Saturday, 13 September 2014 13:20

የዛሬ 40 ዓመት፡፡

Written by 
Rate this item
(5 votes)

(መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም)
… መስከረም ሁለትን ሳስብ ብዙ ነገር ወደ አዕምሮዬ ይመጣል፡፡ ደርግ ከንጉሰ ላይ ሥልጣን ከተረከበ በኋላ በየዓመቱ መስከረም ሁለት ትልቅ ክብረበአል ነበር፡፡ ወጣቱ አብዮት የሚባለውን ሲያይ መጀመሪያ አካባቢ ጉጉና ደስተኛ ነበር፡፡ በአሉም በሠራዊቱ የተለያዩ ትርኢቶች ታጅቦ፣ በየአመቱ በአብዮት አደባባይ (መስቀል አደባባይ) በከፍተኛ ድምቀት ይከበር ነበር፡፡ ወታደሩ ከ4-5 ሰአት የሚዘልቅ ትርኢቶችን ያቀርባል፡፡ በታላቁ ቤተ-መንግስትና በብሔራዊ ቤተመንግስትም በእለቱ ጓድ መንግሥቱ ኃለማርያም እና ባለቤታቸው ወ/ሮ ውብአንቺ ቢሻው በተገኙበት ለሁሉም የቤተመንግስቱ ጠባቂዎች ታላቅ ግብዣ ይደረግ ነበር፡፡
መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ደግሞ ሲታወስ ደርግ አዋጁን ከተናገረ በኋላ፣ ህዝቡ የእርስ በእርስ ግጭት ጠብቆ ነበር፡፡ ከፍተኛ እልቂት ይመጣል ተብሎ ተሠግቶ ነበር፡፡ ታንኮችና መትረየስ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ይርመሰመሱ ነበር፡፡ ሰው መተያየት ፈርቷል፣ መኪናዎቹንና ታንኮቹን ቀና ብሎ ማየት ፈርቷል፡፡ ሰው በአጠቃላይ እርስ በእርስ ተፈራርቷል፡፡ ምናልባት ሌሊት አሜሪካን በአውሮፕላን ወረራ ፈጽማ ወይም እስራኤል መጥታ ንጉሱን ይወስዳሉ የሚሉ ሃሳቦች በፍራቻ መሃል ይንሸራሸሩ ነበር፡፡
ክቡር ዘበኛ እና ወታደሩ ሊጋጭ ይችላል የሚል ስጋትም ነበር፡፡ ነገር ግን ክቡር ዘበኛ ምንም የወሰደው እርምጃ የለም፡፡ የመሣሪያ ድምጽ እንኳ በእለቱ ኮሽ አላለም፡፡ መውረዳቸውን አምኖ ተቀብሏል፡፡ ይህ ባይሆን እንኳ መፈንቅለ መንግስት አድራጊው ወገን፣ ክቡር ዘበኛ ካንገራገረ ማጥቃት የሚችል ሠራዊት በቤተ-መንግስቱ በድብቅ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡
ንጉሡ ከቤተ-መንግስታቸው በደርጉ ሃይሎች ተከበው፣ በተዘጋጀችለቸው ቮልስዋገን መኪና ውስጥ ገብተው ወደ 4ኛ ክ/ጦር ሲወሰዱ፣ ብዙ ህዝብ በመንገድ ላይ ወጥቶ ይመለከት ነበር፡፡ በእድሜ ጠና ባሉት ሰዎች ላይ የማዘን ስሜት ይስተዋል ነበር፡፡ ወጣቱ ደግሞ “ሌባው! ሌባው! ሌባው!” የሚል ስድብ በፉጨትና በጩኸት እያጀበ ይሰነዝራል፡፡ ወጣቱ በጣም ይሳደብ ነበር፡፡ በተለይ ቮልስዋገኗ መስቀል አደባባይ አካባቢ ስትደርስ የነበረው ፉጨትና ጭብጨባ ልዩ ነበር፡፡
ደርጉ ዋና ዋና የሚባሉትን የመንግስት ስልጣኖች በሚገባ በቁጥጥሩ ስር ከዋለ በኋላ ስለነበር እሣቸውን ከስልጣን ያወረደው መንገዱ ሁሉ የቀና ሆኖለታል፡፡ ጃንሆይም ይህን ስለሚያውቁ በአጋዦቻቸው አማካይነት ሌላ እርምጃ ለመውሰድ አላንገራገሩም፡፡ ዝም ነው ያሉት፡፡ ወደ ቮልስዋገኗ እንዲገቡ ሲጠየቁ አላንገራገሩም፡፡ ለምን በቮልስዋገን ተወሰዱ? ተብሎ ሲታሰብ ደርግ እሣቸው መሆናቸው ሳይታወቅ እንዲሄዱ የተጠቀመበት ቴክኒክ ነበር፡፡ ተራ ሰው እንዲመስሉና ግርግር እንዳይፈጠር ነው፡፡ ነገር ግን ሰው አውቆታል፡፡ በኋላ ዳርና ዳር መትረየስ የጫኑ ጂፖች አጅበዋቸው ሲሄዱ ሰው ከፉጨትና ጭብጨባ፣ ስድብ በቀር አንዲት ጠጠር እንኳ አንስቶ አልወረወረም፡፡ በዚያ ላይ ደህንነቱ በሰው መሃል ተሰግስጓል፡፡ ወታደሩም አንዳንዱ ሲቪል ለብሷል፡፡ ጃንሆይ ከስልጣን ከወረዱ በኋላ በእውነቱ ምስኪናዊ ህይወት ነው ያሳለፉት፡፡ ማንም ጠያቂ የላቸውም ነበር፡፡ የሚቀርባቸውም ሰው አልነበረም፡፡ ብቻቸውን አንድ ቤት ውስጥ ነበር የሚኖሩት፡፡ ንጉሱ ዘወትር ፊታቸውን ወደ ቤተክርስቲያኑ አዙረው ፀሎት ሲፀልዩ ስታይ በጣም ያሳዝኑ ነበር፡፡ ማንም አያናግራቸውም፤ አይጠጋቸውም ነበር፡፡ አንዲት ምግብ የምታበስል ልጅ አለች፤ እሷም ብትሆን በተወሰነ ሰዓት መጥታ ስራዋን ሰርታ ነው የምትሄደው፡፡ አርብ እና አሮብን ጠንቅቀው ይፆሙ ነበር፡፡ ልጅቱም ዘግይታ ነው ምግብ የምትሰራላቸው፡፡ ልጅቱ ልብሱን አዘጋጅታላቸው ትሄዳለች፡፡ ራሳቸው ይለብሳሉ፡፡ በዚህ መልኩ በዚያው በቤተ መንግስቱ በቀን እስረኝነት ከሰው ተገልለው ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ ህይወታቸው ማለፉ ተነገረ…
(“ህይወት በመንግስቱ ቤተ-መንግስት” የተሰኙ ተከታታይ መፅሃፎች ደራሲና የቀድሞ ልዩ ሃይል አባል ወ/ር እሸቱ ወንድሙ ለአዲስ አድማስ ከፍተኛ ሪፖርተር አለማየሁ አንበሴ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም አስመልክቶ ከሰጡት ቃለ ምልልስ የተወሰደ፡፡)

Read 3327 times