Saturday, 20 September 2014 10:23

በቃሊቲ ጉምሩክ ግቢ በአፈር መደርመስ 3 ሰዎች ህይወታቸው አለፈ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

            ለአዲስ አበባ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት ግንባታ ቃሊቲ ጉምሩክ ግቢ ውስጥ በቁፋሮ ስራ ላይ በነበሩ 7 የቀን ሰራተኞች ላይ ከትናንት በስቲያ የአፈር መደርመስ አደጋ አጋጥሞ የሶስቱ ህይወት ወዲያው ሲያልፍ አራቱ ህይወታቸው ሊተርፍ ችሏል፡፡ ቃሊቲ ወረዳ 6 ጉምሩክ ግቢ ውስጥ ለባቡር ፕሮጀክት የጉድጓድ ቁፋሮ ሲያከናውኑ አፈር ከተደረመሰባቸው 7 ሰራተኞች መካከል የአራቱን ህይወት ያተረፉት የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከልና መቆጣጠሪያ ባለስልጣን የነፍስ አድን ሰራተኞች ሲሆኑ ሶስቱ ህይወታቸው አልፎ አስከሬናቸው እንደወጣ ታውቋል፡፡ በህይወት የተረፉትም በአካባቢው ወደሚገኝ የህክምና ተቋም ተወስደው ህክምና ተደርጎላቸዋል፡፡ ሐሙስ ረፋድ 4፡30 ገደማ በደረሰው በዚህ አደጋ የሞቱት ሰራተኞች እድሜ ከ20 እስከ 23 እንደሆነ የገለፁት የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከያ የኮሙኒኬሽን ኦፊሰር አቶ ንጋቱ ማሞ፤ ከሁለት ወር በፊት በንፋስ ስልክ ክ/ከተማ ባርኔሮ አካባቢ የባርኔሮ ኮንስትራክሽን 3 የቁፋሮ ሰራተኞችም አፈር ተደርምሶ ህይወታቸውን እንዳጡ በማስታወስ ይህን መሰሉ አደጋ እየተደጋገመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህ መሰሉ አደጋ በተደጋጋሚ ህይወታቸውን እያጡ ያሉት የቀን ሰራተኞች መሆናቸውን ያመለከቱት አቶ ንጋቱ፤ አሰሪዎች ለሰራተኞቻቸው የደህንነት መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ከሟሟላት በተጨማሪ አስፈላጊ የስራ ላይ ደህንነት አጠባበቅ ስልጠና ሊሰጧቸው እንደሚገባ አሳስበዋል - በሰሞኑ አደጋ ህይወታቸው ያለፈው ወጣቶችም ሆኑ የተረፉት በወቅቱ ምንም አይነት የአደጋ መከላከያ አለማድረጋቸውን በመጥቀስ፡፡

Read 1709 times