Saturday, 06 September 2014 10:51

የዓመቱ አነጋጋሪና አወዛጋቢ ክስተቶች

Written by 
Rate this item
(13 votes)

                በዓመቱ መጀመሪያ በመስከረም ወር 2006 ዓ.ም ለ12 ዓመታት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በመሆን ያገለገሉት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፤ ከስልጣናቸው የወረዱ ሲሆን በቦታቸውም ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ተተክተዋል፡፡ በአምባሳደርነት ዘመናቸው የውጭ አገር ኢንቨስተሮችን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣትና አገር ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ በማግባባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው የሚነገርላቸው ዶ/ር ሙላቱ፤ የፕሬዚዳንትነት ስልጣናቸውን ከተረከቡ በኋላም ሥራቸው በቤተመንግስት አካባቢ የተገደበ አልሆነም፡፡ በተለያዩ አገራት እየዞሩ የውጭ ኢንቨስተሮችን የማግባባት ሥራቸውን ቀጥለውበታል፡፡
በዓመቱ ከተከናወኑ አነጋጋሪ ጉዳዮች መካከል አንድነት ፓርቲ ከሰላማዊ ሰልፍ ጋር በተገናኘ የመብት ጥሰትና መጉላላት ተፈጽሞብኛል በማለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባንና የከተማዋን ፖሊስ ኮሚሽን በፍ/ቤት መክሰሱ ተጠቃሽ ነው፡፡
ፍ/ቤቱም ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ “ክሱ ለክስ የሚያበቃ ምክንያት የለውም፣ አስተዳደራዊ ውሣኔ ያገኝ የሚል ውሣኔ የሰጠ ሲሆን ፓርቲውም በጊዜው ይግባኝ እንደሚጠይቅ ገልፆ ይግባኝ ለመጠየቅ በሂደት ላይ ይገኛል፡፡  
የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ እንዲሁም የኢዴፓ መስራችና ሊ/መንበር የነበሩት አቶ ሙሼ ሰሙ ራሳቸውን ከፖለቲካ ፓርቲ ያገለሉት በዚሁ ባሳለፍነው ዓመት ነው፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ከጤና ጋር በተያያዘ፣ አቶ ሙሼ ደግሞ “የጥሞና ጊዜ እፈልጋለሁ” በሚል የፓርቲ ፖለቲካ በቃን ብለዋል፡
ሹመትና ህልፈት
የአማራ ክልልን ለ8 ዓመታት በርዕሰ መስተዳደርነት የመሩት አቶ አያሌው ጎበዜ፣ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በአምባሳደርነትና በትምህርት ሚኒስትርነት የተመደቡት ባሳለፍነው ዓመት ሲሆን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት አቶ አለማየሁ አቶምሳ ባደረባቸው ህመም ህክምና ሲከታተሉ ቆይተው ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል፡፡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የህዝብ ተሳትፎና ንቅናቄ ክላስተር አስተባባሪና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ሙክታር ከድርም የክልሉ ፕሬዚዳንት በመሆን የተሾሙ ሲሆን  በሳቸው ቦታ ወ/ሮ አስቴር ማሞ ተተክተዋል፡፡
የሳኡዲ ስደተኞችን ማባረር
የሳኡዲ አረቢያ መንግስት የመኖሪያ ህጋዊ ፍቃድ የላቸውም በሚል ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ የበርካታ ሃገር ዜጎችን ከሃገሩ በኃይል ማስወጣት የጀመረው ባሳለፍነው ዓመት ጥቅምት ወር  መጨረሻ ገደማ ነበር፡፡ የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ህገወጥ ስደተኞች ባላቸው ላይ በወሰደው የማባረር እርምጃ ከ150ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገር ቤት መመለሳቸው የሚታወስ ሲሆን የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ትኩረት በሳበው በዚህ ክስተት፣ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሳኡዲ ኤምባሲዎች በር ላይ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ተቃውሞአቸውን ገልፀዋል፡፡ በአዲስ አበባ ለተመሳሳይ ዓላማ ሰማያዊ ፓርቲ የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ግን በፖሊስ በመበተኑ ሳይደረግ ቀርቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በየአረብ ሃገራቱ ለስራ የሚጓዙ ዜጎች ጉዳይ አሳስቦኛል በማለት ወደ የትኛውም የአረብ ሃገራት ለጉልበት ስራ የሚደረግን ጉዞ ለ6 ወር ያህል ማገዱ የሚታወስ ሲሆን እገዳው 9ኛ ወሩን ቢይዝም እስካሁን አልተነሳም፡፡
“የረዳት አብራሪው የአውሮፕላን ጠለፋ”
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለ5 ዓመታት በረዳት አብራሪነት ያገለገለው ሃይለመድህን አበራ፤ በጥር ወር አጋማሽ ላይ ከአዲስ አበባ ወደ ጣሊያን ሲበር የነበረውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን  ጠልፎ ስዊዘርላንድ ማሳረፉ ከዓመቱ አነጋጋሪና ትኩረት ሳቢ ጉዳዮች አንዱ ነበር፡፡
ረዳት አብራሪው አውሮፕላኑን ለምን እንደጠለፈ እስካሁንም ይሄ ነው የሚባል አሳማኝ ምክንያት አልተገኘለትም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ጠላፊው ተላልፎ እንዲሰጠው የጠየቀ ቢሆንም አዎንታዊ ምላሽ አላገኘም፡፡ ጠላፊው የስዊዘርላንድን መንግስት ጥገኝነት ጠይቆ እንደተፈቀደለትና አሁን እዚያው በእስር ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ፍትህ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ በጠላፊው ላይ  ክስ መስርቶ ፍ/ቤት የአቃቤ ህጎችን ምስክርነት በመስማት  ላይ ይገኛል፡፡
መፍትሔ ያልተበጀለት “የሙስሊሞች ጉዳይ”
“ከሁለት ዓመት በፊት የታሰሩት ሙስሊም መሪዎቻችን ይፈቱ፣ ድምፃችን ይሰማ” የሚሉ ንቅናቄዎች እየተካሄዱ ነው ዓመቱ ያለፈው፡፡ ሐምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም አርብ በታላቁ አንዋር መስጊድ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ  ተከትሎ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ በሰዎች ላይ ድብደባና ጉዳት መድረሱ ይታወሳል፡፡ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ታስረው የነበረ ሲሆን በነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ በዋስ ተለቀዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የቀድሞው “አዲስ ጉዳይ” መፅሄት የፎቶግራፍ ባለሙያ አዚዛ አህመድ እና የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባል ወይንሸት ሞላ ይገኙበታል፡፡
የታሰሩት ሙስሊሞች ጉዳይ በፍ/ቤት መታየቱን የቀጠለ ሲሆን ተጠርጣሪዎቹ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን በማሰማት ሂደት ላይ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡
አዲሱ ማስተር ፕላን የቀሰቀሰው ተቃውሞ
ሌላው የዓመቱ አብይ ክስተት የአዲስ አበባና በኦሮሚያ ልዩ ዞን ስር የሚተዳደሩ ከተሞች የጋራ ማስተር ፕላን የተነሳ የተቀሰቀሰው ተቃውሞና ረብሻ ሲሆን የሰው ህይወትን ጨምሮ በርካታ ጉዳትና ውድመት ደርሷል፡፡
በአገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ የኦሮሚያ ተወላጅ ተማሪዎች በሚያዚያ ወር አጋማሽ ላይ ባስነሱት ተቃውሞ ሳቢያ ከፖሊስ ጋር ግጭት መፈጠሩ ይታወሳል፡፡
ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በአምቦ ከተማ በተፈጠረው ግጭት 30 የሚደርሱ ሰዎች መሞታቸውን ሲዘግቡ፣ የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በበኩላቸው፤ በአጠቃላይ የ11 ሰዎች ህይወት ማለፉን ዘግበዋል፡፡
ተቃውሞውን ለማስቆም በፀጥታ ሃይሎች ከተወሰደው እርምጃ ባሻገር ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ውዝግብ ባስነሳው የጋራ ማስተር ፕላን ዙሪያ ከተማሪዎችና ከህብረተሰቡ ጋር ለበርካታ ሳምንታት ውይይት እንዳደረጉም አይዘነጋም፡፡
“አስደንጋጩ” የጋዜጠኞችና ጦማሪያን እስር
መንግስት በሽብርተኝነት ጠርጥሬያቸዋለሁ በማለት  3 ጋዜጠኞችና 6 ጦማሪያን ማሰሩ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ትኩረት የሳበ ሌላው የዓመቱ ጉልህ ክስተት ነበር፡፡ አብዛኞቹ ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትም እስሩን ከመጪው አገራዊ ምርጫ ጋር በማያያዝ የመንግስት ፍርሃት የፈጠረው ጉዳይ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
በሚያዚያ ወር አጋማሽ ላይ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ፣ ኤዶም ካሳዬ፣ አስማማው ሃይለጊዮርጊስ እንዲሁም “ዞን 9” በተሰኘ ድረገጽ ፀሐፊነታቸው የሚታወቁት አጥናፉ ብርሃኔ፣ ማህሌት ፋንታሁን፣ ዘላለም ክብረት፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ በፈቃዱ ሃይሉና አቤል ዋበላ ተይዘው መታሰራቸው የሚታወስ ነው፡
መንግስት በተጠርጣሪዎቹ ላይ በሽብርተኝነት ከተፈረጁ ድርጅቶችና ተቋማት ጋር በመተሳሰር እንደሚሰሩ ደርሼበታለሁ በሚል ክስ የመሰረተባቸው ሲሆን ጉዳያቸው በፍ/ቤት በመታየት ላይ ይገኛል፡፡
የአቶ አንዳርጋቸው መያዝና የተቃዋሚ አመራሮች እስር
በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በአሸባሪነት ከተፈረጁት አምስት የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ የሆነው የ“ግንቦት 7” ዋና ፀሐፊ የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ በየመን መያዝና ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፎ መሰጠት የተጠናቀቀው አመት ያልተጠበቀ ክስተት ነበር፡፡ የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው አቶ አንዳርጋቸው፤ ቀደም ሲል በሌሉበት በተመሰረተባቸው የአሸባሪነት ክስ የሞት ፍርድ እንደተወሰነባቸው ይታወሳል፡፡
እኚህ የግንቦት 7 ከፍተኛ አመራር በኢትዮጵያ መታሰራቸውን ተከትሎ በተለያዩ የአሜሪካና አውሮፓ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በእንግሊዝ ኢምባሲዎች ደጃፍ ላይ በመሰባሰብ ተቃውሞ ማሰማታቸውን ቀጥለዋል - እንግሊዝ ዜግነት ለሰጠችው ሰው ተገቢውን ጥበቃና ከለላ አልሰጠችም በሚል፡፡
አንዳንዶች እንደሚሉት፤ የአቶ አንዳርጋቸው ጦስ ለአገር ውስጥ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችም ተርፏቸዋል፡፡ እሳቸው በታሰሩ ማግስት በሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሃብታሙ አያሌውና የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ም/ኃላፊ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ብሄራዊ ም/ቤት ም/ሰብሳቢ አቶ የሽዋስ አሰፋ እንዲሁም የአረና ፓርቲ አመራር አባል አቶ አብርሃ ደስታ በሽብር ተጠርጥረው የታሰሩ ሲሆን ጉዳያቸውም በፍ/ቤት እየታየ ነው፡፡
የግል የሚዲያ ተቋማት ክስ፤ የአሳታሚዎችና ጋዜጠኞች ስደት
መንግስት በ“ፋክት” ፣ “ሎሚ” ፣ “አዲስ ጉዳይ”፣ “እንቁ”፣ “ጃኖ” መፅሄት እና “አፍሮ ታይምስ” ጋዜጣ አሳታሚዎችና ባለቤቶች ላይ የወንጀል ክስ መመስረቱን በቴሌቪዥን የገለፀው  በሐምሌ ወር መጨረሻ ነበር፡፡ ከመግለጫው ጥቂት ሳምንት በኋላ ለፍ/ቤት የቀረበው የአሳታሚዎችና የስራ አስኪያጆቹ ክስ ጠቅለል ብሎ ሲታይ በተለያዩ የህትመት ውጤቶቻቸው በፃፏቸው ፅሁፎች በህገ-መንግስታዊ ስርአቱ ላይ አመፅ ቀስቅሰዋል፣ በሃሰት ወሬ ህዝብን በመንግስት ላይ የሚያነሳሱ ፅሁፎችን አትመዋል የሚል ሲሆን የፍ/ቤት ሂደቱም ቀጥሏል፡፡
የመንግስትን ክስ ተከትሎ ከ “ፋክት” መፅሄት አሳታሚ በስተቀር የሁሉም ተከሳሽ የሚዲያ ተቋማት ባለቤቶች ሃገር ለቀው የወጡ ሲሆን በአጠቃላይ 16 ያህል የግል ፕሬሱ አባላት አገር ለቀው ተሰደዋል፡፡ መንግስት በበኩሉ፤ በጋዜጠኞች ላይ የተመሰረተ ክስ ስለሌለ የተሰደደ አንድም ጋዜጠኛ የለም ብሏል፤ ጋዜጠኞቹ ለተሻለ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከአገር መውጣታቸውን በመጠቆም፡፡
“ብዙ የተባለለት የደሞዝ ጭማሪ”
ብዙ የተነገረለትና በጉጉት የተጠበቀው የመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪም የተደረገው በዚህ ዓመት ሐምሌ ወር ጀምሮ ነው፡፡ ጭማሪው ከፍተኛ ይሆናል በሚል ግምት ከፍተኛ የመነጋገሪ አጀንዳ ሆኖ የቆየው የደሞዝ ጭማሪው ብዙዎች እንደጠበቁት ግን አልሆነም፡፡ ጭማሪው ከ33 እስከ 46 በመቶ ብቻ ነበር፡፡ ጭማሪውን ተከትሎም ነጋዴው በመሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋ ላይ ጭማሪ እንዳያደርግ መንግስት ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ቆይቷል፤ ማስጠንቀቂያውን የጣሱ “ህገወጥ” ነጋዴዎች ላይም እርምጃ መወሰዱን መንግስት አስታውቋል፡፡
“ዓለምን ያስደነገጠው ኢቦላ”
በምዕራብ አፍሪካ አገራት ተከስቶ ወደሌሎች የአፍሪካ አገራት የተስፋፋው ኢቦላ፤ መላውን ዓለም ድንጋጤ ውስጥ የከተተው በዚሁ ዓመት ላይ መገባደጃ ላይ ሲሆን አሁንም ስጋት እንደሆነ ቀጥሏል፡፡  
ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት (WHO) ከትላንት በስቲያ ይፋ ባደረገው መረጃ፤ ቫይረሱ በተከሰተባቸው የአፍሪካ አገራት 2ሺ ገደማ ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸውን አስታውቋል፡፡
 ኢትዮጵያም የዚህ ቫይረስ ተጠቂ እንዳትሆን ከወዲሁ ለመከላከል የተለያዩ የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን መንግስት አስታውቋል፡፡ ቦሌ አየር መንገድን ጨምሮ በተለያዩ የድንበር አካባቢዎች ጊዜያዊ የምርመራ ጣቢያዎች የተቋቋሙ ሲሆን በአዲስ አበባም 50 አልጋዎች ያሉት ልዩ ሆስፒታል መዘጋጀቱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡


Read 8859 times