Print this page
Saturday, 13 September 2014 13:13

የዘመን መለወጫና አፄ ቴዎድሮስ

Written by  ኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(3 votes)

“ይማሯል እንደ አካልዬ! ይዋጉዋል እንደ ገብርዬ!”

         ይህን የተናገሩት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ናቸው፡፡ በዘመናቸው የነበሩ ካህናትና የእስልምና መሪዎች “እኔ እበልጣለሁ ሊቁም እኔ ነኝ” እየተባባሉ ያስቸገሩ ነበርና ሁለቱን ወገኖች የሚፈትኑበት አጋጣሚ ሲፈልጉ ዘመን መለወጫ ደረሰ፡፡ የዘመን መለወጫ ዕለት ደግሞ ክርስቲያኑም ሙስሊሙም በፌስታ የሚያከብሩት ቀን ነው፡፡
እናም አፄ ቴዎድሮስ የእስልምናም ሆነ የክርስትና ሊቃውንትን ቦሩ ሜዳ (ወሎ) ላይ ሰበሰቡና “እንደምታውቁት አገሬ ድሃ ናት፤ እኔም ድሃ ንጉስ ነኝ፤ ብችል ኖሮ ለክርስቲያኑና ለሙስሊሙ ወገን ብቻ ሳይሆን ለእያንዳንዱ ዜጋ አንዳንድ ሰንጋ ባድለው ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ግን አልቻልሁም፡፡ ስለዚህ ለበአል መዋያ እንዲሆናችሁ ይህን ሰንጋ ሸልሚያችኋለሁና ተካፍላችሁ ብሉ” ይሏቸዋል፡፡ ፈተናው የሚጀመረውም እዚህ ላይ ነው፡፡
ከየቦታው በአዋጅ የተሰበሰበው ቃዲና ቄስ “እኔ ነኝ የምባርክ፣ እኔ ነኝ የምባርክ” በማለት ሽኩቻ ይጀምራል፡፡ በመሃሉ ግን መምህር አካለ ወልድ ሰርፀወልድ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው፣ ነጭ ጭራቸውን በመነስነስ መናገር ሲጀምሩ፣ የካህናቱ ሁካታ ወደ ሌላ ጉርምርምታ ተሸጋገረ፡፡ የንግግራቸው ፍሬ ሃሳብ “ቀድሞ ለመባረክ ጠብ አያስፈልግም፡፡ ስለዚህ ካህናት ቢላዋውን ለሙስሊሞች ስጡ እነሱው ይባርኩት” የሚል ነው፡፡
በዚህ ንግግራቸው ሙስሊሞቹ በአሸናፊነት ስሜት ሲደሰቱ፣ የካህናቱ ወገን በበኩሉ በ “ተጠቃን” ባይነት መንፈስ ጉርምርምታና እርግማኑን በመምህር አካለ ወልድ ላይ አዥጐደጉደው፡፡ በሙስሊሞች የተባረከው ሰንጋ ቆዳው ከተገፈፈ በኋላ በንጉሱ ትዕዛዝ መሰረት ግማሹ ለካህናት ተሰጠ፡፡ ሊቃውንቱ ግን “ያለ ዛሬ ጥቃት ደርሶብን አያውቅም፡፡ ሃይማኖታችን በንጉሳችን ተዋረደ…” በማለት ወደየመጡበት ጉዞ ሲጀምሩ፣ አሁንም አካለ ወልድ መስቀላቸውን ከበርኖሳቸው ውስጥ አወጡና ድምፃቸውን ከፍ አርገው “በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ በእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን!” ብለው ከበሬው ስጋ መብላት ጀመሩ፡፡ አከታትለውም “ለመሆኑ ከእስልምናም ሆነ ከክርስትና ሊቃውንት መሃል ይህን ጥያቄ የሚመልስልኝ አለ?” አሉና ጥያቄያቸውን ለሁሉም ወገኖች አቀረቡ፡፡ ጥያቄው “ክርስቲያን ያረደውን ሙስሊም አይብላ፣ ሙስሊም ያረደውን ክርስቲያኑ አይቅመስ የሚል ትዕዛዝ በመጽሐፍ ቅዱስ ወይም በቅዱስ ቁርዓን ተጽፎ እንደሆነ ንገሩኝ” የሚል ነው፡፡
ሙስሊምም ሆነ ክርስቲያኑ ራሱ በራሱ ላይ የፈጠረው የመራራቂያ ድንበር እንጅ በተለይ በስጋ ላይ የተደነገገ ህግ ባለመኖሩ፣ የሁለቱም ወገን ሊቃውንት በትዝብትና በባዶነት ስሜት መተያየት ጀመሩ፡፡
አፄ ቴዎድሮስ የሁለቱን ወገን ምሁራን መፈተን የፈለጉበት ነጥብም ይኸው ነበርና የመምህር አካለ ወልድን ሊቅነት በማድነቅ “ስሚኝ አንች ቆማጣ ቆመጥማጣ ሁሉ ሁልሽም በየፊናሽ ተምሬያለሁ እያልሽ በወገኔ ላይ ትደነፊያለሽ፤ ዕውቀት ማለት የአካልዬ ነው፤ ይማሯል እንደ አካልዬ ይዋጉዋል እንደ ገብርዬ!” በማለት የሊቁን አካለወልድን ዕውቀት ከጀግናው ፊታውራሪ ገብርዬ የጦር ሜዳ ውሎ ጋር በማነፃፀር አወድሰዋል፡፡ ፈተናውን ያለፉ መምህር አካለ ወልድ ብቻ ናቸዋ! በማንኛውም የዓለም ክፍል ሃይማኖት በምግብ ላይ የሚያሳድረው ልዩነት የለም፤ ግን እኛ አገር ላይ ሲደረግ ነበር፤ ይደረጋልም፡፡
ከመንዜው ሊቅ አባታቸው መምህር ሰርፀ ወልድና ከመርሃቤቴዋ እናታቸው ወ/ሮ ወለተ ኪሮስ በ1824 ገድመ ፋራ (ገዳመ ፋራ) ልዩ ስሟ ውቢት በተባለች አምባ የተወለዱት አካለ ወልድ ዜማ ለመማር፣ ከትውልድ ቀያቸው ርቀው የእናት አባታቸውን ግቢ ለቀው አልሄዱም፡፡ እስከ 12 አመታቸው ፆም ድጓ ድረስ ያለውን የዜማ ትምህርት እዚያው ተማሩ፡፡
ከዚያ በኋላ ግን ገና በልጅነት ዘመናቸው ዕውቀት የጠማቸው አዕምሮ ብሩሁ አካለወልድ ቅኔ ለመማር አኩፋዳቸውን አዝለው፣ ቅላቸውን አንጠልጥለው ወሎ ክ/ሀገር ወደምትገኘውና ዳባት ማርያም ወደ ተባለችው የቅኔ አምባ ተጓዙ፡፡ በዚያም አባጫልቱን ከሚባሉ የቅኔ ሊቅ ቅኔን ከእነ አገባቡ ተምረው፣ በቤተ ክህነት ትምህርት ውስጥ ኃይለኛነቱ (ከባድነቱ) የሚነገርለት የቅኔ መምህር ለመሆን በቁ፡፡
የአዳራሹን ምሰሶዎች ጨብጦ “ነፍሴ ከኢሎፍላዊያን ጋር ትውጣ” እንዳለው ሶምሶን ቅኔን ያህል ከባድ ዕውቀት ይዘው ነፍሳቸው ከትምህርት ጋር እንድትተሳሰር ገና ከጥዋቱ በመወሰናቸው፣ ለሌላ ትምህርት ወደ ጐንደር ተጓዙ፡፡ ጐንደር ከተማ ውስጥ ከሚገኘውና ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ በተባለው ቦታም ቅኔ እያስተማሩ በአታ ከነበሩት ሊቃውንት የመጻሕፍተ ብሉያትን ትርጓሜ አጠኑ፡፡
የመፃሕፍት ትርጓሜ ትምህርት ይበልጥ እየሳባቸው ፍልስፍናው እየማረካቸው በመሄዱም እዚያው ጐንደር ከተማ ውስጥ በሚገኙት በአጣጣሚ ሚካኤልና እልፍኝ ጊዮርጊስ የመጻሕፈተ -ሃዲሳትንና ሊቃውንትን ትርጓሜ እስከ አንድምታው ተማሩና በሊቅነታቸው ላይ ሌላ የዕውቀት ካባ ደረቡ፡፡
ገና ከጉብልነት ዘመናቸው ጀምሮ “የቀለም ቀንድ” የሚል ቅጽል የተሰጣቸው አካለወልድ፤ በዚህ ሳይወሰኑ የመፃሕፍተ መነኮሳትን ትርጓሜ “መምህር ሃብቱ” ከተባሉ ዕውቅ ምሁር አጥንተው የአራቱ ጉባዔያት ወይም የሰማንያ አንዱ መፃሕፍት ቅዱሳት ማህደር በአሁኑ አጠራር “ስፔሻሊስት” መሆናቸውን አረጋገጡ፡፡
አካለ ወልድ በዕውቀት የዳበሩ በሊቃውንት ዘንድ የተከበሩ ቢሆኑም የሹመት አባዜ፣ ወይም እዩኝ፣ እዩኝ ባይነት ያልነበራቸው ይልቁንም የአባቶቻቸውን ፈለግ የተከተሉ ትሁት፣ ሰውን አክባሪና እግዚአብሔርን ፈሪ በመሆናቸው ሊቃውንቱ ትዕግስታቸውን ከኢዮብ፣ ቸርነታቸውንና ሃይማኖታቸውን ከአብርሃም፣ ሊቅነታቸውን ከጐጃሜው አራት አይና ጐሹ እያመሳሰሉ በቅኔ ያወድሷቸው ነበር፡፡
በዚህ የተነሳ ከካህናት ጋር እምብዛም ተዛምዶ ያልነበራቸው ዳግማዊ ቴዎድሮስ ሳይቀሩ ከሌሎች ሊቃውንት በተለይ ሲያደንቋቸው፣ ሲንከባከቡዋቸውና ሲያከብሯቸው ኖረዋል፡፡ ብዙውን ጊዜ አፄ ቴዎድሮስ ችሎት ሲቀመጡም ሆነ ሃይማኖታዊና ስጋዊ ጉዳዮች ላይ ለሚነሱ ክርክሮች መፍትሔ የሚሆኑ የፍትሃ ነገስት አንቀፆችን በመጥቀስ ያግዙ እንደነበር ታሪክ እማኝነቱን ይሰጥላቸዋል፡፡ ለዚህም አይደል አፄ ቴዎድሮስ ከጀግና ገብርዬን ፣ ከሊቅ መምህር አካለ ወልድን ማድነቅ ይቀናቸው የነበረው!
በወቅቱ ካህናት ሸፍጥና ቴዎድሮስ እንደ “ወደል ጋለሞታ” ሲቆጥሮአቸው በነበሩ መሳፍንት ሴራ ተከታይ እየራቃቸው፣ ጉልበት እያነሳቸው በሄዱበት ወቅት በጀኔራል ናፒር በተመራው ወራሪው የእንግሊዝ ጦር “እጄን አልሰጥም” በማለት ቴዎድሮስ የጀግና ሞታቸውን ከሞቱ በኋላ ሊቁ አካለ ወልድ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ሸዋ ሄዱ፡፡
የመምህር አካለ ወልድን ሸዋ መግባት የሰሙት ንጉስ ምኒልክ፤ ድሮ አፄ ቴዎድሮስ ግቢ በምርኮኛነት ለ10 አመታት ሲኖሩ የአካለ ወልድን ሊቅነት አሳምረው ያውቁ ነበርና በታላቅ አክብሮት ተቀበለው መጀመሪያ የቁንዲ ጊዮርጊስ ቀጥሎም የፍርኩታ ኪዳነ - ምህረት አስተዳዳሪ አድርገው ሾመዋቸዋል፡፡
በማስተማር ችሎታቸው የሚደነቁት አካለ ወልድ፤ ፍርኩታ ላይ ሳሉ በንጉስ ምኒሊክና በአፄ ዮሐንስ መካከል ፖለቲካዊ ችግር በመፈጠሩ ምኒልክን ግራ ገባቸው፡፡ ጦርነት እንዳይገጥሙ ሃይላቸው ከአፄ ዮሐንስ ጋር የማይመጣጠን በመሆኑና ይልቁንም ዮሐንስ እንግሊዞች በአስታጠቋቸው መስሪያ በመመካት፣ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉበት ወቅት በመሆኑ ለምኒልክ የሚበጀው መንገድ ችግሩን በውይይት መፍታት ብቻ ነበር፡፡ ለአስታራቂነት ደግሞ በወቅቱ ከካህናት የበለጠ ከዮሐንስ ፊት የሚቀርብ ሃይል አልነበረም፡፡
ስለዚህ ምኒልክ በሸዋ ውስጥ አሉ የሚባሉትን ሊቃውንት ሰብስበው፣ ወደ ዮሐንስ አራተኛ ሲልኩ መምህር አካለ ወልድ ሰርፀወልድም የቡድኑ መሪ በመሆን ተመረጡና ወደ መቀሌ ገሰገሱ፡፡
ጦር ሊያማዝዝ ጥቂት ቀርቶት የነበረው የዮሐንስ 4ኛና የንጉስ ምኒሊክ ጠብ በዕርቅ እንደደመደም ካደረጉት ሊቃውንት መሃል አካለ ወልድ ቀዳሚው መሆናቸውን ዮሐንስ በመርዳታቸውም ከዚያን ጊዜ ጀምረው አይናቸውን በሊቁ ላይ ጣሉ፡፡ እናም መምህር አካለ ወልድ በወሎ ክፍለሀገር የክርስትና ዕምነትን እንዲያስፋፉ በአፄው ትልቅ ሃላፊነት ተጣለባቸው፡፡
መምህር አካለ ወልድ በወሎ ውስጥ በሚገኙ አውራጃዎች እየተዘዋወሩ፣ ህዝብ በማስተማር በርካታ ምዕመናንን በማፍራታቸው፣ ከፃድቁ አባ ኢየሱስ ሞአ ቀጥለው በክፍለሀገሩ ውስጥ ታላቅ ሃዋርያዊ ተልዕኮ የተወጡ የዘመኑ ፃድቅ እስከመባል በቅተዋል፡፡
ሊቁ አካለ ወልድ አስተማሪ፣ ዮሐንስ 4ኛ የአገር መሪ በነበሩበት ወቅት ወሎ ውስጥ አንድ ተአምር መታየቱም ከታሪካቸው ላይ በዝርዝር ተጽፏል፡፡ በአጭሩ እንዲህ ይነበባል:- “ከእምባቦ ጦርነት በኋላ አፄ ዮሐንስ፤ ንጉስ ተክለ ሃይማኖትና ንጉስ ምኒሊክ ለምክክር በተሰባሰቡበት በቦሩ ሜዳ ምስራቃዊ ክፍል በሚገኘው በአፄ ዮሐንስ ቤተ መንግስት ላይ ከፍተኛ ተአምር ታዬ፡፡
“መስከረም 10 ቀን 1876 ዓ.ም በዘመነ ሉቃስ ከሌሊቱ በአምስት ሰአት ንጉስ ምኒሊክ ከእነሰራዊታቸው ሶስት ገደል ከሚባለው ቦታ ላይ ሰፍረው ሳለ፣ በአፄ ዮሐንስ ቤተመንግስት ላይ ብርሃን ሰፍሮበት ታዬ፡፡ ከዚያ በዚያው የነበሩ ሁለቱ ንጉሶች፣ ሶስት ጳጳሳትና እጨጌ ቴዎፎሎስ ቤተመንግስቱ የተቃጠለ መስሏቸው እየተሯሯጡ ሄደው ቢመለከቱ፣ እሳት የሌለው ብርሃን ብቻ እንደ ታላቅ ቃጠሎ ሲንቦገቦግ አዩና በምስጢሩ ተደነቁ፡፡
“በዚህም አፄ ዮሐንስ ከእንግዲህ በኋላ ይህ ቤት የእግዚአብሔር አንድነትና ስስትነት መንገሪያ፣ የመስዋዕት መሰዊያ እንጅ የእኔ ሊሆን አይገባም ብለው ወዲያውኑ ቡራኬ እንዲደረግበት አዝዘው፣ ቦታው በጳጳሳቱና በእጨጌው ተባረከ፤ ያ ብርሃንም ሌሊቱ ሲያልፍ ከቀኑ ብርሃን ጋር ተቀላቀለ እንጅ ሌሊት ታይቶ አልጠፋም፡፡ ከዚያም አፄ ዮሐንስ ግምጃ ድንኳን አስተክለው፣ የስላሴን ታቦት አስገቡና የደብሩን ስም አበራ ስላሴ አሉት፡፡ ለዚያ ቅዱስ ስፍራ አስተማረና አስተዳዳሪ ይሆኑ ዘንድም የወሎን ህዝብ በማስተማር ላይ የሚገኙት መምህር አካለ ወልድ በንጉሱ ትዕዛዝ ተሾሙ”
እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባ ቁምነገር፣ ሊቁ ፊት በአፄ ቴዎድሮስ በኋላም በንጉስ ምኒሊክና በአፄ ዮሐንስ የነበራቸው ተቀባይነት የቱን ያህል የጐላ እንደነበር ነው፡፡
አበራ ስላሴን በማስተዳደር ላይ ሳሉ፣ ቤተክርስቲያኑን ንጉስ ሚካኤል አሳምረው መስራታቸውንም የቤተ-ክርስቲያኑ ታሪክ ይመሰክራል፡፡
መምህር አካለወልድ አበራ ስላሴ ላይ በቆዩባቸው ጊዜያት ታላቁ ተግባራቸው ማስተማር ነበርና ከ500 በላይ ደቀመዛሙርት ለማፍራት ችለዋል፡፡ “የቦሩ ሜዳዎቹ ባይሆን ኖሮ ያን ሁሉ ተማሪ ምን ይችለው ነበር?” ሲሉ በወቅቱ አድናቆታቸውን የሰጡ ተመልካቾች የሰጡት ቃል ዛሬም በዕማኝነት ይገኛል፡፡
ያን ሁሉ ወፈ ሰማያት ተማሪ ሲያስተምሩ ቀለብና ልብስ የሚችሉት ራሳቸው መምህር አካለ ወልድ ነበሩ አሉ፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የመጀመሪያው የአዳሪ ት/ቤት በአገራችን የተመሰረተው በመምህር አካለ ወልድ ነው ማለት ነው፡፡ የሊቆች ሊቅ አካለ ወልድ ጉባዔ ዘርግተው ቦሩ ሜዳ በሚገኘው አበራ ስላሴ ደብር በርካታ ሊቃውንትን ለፍሬ ከማብቃታቸው በተጨማሪ ቁጥራቸው የት የለሌ የሆኑ የተለያዩ የግዕዝ መጻሕፍትን ብራና እየለመፁ፣ ብዕር እየቀረፁ ጽፈዋል አስጽፈዋል፡፡ የሰማንያ አሃዱ መፃሕፍት ትርጓሜ በአግባቡ እንዲጠና እንዲጠበቅና ይበልጥ እንዲራቀቅ የቅኔ ትምህርት እንዲመጥቅ ካደረጉት ከእነ ኤስድሮስ፣ ተዋነይ፣ ያሮድና አራት አይና ጐሹ ጋር የሚመደቡ የሊቆች ቀንድ መሆናቸውን የህይወት ታሪካቸውና የተለያዩ ሊቃውንት ስራዎች ይመሰክራሉ፡፡ ይህን ታላቅ አገልግሎታቸውን ለማዘከርም ደሴ ውስጥ አንድ የአንደኛና መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በስማቸው ተሰይሟል፡፡ በ1942 የተመሰረተው ይህ ት/ቤት፤ ታሪካቸውን በጽሑፍ ከመያዝ አልፎ ፎቶ ግራፋቸውን ከዘመድ አዝማድ አፈላልጐ በቅርስነት ማስቀመጡን ሳይ ለሊቁ የተሰጠውን ክብር እንድገነዘብ ረድቶኛል፡፡ “መልካም ስም ከማር ትጣፍጣለች” የሚባለው ለአካለ ወልድ ሰርፀ ወልድ አይነቱ የአገር ሃብት የተነገረ አይደል?! መልካም በዓል!

 

Read 10091 times