Saturday, 13 September 2014 15:54

ሳቅ አታ‘ቅም

Written by 
Rate this item
(6 votes)

ሳቅ አታ‘ቅም
“ሳቅ አታ‘ቅም አሉኝ - ሳቅ እንዳስተማሩኝ
ሳላ‘ቅ ብስቅ እንኳን - ከሳቅ ላይቆጥሩልኝ
እንዴት ብዬ ልሳቅ፣ ሳቅስ መች ለምጄ?
በጭጋግ ታፍኜ፣
በጉም ተጀቡኜ፣
በዶፍ ተወልጄ፡፡”
አትበል ወዳጄ፡፡
* * *
በጉም መሃል እንጅ - የወጣችው ፀሐይ
ነፍስን እያሳሳች - ሀሴት የምታሳይ
ብቻዋን ስትቆም - በጠራራው ሰማይ
ንዳድ ሀሳብ ዘርታ - ባሳር ምታጋይ፡፡
ብቻ ሲሆንማ - ሳቅም ጠራራ ነው፤
ጥርስን ያራቆተ - የከንፈርህ ግዳይ፡፡

ቅርብኝ
ኖኅን መሰኘት አምሮህ - ታንኳ ቢጤ ስትገነባ
አምላክ ያዘዘህ ቀርቶ - ወዳጅህ መርከብህ ከገባ
ዓለም የጨው ክምር ሆና - ፍጥረታቷ ሲረግፉ
ድንገት ታንኳህ ላይ ብገኝ - ነፍሴን አርዷት ዶፉ
ርግቧን መሆን አልሻም፤ ከጎንህ እንዳልገኝ
የትም እንደወጣሁ ልቅር፤ ላንተስ ቁራህን ያድርገኝ
(በቅርቡ በደሴ ከተመረቀው የገጣሚ አካል ንጉሴ “ፍላሎት (የነፍስ አሻራዎች)” 2006፤ የግጥም መድበል የተወሰዱ)


=========


ኢዮሀ!
ኢዮሀ!
አበባ ፈነዳ!
ፀሀይ ወጣ ጮራ፡፡
ዝናም
ዘንቦ
አባራ፡፡
ዛፍ
አብቦ
አፈራ፡፡
ክረምት መጣ ሄደ
ዘመን ተወለደ፡፡
ዓለም አዲስ ሆነ፡፡
ለሊት ሲነጋጋ
ጋራው ድንጋይ ከሰል
የተተረከከ ፍም እሳት ደመናው
ፀሐይ ያነደደው፡፡
ዓለም ሞቆ
ደምቆ፡፡
ብርሃን ሲያሸበርቅ
ጤዛው ሲያብረቀርቅ፤
ሕይወት ሲያንሰራራ
ፍጥረት ሲንጠራራ
ዘመን ተለወጠ መስከረም አበራ፡፡
“ኢዮሃ አበባዬ፡፡”
(ከገብረክርስቶስ ደስታ)

 

Read 4661 times