Saturday, 13 September 2014 13:53

የዋልያዎቹ የሞሮኮ ጉዞ አጠያያቂ ሆነ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

       የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ2015 እኤአ ሞሮኮ ላይ ለሚስተናግደው 30ኛው አፍሪካ ዋንጫ የሚያልፍበት ዕድል ተመናመነ፡፡ ባለፈው ሳምንት በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች በዋልያዎቹ ላይ ደረሱት ምክንያት ሆነዋል፡፡ በምድብ 2 የማጣርያ ጨዋታቸውን ከሳምንት በፊት በሜዳቸው የጀመሩት ዋልያዎቹ በደጋፊያቸው ፊት በአልጄርያ 2ለ1 ሲሸነፉ፤ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ደግሞ ከሜዳቸው ውጭ በብላንታዬር ከማላዊ ጋር ተገናኝተው 3ለ2 ተረተዋል፡፡ በሁለቱ ጨዋታዎች 3ቱን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጎሎች በአልጄርያ ላይ ሳላዲን ሰኢድ በፍፁም ቅጣት ምት እንዲሁም ማላዊ ላይ ጌታነህ ከበደ እና ዩሱፍ ሳላህ አስመዝግበዋል፡፡ በሌሎች የምድብ 2 ጨዋታዎች ማሊ በዋና ከተማዋ ባማኮ ላይ በመጀመርያ ጨዋታዋ ማላዊን 2ለ0 አሸንፋ ባለፈው ረቡእ ደግሞ አልጄርስ ላይ በአልጄርያ 1ለ0 ተሸንፋለች፡፡ ከምድብ ማጣርያው ሁለት ዙር ጨዋታዎች በኋላ በምድብ 2 አልጄርያ በ6 ነጥብ እና በ2 የግብ ክፍያ መሪነቱን ይዛለች፡፡ ማሊ በ3 ነጥብ እና በ1 የግብ ክፍያ እንዲሁም፤ ማላዊ በ3 ነጥብ እና በ1 የግብ እዳ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ተከታትለው ይዘዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ያለምንም ነጥብ በሁለት የግብ እዳ መጨረሻ ነው፡፡
በሁለቱ የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች ሽንፈት የገጠመው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሚያልፍበት እድል መመናመኑ በተለያዩ አቅጣጫዎች አነጋጋሪ እየሆነ መጥቷል፡፡ ዋልያዎቹ በቀሪዎቹ አራት የማጣርያ ግጥሚያዎች ሁሉንም በማሸነፍ ከፍተኛውን ነጥብ መሰብሰብ ካልቻሉ የሞሮኮ ጉዟቸው አይሳካም፡፡ አንዳንድ የስፖርት ቤተሰቦች የአሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ቡድን በቅድመ ዝግጅት የተሻሉ ስራዎች ማከናወኑን ቢያደንቁትም ይህ ሁኔታ በውጤት ሊተረጎም አለመቻሉ ክፉኛ አሳዝኗቸዋል፡፡ በቡድኑ ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች የመጀመርያው ተጠያቂ አሰልጣኙ ሊሆኑ እንደሚገባ የገለፁም በርካቶች ናቸው፡፡ ዋና አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ በወር 18 ሺ ዶላር እየተከፈላቸው ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ ካላሳለፉ ኪሳራ ነው የሚል ሃሜት በዝቷል፡፡ ጎን ለጎን ብሄራዊ ቡድኑን በወጣት ተጨዋቾች በማጠናከር በተሟላ መሰረት ላይ እንዲገነቡ ለፖርቱጋላዊው በቂ የስራ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸውም እየተነገረ ነው፡፡ በአልጄርያው ሽንፈት ላይ የሜዳው አለመመቸት እና የታኬታ ችግር፤ በማጥቃት እንቅስቃሴዎች ላይ ከአሰልጣኙ መመርያ ውጭ ብዙዎቹ ዋልያዎች ረጅም ኳስ በተደጋጋሚ በመጣል ስኬታማ አለመሆናቸው እና የተገኙትን ከ5 በላይ የማግባት አጋጣሚዎች ያለመጠቀም ሁኔታዎች እንደምክንያት ይቀርባሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከማላዊ ጋር ባደረገው ሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ በተከላካይ መስመሩ ከፍተኛ መረበሽ እና ስህተት እንደነበረበት የብላንታዬር ጋዜጦች ሲዘግቡ፤ በአንፃሩ ኡመድ ኡክሪ በመጀመርያው ግማሽ ከዚያም ሳላዲን ሰኢድ፤ ጌታነህ እና ሌሎች የቡድኑ የማጥቃት ሙከራዎች ዋልያዎቹ ቢያደርጉም አጨራራሱ አልሆነላቸውም ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ስታድዬም በመጀመርያው የማጣርያ ጨዋታ የገጠመውን ሽንፈት ተስፋ አያስቆርጠንም ብለው የነበሩት ፖርቱጋላዊው ማርያኖ ባሬቶ በሁለተኛው ግጥሚያ ከስህተቶቻችን ተምረን ነጥብ ለማግኘት እንፈልጋለን ቢሉም አልተሳካላቸውም፡፡
ላለፉት ሶስት አመታት ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር በመጫወት ልምድ ያላቸውን ልጆች ለሁለት ወራት በከፍተኛ ደረጃ ያዘጋጁት አሰልጣኙ ፤ በተጨዋች ምርጫቸው አስራት መገርሳ፤ በሃይሉ አሰፋ እና ዳዊት እስቲፋኖስን ባለማካተታቸው ተተችተዋል፡፡ ታደለ መንገሻ እና ናትናኤል ዘለቀ የመሰሉ ወጣቶች ወደ ቡኑ በመቀላቀል እና በተከላካይ መስመር ቶክ ጀምስ፤ ሳላዲን በርጌቾን በማጣመር መስራታቸው ደግሞ እንደ ጥሩ ለውጥ ተደንቆላቸዋል፡፡ በተለይ በናትናኤል ዘለቀ ላይ ያላቸው እምነት እና ተስፋ በሁለቱም ጨዋታዎች በገሃድ መረጋገጡ ብዙ ስፖርት ቤተሰብን አስደስቷል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋች የሆነው ናትናኤል ዘለቀ ‹‹ አዲሱ ዋልያ›› ተብሎ እየተሞካሸ ሲሆን፤ በተለይ በአልጄርያው ጨዋታ በተሟላ ብቃት የሰጠው አስተዋፅኦ እና የስነልቦና ጥንካሬው የጨዋታው ኮከብ እንደሚያደርገው አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ መስክረውለታል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከወር በኋላ በ3ኛው እና በ4ኛው የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች በአንድ ሳምንት ልዩነት በሜዳው እና ከሜዳው ውጭ የሚገናኘው ከምእራብ አፍሪካዋ ቡድን ማሊ ጋር ይሆናል፡፡ 5ኛውን የምድብ ማጣርያ ጨዋታ ከ2 ወራት በኋላ ከሜዳው ውጭ ከአልጄርያ ጋር ሲገናኝበት በሳምንቱ በማጣርያው የመጨረሻ ስድስተኛ ጨዋታ ማላዊን በአዲስ አበባ ስታድዬም ያስተናግዳል፡፡

Read 3656 times