Saturday, 30 August 2014 11:17

ቢዚ ሲግናል ያቀነቀነበትን የሙዚቃ ድግስ 12 ሺ ሰው ታድሞታል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)
  •  ከትኬት ሽያጭ ቢያንስ 5 ሚሊዮን ብር እንደተገኘ ተገምቷል *
  • “ኮንሰርት” የሚወዱ “የእጅ አመለኞች” አስቸግረው ነበር

ከወራት በፊት ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው “ሬጌ ዳንሶል ኢን ኢትዮጵያ ቁጥር 1” የሙዚቃ ኮንሰርት የተሰረዘው ከቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ጋር በመገጣጠሙ እንደነበር አዘጋጁ “አውሮራ ኤቨንት ኦርጋናይዘርስ” መግለጹ ይታወሳል፡፡ የኮንሰርቱ ተጋባዥ ከያኒ ጃማይካዊው ቢዚ ሲግናል ለሸገር ሬዲዮ በሰጠው ቃለምልልስ ደግሞ፤ “ኮንሰርቱ የተሰረዘው በተለያዩ ምክንያቶች በተከሰቱ መዘግየቶች ነው” ብሎ ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ “ለሁሉም ጊዜ አለው” እንዲሉ፣ ኮንሰርቱ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በሚሊኒየም አዳራሽ በርካታ ታዳሚያን በተገኙበት ተካሂዷል፡፡ የምሽቱ ድባብ ከምሽቱ 2፡00 ላይ የተጀመረው የሙዚቃ ኮንሰርቱ፤ በአገራችን የሬጌ ሙዚቃ አቀንቃኞችና በዲጄ እየተሟሟቀ የዘለቀ ሲሆን ራስ ጃኒ፣ ሲዲኒ ሳልመን፣ ጃሉድ አወል፣ ሃይሌ ሩትስ እና ጆኒ ራጋ ማራኪ ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡

በየመሃሉ በዲጄ ባባ ትንፋሽ እያገኙ መድረኩን ያደመቁት ኢትዮጵያዊ ድምፃዊያን፤ በታዳሚው ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን አግኝተዋል፡፡ መድረኩ በጥሩ ሁኔታ ተዘጋጅቷል፤ የላይትና የድምፁ ቅንብር እንከን የለሽ ነበር፡፡ ኮንሰርቱ ተጀምሮ እስከሚያልቅ አንድም የድምፅ መቆራረጥና መረበሽ አላጋጠመም፡፡ ድምፃዊያኑ ለኮንሰርቱ በቂ ዝግጅት ለማድረጋቸው በመድረክ ያሳዩት ጥንካሬና ብቃት ምስክር ነው፡፡ ራስ ጃኒ የምሽቱ ምርጥ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ጃሉድ “የገጠር ልጅ ነኝ”፣ “አሻበል ያሆ”፣ የእርግብ አሞራ እና ሌሎችንም ስራዎቹን በጥሩ ሁኔታ በመጫወት ታዳሚውን የማረከ ሲሆን ሃይሌ ሩትስ በበኩሉ፤ “ባዶ ነበር”፣ “እርጅና መጣና” በተሰኙ ታዋቂ ዘፈኖቹ ተመልካቹን አዝናንቷል፡፡ ጆኒ ራጋም አነቃቂ ምሽት ለመፍጠር ችሏል፡፡ ጆኒ ራጋና ሃይሌ ሩትስ በጋራ ተቀናጅተው ያቀረቡት ሥራም ልዩ አድናቆት የተቸረው ነበር፡፡ በየመሃሉ ዲጄ ባባ መድረኩን በሙዚቃ እያደመቀ፣ አርቲስቶቹም ትንፋሽ እየሰበሰቡ፣ ታዳሚውም ልቡ እስኪወልቅ እየጨፈረና እየዘለለ ጊዜው ወደ አምስት ሰዓት ነጐደ፡፡

የዕለቱ “ሰርፕራይዝ” መድረኩን በጥሩ ሁኔታ በመምራት የተሳካለት ጋዜጠኛ አንዷለም ተስፋዬ፤ በኮንሰርቱ መጀመሪያ ላይ “ሰርፕራይዝ” እንዳለ በመግለጽ የታዳሚውን ልብ አንጠልጥሎት ነበር፡፡ እናም የመድረኩ መብራት ደብዝዞ፤አይን የማያጨልም ድባብ ተፈጠረ፡፡ ሰፋፊ ኮፍያ ያደረጉ ሰዎች ደንገዝገዝ ባለው ድባብ ውስጥ እየሮጡ ወደ መድረኩ በመግባት ቦታ ቦታቸውን ያዙ፡፡ ታዳሚው ለ“ሰርፕራይዙ” ጓጉቶ ነበር፡፡ የመድረኩ መብራት ፏ ብሎ በራ፡፡ “ሰርፕራይዟ” ዘፋኝ፤ ነጭ ብልጭልጭ ቲ-ሸርትና ነጭ ቁምጣ ለብሳ ብቅ አለች፡፡ ጭብጨባና ፉጨቱ ቀለጠ፡፡ ድምጻዊት ቤቲ ጂ. “ከአንተ አይበልጥም” የሚለው ዘፈኗን በዳንስ ቡድኗ ታጅባ፣ አብራ እየተውረገረገች አስነካችው፡፡ እየዘፈነችና እየጨፈረች ታዳሚውን አስጨፈረችው፡፡ ሁለተኛ ዘፈኗም ቀጠለ፡፡ በጣም ግሩም አቀራረብ ነበር ያሳየችው፡፡ ሥራዋን ጨርሳ ከመድረክ ስትወርድም በህዝቡ አድናቆትና ሆታ ተሸኝታለች፡፡ የታዳሚውን ልብ የነካ ስራ “እኔ የፕሮግራሙ አዘጋጅ ሆኜ እንኳን አላወቅሁም፤ በጣም የተገረምኩበትና የተደነቅሁበት ጉዳይ ነው” ይላል፤የ“አውሮራ ኤቨንትስ ኦርጋናይዘርስ” ዋና ስራ አስኪያጅ ሸዊት ቢተው፡፡ ቤቲ ጂ.፣ ጃሉድ አወል፣ ሃይሌ ሩትስ እና አንድ ፊቱ አዲስ የሆነ አርቲስት ወደ መድረክ ወጡና ማንም ያልጠበቀውን ዘፈን መዝፈን ጀመሩ፡ “ነገን ላያት እጓጓለሁ” በማለት፡፡

ይሄን ጊዜ ታዳሚው መጮህ፣ ማልቀስና ማፏጨት ያዘ፡፡ በድንገተኛው ዘፈን አዳራሹ ተደበላለቀ፡፡ ከአመት በፊት በድንገት ህይወቱ ያለፈውን የሬጌውን አቀንቃኝ ድምፃዊ ኢዮብ መኮንን ለመዘከር ታስቦ የቀረበው ሙዚቃ የመላ ታዳሚውን ልብ የነካ ነበር፡፡ በመሃል “ወይኔ እዮቤ ውውው…” በማለት ጩኸቷን ያቀለጠችው አንዲት ወጣት ታዳሚ፤እንባዋ በጉንጯ እየወረደ ደረቷን መድቃት ጀመረች፡፡ ጓደኞቿ ተረጋጊ እያሉ ቢያፅናኗትም አልቻለችም፡፡ “እዮቤን በጣም ነው የማደንቀው፤ አሟሟቱም በጣም ያሳዝናል” እያለች ማልቀሷን ቀጠለች፡፡ የብዙሃኑ ታዳሚ ጩኸት፤ ፉጨትና ዝላይማ በቃላት ለመግለጽ አዳጋች ነው፡፡ “ነገን ላያት እጓጓለሁ” ቀጠለ፡፡ አርቲስቶቹ በጣም ያምሩ ነበር፤የሙያ አጋራቸውን የዘከሩበት መንገድም አንጀት ይበላል፡፡ “ይህንን ሃሳብ ያፈለቁት ዝግጅቱን ከእኛ ጋር በአጋርነት የሰሩት የሲግማ ኢንተርቴይንመንት የስራ ባልደረባ ብሩክ እና የአውሮራ ማኔጅመንት አባል ዳዊት ናቸው” ይላል ሸዊት፡፡

ያረፈደው የክብር እንግዳ እኩለ ሌሊት አለፈ፡፡ የእለቱ የክብር እንግዳ ብቅ አላለም፡፡ ዲጄ ባባ የመሸጋገሪያውን ሙዚቃ እያጫወተ 7፡45 ሆነ፡፡ የመድረኩ አጋፋሪ አንዷለም ተስፋዬ ብቅ አለ፡፡ “አሁን በጉጉት የምትጠብቁት እንቁ ድምፃዊ ቢዚ ሲግናል ወደ መድረክ ይመጣል” ሲል አዳራሹ በጩኸት ተሞላ፡፡ ከስንት ጥበቃ እና ጉጉት በኋላ ቢዚ ሲግናል ወደ መድረክ ሲመጣ አዳራሹ ይበልጥ ተናጋ፡፡ ዳልቻ ኮት በነጭ ሸሚዝና ጠቆር ባለ ግራጫ ሱሪ ያደረገው ቢዚ ሲግናል፤ ነጭ ፍሬም ያለው ጥቁር መነፅር ፊቱ ላይ ሰክቶ ለታዳሚው ሰላምታ ሰጠ፡፡ የእሱን ዘፈን ለመስማት ዝግጁ መሆን አለመሆናችንን ጠየቀ፤ “Are you feeling good?” (በጥሩ ስሜት ውስጥ ናችሁ እንደማለት) ታዳሚው በፉጨት እና በጭብጨባ ምላሽ ሰጠ፡፡ በዚህ ምሽት ከዚህ ውብ ህዝብ ጋር በመገናኘቱ የተሰማውን ደስታ አርቲስቱ ገለፀ፡፡ በግምት በ20ዎቹ አጋማሽ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ቢዚ ሲግናል፤ እንደብዙዎቹ የሬጌ ሙዚቀኞች ፀጉሩ ድሬድ አይደለም፡፡

ምንም እንኳ በዘፋኝነት ይበልጥ የታወቀው “One more night” የተሰኘውን የፊል ኮሊንሰን ቀደምት ስራ ሪሚክስ አድርጎ ከተጫወተ በኋላ ቢሆንም በርካታ የራሱን ስራዎችም አበርክቷል፡፡ ቢዚ ሲግናል ወደ መድረክ የመጣው ታዳሚው በጭፈራ ጉልበቱን ከጨረሰ በኋላ ነበር፡፡ በየመሃሉ “ቢዩቲፉል ሌዲስ” እያለ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን በማድነቅ ማቀንቀኑን ቀጠለ፡፡ አጠገቤ የነበሩ በቡድን የታደሙ ሰዎች “በቃ ያቺን ዋን ሞር ናይት ይዝፈናትና እንሂድ” ሲሉ ሰማኋቸው፡፡ እርሱ ግን አውቆም ይሁን ሳያውቅ ዘፈኗን ወደ መጨረሻ ላይ አደረጋት፡፡ ሲግናል እስከ ሌሊቱ 9፡41 ድረስ መድረክ ላይ ነበር፡፡ ታዳሚው ግን ከቢዚ ሲግናል ይልቅ በኢትዮጵያዊያን አርቲስቶች ይበልጥ መደሰቱን ታዝቤአለሁ፡፡ የኮንሰርቱ አንዳንድ እንከኖች በምሽቱ ድራፍትና ሃሺሽ እኩል ሲጠጡ አመሹ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ሀሺሽ በየደቂቃውና በየቅርብ ርቀቱ ይጨሳል፤ እንደጉድ ይጦዛል፡፡ ለሽታው ባዕድ የሆነ ያጥወለውለዋል፡፡ ያስመለሳቸውም ነበሩ፡፡ አጠገቤ የነበረ አንድ ታዋቂ አርቲስት፣ ሃሺሽ ከሚያጨስ አንድ ወጣት ጋር አንገት ለአንገት ሲተናነቅ አይቻለሁ- “ሌላ ቦታ ሄደህ አጭስ” በሚል፡፡ በርካታ ኪስ አውላቂዎችም (ሌቦች) አሰላለፋቸውን አሳምረው ነበር፡፡

ቦርሳዎች፣ ሞባይል ስልኮች፣ የኪስ ቦርሳዎችና ሌሎች ንብረቶች ለመንታፊዎች ሲሳይ ሆነው አምሽተዋል፡፡ አንድ የውጭ ዜጋ “ዋሌቴን ተሰርቄአለሁ፤ ውስጡ ፓስፖርት አለው፤ እባካችሁ እዚሁ እንዳልቀር ፓስፖርቱን እንኳን መልሱልኝ” የሚል መልዕክት በመድረክ አጋፋሪው አስነግሯል፡፡ ባለረጃጅም ተረከዝ ጫማዎችን የተጫሙ ሴቶች እግራቸውን ሲደክማቸው ጫማቸውንና ቦርሳቸውን መሬት ቁጭ አድርገው ሲጨፍሩ የሌባ ሰለባ ሆነዋል፡፡ አንዲት ወጣት “ሌላው ቢቀር ጫማዬን እንኳን ባገኝ---” በማለት እንባዋ እንደጎርፍ እየፈሰሰ፣በታዳሚው ስር በመሽሎክሎክ ጫማዋን ስትፈልግ አስተውያለሁ፡፡ የ“አውሮራ ኤቨንትስ ኦርጋናይዘርስ” ዋና ሥራ አስኪያጅ ሸዊት ቢተው ስለስርቆቱ ጠይቀነው ሲመልስ፤ “የእኛ ኮንሰርት የመጀመሪያ ከማይመስልባቸውና ከሚለይባቸው ጉዳዮች መካከል በምሽቱ ከካራማራ ፖሊስ ጋር በመተባበር አዳራሽ ውስጥ ሆነው የሰው ንብረት የሰረቁ ሌቦችን ይዘን ሞባይል፣ ቦርሳ፣ ፓስፖርትና ሌሎች ንብረቶችን ለባለቤቶቹ ማስመለሳችን ነው” ብሏል፡፡ ከተሰረቁት እቃዎች አብዛኞቹ ለባለቤቶቹ እንደተመለሱና አንድ ሁለት ሰዎች ብቻ እቃቸውን ማግኘት እንዳልቻሉ ሸዊት ተናግሯል፡፡ ኮንሰርቱን ከ10 እስከ 12ሺህ የሚደርሱ ሰዎች እንደታደሙት ከዚህም ውስጥ 2ሺህ ያህሉ በተጋባዥነት እንደገቡ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከትኬት ገቢም ቢያንስ 5 ሚሊዮን ብር ገደማ እንደተገኘ ተገምቷል፡፡

Read 2345 times