Saturday, 31 December 2011 11:05

ዓለምን የለወጡ ድንቅ ፈጠራዎች

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(11 votes)

የሰዓት ፈጠራ ለሳይንስ ማበብ ምክንያት ሆኗል

የዓይን መነፅር የተፈለሰፈው በኢጣሊያ ነው

ያለፈው ሚሌኒየም ሊታመኑ በማይችሉ እጅግ በርካታና በጣም ጠቃሚ አዳዲስ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ውጤቶች የተንበሸበሸ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከእነዚህ የፈጠራ ውጤቶች የትኞቹ ናቸው ለሰው ልጅ በጣም ጠቃሚ አገልግሎት ሰጥተው ዓለምን የለወጡት? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ በሚሌኒየሙ ከተፈጠሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የፈጠራ ውጤቶች በጣም ጠቃሚ የሆኑትን 10 ፈጠራዎች ለመለየት፣ ሁነኛ መመዘኛ ሊኖረን ይገባል፡፡

ፈጠራዎቹ ጠቃሚ ነገር ለመሥራት ፍፁም የተለየ የአሠራር ዘዴ፤ ወይም ቀደም ሲል በፍፁም በማይታሰብ መንገድ የተፈጠሩ መሆን አለባቸው፡፡ ፈጠራዎቹ ወዲያውም ባይሆን እየቆየ በርካታ ሰዎች የሚጠቀሙበት ወይም የሚታዩ መሆን አለባቸው፡፡ የእነዚህ ዋነኛና አዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችና ሳይንሳዊ ግኝቶች ተፅዕኖ ወይም ውጤት ወዲያው ታይቶ የሚጠፋ ሳይሆን በሙያው ዓለም ለረጅም ጊዜ ዘልቆ የሚቆይ መሆን አለበት የሚሉትን ነጥቦች መመዘኛ እናድርግ፡፡ በእነዚህ መመዘኛዎች መሠረት አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶች በተፈጠሩበት የጊዜ ቅደም ተከተል ብናስቀምጣቸው፣ ሜካኒካል ሰዓት፣ የመስታዋት ሌንስ፣ የማተሚያ መሳሪያ፣ የእንፋሎት ሞተር፣ ቴሌግራፍ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ መስመር አልባ መገናኛ አንቲባዮቲክና (ፀረ-ባክቴሪያ መድኃኒት) ትራንዚስተር ይሆናሉ፡፡ አውሮፕላን፣ ቴሌፎን፣ አውቶሞቢል፣ ኮምፒዩተር፣ … የመሳሰሉ እጅግ የላቀ ጠቀሜታ ያላቸው በርካታ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በዝርዝሩ ውስጥ አልተካተቱም፡፡ ያለ ምክንያት አይደለም የተዘለሉት፡፡ ቀደም ሲል በተፈጠረ ግኝት ላይ ተመስርተው ስለተሠሩ እንዲሁም በአንድ ወይም በሌላ መልኩ በዝርዝሩ ስለተካተቱ ነው፡፡ ለምሳሌ ቴሌፎን ከመፈጠሩ ከ10 ዓመት በፊት አንስቶ ድምፅ ሲያስተላልፍ የቆየ በጣም ጠቃሚ ሰው ሠራሽ መሳሪያ እያለ፣ በ1870 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) የተሠራው ቴሌፎን አዲስ የፈጠራ ውጤት ሊሆን አይችልም፡፡ አሜሪካዊው አሌክሳንደር ግርሃምቤል ቴሌፎንን የሠራው ቴሌግራፍን ለማሻሻል ሲጥር ነው፡፡ ስለዚህ ስልክ ቀደም ሲል በነበረ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ላይ ተመስርቶ የተገኘ ውጤት ነው እንጂ፣ ቀደም ሲል በፍፁም ያልነበረና ያልተሞከረ አዲስ ጥበብ አይደለም፡፡ እዚህ ያልተጠቀሱና የሰውን ልጅ ሕይወት የበለጠ ምቹ ያደረጉ ሌሎች በርካታ ግኝቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በተመሳሳይ ምክንያት ነው በዝርዝሩ ውስጥ ያልተካተቱት፡፡የፈጠራና (invention) የግኝት (discovery) ልዩነት እንደሚታሰበው ቀላልና ግልጽ አይደለም፡፡ “ግኝት” ቀደም ሲል የነበረ፣ ነገር ግን በትኩረት ያልታየ፣ “እንዲህ ባደርገው እንዲህ ሊሆን ይችላል” በሚል ሙከራ የሚገኝ ነገር ነው፡፡ “ፈጠራ” ግን፣ ቀደም ሲል በፍፁም ያልነበረና የማይታወቅ፣ በሰው ልጅ ጥበባዊ አዕምሮ የተፈጠረ አዲስ መሳሪያ ወይም መገልገያ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ የጥንት ሰዎች የውሃ ጠብታና የተወሰኑ የከበሩ ድንጋዮች የብርሃንን አቅጣጫ በሚገምቱት መንገድ እንደሚቀይሩ ያውቁ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የመስተዋት ቅርፅ በሚያወጣ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው የመነፅር፣ የማይክሮስክፕ፣ የቴሌስኮፕና የካሜራ ዋነኛ አካል የሆነውን ሌንስ ፈጥረው ብርሃንን መቀያየር የቻሉት የመካከለኛው ዘመን ሰዎች ናቸው፡፡ በተመሳሳይ ሰዎች ለሺህ ዓመታት በኤሌክትሪክሲቲ ላይ ባደረጉት ጥናት የተፈጥሮ ኃይል መሆኑን ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን፣ ኤሌክትሪሲቲን በብዛት በማምረት በየቤቱና በየፋብሪካው በማድረስ ዓለምን መለወጥ የቻለው የ20ኛው ክፍለ ዘመን የቴክኖሎጂ እመርታ ነው፡፡ ኮምፓስ፡- የአውሮፓ አሳሾች አሜሪካ መድረስ የቻሉት በየት በኩል መሄድ እንዳለባቸው ስላወቁ ነው፡፡ ደመና በሌለበት ግልፅ ቀንና ሌሊት በፀሐይና በኮከቦች (በተለይም የሰሜን ኮከብ) አቅጣጫ እየተመሩ ነበር የሚጓዙት፡፡ ነገር ግን ረዥም ጉዞ ሲያደርጉ ሰማዩ ለወራት በደመና ይሸፈናል፡፡ በዚህም የተነሳ፣ መርከበኞች መንገዳቸውን ይስታሉ፡፡ የኮምፓስ መፈልሰፍ ግን መርከበኞች፣ ሩቅና የማይታወቁ መሬቶች ለማሰስ (ለማግኘት) ረድቷቸዋል፡፡ ኮምፓስን እገሌ ፈጠረው ለማለት አይቻልም፡፡ የጥንት ሰዎች እንደ ቆርቆሮ፣ ብረት፣ ወርቅ፣ መዳብ ያሉ በጣም ትናንሽ ጠጣር ማዕድናት፣ እንደ ማግኔት መሳብ የሚችል ልዩ ባህርይ እንዳላቸው ያውቁ ነበር፡፡ የእነዚህ ማዕድናት ስባሪ በክር ታስሮ ሲንጠለጠል፣ በሰሜን ኮከብ አቅጣጫ ያመለክታል፡የእነዚህን ማዕድናት እንደ መርፌ የሾለ ድንጋይ የመሳሰሉ ማዕድናትን፣ አቅጣጫዎች በተበጁለት ማስቀመጫ (መያዣ) ውስጥ ደራርቦ ማስቀመጥ የ13ኛው ክፍለ ዘመን አውሮፓ ሐሳብ ይመስላል - ምንም እንኳን ሐሳቡን የአረብ ነጋዴዎች ከቻይና ያመጡት ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ቢኖርም፡፡ ያም ሆነ ይህ፣ በ14ኛው ክፍለ ዘመን፣ ኮምፓስ በስፋት ሥራ ላይ ውሎ ነበር፡፡ ባለፈው ሚሊኒየም፣ ለባህር ጉዞ መሳካት አስተዋጽኦ ካደረጉ ብዙ ቴክኖሎጂዎች መካከል እጅግ የላቀ ጠቀሜታ የሰጠው ኮምፓስ ነው፡፡ ተአምራዊ የሚመስለውን የአቅጣጫ ጥቆማውን በመጠቀም ባህረኞች በጣም ሩቅ የሆኑ ጉዞዎችን በማድረግ ከዚያን በፊት የማይታወቁ አካባቢዎችን ለማሰስና ለማወቅ ድፍረት አገኙ፡፡ የአውሮፓ አሳሾች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አሜሪካ ያደረጉት ጉዞ፣ ምናልባት ሺህ ዓመቱን የቀየረ (የለወጠ) ብቸኛው የሥልጣኔ ክንውን ሊባል ይችላል፡፡ ሜካኒካል ስዓት፡- የጥንት ሰዎች የቀኑን ጊዜ (ሰዓት) በግምት የሚያውቁበት ዘዴ ነበራቸው፡፡ ለምሳሌ፡- የጥንት ግብፃውያን በጥላ ጊዜን የሚያውቁበት ዘዴ “Sundial” ይባላል፡፡ ሳንዳይል ሁለት ክፍሎች አለው፡፡ በሰዓት የተከፋፈለ ዝርግ ወይም ጠፍጣፋ ወለልና በመሬት ዛቢያ ትይዩ ወለሉ መኻል የተተከለ ጥላ ፈጣሪ ዘንግ፡፡ መሬት በራሷ ዛቢያ ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ ስትሽከረከር የዘንጉ ጥላ፣ ጠፍጣፋና ዝርጉ ወለል ላይ በተሰመሩት የዕለቱ ሰዓቶች ላይ ሲያርፍ እንደዛሬው እቅጩን ባይሆን እንኳ የተቀራረበ የጊዜ ግምት ይሰጣቸው ነበር፡፡ ዘዴዉ የሚሠራው ፀሐይ በምትፈጥረው ጥላ ስለሆነ በሌሊትና በክረምት ወቅት አይሠራም፡፡ ደመና በሚበዛው የአውሮፓ አየር ሁኔታም ያን ያህል አያገለግልም፡፡  ጥንታውያን ግብፆች ሌላ የሰዓት መቁጠሪያ ዘዴ ነበራቸው - የውሃ ሰዓት፡፡ በዚህ ዘዴ ሁለት የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከሮች ላይና ታች ተደርገው ይቀመጣሉ፡፡ ከላይኛው ማጠራቀሚያ የውሃ ጠብታ በተወሰነ ፍጥነት፣ ጠብ ጠብ እያለ ወደ ሁለተኛው ማጠራቀሚያ እንዲገባ ይደረጋል፡፡  ሁለተኛው ማጠራቀሚያ ውስጥ አመልካች ቀስት የታሰረበት ተንሳፋፊ ነገር የውሃው መጠን ሲጨምር ከፍ እያለ ይሄዳል፤ ቀስቱም ከዕለቱ ጊዜ ጋር ተቀራራቢ ሰዓት ያመለክታል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ ሜካኒካል (በእንቅስቃሴና በኃይል ሕግ የሚሠራ) ሰዓት በአውሮፓ ብቅ ያለው በ14ኛው ክፍለ ዘመን ነበር፡፡ ታሪክ ታዲያ ሰዓትን በብቸኝነት የፈጠረው እገሌ ነው በማለት ለማንም ሰው የፈጠራ ባለቤትነት መብት (እውቅና) አልሰጠም፡፡ በአሁኑ ወቅት በክብደታቸው ቀላልነት በእጃችን የምናስራቸው ሰዓቶች መጀመሪያ አካባቢ ክብደታቸው በጣም ከባድ፣ መጠንና ቅርፃቸው ለአጠቃቀም የማያመቹ፤ የማያምሩና አስጠሊታ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ በ14ኛው ክፍለ ዘመን ሄነሪ ደ ቪክ፤ በፓሪስ ለሮያል ፓላስ የሠራው ሰዓት 227 ኪ.ግ ይመዝን ነበር፡፡ የድሮዎቹ ሜካኒካል ሰዓቶች የሚቆጥሩት ሰዓት ብቻ ነበር - ደቂቃና ሶኮንድ አልነበራቸውም፡፡ በዚህ የተነሳ በየቀኑ ሁለት ሰዓት ያህል ጉድለት ያሳዩ ነበር፡፡ የተለያዩ ማሻሻያዎች በየጊዜው ተደርገዋል፡፡ ለምሳሌ፣ በደቹ የሥነ ኮከብ አጥኚ ክርስቲያን ሁጃንስ በ1657 ዓ.ም በቀረበው ሐሳብ ላይ በመመሥረት በተደረገው የፔንዱለም (በስበት ኃይል ወደፊትና ወደኋላ የሚንቀሳቀስ) ማሻሻያ ትክክል በሚያስብል መልኩ ጊዜን በደቂቃና በሰኮንድ መለካት ተችሏል፡፡ በሰው ሠራሽ ዘዴ ጊዜን መለካት በየሥልጣኔው የተደረገ ከባድና ተደጋጋሚ ውጣ-ውረድ ውጤት ነው፡፡ መርከበኞች ያሉበትን ወይም የሚደርሱበትን ሎንግቲዩድ የሚያሰሉት ትክክለኛ የጊዜ ልኬት ላይ ተመስርተው ስለሆነ፣ ሰዓት ለባህር ላይ ጉዞ ከሚያስፈልጉ ጠቃሚ መሳሪያዎቹ አንዱ ሆነ፡፡ ሳይንሳዊ ምርምሮች ብዙ ጊዜ ትክክለኛ የጊዜ ቀመር ስለሚያስፈልጋቸው የሰዓት ፈጠራ ሳይንስ እንዲያብብ ምክንያት ሆኗል፡፡ በተለያዩ የቢዝነስና የኢንዱስትሪ ክንውኖች፣ ድርጊቶችና የሰው ልጅ እንቅስቃሴ መቀናጀት ስላለባቸው የሰዓት አስፈላጊነትና ጠቃሚነት ከምን ጊዜውም በላይ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ዛሬ በየጊዜው እያደገ ያለው የኢንዱስትሪው ዓለም በከፍተኛ ደረጃ በሰዓት የተከፋፈለ ነው፡፡ መቼ መሥራት፣ መጫወት (መዝናናት) መብላትና መተኛት … እንዳለብን የሚመራን ሰዓታችን ነው፡፡ በነገራችን ላይ፡- የአሜሪካ “ናሽናል ኢንስቲትዩት ኦፍ ስታንዳርድ ኤንድ ቴክኖሎጂ”፣ ዲሴምበር 29 ቀን 1999 ዓ.ም በፈረንሳይ - ፓሪስ ካለው ሰዓት ጋር ተመሳሳይ የሆነ በዓለም እጅግ ትክክለኛ የአቶሚክ ሰዓት ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ ሰዓት አንድ ሴኮንድ ሳይጨምር ወይም ሳይቀንስ ለ20 ሚሊዮን ዓመታት ጊዜን ሳያዛንፍ በትክክል ይለካል፡፡ የመስተዋት ሌንስ፡- ዘመናዊውን ዓለም የቀረፁ በርካታ ሳይንሳዊ ግኝቶች እውን የሆኑት ሰዎች የማየት ችሎታቸውን ከፍ ያደረጉ መሳሪያዎችን በመፍጠራቸው ነው፡፡ በጣም ጥቃቅንና ደቃቅ ወይም እጅግ በጣም ሩቅ የሆኑ ነገሮችን ለማየት የሚያገለግሉ የመስተዋት ሌንሶች የሰው ልጅ ሕይወት በከፍተኛ ደረጃ እንዲለወጥ አድርገዋል፡፡ የመጀመሪያዎቹ የለሰለሱ ትናንሽ መስተዋቶች ጥቅም ላይ የዋሉት ለማይክሮስኮፕ (አጉልቶ ማያ) ወይም ለቴሌስኮፕ (ሩቅ መመልከቻ) አልነበረም፡፡ የማየት ችግር ያለባቸውን ሰዎች እይታ ለሚያሻሽለው የዓይን መነፅር ነበር፡፡ የዓይን መነፅር ባይፈለሰፍ ኖሮ፣ ምናልባትም የኅትመት ውጤት ተወዳጅ ለመሆን ረዥም ጊዜ ሊወስድበት ይችል ነበር በማለት መከራከር ይቻል ይሆናል፡፡ ለምን መሰላችሁ? አብዛኛው ሰው ዕድሜው እየጨመረ ሲሄድ፣ “ፋር ሳይትድነስ” የተባለ (ትናንሽ ነገሮችን ከቅርብ ያለመለየት) ችግር ይፈጠርበታል፡፡ በዚህ የተነሳ የኅትመት ውጤቶችን ለማንበብ ወደ ፊቱ ቀረብ ሲያደርግ ፊደሎች ጥርት ብለው አይታዩም - ይደበዝዛሉ፡፡ ይህን ችግር የሚያስተካክል መነፅር ካልተጠቀሙ በስተቀር ማንበብ አይቻልም ባይባልም፣ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ምንም እንኳ ቻይና ከብዙ ምዕተ-ዓመታት በፊት በደንብ ያልለሰለሰና ጥራት የሌለው መነፅር ሳትጠቀም እንዳልቀረ ቢገመትም የመጀመሪያው የዓይን መነፅር የተፈለሰፈው በኢጣሊያ ነው - በ13ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ፡፡ በርቀት ያለን ነገር አቅርቦ የሚያሳይ የመስተዋት ሌንስ (ቴሌስኮፕ) ሳይሠራ በርካታ ምዕተ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ የቴሌስኮፕ ፈጠራ ባለቤትነት መብት (ክብር) የተሰጠው ለደቹ (ኔዘርላንድስ - ሆላንድ) ተወላጅና መነፅር ሠሪ ሃንስ ሊፐርሸይ ሲሆን በ1608 ሊፐርሸይ የሠራውን “መመልከቻ” ለደች መንግሥት አቅርቦ አሳይቷል፡፡ መንግሥትም ወዲያውኑ ለወታደራዊ (ሚሊተሪ) አገልግሎት ጠቃሚ መሳሪያ እንደሆነ ተገነዘበ፡፡ በቀጣዩ ዓመት (1607) ኢጣሊያዊው የፊዚክስና የጠፈር ሳይንቲስት ጋሊሊዮ ጋሊሊ፣ የሊፐርሸይን ፈጠራ አሻሽሎ ለጠፈር (ለሰማይ) ጥናት ተጠቀመበት፡፡ የጋሊሊዮ ቴሌስኮፕ፣ የሚታየው ነገር ካለው ተፈጥሯዊ መጠን 20 ጊዜ አግዝፎ (አጉልቶ) የሚያሳይ ነበር፡፡ ጋሊሊዮ በዚያ ቴሌስኮፕ፤ ጨረቃ መሬትን እንደምትዞረው ሁሉ፣ ጁፒተርን የሚዞሩ ጨረቃዎች እንዳሉ አየ፡፡ በዚህም የተነሳ እስከዚያን ጊዜ ድረስ “ሁሉም የሰማይ አካላት (ፀሐይን ጨምሮ) በመሬት ዙሪያ ይሽከረከራሉ” የሚለውን  የተሳሳተ እምነት የሚሽር (የሚቃረን) ሐሳብ አቀረበ፡፡ የጋሊሊዮ ቴሌስኮፕ የፀሐይን ጥቋቁር ነጠብጣቦች፣ የጨረቃን ተራሮችና ሸለቆች፣  አራቱን የጁፒተር ትላልቅ ጨረቃዎች ያነሳየ ሲሆን ቬነስ የተለያዩ ወቅቶች እንዳላትም ማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ የጋሊሊዮ ቴሌስኮፕ እይታ ዓለማችንን በዋነኛነት የቀየረው ሳይንሳዊ አብዮት እንዲፈነዳ ከፍተኛ መነሳሳት ፈጥሯል፡፡ በነገራችን ላይ ጋሊሊዮ በፊዚክስና በአስትሮኖሚ (የጠፈር ሳይንስ) ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በፊዚክስ ጥናቱ፣ የተለያየ ክብደት ያላቸው ነገሮች አየር ከሌለበት (ቫክዩም) ቦታ እኩል ቢለቀቁ የመሬት ስበት ተፅዕኖ ሳይፈጥርባቸው መሬት ላይ እኩል ይወድቃሉ በማለት ሕግ ቀምሮ በተግባር አሳይቷል፡፡ እንዲሁም በግድግዳ ሰዓት ውስጥ ወደፊትና ወደኋላ እያለ የሚንቀሳቀሰው ፔንዱለም፤ ጉልበት ወይም የኃይል ምንጭ የሚያገኘው ከመሬት ስበት እንደሆነ አሳይቶ ሕግም አርቅቋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጋሊሊዮ፣ በ1589 ዓ.ም በፓሪስ ዩኒቨርሲቲ ሂሳብ አስተምሯል፡፡ በ17ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ፣ ሆላንድ በመነፅር ሥራ የተንበሸበሸችበት ወቅት ነበር፡፡ በ1600 ገደማ፣ ማይክሮስኮፕ (ጥቃቅን ነገሮችን አጉልቶ የሚያሳይ መሳሪያ) ተፈለሰፈ፡፡ ይሁን እንጂ ይህን መሳሪያ የፈጠረው እገሌ ነው ብሎ እውቅና ለመስጠት አስቸጋሪ ነው፡፡ በ1625 ዓ.ም ይህን አዲስ መሳሪያ የሚያመርት የመስተዋት ወርክሾፕ ተቋቋመ፡፡ በ1600 መጨረሻ ዓመታት ሳይንቲስቶቹ በውሃ ጠብታ ውስጥ ያሉትን ማክሮቦችና ሕይወት ያላቸውን ሴሎች ተፈጥሯዊ የአካል አቀማመጥ ለመመልከት ማይክሮስኮፕ ይጠቀሙ ነበር፡፡ የዚህና የሌሎች ማይክሮስኮፖች ግኝት የባዮሎጂን ዕድገት ወደላቀ ደረጃ አሸጋገረው፡፡ የደች ተወላጅና የተፈጥሮ ፍጥረታትን (እንስሳት፣ ተክሎች፣ አዕዋፍት …) የሚያጠናው አንቶኒ ቫን ሌዊን ሆክ፤ የራሱን ማይክሮስኮፕ ሠርቶ፣ ያኔ እሱ animalclues ብሎ   የሚጠራቸውን፣ ዛሬ ግን ባክቴሪያና ፕሮቶዟ በመባል የሚታወቁትን ያየው በ1600ዎቹ ዓመታት ነበር፡፡ በሽታ ማዳንን ጨምሮ ስለበሽታዎች፣ ስለህክምናቸውና ስለመከላከያ ዘዴያቸው ያለን አብዛኛው እውቀት፣ ማይክሮስኮፕ በመጠቀማችን የተገኘ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የማተሚያ መሳሪያ፡- እስቲ መጻሕፍት፣ መጽሔቶች ወይም ጋዜጦች የሌሉባትን ዓለም አስቡ፡፡ እስከ 15ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የሚፈለገው ምናባዊ እይታ ትንሽ ነበር፡፡ ምክንያቱም ማንበብና መጻፍ የሚችሉ ሰዎች ጥቂት ነበሩ፡፡ እነሱም ቢሆኑ ለማንበብ የነበራቸው ምርጫ በጣም አናሳ ነበር፡፡ ለበርካታ ሺህ ዓመታት እውቀት ሲተላለፍ የቆየው፣ በአፍና እጅግ አድካሚና ውድ በሆነው በእጅ የሚፃፉ መረጃዎች አማካኝነት ነበር፡፡ የማተሚያ መሳሪያ፤ ከሥነ ጽሑፍ እስከ ሳይንስ፣ ከፖለቲካ እስከ ሃይማኖት ያሉ በርካታ የሰው ልጅ እንቅስቃሴ መረጃዎችን ተጨባጭና ርካሽ በሆኑ መንገዶች በስፋት ማሰራጨት ያስቻለ ፈጠራ ነው፡፡ ያለፈውን ሺህ ዓመት (20ኛው ክፍለ ዘመን) የለወጠ አንድ ብቸኛ ነገር ምንድነው? ቢባል የማተሚያ መሳሪያ ነው፡፡ ይህ መሳሪያ እስከ ዛሬ የዘለቀውን ሥነ-ጥበባዊ (አርቲስቲክ) አገላለጽና ሳይንሳዊ የዕድገት ዘመን አቀጣጥሏል፡፡ ከ1000 ዓ.ም (1ኛው ክፍለ ዘመን) በፊት ጥቂትም ቢሆን አውቶማቲክ መሰል ይዘት ያለው ማተሚያ እንደነበር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ቻይናውያንና ኮርያውያን ትላልቅ ፊደሎች የሚያትሙበት ዘዴ ነበራቸው፡፡ እንዴት መሰላችሁ ዘዴው? ፊደሎች ወይም ሥዕሎች በጠፍጣፋ እንጨት ወይም በሌላ ነገር ላይ ይቀረፁና ቀለም ይቀባሉ፡፡ ከዚያም በወረቀት ወይም በጨርቅ ወይም በሌላ ነገር ተሸፍነው ክብደት ባለው ነገር ይዳመጣሉ ወይም ይታሻሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የፊደሉ ወይም የሥዕሉ ቅርፅ በተሸፈነው ነገር ላይ ይታተማል - እንደማኅተም ማለት ነው፡፡ በ2ኛው ክፍለ ዘመን ቻይናውያን ጽሑፍ የሚያትሙበት ጥሩ የሚባልና በስፋት የተሰራጨ ዘዴ ነበራቸዉ፡፡ ቻይናውያኑ፣ በዚሁ ክፍለ ዘመን በወረቀት ፈጠራ ጥበባቸው የፈር-ቀዳጅነት እውቅና አግኝተዋል፡፡ የማተሚያ ዘዴ ወደ ምዕራቡ ዓለም የተሻገረው በጣም ዘግይቶ ነው፡፡ይጦች አማካይነት የሚተላለፍ (ቡቦኒክ ፕላግ ወይም “ብላክ ዴዝ” የተባለ ወረርሽኝ፣ አውሮፓን ክፉኛ አተራምሷት ነበር፡፡ ይህ ትኩሳት በመፍጠር አካልን የሚያሳብጥ ወረርሽኝ በአኅጉሩ የነበሩትን ማንበብና መጻፍ የሚችሉ ሰዎችን ፈጀ፡፡ በዚህ የተነሳ መጻሕፍት በእጅ የሚገለብጡ ሰዎች በጣም ጥቂት በመሆናቸው መጽሐፍ በእጅ ማስገልበጥ እጅግ በጣም ውድ ሆነ፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በዚያኑ ወቅት፣ ናይሌን በአኅጉሩ በስፋት ተሰራጭቶ  ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ የወረቀት አቅርቦት ርካሽ በሚባል አንፃራዊ ዋጋ ከፍ እንዲል አደረገ፡፡ የእነዚህ ሁለት ጉዳዮች መጣመር ለማተሚያ መሳሪያ መቋቋም አመቺ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታን ፈጠረ፡፡ የአዲሱን ጠቃሚ የፈጠራ ውጤት እውን መሆን ያረጋገጠው በ1400ዎቹ ዓመታት የተፈለሰፈው የብረት ተንቀሳቃሽ መሳሪያ ነው፡፡ በ1450 ዓ.ም ገደማ ዮሐንስ ጉተምበርግ የተባለ ጀርመናዊ አንጠረኛ ወሳኝ የሆኑ በርካታ የማተሚያ ቴክኖሎጂዎችን ገጣጠመ፡፡ በዚህ ቴክኖሎጂ በአናታቸው ፊደሎች የተቀረፀባቸው፣ እኩልና ተመሳሳይ ቅርፅ ያላቸው ብረቶች ይመረታሉ፡፡ የዚህ ፈጠራ በጣም ጠቃሚ ነገር የተመረቱትን ፊደላት እንደተፈለገው ቦታ እያቀያየሩ ያለገደብ ለአዲስ ጽሑፍ (ቴክስት) መጠቀም መቻል ነው፡፡ በነገራችን ላይ የአገራችን ማተሚያ ቤቶች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ - ኮምፒዩተር መጠቀም ከመጀመራቸው በፊት ለረዥም ጊዜ በዚህ ዘዴ ሲገለገሉ ነበር፡፡ የመጽሐፍ፣ መጽሔት፣ ጋዜጣ … ጽሑፍ፣ ስፑል በሚባል የተጠቀለለ ወረቀት ላይ በታይፕ ይጻፋል፡፡ ታይፑ ለየት ያለ ስለሆነ፣ በስፑሉ ላይ ፊደል አይጽፍም - በሚፈለጉት ፊደላት ቅርፅ ስፑሉን ይበሳል፡፡ ከዚያም ስፑሉ ወደ ካስተር ክፍል ይሄዳል፡፡ በዚህ ክፍል ያሉ መሳሪያዎች ስፑሉን ሲያጐርሷቸው በታዘዙት መሠረት ፊደሎቹን በእርሳስ (መጻፊያው አይደለም) ላይ ቀርፀው ያወጣሉ፡፡ ጽሑፉ ሲጠናቀቅ ይታሰርና ቀለም ተቀብቶ በወረቀት ይሸፈንና ይዳመጣል፡፡ጨረሻም ወረቀት ላይ የተገለበጠው ከዋናው ጽሑፍ ጋር እየተናበበ ይታረማል፡፡ ስለ አሠራሩ የበለጠ ግንዛቤ ለማግኘት ብርሃንና ሰላም፣ አርቲስቲክ ንግድ ማተሚያ፣ … ድርጅቶች ቢጠየቁ ይተባበራሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ጉተንበርግ ፊደላቱን በከፍተኛ ኃይል በመጫን ጥራት ያለው ጽሑፍ የሚሰጥ የእጅ ማተሚያም ንድፍ ቀርፆ ነበር፡፡ የጉተንበርግ የኅትመት ጥበብ ሞገስ ሆኖ እስከ ዛሬ የዘለቀው የመጀመሪያው ፈር ቀዳጅ የኅትመት ውጤት መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ የማተሚያ መሳሪያ በመካከለኛው ዘመን መጨረሻ የምሁራንን የታመቀ የንባብ ፍላጐት አቀጣጥሎ ወደ እውቀት ዘመን አሸጋግሯል፡፡ ይህ መሳሪያ ባይፈጠር ኖሮ ምናልባትም የባህል፣ የክህሎት፣ ወይም የተረሳ ወይም የተናቀ ነገር ዳግም መወለድ ወይም እንደገና መታደስ (ሬኔሳንስ) በፍፁም ላይከሰት ይችል ነበር፡፡ ለአብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል መጻሕፍት በርካሽ ዋጋ ማቅረብ ባይቻል ኖሮ በ1500 ዓመታት አጋማሽ በገጠሪቷ እንግሊዝ ዝቅተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን የነበረው የጆን ሼክስፒር ልጅ ምናልባት በአሁኑ ወቅት በታሪክ ውስጥ እጅግ የላቁ እየተባሉ የሚሞካሹትን ድራማዎች ለመጻፍ፣ በፍፁም ላይነሳሳ ይችል ነበር፡፡ በአጠቃላይ ሥልጣኔ፣ ከጉተንበርግ ፈጠራ ያገኘው ጥቅም ይሄን ያህል ተብሎ የሚለካ አይደለም፡፡ በእንፋሎት የሚሰራ ሞተር መኪና ወይም አውሮፕላን ካለፈው ሚሊኒየም እጅግ ጠቃሚ ፈጠራዎች ዝርዝር ውስጥ ሊካተቱ ይገባል ሊባል ይችላል፡፡ ነገር ግን አልተካተቱም፡፡ እነዚህ ግኝቶች የተቃጠለ (የነደደ) ነዳጅ ለመጀመሪያ ጊዜ በብዛት ወደ ሜካኒካል ኢነርጂ የለወጠው የእንፋሎት ሞተር ቀስ-በቀስ እየተሻሻለ የተገኙ ውጤቶች ናቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ የእንፋሎት ሞተሮች የኃይል ምንጭ እንጨት ነበር - ወደ ኋላ ላይ ደግሞ ከሰል ሆነ፡፡ የእንፋሎት ሞተር፣ እንደተቀሩት ጥቂት ቴክኖሎጂዎች ሁሉ የኢንዱስትሪውን ዓለም የለወጠ ነው፡፡ ይህ ፈጠራ ሰዎች በጡንቻቸውና በእንስሳት ጉልበት ላይ ብቻ ከመወሰን ነፃ አወጣቸው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ የኢንዱስትሪውን አብዮት የመሩት ፋብሪካዎች እውን እንዲሆኑ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ እንዲሁም ለመጀመሪያው በፋብሪካ የተሠራ ባለከፍተኛ ፍጥነት ተንቀሰቃሽ ትራንስፖርትም ዋነኛ ብልት ነበር፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ (የእንፋሎት ሞተር) ለመጀመሪያ ጊዜ ብቅ ያለ ጥንታዊ የፈጠራ ምሳሌ ነው፡፡ በ1698 ዓ.ም እንግሊዛዊው ኢንጂነር ቶማስ ሳቭሬይ፤ በማሞቂያ (ቦይለር) የተፈጠረ እንፋሎት በኃይል ምንጭነት የሚጠቀም የውሃ ፓምፕ ሠራ፡፡ የሳቭሬይ ሞተር ዲዛይን ጥቅም ላይ ውሎ ባያውቅም ላፈለቃቸው ሐሳቦች በርካታ የባለቤትነት መብት ወስዷል፡፡ በ1712 ዓ.ም ደግሞ እንግሊዛዊው አንጥረኛ ቶማስ ኒውኮመን የተሻለ ጠቀሜታ ያለው የእንፋሎት ሞተር ሠራ፡፡ የኒውኮመን መሳሪያ መጀመሪያ አካባቢ ከከሰል ጉድጓዶች ውሃ ለመምጠጥ አገልግሏል፡፡ ሆኖም ግን አብዛኛውን ጊዜ በእንፋሎት ሞተር ፈጠራ እውቅና የተሰጠው ለስኮትላንዱ ኢንጂነር ጀምስ ዋት ነው፡፡ የዋትን ሞተር ከቀደምቶቹ በላቀ ደረጃ የበለጠ ብቃት እንዲኖረው ያደረገው እንፋሎቱን የሚያቀዘቅዝ የተለየ ክፍል ስለነበረው ነው፡፡ ዋት ለፈጠራው እውቅና ያገኘው በ1769 ነበር፡፡ ዋት ሞተሩ እንዳይደርቅ የሚያለሰልስ የዘይት ቅባትና የሙቀት መከላከያ የመሳሰሉ ሌሎች ማሻሻያዎች አድርጓል፡፡ በእነዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ በእንፋሎት ኃይል ወደ ላይና ወደ ታች የሚለውን ፒስተን፣ በክብ መስመር እንዲዞር የሚያደርግ ጥርሽ (ኩሽኔት) ዘዴም ነድፏል፡፡ የዋት ሞተር፤ ፋብሪካዎችን ከውሃ ጥገኝነት ከማላቀቁም በላይ የከሰል ክምችት ላላቸው አገሮች ደግሞ መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡ ታላቋ ብሪታኒያ ደግሞ ከፍተኛ የከሰል ክምችት ነበራት፡፡ ይህም በ18ኛውና በ19ኛው ክፍለ ዘመን የእንግሊዝን መስፋፋት አጧጧፈው፡፡ በኢንዱስትሪ፣ ንግድና ወደ ምዕራቡ ዓለም ወደ አሜሪካ በተደረገው መስፋፋት በእንፋሎት ኃይል የሚንቀሳቀሱ ባቡሮች ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በመቀጠልም በሞተር ውስጥ ተቀጣጥሎ (ነድዶ) ከባድ ነገሮችን በኃይል ወደፊት የሚያፈናጥረው (የሚገፋው) ኢንተርናል ካምባስሽን ኢንጅንና የኤሌክትሪክ ማመንጫ ጣቢያዎች በእንፋሎት ሞተር የሚከናወኑትን አብዛኞቹን ሥራዎች ተኩ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ግኝቶት በእንፋሎት ሞተር ትከሻ ላይ ተንጠላጥለው የተገኙ ናቸው፡፡

ዓለምን የለወጡትን ቀሪ ድንቅ ፈጠራዎች እንመለስባቸዋለን፡፡

 

 

Read 13171 times Last modified on Saturday, 31 December 2011 11:09