Saturday, 30 August 2014 10:55

የኢትዮጵያ ስኬታማ ሴቶችን ታሪክ ያዘጋጀችው አሜሪካዊት

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ሜሪ ጄን ዋግል ትባላለች፡፡ አሜሪካዊት ናት፡፡ በሙያዋ የከተማ ፕላን አውጪ (Urban planner) ብትሆንም በ2013 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መጥታ ላለፉት ሶስት ዓመታት ገደማ የስኬታማ ኢትዮጵያዊያን ሴቶችን ታሪክ የሚዘክር መፅሃፍ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ስታዘጋጅ ቆይታለች፡፡ በመጪው መስከረም ወር መጨረሻ ላይ በእንግሊዝኛና በአማርኛ ቋንቋ የተዘጋጁት የ64 ስኬታማ ሴቶችን ታሪክ የያዙ መፅሀፍት ለንባብ የሚበቁ ሲሆን መፃሕፍቱ  ታዳጊ ሴቶች ላይ አተኩረው ለሚሰሩ የስልጠና ማዕከላትና ት/ቤቶች በነፃ ይሰራጫል ተብሏል፡፡ የአዲስ አድማስ ከፍተኛ ሪፖርተር አለማየሁ አንበሴ “ተምሳፀለት  የተሰኘው መፅሃፍ ጠንሳሽና አዘጋጅ ከሆነችው ሜሪ - ጄን ዋግል ጋር በመፅሃፉ ዙሪያ ያደረገው ቃለምልልስ እንዲህ ቀርቧል፡፡

          የስኬታማ ኢትዮጵያዊያን ሴቶችን አጭር የህይወት ታሪክ የሚዘግብ መፅሀፍ ማዘጋጀትሽን ሰምቻለሁ፡፡ መፅሃፉን ለማዘጋጀት ምን አነሳሳሽ? እስቲ ስለመፅሃፉ ጠቅለል አድርገሽ ንገሪኝ…
ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ም ነው፡፡ አመጣጤም ከትውልድ ሃገሬ ውጪ ያሉኝን ልምዶች ለማካበት ነበር፡፡ በአጋጣሚ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ጥምረት ፕሬዚዳንት ከሆኑት ወ/ሮ ሳባ ገ/መድህን ጋር የሃገሪቱ ሴቶች ላይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተፃፉ መፅሃፎችን ማፈላለግ ጀመርኩ፡፡ ነገር ግን እንዳሰብኩት ላገኝ አልቻልኩም፡፡ በወ/ሮ መአዛ አሸናፊ የተፃፈው የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎን የሚተርክ መፅሃፍ ብቻ ነው ላገኝ የቻልኩት፡፡ ከዚህ ቀደም በሌሎች የአፍሪካ ሃገሮች በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተፃፉ የታላላቅ ሴቶችን ታሪክ አግኝቻለሁ፡፡ የኢትዮጵያዊያንን ስኬታማ ሴቶች የሚዘክር መፅሃፍ ግን ላገኝ አልቻልኩም፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተደራጀ መፅሃፍ ማዘጋጀት ቢቻል፣ የሃገሪቱ ታዳጊ ወጣት ሴቶች የቀደሙትን ሴቶች ታሪክና ልምድ እንዲሁም ጥንካሬ በሚገባ ተረድተው እንዲያድጉ ማድረግ ይቻላል በሚል መፅሃፉን ለማዘጋጀት ወሰንኩ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ወ/ሮ ሳባን ሳማክራት በጣም ተደሰተች፡፡ መፅሃፉ ጠቃሚ ነው ቀጥይበት አለችኝ፡፡
በዚህ መልኩ ስለውጤታማ ሴቶች መረጃዎች ማሰባሰብ ጀመርኩ፡፡ አብዛኞቹ ታሪኮች በጋዜጣና በመፅሄቶች ተበታትነው የሚገኙ ከመሆናቸውም በላይ ያልተሟሉ ናቸው፡፡ የተወሰኑ የአዲስ አበባ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን መርጠን መረጃዎችን በመፈለግ እንዲረዱን ጠየቅን፡፡ እነሱም ትብብራቸውን አልነፈጉንም፡፡ የታሪኩ ባለቤቶችና ቤተሰቦቻቸውን አፈላልጎ በማግኘት፣ ቃለመጠይቆችን ማድረግ፣ በእነሱ ዙሪያ የተፃፉትን ዘገባዎች ማሰባሰብና ሌሎችንም የስራው ሂደቶች አብረን ተወጥተናል፡፡ ሁሉም ሲያገለግሉ የነበረው በበጎ ፈቃደኝነት ነበር፡፡
በዝግጅቱ ወቅት ቃለመጠይቅ የተደረገላቸው ባለታሪኮች ራሳቸው ቃለ መጠይቃቸውን በራሳቸው ቋንቋ አርመው እንዲመልሱልን አድርገናል፡፡ ከ300 በላይ ሴቶች ነበሩ የተመረጡት፤  ከዚያ ውስጥ ነው ወደ 64 የሚሆኑት ተመርጠው በመፅሃፉ የተካተቱት፤ ነገር ግን የሁሉም ታሪክ ለታዳጊ ሴቶች የሚያጋራው የራሱ ነገር አለው፡፡ ለዚህ ሲባል በድረገፃችን ላይ የሁሉንም ሴቶች ታሪክ አስፍረናል፡፡
ፎቶግራፎችን በተመለከተም ታዋቂዋ ፎቶግራፍ አይዳ ሙሉነህ እንድታነሳ አድርገናል፡፡ ለሁለት አመት ገደማ የእነዚህን ባለታሪኮች ፎቶግራፍ ስታሰባስብና በስራ ላይ እያሉ ስታነሳ ቆይታለች፡፡ ፎቶግራፎቹ አለማቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁና ጥራት ያላቸው ናቸው፡፡ የታተመውም በአሜሪካን ሃገር ሎሳንጀለስ በሚገኘው ፀሃይ ፕሬስ ማተሚያ ቤት ነው፡፡
በመፅሃፉ የተካተቱት ባለታሪኮች እንዴት ነው የተመረጡት?
በመፅሃፉ የተካተቱ ባለታሪኮችን ስንመርጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገናል፡፡ ሴቶቹ ከተለያዩ የስራ ዘርፎች የተመረጡ ናቸው፡፡ ገበሬ ከሆኑት ጀምሮ የህዝብ መሪ እስከሆኑት ሴቶች ድረስ በጥልቀት ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡ የመጀመሪያዋ አውሮፕላን አብራሪ ሴት፣ የኮንስትራክሽን ክሬን ባለሙያ፣ አርቲስት፣ ሃኪም አምባሳደር… የመሳሰሉት በመፅሀፉ ተካተዋል፡፡ ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች ለመምረጥ ተችሏል፣ ከኪነ- ጥበብ፣ ከማህበራዊ እንቅስቃሴዎች፣ ከህዝብና የመንግስት ሰራተኞች፣ ከመገናኛ ብዙሃን፣ በቢዝነስ ስኬታማ ከሆኑት፣ ከህክምና ሌሎችም የተመረጡ ናቸው፡፡ ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ እንዲሆኑም ጥረት ተደርጓል፡፡ 64 ሴቶችን ብቻ ስንመርጥ በሃገሪቱ ስኬታማ እነዚህ ብቻ ናቸው ማለታችን አይደለም፡፡ የግዴታ መምረጥ ስላለብንና ማሳያ ይሆናሉ ብለን ስላሰብን እንጂ፡፡ የ300ዎቹን ሴቶች ታሪክ በሙሉ በመፅሃፉ ባናካትትም ድረገፃችን ላይ ታሪካቸው እንዲቀመጥ አድርገናል፡፡ ለወደፊት ታሪካቸው  በሌላ መፅሃፍ ታትሞ ሊወጣ ይችል ይሆናል፡፡ የ64 ሴቶች ታሪክ የያዘው ይህ አዲስ መፅሀፍ ግን የአዲስ ዓመት ስጦታ ይሆናል፡፡
የመፅሃፉ ፋይዳ ምንድን ነው? የትኛውን የህብረተሰብ ክፍልስ ያለመ ነው?
መጀመሪያ መፅሀፉ ታሳቢ የሚያደርገው ታዳጊ ሴቶችን ነው፡፡ እነዚህ ታዳጊዎች ለወደፊት የህይወት አቅጣጫቸውን ለመወሰንና በጥንካሬ ለመጓዝ ባለታሪኮቹ ምሳሌ ይሆኗቸዋል፡፡ ብዙውን ጊዜ የሚታሰበው ሴቶች ትምህርት ተማሩም አልተማሩም የሆነ እድሜ ላይ ሲደርሱ ባል ማግባት እንዳለባቸው ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ወይ የቤት እመቤት ይሆናሉ አሊያም ባሎቻቸውን በስራ የማገዝ ኃላፊነት ይሸከማሉ፡፡ ትልቅ ደረጃ ስለመድረስ አይታሰባቸውም፡፡ ነገር ግን የእነዚህ ሴቶች የህይወት ተሞክሮ ስኬታማ መሆን እንደሚቻል ለታዳጊዎች በሚገባ ያስተምራል፡፡ ማድረግ የሚፈልጉትን ለማድረግ ምንም የሚሳናቸው ነገር እንደሌለ የባለታሪኮቹ ታሪክ ለታዳጊዎቹ ያሳያል፡፡
በመፅሀፉ ዝግጅት ወቅት ፈታኝ የነበሩ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
አንዱ ትልቁ ፈተና የነበረው ሴቶቹን ማግኘት ነው፡፡ አንዳንዶቹ ታሪካቸውን ለመናገር አይደፍሩም፤ እንደውም የአንዷን ሴት ታሪክ ለማግኘት 3 ጊዜ ያህል መመላለስ ግድ ሆኖብን ነበር፡፡ የኢንተርኔት፣ የስልክ ችግሮችም ነበሩ፡፡ ሴቶቹን እንደልብ ማግኘት አንችልም ነበር፡፡ ታሪኮቹን ማረምም የራሱን ሰፊ ጊዜ ወስዷል፡፡ በመፅሃፉ ዝግጅት ላይ የተሳተፉትን ሰዎች ጊዜ ከተገቢው በላይ የተሻማ መፅሀፍ ነው፡፡ የተሰባሰቡትን መረጃዎች በፅሁፍ፣ በፎቶግራፍ፣ በዲዛይን ማቀናበር በራሱ አስቸጋሪና ጊዜ የወሰደ ነበር፡፡ ነገር ግን በበጎ ፈቃደኝነት የተሳተፉ ተማሪዎችን ጨምሮ የፎቶግራፍ እና ዲዛይን ስራውን የከወኑት ባለሙያዎች ለስራቸው ታማኝ በመሆናቸው ውጤታማ መሆን ተችሏል፡፡
መፅሃፉን ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ  መተርጎም በራሱ ከባድ ነበር፡፡ የትርጉም ስራውን የሰራው ኢዮብ ካሣ እና የፊደል ለቀማ (Proof readeing) የሰሩት ሰዎች እጅግ የሚደንቅ ስራ ሰርተዋል፡፡ ከእነዚህ ሰዎች ጋር በመስራቴ ኩራት ይሰማኛል፡፡
የገንዘብ ድጋፍ ያደረገው ማን ነው?
በአብዛኛው የመፅሃፉ ዝግጅት የተሰራው በበጎ ፍቃደኞች እገዛ ነው፡፡ መፅሃፉ ለንባብ ሲበቃ ለሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች፣ ለቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛዎችና ለመሳሰሉት የትምህርት ተቋማት በነጻ ነው የሚሰራጨው፡፡ በመፅሃፉ ዝግጅት ወቅት 13 ያህል ተቋማት ትብብር አድርገውልናል፤ ድጋፋቸውንም ቸረውናል፡፡ የስዊድን መንግስት፣ ኮካኮላ ኩባንያ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሴቶች ጉዳይ፣ የእንግሊዝ አለማቀፍ የልማት ተቋም (DFIO)፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የፈረንሳይ ኤምባሲ፣ የአሜሪካ ኤምባሲ፣ አይፓስ ኢትዮጵያ፣ ዴቪዲና ሉሲ አለማቀፍ ፋውንዴሽን፣ ፓዌ ኢትዮጵያ፣ አይርሽ ኤይድ የተለያዩ ድጋፎችን አድርገውልናል፡፡ መፅሀፉ ታዳጊ ሴቶችን በተለያዩ ሙያዎች ለሚያሰለጥኑ የትምህርት ተቋማት በነፃ እንዲበረከት የእነዚህ ተቋማት ድጋፍ ወሳኝ ሚና አለው፡፡
መፅሀፉ መቼ ነው አንባቢያን እጅ የሚደርሰው?
የመጀመሪያው የመፅሃፉ ህትመት ለሽያጭ አይቀርብም፡፡ እንዳልኩህ በነፃ ነው የሚታደለው፡፡ በቀጣይ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ጥምረት የእንግሊዝኛና የአማርኛ ትርጉም መፅሃፉን ይፋ ሲያደርግ ምናልባት ለሽያጭ ሊቀርብ ይችላል፡፡ የዚህ መፅሃፍ ምረቃ የሚካሄደው መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም ነው፡፡ የምረቃ ቦታውም በብሄራዊ ሙዚየም ይሆናል፡፡ የፎቶግራፍ ባለሙያዋ አይዳ ሙሉነህ ያነሳቻቸው ፎቶዎችም በኤግዚቢሽን መልክ ይቀርባሉ፡፡ በሌሎች ሃገሮች ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ላይ ሰርተሽ ታውቂያለሽ?
አይ! በሌላ ሃገር እንዲህ አይነት ስራ ላይ ተሳትፌ አላውቅም፡፡ በሙያዬ የከተማ ፕላን አውጭ ነኝ፡፡ በአሜሪካ በቤቶች ልማት ላይ  ሰርቻለሁ፡፡ በመፅሃፍ ዝግጅት ደረጃ የአሁኑ የመጀመሪያዬ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የነበረሽን ቆይታ እንዴት ትገልጭዋለሽ?
ኢትዮጵያን በጣም ወድጃታለሁ፡፡ አስደናቂና ውብ ሃገር ነች፡፡ ባህሉ ጥልቅ ነው፣ በቤተሰብና በሃይማኖት ዙሪያ ማዕከል ያደረገ ትስስሮሽና ባህል አላችሁ፡፡ ሰው አሜሪካ በበጎ ፍቃደኝነት አገልግሎት የተሻለች ናት ሲል እሰማለሁ፤ እኔ ግን እዚህም የበጎ ፍቃደኝነት አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ቁርጠኝነት እንዳለ በሚገባ አይቻለሁ፡፡ የሃገሬውን ምግቦችም ወድጃቸዋለሁ፤ ሽሮ ወጥ በጣም ነው የምወደው፡፡ ማኪያቶው ደግሞ የትም ሃገር የማይገኝ ልዩ ጣዕም ያለው ነው፡፡
ቀጣይ እቅድሽ ምንድን ነው?
መፅሀፉ ከተመረቀ በኋላ ወደ አሜሪካ እመለሳለሁ፡፡ መኖሪያ ቤቴ ሎስ አንጀለስ ነው፡፡ በሎስ አንጀለስ መደበኛ ስራዬን እቀጥላለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ በኢትዮጵያ የሰራሁትን ፕሮጀክት እዚያም ለመስራት እቅድ አለኝ፡፡
ስለቤተሰብሽ ሁኔታ ልትነግሪኝ ትችያለሽ?
አግብቼ ሶስት ልጆች ወልጄ ፈትቻለሁ፡፡ ሶስት ቆንጆ ሴት ልጆች አሉኝ፡፡ ሁሉም በተለያየ ቦታ ነው የሚኖሩት፡፡ አንዷ ህንድ፣ ሌላዋ ሎስአንጀለስ፣ አንዷ ደግሞ ኒውዮርክ ነው የምትኖረው፡፡ አያትም ሆኛለሁ፤ በህንድ ሁለት የልጅ ልጆች አሉኝ፡፡ ለ5 ዓመት በህንድ ኖሬያለሁ፣ ይሄ ደግሞ የተለያዩ ባህሎችን ለማወቅ አግዞኛል፡፡ ወደ ትምህርት ሁኔታ ስመጣ በከተማ ፕላን ሁለተኛ ዲግሪ አለኝ፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪ በመንግስት አስተዳደር ወስጃለሁ፡፡  በተማርኩባቸው የሙያ መስኮች በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎችም ሃገሬን አገልግያለሁ፤ በማገልገል ላይም እገኛለሁ፡፡

Read 10554 times