Saturday, 13 September 2014 13:49

እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር..መሑሀ

አዲሱ አመት ..2007.. ዓ/ም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም ፣የጤናና የብልጽግና እንዲሆን ይመኛል፡፡
የዘመን መለወጫን ምክንያት በማድረግ ከእለቱ ጋር የነበረ ገጠመኝ ልናስነብባችሁ ወደድን፡፡ በመሆኑም ተከታዩን እነሆ ለንባብ ፡፡
.....ነገሩ ያጋጠመኝ በ2006 ዓ/ም መግቢያ ጳጉሜ 4/2005 ነው፡፡ እኔ በእድሜዬ ገና ሰላሳው የገባሁ ስሆን እዩኝ እዩኝ የምል .....መሬቱን ሲረግጠው ድንጋዩ ይፈነቀላል የምባል እይነት ነኝ፡፡.. ታድያ ...አለባበሴን አሳምሬ በአዲስ ዘመን ዋዜማ ነበር ወደ ከተማው ብቅ ያልኩት፡፡ እኔ ወንደላጤ ነኝ፡፡ ቤተሰብ እንዳለው ሰው በግ ወይንም ዶሮ ከሚሸጥበት ሳይሆን ያመራሁት ወደ ልብስ ተራው ነበር፡፡ ብዙም ባይሆንም በመጠኑ ደመወዜ እንደልብ የሚያንቀሳቅሰኝ ነበር፡፡ ከአንድ ኃብታም ድርጅት ውስጥ በአስተዳደ ሩም ፣በእቃ ግዢነቱም ፣በጠቅላላ አገልግሎትነቱም ፣ባለጉዳይ በማነጋገሩም ፣ በመወ ሰኑም ፣በማስወሰኑም...ብቻ ሰውየው ሌላ ሰው መቅጠር ስለማይፈልጉ እኔን ብቻ ከላይ ከታች ስለሚያመላልሱ...እኔም ታድያ ደህና አድርጌ ነበር የተጠቀ ምኩበት፡፡ አሁን ግን አንድ ወር ሆኖኛል ስራዬን ከለወጥኩ.....
ወደ ዘመን መለወጫው ገጠመኝ ልመለስና የ2006/መግቢያ የልብስ ገበያ በዋጋው ብዙም የሚታማ አልነበረም፡፡ ታድያ እየዞርኩኝ ጫማ ስመለከት አንዲት ኮረዳ በድንገት ገጠመችኝ፡፡
... ያነሳሁትን ጫማ እጄ ላይ አይታ...እውይ ባባትህ ...ያምራል ...ብትለካውስ? አለችኝ፡፡
...እኔም ቀና ብዬ ስመለከታት የሆነች ቆንጆ ልጅ ናት፡፡ መለስ አድርጌም...ምን ያረጋል ቢያምር... የወደድሽው አንቺ እንጂ ...ስላት...ታድያ እኔ ከወደድኩልህ መች አነሰህ? አንተ ደግሞ ጉረኛ ነህ መሰለኝ...ብላ ከት ብላ ሳቀች፡፡ አ.አ.ይ እኔ እንኩዋን ጉረኛ አይደለሁም፡፡ ግን እውነ..ን ነውኮ ...ሌሎች አያምርም ቢሉኝስ...ዋጋው ደግሞ ውድ ነው አልኩዋት፡፡
...እንገግዲህ...አለችኝና ትታኝ ወጣች፡፡ እኔ ግን አብሮአት ልቤ ሸፈተ፡፡ ጫማውን መግዛቱን ትቼ እሱዋን ተከተልኩዋት፡፡
..እኔ የምልሽ...
- ምንድነው የምትለኝ...
..የአዲስ አበባ ልጅ ነሽ?...
ከት ብላ ሳቀች፡፡ ምነው? አልኩዋት
- እንጃ...ጥያቄህ አስቆኝ ነዋ...መልሱዋ ነበር፡፡
..ምን ያስቃል...ሁኔታሽ...ንግግርሽ...ሁሉ ደስ ብሎኝ ነውኮ...
- ከአዲስ አበባ ውጭ ያለ ሰው እንደእኔ አይናገርም? አለችኝና ወዲያው
በማስከተል ...ዋናው ነገር... ጫማውን ገዛኸው? አለችኝ፡፡
..አንቺ ትተሸኝ ስትሄጂ ተውኩት...
- ለምን?
..እንዳታመልጪኝ... ልከተልሽ ...ብዬ ነዋ...
- በል ...ና እንሂድና መጀመሪያ ጫማውን ግዛና ከዚያ በሁዋላ እናወራለን...አለችኝ፡፡
በዚህ መልክ ነበር የእኔና የሜላት ግንኙነት የተጀመረው፡፡ ከዚያም ለአንድ ሶስት ወር ገደማ ሻይ ቡና እየተባባልን ቆየን፡፡ ሜላት በጣም ጨዋ ልጅ ነች፡፡ የሰው ገንዘብ በፍጹም አትፈልግም፡፡ አንድ ነገር ላድርግልሽ ስላት ፍጹም ፍቃደኛ አይደለችም፡፡ ለምንበላው ምግብ እንኩዋን ቢያንስ ሻይ ቡናውን ካልቻለች አይመቻትም፡፡ በቃ ...ለትዳር ጉዋደኛ የምትሆነኝ ልጅ አገኘሁ...የእንቁጣጣሽ ስጦታዬ ነች ብዬ አሰብኩ፡፡ ለእናት እና አባ.. ሁኔታውን አጫወትኩዋ ቸው፡፡ ቤተሰቤ በሙሉ ተደሰተ፡፡ መቼ ነው ታድያ ሽማግሌ የምንልከው የሚለው ጭቅጭቅ ከቤተሰቤ እያየለ ሲመጣ እስቲ ቆይ... ከእርሱዋ ጋር እኮ ገና አላወራነውም...እኔ የእራሴን ፍላጎትና ግምት ነው የነገርኩዋችሁ...አልኩዋቸው፡፡
...አንድ እሁድ እኔና ሜላት ለምሳ ቀጠሮ ያዝን፡፡ አብረን እየተመገብን እያለን...ላጎርሳት ስሞክር ...አአይ...አለችና ፊቷ ቅጭም አለ፡፡
..ምነው?...የእኔ ጥያቄ ነበር...
- አአይ...እኔ ጉርሻ አልወድም...
..ለምን?
- አባ..ን ስለሚያስታውሰኝ...ሰው ሲያጎርሰኝ አልወድም...
ለካንስ አባትዋ ሞተዋል፡፡ አዘንኩኝ፡፡ እንደገና ሀሳቤን ሰብሰብ አደረግሁና...
..አኔ የምልሽ...
- እህ...
..ለምን... እ.....ስላት... ገና ሀሳቤን ሳልቋጭ...
-ገብቶኛል ልትለው የፈለግኸው ነገር ገ ብ ቶ ኛ ል... አለችኝ፡፡
.. ታድያ ...ምን ችግር አለው?
-ምንም ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን እኔ እነግርሀለሁ፡፡ አለችኝ፡፡
የዚያን እለት በዚሁ ተለያየን፡፡ ከዚያ በሁዋላ ስልክ ብደውል ...ቀድሞ ሳገኛት የነበረበት ካፊ..ሪያ እና ምግብ ቤት ብሔድ...ማንም...ምንም መረጃ ሊሰጠኝ አልቻለም፡፡ አጣሁዋት፡፡ግራ ተጋባሁ፡፡ በጣም ፈለግሁ ዋት...አላገኘሁዋትም፡፡ ጉዋደኛዋን ቤተሰብዋን...ማንንም አላውቅም፡፡ ታመምኩ ፡፡ አድራሻ አልሰጠችኝም፡፡ የት ነው የምትሰሪው ስላት በግልዋ እየተዟዟረች እንደም ትሰራ ነው የነገረችኝ፡፡ እንዲሁ ...ስጨነቅ... ስጨነቅ... ግንቦት 15/2006 /አንድ መልእክት ደረሰኝ፡፡ እንዲህ ይላል...
.....በድንገት ገበያ ላይ የገኘሁህ ወድ ጉዋደኛዬ...እንደምን ሰነበትክ፡፡ ድንገት ስለጠፋሁብህ በመጠኑም ቢሆን እንደጎዳሁህ ይሰማኛል፡፡ ስሜትህን እንዳልጎዳ ብዬ እንጂ እኔ ሚስት ለመሆን ቀርቶ ከወንድ ጋር እንኩዋን ለመገናኘት ገና በሕክምና የማስተካክለው የጤና ጉዳይ ስለነበረኝ አልደፍርም ነበር፡፡ በቤተሰብ አባል ተደፍሬ ...በድብቅ ...በህገ ወጥ መንገድ ጽንስ በማቋረጥ ምክንያት ማህጸኔ ተጎድቶ ስለነበር ለሕክምና ወደ ሆስፒታል መግባት ነበረብኝ፡፡ የመጨ ረሻ ምሳ የበላን ማግስት ነበር ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የገ ባሁት፡፡ ያንን የምሳ ቀጠሮ ብመለስም ባልመለስም ብዬ ሆን ብዬ ነበር ያመቻቸሁት፡፡ አሁን ሕክምናዬን ጨርሼ እቤ.. ገብቻለሁ፡፡ ከፈለግህ ጠይቀኝ፡፡ ላለፈው ይቅርታ አድር ግልኝ፡፡ አሁን እግዚአብሔር ይመስገን ጤነኛ ነኝ፡፡..... ይላል ...በመልእክተኛ የመጣው ደብዳቤ፡፡
እጅግ በጣም ነበር ያዘንኩትም ...የተደሰትኩትም፡፡ ታማ ሆስፒታል በነበረችበት ወቅት ከጎኗ ብሁን ኖሮ እወድ ነበር፡፡ ነገር ግን ያንን እድል አልሰጠችኝምና አዘንኩ፡፡ በሌላ በኩል... ከሕመሙዋ ድና በመውጣቷ ደግሞ በጣም ተደሰትኩ፡፡ ለማንኛውም ሁኔታዋን ለማየት በሰ ጠችኝ አድራሻ ከቤትዋ ሄጄ አገኘሁዋት፡፡ ተቃቅፈን ተላቀስን፡፡ ለካንስ እርሱዋም ወድዳኝ ነበር፡፡ ጭራሽ ፍቅሬ በረታ፡፡ በእቅፍዋ ስር እንድሆን...በእቅፌ ስር እንድትሆን ሁለታችንም ወደድን፡፡
እነሆ...በተገናኘን በአንድ አመታችን...ዛሬ መስከረም 3/2007 ዓ/ም ሰርጋችን ነው፡፡
.....ደስ ብሎናል ...ደስ ይበላችሁ....
ይስሐቅ ብርሐኔ/ከአዲስ አበባ/መሳለሚያ

Read 3367 times