታ የሚያወድሱ ተረቶችና ታሪኮችን ብዙ ግዜ ሰምተው እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡

የአባባሎቹንና የታሪኩን እውነተኝነት ምናልባትም በራስዎ ማህበር ውስጥ አረጋግጠው ይሆናል፡፡ ማኅበር ካለዎት ማለቴ ነው፡፡ ለመሆኑ ግን ማኅበር የሌለው ሰው አለ እንዴ? የማኅበራዊ ሳይንስ ጠበብቶች “ሁላችንም የማኅበር ውጤቶች ነን” ይላሉ፡፡ በእርግጥም ማኅበር የብዙዎቹ ችግሮቻችን ቁልፍ ወይም የህልውና ጥያቄ እየሆነ ከመጣ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ በሀገራችን ከትውልድ ወደ ትዉልድ ሲሸጋገሩ የኖሩትን እንደ እድር እና ዕቁብ ያሉትን ማኅበራት ለአብነት መጥቀሰ ይቻላል፡፡ በተለይ ፍላጎትና አቅማቸውን ተጠቅመዉ ካሉባቸው ችግሮች እንዳይወጡና ለሌላውም እንዳይተርፉ የተለያዩ መሰናክሎች ለሚጋረጥባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች፤ ህብረት መፍጠሩ እና መደራጅቱ መሰናክሎቹን በጥበብ ለማለፍ የሚመከር የብልሆች መፍትሄ ነው፡፡

ለአብነት “ከአንድ ብርቱ ሁለት መዳኒቱ” በማለት ማህበር በመመስረት ያሉባቸውን ችግሮች ሁሉ ቀስ በቀስ እየፈቱ፤ ከስልሳ ተነስተዉ ዛሬ ሶስት ሺ አባላት ማፍራት የቻሉትን የአማራ ክልል ነጋዴ ሴቶች ማህበር አባላት ማንሳት ይቻላል፡፡እነዚህ ሴት ነጋዴዎች ያሉባቸውን ችግሮች በማህበራቸው አማካኝነት በመታገላቸውና ለሚመለከታቸው ክፍሎች ድምፃቸውን ማሰማት በመቻላቸው ተሰሚነትና ምላሽ እያገኙ መሄድ ችለዋል፡፡ በመሆኑም አባላቱ የተለያዩ የንግድ ስልጠናዎችን፤ የብድር አቅርቦቶችን፤ ለመስሪያ የሚሆኑ ቦታዎችን፤ በባዛሮችና በንግድ ትርኢቶች ላይ የመሳተፍ ዕድሎችን በማኅበራቸው አማካኝነት ማግኘት ችለዋል፡፡ የማኅበሩ ፕሬዝዳንት የሆኑት ወ/ሮ ንግስት፤ በማኅበር መደራጀታቸው ካስገኛላቸው ጠቀሜታ አንዱ የስራ ዕድሎችን እንደሆነ ሲገልጹ፤ “በ1997 ዓ.ም የባህር ዳር ፔዳጎጂካል ሳይንስ ዩኒቨርስቲ ‘ለአንድ አመት በኮንትራት ምግብ ለማዘጋጀትና ለማቅረብ የሚችል እፈልጋለሁ’ ብሎ ነበር፡፡ ማህበራችን በወቅቱ ፕሬዝዳንት በነበሩት በወ/ሮ ፍሬአለም ሺባባዉ አማካኝነት የማህበሩ አባላት የሆኑ 37 ነጋዴዎች ኮንትራት እንዲወሰዱና እንዲሰሩ አድርጓል፡፡ በዚያን ወቅት አብረውን ይሠሩ ከነበሩት ሴቶች ጂ ፕላስ 3 እስከ መስራት የደረሱ፤ብዙ የተለወጡ አሉ፡፡

” የአማራ ነጋዴ ሴቶች ማህበር የደሴ ቅርንጫፍ አስተባባሪ የሆነችው ወይዘሪት ህለተ ወርቅ ነጋዴ ሴቶች ከማህበሩ ስላገኙት ጥቅም እንዲህ ትገለፀዋለች፡- “አብዛኞቹ ሴት ነጋዴዎች የንግድ እንቀስቃሴያቸው ባሉበት ቦታ ብቻ የተወሰነ ነበር፡፡ ከቤትዋ ወጥታ ምርትዋን ማስተዋወቅ፤ ሰው ፊት ቆሞ መናገር፤ የንግድ ትስስርና ከሰው ጋር ግንኙነት መፍጠር አልተለመደም፡፡ ማህበሩ ባዛር እና የንግድ ትርኢቶችን ሲያዘጋጅ አንዱና ትልቁ ምክንያት የተጋነነ ትርፍ ይዛ ወደ ቤትዋ እንድትገባ ሳይሆን፤ አንደኛ እርስዋ ነጋዴ ናትና ነጋዴነትዋ ይታወቃል፡፡ ሁለተኛ ምርትዋን ታስተዋዉቃለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለቀጣይ የንግድ እንቅስቃሴዋ የሚረዳትን ግንኙነት ከማህበረሰቡ ጋር ትፈጥራለች፡፡” የአማራ ክልል ነጋዴ ሴቶች ማህበር (አክነሴማ) በርካታ ነጋዴ ሴቶች የማህበሩ አባል በመሆን ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ በችግር ምክንያት ልጆችዋን ይዛ ጎዳና እስከመዉጣት ደርሳ የነበረችውና በ አሁኑ ወቅት በ 500 ሺ ብር ወጪ የራስዋን ቤት እስከ መስራትና የባልትና ምርቶችን እያዘጋጀች በመሸጥ የምትተዳደርበትን የራስዋን ሱቅ እስከ መክፈት የደረሰችዉ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ ወ/ሮ አገሬ አሰፋ፤ ወደማህበሩ የገባችበትን ሁኔታና ያገኘችዉን ጥቅም እንዲህ ትገልፀዋለች:- “በሶ፣ ሽሮ፣ በርበሬ፣ምስርና የመሳሰሉትን የባልትና ዉጤቶች በቤቴ ሆኜ ካዘጋጀሁ በኋላ በየሱቁ እየዞርኩ ነበር የማስረክበው፡፡ በዚህም የድካሜን ያህል አላገኝበትም ነበር፡፡ የራሴን ሱቅ ከፍቼ ብሰራ የበለጠ ዉጤት እንደማገኝ የመከሩኝና ያበረታቱኝ የአማራ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ናቸው፡፡ ከአማራ ብድርና ቁጠባ ብድር እንድወስድ፣ የራሴን ንግድ ፍቃድ እንድይዝና የማህበሩ አባል እንድሆን ሁኔታዎችን አመላክተዉኛል፡፡ በተለያዩ ግዜያትም ስለንግድ የተለያዩ ስልጠናዎች እንድወስድ ረድተዉኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለብኝን የሱቅ ኪራይ ችግር ለማስወገድ በማህበሩ አማካኝነት ስምንት ሆነን ተደራጅተን የቤት መስሪያ ቦታ የማረጋገጫ ደብዳቤ ተሰጥቶናል፡፡ የአንድ ማህበር አባላት ህልውና የማህበሩ ህልውና ነው፡፡

የአባላቱ ጤናማና ጠንካራ እንቅስቃሴ ለማህበሩ አስተማማኝ የህይወት ጉዞ መሰረት ነው፡፡ ጆን ስቴዋርት የተባሉ የማህበራዊ ሳይንስ ሊቅ፣ “The Evolution Manifesto” በተሰኘ መፅሀፋቸዉ ላይ፤ ለአንድ የተቀደስ የጋራ ዓላማ በተመሰረተ ጠንካራ ማህበርና በአባላቱ መሀከል ያለውን ቁርኝት እጅግ ከረቀቀውና ከተወሳሰበው የሰውነታችን አወቃቀርና ጤናማ አሰራር ጋር አነፃፅረዉ ይገልጹታል፡፡ “እያንዳንዳችን በሚሊዮን፤በቢሊየን የሚቆጠሩ ሴሎች ጥምረት ውጤት ነን፡፡ እንደ ልብ፣ ኩላሊት፣ ሳንባና የመሳሰሉት የሰውነታችን ክፍሎች የተገነቡት በእነዚህ ሴሎች አንድነትና ውህደት ነው፡፡ በእነዚህ ህዋሳቶቻችንና የሰዉነት ክፍሎቻችን መሀከል ያለው ጥልቀትና ስፋት ያለው ህብረት፡- ምግብ ስልቀጣውን፣የደምና የኦክስጅን ዝውውር ስርአቱን፣ ሊያጠቁን የመጡትን የበሽታ ህዋሳት የመከላከሉን፣ ችግሮቻችንን ለመፍታት የምንጠቀምበት ጥበብ የማፍለቁንና ሌሎች ግዳጆችን በሙሉ ያለማስተጓጎልና ያለእንከን እንዲከናወን ያደርጋል፡፡

ከህዋሳቶቻችንና ከሰውነት ክፍሎቻችን የአንዱ ከአገልግሎት ውጪ መሆን በጠቅላላው ሰውነታችን ላይ የሚያስከትለው መናጋት እስከሞት ሊያደርሰን እንደሚችለው ሁሉ፤ የአንድ ማህበር አባላት ውድቀትና ጥፋት ማህበሩን እከመፍረስ ሊያደርሰው ይችላል” ይላሉ:: በዚሁ መሰረት የአማራ ነጋዴ ሴቶች ማህበር የአባላቱን የንግድ እንቅስቃሴ የሚያዉኩ ችግሮች ለማስወገድ የማይዘይደው መላ፣ የማያንኳኳው በር፣የማይጮኸው ጩኸት፣ በአጠቃላይ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። እንደ ምሳሌ “የአባቶች ቡድን”ን እንቅስቃሴ ማየት ይቻላል። የአባቶች ቡድን የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ፣ወንዶች ለትዳር አጋሮቻቸውና ለልጆቻቸው በፊት ከነበራቸው በተሻለ መልኩ አሳቢና አጋዦች እንዲሆኑ ታስቦ እ.ኤ.እ በ1980 መጨረሻ በስዊድን የተጀመረ እንቅስቃሴ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በአክነሴማ አማካኝነት ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ እንደሚታወቀዉ በሃገራችን ጾታን መሰረት አድርገው በሴቶች ላይ የሚደርሱት ተጽእኖዎች ብዙ ናቸው። ከእነዚህ ተፅእኖዎች አንዱ ‘የሴትና የወንድ’ በሚል ለዘመናት የኖረው ያልተመጣጠነ የስራ ክፍፍል ነው፡፡

ማህበሩ ይህን ችግር ለማስወገድ በየዞኑ እንዲቋቋሙ ባደረጋቸው የአባቶች ቡድን አማካኝነት ትልቅ ስራ እየሰራ መሆኑን የማህበሩ ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ሲገልፁ፤ “አባቶች በቡድን ሆነው ወደ 5 በሚደርሱ ዋና ዋና ርዕሰ - ጉዳዮች ላይ እርስ በርሳቸው ይማማራሉ፡፡ አንድ የባህሪ ለዉጥ እንዲያመጣ የሚፈለግ አባዎራ፤ በቤቱ ውስጥ ምን ምን እንደሚያደርግ፤ ከቤተሰቡ ጋር ያለው ግንኙነት ምን መልክ እንዳለው ይገለፃል፡፡ በአርአያነቱ የተመረጠውና አስቀድሞም በስልጠና የተደገፈዉ አባዎራ ደግሞ ጠቅላላ ለቤቱ ያለውን አቋም እና በዚያ ያገኘውን ጥቅም በመግለጽ ልምዱን ያካፍላል፡፡ በዚህ አይነት መማማሩ ይቀጥላል፡፡ በዚህም በርካታ አባዎራዎች በመለወጣቸዉ የትዳር አጋሮቻቸዉ የሆኑ ነጋዴ ሴቶች ያለመሳቀቅ፣ በነፃነት ለንግድ ስራቸዉ በቂ ጊዜ በመስጠት ዉጤታማ መሆን እየቻሉ ናቸዉ፡፡” ከዚህ በላይ በጥቂቱ ለመግለጽ እንደተሞከረዉ፣ በማህበር መደራጀት ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ የአማራ ክልል ነጋዴ ሴቶች ማህበር በክልሉ ካሉ ሴት ነጋዴዎች አልፎ በመላ ሀገሪቱ ያሉ ሴት ነጋዴዎች በማህበር እንዲደራጁ የአንበሳውን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡ ማህበሩ በአሁን ወቅት በ 3 የክልል ከተሞች ማለትም በደብረ ብርሃን፤ በወልድያ እና በደብረ ታቦር ቢሮዎች በመክፈት የአባላቱን ቁጥር ወደ 4000 የማሳደግ እቅድ ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ ነዉ፡፡ በዚህ አጋጣሚም አክነሴማ በክልሉ የሚኖሩ ነጋዴዎችን ለአባልነት ይጋብዛል፡፡

Read 3425 times