Saturday, 20 September 2014 10:26

በተከሰሱ መፅሄቶች ላይ ውሳኔ ለመስጠት ፍ/ቤት ኦሪጂናል መፅሄቶች እንዲቀርቡለት አዘዘ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

         በ“አዲስ ጉዳይ”፣ በ“ሎሚ” እና በ“ፋክት” መፅሄት አሳታሚዎችና ሥራ አስኪጆች ላይ ለተመሰረቱት የወንጀል ክሶች የቀረቡት ማስረጃዎች ከየመፅሄቶቹ ገፆች የተቆራረጡና ኮፒ የተደረጉ መሆናቸውን የጠቆመው ፍ/ቤት፤ አቃቤ ህግ ኦርጂናል መፅሄቶችን በማስረጃነት እንዲያቀርብ ትዕዛዝ በማስተላለፍ ለፍርድ ውሳኔ በድጋሚ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ፡፡ ፍ/ቤቱ ከትላንት በስቲያ በዋለው ችሎት አቃቤ ህግ ከጥቅምት 3 በፊት ኦሪጂናል መፅሄቶችን በማስረጃነት እንዲያቀርብ አዟል፡፡ የ“አዲስ ጉዳይ” መፅሄት አሳታሚ ሮዝ አሳታሚና ስራ አስኪያጁ አቶ እንዳልካቸው ተስፋዬ፣ የ“ሎሚ” መፅሄት አሳታሚ ዳዲሞስ ኢንተርቴይመንትና ፕሬስ ስራዎችና ስራ አስኪያጁ አቶ ግዛው ታዬ እንዲሁም የ“ፋክት” መፅሄት አሳታሚ ኢንተርቴይመንትና የፕሬስ ስራዎች ኃ/የተ/የግ/ማህበርና ስራ አስኪያጅ ፋጡማ ኑርዬ በጋዜጣ ጥሪ ተደርጎላቸው ባለመቅረባቸው ጉዳያቸው በሌሉበት እየታየ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት ታትመው በወጡ መፅሄቶቻቸው ሃሰተኛ ወሬዎች በማውራት፣ ለአመፅ የሚያነሳሱ ፅሁፎችን ለህዝብ በማድረስ፣ በህገ መንግስቱና በህገ መንግስታዊ ስርአቱ ላይ አመፅ ለማስነሳት ሞክረዋል የሚሉ ክሶች እንደቀረበባቸው ይታወሳል፡፡ ከ“ፋክት” መፅሄት አሳታሚ ድርጅት ስራ አስኪያጅ በስተቀር የሁሉም ተከሳሽ መፅሄቶች ሥራ አስኪያጆችና ባለቤቶች አገር ለቀው መውጣታቸው ይታወቃል፡፡

Read 2338 times