Saturday, 13 September 2014 13:11

አገሪቱን ወደኋላ ሲጎትቱ የኖሩት ወገኛ ሃሳቦች

Written by  ዮሐንስ ሰ.
Rate this item
(16 votes)

           ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ሌሎችን ለመርዳት የሚችሉ ስኬታማ ሃብት ፈጣሪዎችን በማፈላለግ ልምድ ከማቃመስና በአርአያነታቸው ከማነቃቃት ይልቅ፤ የሚስኪኖችን ጓዳ ጎድጓዳ እያነፈነፈና እንባ እያራጨ በሬዲዮ ወይም በቲቪ ለአደባባይ የሚያቀርብ የ“ልመና ሾው”፣ እንደ ትልቅ ስራ መታየት አለበት? የሰው ልጅ ትልቅነትን በማንኳሰስ፣ ሚስኪንነትን ማምለክ ይመስለኛል። የመርካቶ ጉሊቶች (“ባህላዊ ገበያ”) በአዳዲስ ሕንፃዎች እንዳይጠፋ በመጠበቅ ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚመኝ ወይም፣ ኮንዶምኒየም ቤት ለማግኘት እየናፈቀ የአራት ኪሎ ጭርንቁስ ሰፈር በኮንዶምኒዬም ይጥለቀለቃል ብሎ የሚሰጋ የ“ድህነት ጠበቃ” ሲናገርስ፣ እንዴት ከቁም ነገር ይቆጠራል? ወይስ “ወገኛ” እንበለው?
አዳሜ ልጆቹን በግል ትምህርት ቤት ለማስመዝገብ ሲሟሟት፣ “የግል ትምህርት ቤቶች የሬዲዮ ትምህርትን ስለማይጠቀሙ መዘጋት አለባቸው” ብሎ ባለስልጣናትን የሚያፋጥጥ የመንግስት ጋዜጠኛንም ተመልከቱ። “ጀግናው ተቆርቋሪ ጋዜጠኛ” ልንለው ነው? ይሄም “ወገኛ” ቢባል ሳይሻል አይቀርም። ይህም ብቻ አይደለም። መንግስት፣ በርካታ ፕሮጀክቶቹ መጓተታቸውን ሙሉ ለሙሉ ሳይሆን በከፊል በማመን “ፕሮጀክቶቹ በታቀደላቸው አቅጣጫ እየተከናወኑ ነው” የሚል አባባል ሲፈጥር፣ በሌላ በኩል ግን በድርቅናም ይሁን በሌላ ምክንያት “ፕሮጀክቶቹ በታቀደላቸው ጊዜ እየተገነቡ ነው” የሚለውን አባባል የሙጢኝ የያዘ የመንግስት ሚዲያ ታገኛላችሁ። “ፕሮጀክቶች ተጓተቱ” ብሎ የሚዘግብ የግል ጋዜጣ ካጋጠማቸው፣ “ጨለምተኛ” ብለው ሲያዋክቡትስ? ይሄ “ወገኛነት”ም የባሰ ሳይሆን አይቀርም። እውነትንና አእምሮን ካለማክበር ጋር አብሮ የሚመጣ ፕሮፓጋንዳን የማራገብ አመልና ነፃነትን የማፈን ዝንባሌ ይመስላል።
ምን ይሄ ብቻ! የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከመንግስት ስራ ሳይጠብቁ የራሳቸውን ህይወት ለማሻሻል የቢዝነስ ፈጣሪ (አንተርፕረነር) እንዲሆኑ እየተመኘ፣ በሌላ በኩል 150ሺ ተማሪዎችን ሰብስቦ ከራሳቸው ሕይወት በፊት ለአገር ልማት የ“ሚጠበቅባቸውን” እንዲሰሩ የሚሰብክ፣ ... የቢዝነስ ሰዎችንም “ስግብግብ” እያለ የሚያሳድድ ፓርቲና መንግስት ምን ይባላል? በራስ ጥረት የራስን ሕይወት ማሻሻልና ሃብት ማፍራት...፣ ትክክለኛና ጠቃሚ፣ ተገቢና ቅዱስ ተግባር አይደለም እንዴ?...
አገራችን እነዚህን በመሳሰሉ የተምታቱና የተጣመሙ፣ ወገኛና ጭፍን ሃሳቦች የተሞላች ናት። ከሃሳብነት አልፈው የማይሻገሩና ኑሯችንን የማይነኩ ብናኞች ሊመስሉን ይችላሉ። በእርግጥም፣ የተምታቱና ወገኛ ሃሳቦች በዙሪያችን ቢንሰራፉም፣ ዞር ዞር ብለን በአይን የሚታዩና የሚዳሰሱ ተግባራትን ስንቃኝ፣ ተስፋ የሚሰጡ የሥራ ጥረቶችንና የእድገት ጅምሮችን እንመለከታለን። ስለዚህ፣ የተምታቱ ወገኛ ሃሳቦች ችግር አይፈጥሩም ማለት ነው? “አዎ ችግር አይፈጥሩም” የምንል ከሆነ፣ ከአገሪቱ የቅርብ ጊዜ ታሪኮች ላይ ዋናውንና ትልቁን ትምህርት ስተነዋል ማለት ይቻላል። እንዴት?
እስቲ በቅድሚያ፣ አንዳንዶቹን ቀረብ ብለን እንመልከታቸው። በአዲስ አበባ የሬዲዮ ትምህርት የማይሰጡ የግል ትምህርት ቤቶች ለምን አልተዘጉም ብሎ ባለስልጣናትን የሚያፋጥጥ “ጀግና” ጋዜጠኛ ማን ነው? የኢቲቪ ጋዜጠኛ ነዋ! እና ደግሞ “ብዙዎቹ የግል ትምህርት ቤቶች፣ ለማስተማሪያነት ታስቦ የተገነባ ህንፃ እንደሌላቸው መረጃዎች ያመለክታሉ። እነዚህን ለመዝጋት እርምጃ መውሰድ ነበረባችሁ፤ እናንተ ግን ማስታመም ታበዛላችሁ፤ ይሄ ሃላፊነትን አለመወጣት ነው” ... በማለት ባለስልጣናቱን ወጥሮ ይዟቸዋል - “መረጃዎችን” እየጠቀሰ። በእርግጥም፣ ስልጣኔን የምንፈልግ ከሆነ የመጀመሪያው ቁምነገር፣ አእምሮን መጠቀም፣ ለእውነት ክብር መስጠትና የማሰብ ነፃነትን ማስፋፋት ነው። እናም፣ ሃሳቦቻችንን በሙሉ በመረጃ ወይም በእውነታ ላይ የተመሰረቱ መሆን ስላለባቸው፤ ጋዜጠኛው መረጃዎችን መጥቀሱ ያስመሰግናል።
አዎ፤ ብዙ የግል ትምህርት ቤቶች፣ በሬዲዮ የሚሰራጨውን ትምህርት አይጠቀሙበትም። ለትምህርት ታስቦ የተሰራ ህንፃም የላቸውም። ነገር ግን ሌሎች መረጃዎችም አሉ። አንደኛ በቅርቡ በሰቆጣ የሻዳይ በዓል ሲከበር እንደተጠቀሰው፣ በአንድ ዞን ውስጥ ከሚገኙ የመንግስት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል በርካታዎቹ፣ የዛፍ ጥላን እንደመማሪያ ክፍል ይጠቀማሉ። ከ500 በላይ የዛፍ ጥላ ክፍሎች! ከ10ሺ ተማሪዎች በላይ መሆኑ ነው። ይህም ብቻ አይደለም። በአዲስ አበባና በየክልሉ፣ የመማሪያ መጽሐፍ ሳያገኙ አመቱ የሚጋመስባቸው የመንግስት ትምህርት ቤቶችን ስናይ አልነበረም እንዴ? ሌሎች መረጃዎችም አሉ። ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሬድዮ፣ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በፕላዝማ ቲቪ የሚቀርቡት ትምህርቶች፣ ይህ ነው የሚባል ጥቅም እንዳላስገኙ በርካታ ጥናቶች አረጋግጠዋል - የትምህርት ሚኒስቴር ጥናት ጭምር።
በዚያ ላይ ለመንግስት ትምህርት ቤቶች የተሰራጩት ሬዲዮኖችና የፕላዝማ ቴሌቪዢኖች በአብዛኛው አገልግሎት አይሰጡም። ይህም መረጃ ነው። በአዲስ አበባ የመንግስት ትምህርት ቤቶች፣ ግማሾቹ የፕላዝማ ቲቪዎች በብልሽት ወይም በአጠቃቀም ችግር አገልግሎት አለመስጠታቸውስ መረጃ አይደለም? አንዳንዶቹን የአጠቃቀም ችግሮች ማስተካከል ይቻል ይሆናል። አብዛኞቹን ብልሽቶች መጠገን ግን አይቻልም። የመለዋወጫ እቃዎች ዋጋ በጣም ውድ ስለሆነ፣ ከምርት አለም የወጡና ጊዜ ያለፈባቸው ስለሆኑ መለዋወጫ እቃ አይገኝላቸውም፤ ከተገኘም የጥገና ወጪው ከቴሌቪዢኑ ዋጋ የሚበልጥ ይሆናል።
ኧረ ለመሆኑ፣ የተሻለ የትምህርት ውጤት የሚመዘገበው የት ነው? በግል ትምህርት ቤቶች! ወላጆች ልጆቻቸውን የት ለማስተማር ይሟሟታሉ - በግል ትምህርት ቤት - ለዚያውም በሺ ብር የሚቆጠር ገንዘብ በየሴሚስተሩ እየከፈሉ። ታዲያ ይሄ ሁሉ መረጃ በግላጭ እየታወቀ፣ “የግል ትምህርት ቤቶች የሬዲዮ ትምህርት አይጠቀሙም” በሚል እንዲከረቸሙ ባለስልጣናትን ማፋጠጥ ምን ይባላል? “ጋዜጠኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ሊያፋጥጥ ይችላል” ሲባል የሰማ ሰው፤ “እኔም ወግ ይድረሰኝ” ሊል ይችላል። ነገርዬው፣ “ወገኛነት” አይደለም የምንል ከሆነ ግን፣ ከወገኛነት የባሰ “ክፋት” ይሆናል።
“የመርካቶ ጉሊቶችና የቆርቆሮ ሱቆች እየፈረሱ ህንፃዎች እየተገነቡ ነው” ብሎ የሚደሰት ሳይሆን “ባህል ጠፋ” እያለ የሚጨነቅ ሰውስ ምንድነው ችግሩ? “ሲሉ ሰምታ...” እንደሚባለው ይመስለኛል። “አካባቢ ጥበቃ”፣ “ባህል ጥበቃ” ሲባል የሰማ ሰው፣ “የጉሊቶች ጥበቃ” ብሎ ሊናገር ይችላል። ከወገኛነት አልፎ፤ የምር ከሕንፃዎች ይልቅ አቧራና ጭቃ የሚፈራረቁበት የጉልት ተራ የሚመርጥ ከሆነ ግን፣ ነገርዬው ከወገኛነትም የባሰ ነው። “የድህነት ጠበቃ” ቢባል ይሻላል - የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖችን ለመተቸት የተጠቀሙበት አባባል ነው።
በአዲስ አበባ እየተዘረጋ ስላለው የኤሌክትሪክ ባቡር መስመር፣ በከተማዋ መስተዳድር የቲቪ ፕሮግራም የተላለፈ ሌላ “ወገኛ ዜና” ልጨምርላችሁ። እንደምታውቁት፣ የታክሲ ስምሪት ቁጥጥር የተጀመረ ሰሞን፣ “ይሄ ነገር የትራንስፖርት እጥረትን ያባብሳል” ብለው ምክር የለገሱ ሰዎች ሰሚ አላገኙም። እንዲያውም፣ “የታክሲ ስምሪት ቁጥጥሩ የትራንስፖርት እጥረትን ያቃልላል” በማለት እልፍ ጊዜ “ዜና” ሰርተዋል - የመንግስት ሚዲያ ተቋማት። ዛሬ ግን ቅኝቱ ተቀይሯል። የአዲስ አበባ ቲቪ ሰሞኑን እንደዘገበው፣ የትራንስፖርት እጥረቱ ተባብሷል - 11 ሰዓት ላይ ከስራ የወጡ ሰዎች፣ ታክሲ የሚያገኙት ማታ 1 ሰዓት እየሆነ ብዙ ሰው መቸገሩን ዘገባው ይገልፃል። የዚህ ሁሉ መጨረሻ ምን መሰላችሁ? “አይዟችሁ - የባቡር መስመሩ እየደረሰላችሁ ነው” የሚል መልእክት ለማስተላለፍ ነው። ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ የባቡር መስመር ከተገነባ ማን ይጠላል? ባቡሮቹ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መሆናቸው ትልቅ ጥቅም እንዳለው አዲስ ቲቪ ሲያስረዳ፣ “የአካባቢ ብክለትን ይከላከላል” በማለት አብስሯል። ወገኛ ይሉሃል ይሄ ነው። ምናለ፣ “የነዳጅ ወጪን ያስቀራል” ብሎ ቢናገር?
እንዲሁ ስታስቡት፣ እዚህ አገር መኪና በዝቶ ነው፣ በመኪና ጭስ አየር እየተበከለ የተቸገርነው? አንድ ቢሊዮን መኪኖች ባሉበት አለም፣ የኢትዮጵያ ድርሻ፣ “አንድ በመቶ” እንኳ አይሆንም። ኧረ “ከሺ መኪና አንድ” ለመድረስ አልቻለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ሁሉም የመኪና አይነቶች 350ሺ ገደማ ናቸው። እንዲያው፣ ብንጨነቅ ብንጨነቅ፣ በመኪና ጭስ እንጨነቃለን? መኪና በበዛና፣ አዲስ አበባ እንደ ኒውዮርክና ለንደን፣ እንደ ቤጂንግና ቶኪዮ በሆነች። ይልቅ ሊያስጨንቀን የሚገባው ብክለት፣ በየደጃፋችን ያለው የቆሻሻ ቱቦ ወይም በየከተማው እንደጥላሸት የሚጠቁረው ወንዝ ነው። ለነገሩ ከዚያ በፊት የምንጠጣው ውሃ ንፁህ እንዲሆንና ተቋርጦ እንዳይሰነብት ማድረግ ይቀድማል። በገጠር ደግሞ፣ በእንጨትና በኩበት ጭስ መታፈንን፣ የደፈረሰ የመጠጥ ውሃና ከከብት ጋር ተዳብሎ ማደርን ለማሻሻል ብንመኝ አይሻልም? ወይስ ባህል ስለሆነ፣ ጠብቀን ልናቆየው ይገባል?
የአረንጓዴ ልማት በተሰኘው ሰነድ ደግሞ ምን አየሁ መሰላችሁ? የነዳጅ መኪኖችን በኤሌክትሪክ መኪኖች የመተካት እቅድ! አውሮፓ ውስጥ ሲነገር የሰሙት መሆን አለበት። የወገኛ ነገር! አሊያማ፣ በተራሮች የምትታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ፣ በየዳገቱ አቅም አንሷቸው የሚቆሙ የኤሌክትሪክ መኪኖች ምን ይሰራሉ? ለዚያውም ከሌላው መኪና በሶስትና በአራት እጥፍ ዋጋ ነው ተገዝተው የሚመጡት። የኤሌክትሪክ መኪኖች ነዳጅ ስለማይጠቀሙ ወጪ የሚቆጥቡ እንዳይመስላችሁ። የባትሪያቸው ወጪ ከፍተኛ ነው። የሞባይል ባትሪ መቀየር እንኳ፣ ቀላል አይደለም።
ወገኛ ሃሳቦች፣ እንዲሁ ለወሬ ያህል የሚነገሩ ቢሆኑ እንኳ ጥሩ አይደለም። ከእውነታ ጋር ያጣሉናል። ግን፣ የወገኛ ሃሳቦች ጉዳት ይህ ብቻ አይደለም። በወሬ ብቻ አይቀሩም። ግልገል ጊቤ 3 የተሰኘው ግዙፍ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ ግንባታ የተጓተተው ለምን እንደሆነ አታውቁም? “ሁሉንም አካባቢ፣ ተራሮችንና ወንዞችንም ጭምር እንደድሮአቸው ሳንነካቸው ልንጠብቃቸው ይገባል። በጠረፎች አካባቢ በጥንታዊ አኗኗር ውስጥ የሚገኙ ጎሳዎችም አኗኗራቸው ሳይቀየር መቀጠል አለበት” የሚሉ የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች፣ ግድቡን ስለተቃወሙ ነው። ቢቃወሙ የት ይደርሳሉ? በአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች ዘመቻ ምክንያት፣ የአውሮፓ ህብረት ለግድቡ ግንባታ ሊሰጠው የነበረውን ብድር ሰርዟል። ከዚያ በኋላ ደግሞ፣ ብድር ለመስጠት ተቃርቦ የነበረው የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ጫፍ ከደረሰ በኋላ ብድር ሳይሰጥ ቀርቷል። ይሄውና የግድቡ ግንባታ ለአመታት ይንፏቀቃል - እስካሁን 3 ዓመት ገደማ የተጓተተው ግንባታ፣ ቢያንስ ተጨማሪ ሁለት አመታት ያስፈልጉታል።
በአዳማ ናዝሬትና መቀሌ፣ በነፋስ የሚሰሩ የሃይል ማመንጫ ተርባይኖችን ለመትከል ስንት ወጪ እንደወጣበት ታውቃላችሁ? ሁለት መቶ ሜጋ ዋት ገደማ ለማመንጨት ከ550 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገደማ። ወንዝን በመገደብ ተመሳሳይ አቅም ያለው የኤሌክትሪክ ማመንጫ ለመገንባት በአማካይ 200 ሚሊዮን ዶላር፣ በዛ ቢባል ደግሞ 250 ሚሊዮን ዶላር ነው። በሌላ አነጋገር፣ 300 ሚሊዮን ዶላር በከንቱ ባክኗል (6 ቢሊዮን ብር መሆኑ ነው)። ለምን? የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች የግድብ ግንባታ ስለሚቃወሙ፣ እነሱን ለማባበል የነፋስ ተርባይኖችን መጠቀም ግዴታ እየሆነ መጥቷላ። 6 ቢሊዮን ብር ቀልጦ ሲቀር ግን በኢትዮጵያ አቅም ቀላል አይደለም። እስካሁን በአመት ለነዋሪዎች የሚተላለፉ የኮንዶምኒየም ቤቶች ወደ 15ሺ ገደማ አይደሉ? የእነዚህን እጥፍ ለመገንባት የሚያስችል ገንዘብ ነው፣ በነፋስ ተርባይኖች ሳቢያ ነፋስ የበላው።
በአጠቃላይ፣ ወገኛ ሃሳቦች ከእውነት ጋር በማጣላት በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ፣ ኑሮና ሕይወትን ሊያበላሹ ስለሚችሉ፣ እውነታ ላይ በተመሰረተ ትክክለኛና ቀና ሃሳብ ልናስተካክላቸው ይገባል - ብቅ ብቅ የሚሉ የስልጣኔና የብልፅግና ፍንጮች ተመልሰው እንዳይጠፉና እንዲያድጉ የምንፈልግ ከሆነ ማለቴ ነው።
አዎ፤ በየቦታው የግንባታ ሩጫና የቢዝነስ ሙከራዎች፣ በየአካባቢያችን የብልፅግና ጥረቶችና ጅምሮች፣ ከታች እስከ ዩኒቨርስቲ የትምህርት ተቋማትና የተማሪዎች ብዛት፣ ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀምና መረጃ የመለዋወጥ ጉጉት... እንዲሁም ተመሳሳይ የስልጣኔ ፍንጮችንና የብልፅግና ጭላንጭሎችን ማየት ራሱ መልካም ነው። ነገር ግን፣ እነዚህ ፍንጮች በታሪክ ታይተው የማይታወቁ አዲስ አጋጣሚዎች እንዳልሆኑና ሊጠፉ እንደሚችሉ ከታሪክ መማር ይኖርብናል።
በየጊዜውና በየዘመኑ፣ የስልጣኔ ጭላንጭሎች ታይተዋል። ከሚኒልክ ዘመን አንስቶ ተፈሪ መኮንን ስልጣን ይዘው የጣሊያንን ወረራ እስከተፈፀመበት ድረስ ያለውን ጊዜ በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። የሳይንስና የነፃነት፣ የብልፅግናና የነፃ ገበያ፣ የሰብዕና ክብርና የህግ የበላይነት ሃሳቦችን ያነገቡ እንደ ገብረሕይወት ባይከዳኝ በመሳሰሉ የስልጣኔ ምሁራን የተለኮሰ የብርሃን ችቦ በድምቀት የፈነጠቀበት ዘመን ነው፤ በጣሊያን ወረራ ተስተጓጎለ እንጂ። በ1950ዎቹ ላይ ደግሞ፣ ዘመናዊ ትምህርት ለሴቶችም ጭምር በፍጥነት መስፋፋት የጀመረበት፣ የቢዝነስ ግንባታዎችና የኢኮኖሚ እድገት ቡቃያዎች የተፈጠሩበት፣ ሕገመንግስት ተሻሽሎ የምርጫ ስርዓትን ለመቀማመስ የተሞከረበት፣ በሁሉም የኪነጥበብ መስኮች ድንቅ ስራዎች ብቅ ብቅ ለማለት የበቁበት የስልጣኔ ፍንጭ ታይቷል። ነገር ግን፣ አልዘለቀም። እነ ገብረሕይወት በትክክለኛ አስተሳሰብ የለኮሱት የስልጣኔ ችቦ እየከሰመ ስለነበረ፣ በትምህርት፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በኪነጥበብ የታየው የስልጣኔ ጅምርና ፍንጭም፣ ቀስ በቀስ እየደከመ የዛሬ አርባ አመት ከሰመ። እንዴት?
በወረራ ሳይሆን፣ በተሳሳተና በተምታታ አስተሳሰብ ሳቢያ ነው፣ የ1950ዎቹ የስልጣኔ ጅምር የከሰመው። በእነማን አማካኝነት? ስለ ሳይንስ እያወሩ፣ የግለሰብ አእምሮንና ነፃነትን የሚያንቋሽሹ፣ ስለ ብልፅግና እያወሩ ሃብት ማፍራትን እንደ ትልቅ ወንጀል የሚቆጥሩና ንብረት ለመውረስ የሚቋምጡ፣ ራስን በማሳነስና በማዋረድ ለአንድ ሶሻሊስት ፓርቲ ሙሉ ለሙሉ ተገዢ መሆንን የሚያወድሱ ኮሙኒስት ምሁራን የተበራከቱበት ዘመን ነዋ። ምን ያህል እንደተበራከቱ ለመገመት ከፈለጋችሁ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ዝነኛ ኮሙኒስት የነበረው ዋለልኝ መኮንን፤ በ1962 ዓ.ም ባሰራጨው ፅሁፍ ውስጥ፣ የኮሙኒዝም አስተሳሰብ በዩኒቨርስቲ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ እንደሰፈነ መግለፁን መጥቀስ ይቻላል። በዘመናችን አነጋገር አብዛኛው ምሁር በመሰረታዊ የፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ ተመሳሳይ አስተሳሰብ በመያዝ፣ “አገራዊ መግባባት” ወይም “ብሔራዊ እርቅ” የተፈጠረበት ዘመን ነው ማለት ይቻላል። ምሁራኑ “የተግባቡት”፣ የተሳሳተና አጥፊ የኮሙኒዝም አስተሳሰብን በጋራ በመያዝ መሆኑ ነው መጥፎነቱ።በዚያን ዘመን የነበረው የሃሳብ ልዩነት፣ በካፒታሊዝም ደጋፊዎችንና በኮሙኒዝም ደጋፊዎች መካከል ሳይሆን፣ በኮሙኒስቶች መካከል እንደሆነ ዋለልኝ በኩራት ይገልፃል። “እኛ ሃቀኛ ኮሙኒስት፤ እናንተ አስመሳይ ኮሙኒስት” እያሉ እርስ በርስ በሚናቆሩ ቡድኖች መካከል ካልሆነ በቀር ሌላ የሃሳብ ልዩነት እምብዛም አልነበረም። ታዲያ፣ በዩኒቨርስቲ የሰፈነው የጥፋት አስተሳሰብ፣ አገሪቱን ለማዳረስና የመንግስት ስልጣን ላይ ለመውጣት ጊዜ አልፈጀበትም። ልክ የዛሬ አርባ አመት፣ መስከረም 1967 ዓ.ም መሆኑ ነው። ከዚያ በኋላ ያለው ታሪክ በስፋት ይታወቃል። ለማሽቃበጥና ለማጨብጨብ ካልሆነ በቀር፣ ሃሳብን ለመግለፅ መተንፈስ የማይሞከርበት ዘመን! “ያሰበ፣ ያሳሰበ...” ሁሉ፣ በገፍ ለእስር፣ ለስቃይና ለግድያ የሚዳርግ አስተሳሰብ! ሃብት ማፍራት እንደወንጀል ተቆጥሮ፣ ንብረት መውረስና መዝረፍ የአገር መተዳደሪያ ህግ ሆኖ አረፈው። በዚህም ሰበብ፣ ድህነት ተባብሶ፣ ረሃብና እልቂት የአገር መለያ ለመሆን ደረሱ። አንዱ ባለስልጣን ወይም ኮሎኔል፣ አንዱ የቀበሌ ሊቀመንበር ወይም ታጣቂ በማንኛውም ሰዓት መጥቶ ሊያስረው፣ ሊገርፈው፣ ሊገድለው፣ ቤቱን ነጥቆ ቤተሰቡን ሊደፍራቸው እንደሚችል የሚያውቅ ሰው፣ በአቅመ ቢስነት አንገቱን ደፍቶ የሚገፋው ደንባራ ኑሮ ምኑ ሕይወት ይባላል? የሰው ክብር ከእንሰሳ በታች የተዋረደበት ዘመን! ምን ለማለት ፈልጌ ነው? ሃሳቦቻችንን በስልጣኔ አቅጣጫ ካላስተካከልን በቀር፤ በአይን የሚታዩና የሚዳሰሱ የስልጣኔ ጭላንጭሎች ይበልጥ እየፈኩና እየበዙ ከመሄድ ይልቅ፣ ለመዳፋን አፈትልከው ወይም ብን ብለው ሊጠፉ ስለሚችሉ፣ ከተምታቱና ከተጣመሙ ወገኛ ሃሳቦች እንራቅ ለማለት ፈልጌ ነው።

 

Read 3548 times