Saturday, 13 September 2014 13:15

ዕርቅና ፍቺ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

‘እውነት’ ይህን ያህል ‘አኩርፋናለች’ እንዴ! ልክ ነዋ… አይደለም ቤተኛችን ልትሆን አልፎ፣ አልፎ እኛ ዘንድ ‘ለቡና ብቅ ማለቱን’ ሁሉ ትታዋለች፡፡ እንደውም እውነት መናገር “ለክርና ማተቤ…” ምናምን ማለት የሀቀኝነት መለኪያ ሳይሆን ‘ከዘመኑ ጋር አብሮ መሄድ አለመቻል’ ነው፡፡

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንኳን ከዘመን ወደ ዘመን አሸጋገራችሁማ!
የማያልቅ የለም አይደል የሚባለው! 2006 እንደ ምንም ብሎ አለቀ፡፡ የተሳካለትም አጨብጨቦ ይዘፍናል፣ ያልተሳካለትም አጨብጭቦ ይቀራል! አጨብጭቦ የቀረው ህዝብ ብዛት በቁጥርና በመቶኛ ተሰልቶ ይነገረንማ!
በቀደም ዕለት በሸገር ኤፍኤም ላይ ‘የዓለም ቋንቋ’ ፕሮግራምን እየሰማሁ ሳለ የገረመኝን ነገር ስሙኝማ…አንዷ ከባለቤቷ ጋር ባለመግባባት የተለያየች አድማጭ ስለ 2007 ዕቅዷ ስትጠየቅ ምን አለች መሰላችሁ… “ከባሌ ጋር መታረቅ…” አይነት ነገር ነው ያለችው፡፡ አሪፍ አይደል!
“መቼ ምክንያት አግኝቼ በተለየኋት/በተለየሁት!” በሚባልበት ዘመን ከባሏ ጋር ለመታረቅ የምታቅድ ሴት ማግኘት የምር ደስ ይላል፡፡
አንድዬ ምኞቷን ያሳካላትማ!
እናማ… በርካታ ትተውን የሄዱ፣ ያባረርናቸው፣ ያባረሩን፣ ትተናቸው የሄድናቸው…ወዘተ ብዙ ልንታረቃቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፡፡
ከ‘ራሳችን’ ጋር መታረቅ አለብን፡፡
የምር እኮ…አለ አይደል… እንደው ነገሬ ብላችሁ ነገረ ሥራችንን ስታዩ…ከራሳችን ጋር ‘የቁርጥ ቀን ጠብ’ ላይ የገባን ነው የሚመስለው፡፡ ራሳችንን መሆን ትተን ሌሎችን ለመሆን የምንሞክረው ከራሳችን ጋር ፍቅር ስላለን ሳይሆን…አለ አይደል…ከራሳችን ስለተጣላን ነው፡፡ የራሳችንን ጓዳ ትተን የሌላውን ሰው ጓዳ የምንናፍቀው ከራሳችን ጋር ስለተጣላን ነው፡፡
2007 ከራሳችን ጋር የምንታረቅበት ዘመን ይሁንልንማ!
ከ‘እውነት’ ጋር መታረቅ አለብን፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…‘እውነት’ ይህን ያህል ‘አኩርፋናለች’ እንዴ! ልክ ነዋ… አይደለም ቤተኛችን ልትሆን አልፎ፣ አልፎ እኛ ዘንድ ‘ለቡና ብቅ ማለቱን’ ሁሉ ትታዋለች፡፡ እንደውም እውነት መናገር “ለክርና ማተቤ…” ምናምን ማለት የሀቀኝነት መለኪያ ሳይሆን ‘ከዘመኑ ጋር አብሮ መሄድ አለመቻል’ ነው፡፡ እናላችሁ…‘እውነት’ የምትለካው ጉዳዩ ለግለሰቡ ይጠቅማል አይጠቅምም በሚለው ነው፡፡ ‘የሚጠቅም’ ከሆኑ ሁለትና ሦስት ዘጠኝ የማይሆንበት ምክንያት የለም፡፡
2007 ከ‘እውነት’ ጋር የምንታረቅበት ዘመን ይሁንልንማ!
ከ‘ትህትና’ ጋር መታረቅ አለብን፡፡
የምር ‘ትህትና’ ምን አድርገናት እንደዘጋችን ይመርመርልንማ፡፡ ከትንሹ እስከ ትልቁ፡ እውቀት ካጠረው እውቀት እስከተረፈው፣ ከ‘ቺስታ’ እስከ ዲታ…ምን አለፋችሁ… ‘ትህትና’ ከሁሉም ጋር “መቃብሬ ላይ ብትቆም…” ምናምን የተባለች ይመስላል፡፡ እናላችሁ…ብዙ ቦታዎች ሰዎች የሚያናግሯችሁ በትህትና ሳይሆን “ጠብ ያለሽ በዳቦ…” አይነት ነው፡፡
የሆነ መሥሪያ ቤት ዘበኛ ልትገቡ ስትሉ “ወዴት ነው?” ሲላችሁ ዱላውን ጠበቅ አድርጎ ይዞና ዓይኖቹን የየተኮሰ የአሜሪካ ፓትሪዮት ሚሳይል አስመስሎ ነው፡፡
2007 ‘ትህትና’ን ይቅርታ ጠይቀናት ቢሆንም የምንታረቅበት ይሁንልንማ!
ከ‘አክብሮት’ ጋር መታረቅ አለብን፡፡
ስሙኝማ…ይቺ አገር እኮ ምን የመሰለ የመከባበር ባህል የነበረባት አገር ናት! በዕድሜ ትልልቅ የሆኑ ሰዎች ወደ ሆነ ክፍል ሲገቡ ከወንበር ብድግ ማለት፣ ታክሲ ወይ አውቶብስ ውስጥ ለአዛውንቶች ወይም ለነፍሰ ጡሮች ወንበር መልቀቅ፣ ለማንም ሰው በትህትና ሰላም ማለት…የመሳሰሉ አክብሮት የተሞላባቸው ባህሪያት ነበሩ፡፡
ዘንድሮ… አይደለም በዕድሜ የገፉ ሰዎች የሆነ ክፍል ውስጥ ሲገቡ ወንበር መልቀቅ፣ ቀድመው ወንበር የያዙ አዛውንቶችን “ተነስ!” ለማለት የሚቃጣን ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ አውቶብስና ታክሲ ላይ ወንበር የመልቀቅን ነገር ተዉት፡፡ አይታሰብም ማለት ይቻላል! “ለጤናሽ እንደምነሽ ከርመሻል?” “ሰላምና ጤና ለአንተ ይሁን…” ምናምን አይነት የመልካም ምኞት ሰላምታዎች ‘ከዕለታት አንድ ቀን…” የተለመዱ መሆናቸው ሁሉ ሊረሳ ምንም አልቀረውም፡፡
2007 ከ‘አክብሮት’ ጋር የምንታረቅበት ዘመን ይሁንልንማ!
ስሙኝማ…እግረ መንገዴን፣ እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ተከታዩዋን የምትመስል ቀልድ ሳትሰሙ አልቀራችሁም፡፡ ሰወዬው ማታ ሲጨልጥ ያድርና ቤቱ ገብቶ ለሽ ይላል፡፡ በማግስቱ ጠዋት ስላሳለፈው ምሽት ለማስታወስ ሲሞክር ሁሉም ነገር ይደባላለቅበታል፡፡ እናላችሁ…በበፊተኛው ምሽት ወዳመሸበት መጠጥ ቤት ተመልሶ ይሄዳል፡፡ ባሬስታውን “ጆን ማታ እዚህ መጥቶ ነበር እንዴ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ባሬስታውም “አዎ፣” ብሎ ይመልስለታል፡፡ ሰውየው ምን ቢል ጥሩ ነው…“እኔ አብሬው ነበርኩ?”
“እኔ አብሬው ነበርኩ?” እስኪመስልብን ድረስ ከመጠጣት ይጠብቀንማ!
እናላችሁ…ከ‘ተፈጥሮ’ ጋር መታረቅ አለብን፡፡
‘ከዕለታት አንድ ቀን…’ በሚባል ጊዜ ይቺ አገር ጥቅጥቅ ባሉ ደኖች፣ በአረንጓዴ መስኮችና ተራራዎች የተሞላች ነበረች፡፡ (ደግ፣ ደግ ለሆኑ ነገሮች “ነበር…” “ነበረች…”፣ ምናምን አይነት የኃላፊ ጊዜ ቃላት ከመጠቀም አላቆ “ነው…” “ነች…” ለማለት ያብቃንማ!”)
እናላችሁ… ድፍን አገር መጥረቢያ ይዞ ይዞር ይመስል መለ መላችንን እየቀረን ነው፡፡
2007 ከተፈጥሮ ጋር የምንታረቅበት ዘመን ይሁንልንማ!
ደግሞላችሁ…ከ‘ምቀኝነት’ ጋር መለያየት አለብን፡፡ስሙኝማ…ከበፊት ጀምሮ የምንሰማት “ሀበሻ ምቀኛ ነው…”፣ የሚሏት ነገር አለች፡፡ እንግዲህ…እንደ ብዙ ነገሮች ይህንንም ጥናት አድርጎ በመቶኛ በምናምን የነገረን ስለሌለ (ምናልባት የሚነግረንም ስለማይኖር!) በአጠቃላይ ማውራቱ አሪፍ ላይሆን ይችላል፡፡ ግን…አለ አይደል…የማይካደው ነገር ምቀኝነት በዝቷል፡፡ የሆነ ጎረቤታችን ፈረንካ ስላገኘ እንመቀኛለን፣ የሆነ ጓደኛችን ሸሚዝ ስለገዛ እንመቀኛለን፣ የሆነች ወዳጃችን ‘አማሪካን ልትሄድ’ ስለሆነ እንመቀኛለን፡፡2007 ከ‘ምቀኝነት’ ጋር ‘የምንፋታበት’ ዘመን ይሁንልንማ! ከ‘እብሪት’ ጋር መለያየት አለብን፡፡ደጋግመን እንደምንለው እብሪት በዝቷል፡፡ ስልጣን ያለውም ስልጣን የሌለውም፤ ገንዘቡ ባንኮችን ያጨናነቀውም ባንክ ምን እንደሆነ የማያውቀውም፤ መአት ኮሌጆች የበጠሰውም፣ በኮሌጅ አጥር ጎን አልፎ የማያውቀውም…እብሪት በሽ፣ በሽ ነው፡፡ በምንም መለኪያ እብሪት ትክክል ሊሆን አይችልም (ይቅርታ፣ ላስተካክልና…“…ትክክል ሊሆን የማይችልበት ሁኔታ ነው ያለው…”) 2007 ከ‘እብሪት’ ጋር ‘የምንፋታበት’ ዘመን ይሁንልንማ!ከ‘ሸር’ ጋር መለያየት አለብን፡፡
ሸር በዝቷል፡፡ የሚገርማችሁ ነገር…አለ አይደል… ዘንድሮ የሆነ ሰው ላይ ሸር ለመፈጸም ምክንያት እንኳን የማያስፈልግበት ዘመን የደረስን ይመስላል፡፡ በአንድ ወቅት እንደተባለው “የዓይናቸው ቀለም ስላላማረን…” ብቻ ክፉ የምናስብባቸው ሰዎች ሞልተዋል፡፡
2007 ከ‘ሸር’ ጋር ‘የምንፋታበት’ ዘመን ይሁንልንማ! ብቻ ምን አለፋችሁ…በርካታ እርቅ ልንፈጽምባቸው የሚገቡ፣ በርካታ ፍቺ ልንፈጽምባቸው የሚገባቸው ነገሮች አሉ፡፡ አንድዬ ሁሉንም ያሳክልንማ!
መልካም አዲስ ዓመት!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

Read 3797 times