Saturday, 13 September 2014 13:47

ለሰቆጣ ተስፋ የፈነጠቀው አዲስ ሆቴል

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(3 votes)

የሰቆጣ ተወላጁ አቶ ጌጡ ብርሃኑ ወደ ንግድ ስራ የገቡት በ30 ብር ነወ፡፡ ለዓመታት ብዙ ችግርና መከራ አሳልፈዋል፡፡ ዛሬ ከወንድማቸው ጋር 3ሚሊዮን ብር የፈጀ ባለ3 ኮከብ ሆቴል ገንብተዋል፡፡ ሆቴሉ ለሳቸው ብቻ ሳይሆን መብራትና መንገድ፣ ውሃና ስልክ ለሌላት ሰቆጣም እንደተስፋ ነፀብራቅ ነው የታየው፡፡ የሻደይ በዓልን ለማክበር ዘንድሮ ወደ ሰቆጣ የተሻገሩ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ያረፉት ዲጂ በተባለው የእነ አቶ ጌጡ ሆቴል ነበር፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው ሰቆጣ ለሥራ በሄደችበት ወቅት አቶ ጌጡን በንግድ ተመክሮዋቸውና በከተማዋ እንቅስቃሴ ዙሪያ አነጋግራቸው ነበር፡፡ እነሆ፡-


ተወልጄ ያደግሁት በሰቆጣ ከተማ ቀበሌ 04 ነው፡፡ የዚህ ከተማ ሰው ከትንሽ ነገር ተነስቶ ነው ትልቅ ደረጃ የሚደርሰው… ለዚህ ደረጃ ከመብቃቴ በፊት ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፌያለሁ፡፡ ይህን ሆቴል የማስተዳድረው ብቻዬን ሳይሆን ከወንድሜ ጋር ነው፡፡
አካባቢው የቱሪስት መስህብ ቢሆንም በቂና ጥራቱን የጠበቀ የሆቴል አገልግሎት የለም…
ቀደም ሲል እንግዶች ወደ ሰቆጣ ሲመጡ ዘመድ ቤት ነበር የሚያድሩት፡፡ ዘመድ የሌለው ደሞ ቤት ተፈልጎ ወይም ትምህርት ቤትና በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ያድር ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ሁሉም የበኩሉን ጥረት በማድረጉ፣ በዓሉ በጥሩ ሁኔታ ተከብሯል፡፡ ችግሩ በከፊል የተቃለለ ይመስለኛል፡፡
ሰቆጣ ወደኋላ የቀረችበት ምክንያት ምንድን ነው?
አካባቢው በጦርነት ውስጥ የነበረ ነው፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎት አልነበረውም፡፡ ጥሩ ሆቴሎችም አይታዩም ነበር፡፡ ወደ ኮረም ስንሄድ መቶ ኪሎ ሜትር በእግር ነበር የምንጓዘው፡፡
አሁንም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ችግሩ አልተፋታም፤ ህዝቡ ሁለትና ሶስት ቀን ትራንስፖርት እየጠበቀ ነው የሚሄደው፡፡ በፈለገውና ባሰበው ሰዓት መጓዝ አይችልም፡፡ መኪኖቹም ወደዚህ መምጣት አይፈልጉም፡፡ አስፓልት አስፓልቱን ነው መስራት የሚመርጡት፡፡ መንገዱ በቶሎ መሰራት አለበት፡፡
ሆቴል የተገነባበት ስፍራ በፊት ምን ነበረ?
ሆቴል የቀለስኩበት ስፍራ በረሃ ነበር፤ ሰው አይኖርበትም፤ ከተማ ቢሆንም እኛ እዚህ አንኖርም ነበር፤ ዋሻ ነው የምንውለው፤ ማታ ነበር ልንተኛ የምንመጣው፡፡ ማንም ሰው በቀን መገበያየት ስለማይችል ቀን ቀን ስፍራው ምድረበዳ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው ከተማዋ አስራ አንድ ጊዜ በአውሮፕላን ተደብድባለች፡፡ ጎረቤቶቻችን በአውሮፕላን ድብደባው መሞታቸውን አስታውሳለሁ፡፡
እንዲህ ያለ ለውጥ ይመጣል፤ ብሎ ያሰበ አልነበረም፡፡ በእርግጥ ትግል ይካሄድ ነበረ፤ ታጋዮቹ ይታገላሉ፤ እኛ ግን ብዙም ተስፋ አልነበረንም፡፡ ይሄ ሆቴል ተሰርቶ፣ መንገድ ተከፍቶ ሌላው የደረሰበት እንደርሳለን ብዬ አስቤም አልሜም አላውቅም፡፡ ግን ደረስን፤ ያ ወቅት ዘግናኝ ነበር፡፡ ሰው በደቂቃ ውስጥ ወደ ሬሳ የሚቀየርበት ጊዜ ነበር፡፡ አውሮፕላን ከሰማይ ላይ የሚጥለው አምስት ኩንታል ክብደት ያለው ፈንጂ ነው፡፡ አንድ ጊዜ አስታውሳለሁ የ19 ዓመት ወጣት ነበርኩ፡፡ አውሮፕላኑ የጣለው ናፓል የሚባል ፈንጂ ነበር፡፡ ህዝቡን ጨፈጨፉት … ያ ወቅት አልፏል እንጂ ሰቅጣጭ ነበር፡፡
ስለንግድ አጀማመርዎ አጫውቱኝ?
ከበለሳ ሀሙሲት ወጥቼ በባለ ሀያ ሊትር ጀሪካን ናፍጣ ገዛሁ፡፡ በለሳም ገበያቸው ማታ ነበር፡፡ እኔ አላወቅሁም ነበር፤ ለካስ ጀሪካኑ ተቀዶ በማስቲካ አያይዘው ነበር የሸጡልኝ፡፡ ትንሽ እንደተጓዝኩ ማስቲካው ለቀቀና ናፍጣው መፍሰስ ጀመረ፡፡ ይታይሽ ሁለት መቶ ሃምሳ ብር ነው የገዛሁት፡፡ ትክክለኛ ዋጋው ግን 220 ብር ነበር፡፡ ደሞ ብቻዬን አልነበረም፤ ትርፍ የጋራ ብለን ከሌላ ሰው ጋር ገንዘብ አጋጭቼ ነው፡፡ ጀሪካኑ በትከሻዬ ላይ ተሸክሜ የ5 ሰዓት መንገድ ተጉዤ ተከዜ ገባሁ፡፡ ተከዜ ለም አፈር አለ… አፈሩን አድርጌበት፤ በነጭ ላስቲክ ስጓዝ፣ ሰቆጣ ለመድረስ የ4 ሰዓት መንገድ ሲቀረኝ ማፍሰስ ጀመረ፡፡ ሲያልፍ እንዲህ ይወራል እንጂ በሰዓቱ እያለቀስኩ ነበር፤ ልከስር ነው ብዬ ፈርቼ ማለት ነው፡፡ ግን እንደማይደረስ የለም፤ በአራተኛ ቀኔ እየተሳብኩ ደረስኩ፡፡ ያሰብኩትን ሰላሳ ብር ባላተርፍም በዋናው ተሸጠና ከእዳ ተረፍኩ፡፡
በንግድ እንቅስቃሴ ከታጋዮች ጋር የምትገናኙበት ወቅት ነበር?
አዎ፡፡ ስኳር እወሰድላቸው፣ ፓንት እሸጥላቸው ነበር፡፡ ለ2ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ 32 ኩንታል መኮረኒ አምጥቼላቸዋለሁ፡፡ ጉባኤው የተካሄደበት አለውቅ የሚባል ወንዝ አለ፤ እዚያ ድረስ አቅርቤላቸዋለሁ፡፡ ቲሸርት ነበረች የታጋዮች … አሁን ያቺን ቲሸርት የት አየኋት? አርቲስት ጎሳዬ ተስፋዬ ለብሷት! ያቺ ቲሸርት ለዚህ ድርጅት ባለውለታ ናት፡፡ አንድ ፓንትም ነበረች፤ ባለዚፕ፡፡ እስከ 2ሺ ብር ትይዛለች፡፡ እሷን ሁሉ እሸጥላቸው ነበር፡፡ እኛ እራሱ ገንዘባችንን ሽፍታ እንዳይወስድብን ደብቀን የምንይዘው በፓንቱ ውስጥ ነበር፡፡ እነሱ እና እኛ ምንም ልዩነት አልነበረንም፡፡ ለንግድ ስንቀሳቀስ ደብዳቤ ሁሉ አደርስላቸው ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ደግሞ በጋማ ከብት ሸቀጣችንን ይዘን ስንጓዝ፣ ዛምራ የተባለ ቦታ ላይ ጎርፍ ያዘን፡፡ ሶስት ሆነን መሸጋገር ስላልቻልን ቢያልፍለት ብለን አደርን፤ ጠዋት ላይ ጎደለ ብለን ስንገባ አንደኛው ጓደኛችንን እስከ አህያ ጭነቱ ጠርጎ ወሰደው… ልጁን አተረፍነው፤ ሸቀጡ ተበላ፡፡
ግን ዞኑ ለትግሉ እንዳበረከተው አስተዋጽኦ ምንም የልማት ስራ አልተሰራለትም፡፡ አሁን እኮ በየቦታው ወረዳ ውስጥ እንኳን አስፓልት ነጥፏል፡፡ እያንዳንዱ ቤተሰብ ኮሎኔልና ጄነራል ደረጃ የደረሱ ታጋዮች ያሉበት ነው … በየቤተሰቡ በትግሉ የተሰዋ አለ፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊነታችን ለእኛም ተገቢው ሁሉ ሊደረግልን ይገባል፡፡
የሆቴሉ የንግድ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
አሁን ይሄ ሆቴል ተሰርቷል፡፡ ነገር ግን ሰው ካልመጣ፣ ተጠቃሚ ካልተገኘ መዘጋቱ ነው፡፡ ቀድሞ እስከ 3 መቶ ኪሎ ሜትር በእግራችን እየተጓዝን ነበር ንግድ የምናጧጡፋው፡፡ መንገድ ሲሰለቸኝ በ500 ብር ኪዮስክ ከፈትኩ፡፡ ሳሙና፣ ኦሞ… አምጥቼ ደረደርኩ… ደሴ እየተጓዝኩ ሸቀጦችን ማምጣት ጀመርኩ፡፡ ኢህአዴግ ደርግን ጥሎ ሥልጣን ሲይዝ በእግር መሄድ አቆምን፡፡ መኪና ላይ እንደ እቃ ተጭነን፣ ከኮረም ሰቆጣ ለመድረስ አንድ ቀን ነበር የሚፈጅብን - መቶ ኪሎ ሜትር፡፡ ኮረም መኪና ለማግኘት አራትና ሶስት ቀን እንጠብቃለን … ሱቋ እያደገች መጣች፤ ወደ 3ሺ ብር አገኘሁ፡፡ በ1987 ዓ.ም ሱቅ እየሰራሁ ሳለ መንግስት የግንባታ ሥራዎችን ጀመረ፡፡ እኔም የቀበሌ ሽንት ቤቶች … ግንባታ ላይ መሳተፍ ያዝኩ፡፡
ግንባታ ላይ ሰርተው ያውቁ ነበር?
በድፍረት ነው የገባሁት፡፡ ከወንድሜ ጋር ሆነንም የት/ቤቶችን ግንባታ በኮንትራት በመውሰድ መስራት ጀመርን፡፡ ከዚያ ብሩ ተጠራቀመ… ይሄን ሁሉ ስንሰራ የአንድ ቀን መንገድ በጋማ ከብት ተጉዘን ብረትና ሲሚንቶ እየጫንን ነው፡፡ ባህር ዛፍ የምንጭነው በሰው ደንደስ ነበር፡፡ ወደ አራት ት/ቤቶች በዚህ ሁኔታ ነው የሰራነው፡፡ ቢሮዎችን፣ መጋዘኖችንና ኮንደሚኒየሞችንም እንገነባ ጀመርን፡፡
በአንዴ ከበራችሁ በሉኛ?
ገንዘብ አጠራቀምና በ130ሺ ብር ኤኒትሬ ገዛን፡፡ እድገታችን እየጨመረ መጣ፤ ቆየት ብለን አንድ ፒካፕ ላንድ ክሩዘር ጨመርን፤ ኮንስትራክሽን ዘርፍ ደረጃ ስድስት ገባን፡፡ ይሄኔ ዶዘር ከቀረጥ ነፃ አስገባንና ሥራችንን ገፋንበት፡፡ በመቀጠልም ሁለት ገልባጮች፣ ፒካፕ፣ ኤሮትራከር፣ ወደ ሶስት መኪኖች ባለቤት ሆንን፡፡ ከዚያ ቁጭ ብለን ከወንድሜ ጋር በመመካከ፣ ሰቆጣ ምንድነው የሚያስፈልጋት ብለን አጠናን፡፡ ሆቴል መሆኑን ተረድተን፣ ቦታ ጠየቅንና የከተማ አስተዳደሩ መሬት ሰጠን፡፡ ሆቴሉን ገነባን፡፡
እንዴት ነው ቱሪስቶች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል?
እስካሁን ሆቴሎች የላችሁም በሚል ምንም እንቅስቃሴ አልነበረም፡፡ ስብሰባዎች አልተለመዱም፡፡ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እኮ ከ2ሺ በላይ የውጭ አገር ቱሪስቶች በዚህ በኩል ያልፋሉ፡፡ ሆኖም እዚህ ማረፊያ የለም ስለሚባል አይቆሙም፡፡ መስቀለ ክርስቶስ ከሰቆጣ ከተማ በ5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው ያለው፡፡ ያንን ለማስጐብኘት እንኳ ቱሪዝም በቱሪስት ጋይዱ ላይ አላካተተውም፡፡ ይሄ ሁሉ ሆቴል የላቸውም በሚል ነው፡፡ ይሄን ሆቴል ስንጨርስ የቱሪዝም ጋይዱ ላይ ያስገቡልናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ መንገዱ ተሰርቶ አስፓልት ከሆነልን በእርግጠኛነት የመለወጥ ተስፋ አለን፡፡
የሆቴል ግንባታው ምን ያህል ፈጀ?
3 ሚሊዮን ብር ገደማ ጨርሷል፡፡ 47 ደረጃቸውን የጠበቁ የመኝታ ክፍሎች አሉት፡፡ የ20 ዓመት ድካምና ልፋት ውጤት ነው፡፡ ከ30 ብር ተነስተን ባለ 3 ሚሊዮን ብር ካፒታል ሆነናል፡፡
የሆቴሉ ደረጃ ባለስንት ኮከብ ሊባል ይችላል?
ስንጨርስ 3 ኮከብ ይሰጡናል፡፡ ፓርኪንግ አለው፤ ወደ 2 መቶ ሰው የሚይዝ አዳራሽ እየገነባን ነው፡፡ የአካባቢው ችግር ውሃ ነው .. ውሃ ቢኖረን ፕላኑ ላይ የመዋኛ ገንዳ አለው፡፡ የአልጋዎቻችን ኪራይ ከመቶ ሃያ እስከ ሁለት መቶ ሃምሳ ብር ነው ፡፡
የወደፊት ዕቅድዎ ምንድነው?
አሁን ወደ ዱባይ ለመሄድ እየተዘጋጀሁ ነው፤ ለሆቴሉ የሚያስፈልጉ እቃዎች ለመጫን፡፡ ወደፊት በሆቴልና በቱሪዝም ዘርፍ ስራችንን ለማስፋፋት የሌላ አገር ተሞክሮን ማየት እፈልጋለሁ፡፡
ቤተሰብ መስርተዋል?
አገው ቤተሰብ ለመመስረት ችግር የለበትም፤ የስድስት ልጆች አባት ነኝ፡፡ እንግዲህ እድሜዬ ወደ አርባ ሶስት ዓመት እየተጠጋ ነው፡፡ ብዙ ስራዎችን የሰራሁት ከወንድሜ ጋር ነው፡፡ አዲስ የተከፈተው ሆቴላችን DG ይባላል፡፡ ደሳለኝና ጌጡ ለማለት ነው፡፡ አሁን እቅዳችን የተሻለ ሆቴል መስራትና ፋብሪካዎችን መገንባት ነው፡፡

Read 3676 times