Saturday, 06 September 2014 11:07

በድሃ ሃገራት በአመት 1 ትሪሊዮን ዶላር በሙስና ይመዘበራል ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በአመት 3.6 ሚ. ዜጎች በሙስና ሰበብ ለህልፈተ ህይወት ይዳረጋሉ

በድሃ ሃገራት በአመት 1 ትሪሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ በሙስና ተመዝብሮ ከአገር እንደሚወጣና በአንድ አመት ጊዜ ውስጥም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በሙስና ሰበብ ለህልፈተ ህይወት እንደሚዳረጉ አንታይፖቨርቲ ኦርጋናይዜሽን ዋን የተባለ ተቋም ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ ቢቢሲ ዘገበ፡፡
በድሀ አገራት የሚታየውን የከፋ ድህነት ለመቅረፍ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ሲደረጉ የነበሩ አበረታች ጥረቶች በሙስና ሳቢያ እየተደናቀፉ እንደሚገኙ የጠቆመው ዘገባው፣ በአገራቱ በከፍተኛ ሁኔታ በመስፋፋት ላይ በሚገኘው ሙስና ሳቢያ በየአመቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ተመዝብሮ እንደሚወጣና ዜጎችም ለህልፈተ ህይወት እየተዳረጉ እንደሚገኙ ገልጧል፡፡
ሙስና በደሃ የዓለማችን አገራት ከበሽታዎችና ከተፈጥሮ አደጋዎች በበለጠ ሁኔታ የኢኮኖሚና የሰብዓዊ ቀውስ እየፈጠረ እንደሚገኝ የገለጸው የተቋሙ ሪፖርት፣ ድርጊቱ የግል ኢንቨስትመንትን የሚያደናቅፍ፣ የኢኮኖሚ እድገትን የሚገታና የንግድ እንቅስቃሴ ወጪዎችን ያለአግባብ የሚያንር ከመሆኑ በተጨማሪ ፖሌካዊ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ያደርጋል ብሏል፡፡በማደግ ላይ ያሉ አገራት የገንዘብ ሃብት በሙስና እየተመዘበረ ከአገር እንዲወጣ መደረጉ፣ የአገራቱ መንግስታት ለጤና እንክብካቤ፣ ለምግብ ዋስትናና ለሌሎች መሰረታዊ መሰረተ ልማቶች ማስፋፊያ በቂ በጀት እንዳይመድቡ እንቅፋት ስለሚፈጥር፣ በአገራቱ በየአመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች፣ በተለይ ደግሞ በርካታ ቁጥር ያላቸው ህጻናት ለህልፈተ ህይወት እንደሚዳረጉ ሪፖርቱ ገልጧል፡፡ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገራት ሙስናን ማጥፋት ቢቻል፣ በየአመቱ 10 ሚሊዮን ተጨማሪ ህጻናትን የትምህርት እድል ተጠቃሚ ማድረግ፣ ለተጨማሪ 500 ሺህ የአንደኛ ደረጃ መምህራን ደመወዝ መክፈል እንዲሁም ከ11 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎችም የጸረ ኤች ኤቪ ኤድስ መድሃኒት በአግባቡ ማዳረስ ይቻል እንደነበርም በሪፖርቱ መገለጹንም ዘገባው ጨምሮ ገልጧል፡፡

Read 1742 times