Print this page
Saturday, 30 August 2014 10:52

“በትጥቅ ትግሉ የታጋዮችን ልብስ እሰፋ ነበር”

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(2 votes)

           ከተማዋ “ፋጥግዚ” ነበር የምትባለው፡፡ አንበሳና ነብር የሚውልባት ዱር ጫካ ነበረች፡፡ እጅግም ታስፈራ ነበር፡፡ ልጆች ሳለን ከብት አግደን፣ አደን አድነን፣ ገበሬዎች ሆነን አድገንባታል፡፡
አሁን ግን ከተራራ እና ድንጋይ በቀር ጫካና ሸለቆ አላየሁም
ጥንት እኮ ነው የምልሽ..አሁንማ መሬቱም አረጀ መሰለኝ.. ድንጋዩም ቆላውም በረታ፡፡ በጦርነትና በድርቅ  እጅግ ተጎድቷል፡፡ ኢትዮጵያን ካቀኑዋት ሶስቱ ቀደምት ህዝቦች መካከል አንዷ ሰቆጣ ስትሆን ሌሎቹ አክሱምና ጎንደር ናቸው፡፡ ባህላችን፣ ታሪካዊ ቅርሶቻችንና ቋንቋችን የከተማዋን ጥንታዊነት ያሳያሉ፡፡
ያኔ ሰዎች ከስፍራ ስፍራ ሲንቀሳቀሱ በዘራፊዎች ንብረታቸውን ይቀሙ ስለነበረ፣ ገንዘባቸውንና  ወርቃቸውን ዙሪያ ገቡን በምታይው ተራራና ድንጋያማ ስፍራ ይደብቁ ወይንም ይሸጉጡ ነበር፡፡ ሰቆጣ የሚለው የመጣው “ገንዘቡን ሸሸገ..ሸጎጠ..ሰቆጠ..” ከሚለው ሲሆን ከተማዋም “ሰቆጣ” ተባለች፡፡
የዋግኽምራ ዋና ከተማ ከሆነችው ሰቆጣ በ5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውንና በአጼ ካሌብ ዘመነ መንግስት ከአንድ አለት ተፈልፍሎ የተሰራውን የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያን በአምስት መቶ ዓመት የሚበልጠው ውቅር መስቀለ ክርስቶስ፤ የስፍራውን ጥንታዊነት ያሳያል፡፡ በህንጻው ጣሪያ ላይ የላቲንና የግሪክ የሚመስሉ ጥንታዊነት ያላቸው መስቀሎች ሲኖሩት የእብራይስጥ ቋንቋ ጽሑፎችም አሉት፡፡ ከህንጻው ስር መሬት ለመሬት እስከ ውቅር ላሊበላ ድረስ የሚወስድ መንገድ አለው፡፡ (ውቅር መስቀለ ክርስቶስን በጎበኘሁበት ወቅት የደብሩ አለቃ፤ በአንድ ወቅት አንድ የውጭ አገር ዜጋ ኦክስጅንና መብራት ይዞ በውስጥ ለውስጥ ዋሻው ለ20 ደቂቃ ከተጓዘ በኋላ አየር አጠረኝ ብሎ መመለሱን የነገሩኝ ሲሆን ዋሻው ከሰቆጣ ከተማ 128 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት ጋር  እንደሚያገናኝ ገልፀውልኛል፡፡)፡፡ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ የዋግ ሹሞች ቅሪተ አካላት ይገኛሉ፡፡
በህገ ኦሪት (ከክርስቶስ ልደት በፊት) ጊዜ እንደተሰሩ የሚነገርላቸው የሰላምጌ ማሪያም፤ የደብረ ጸሐይ ወይብላ ማርያምና የመሳሰሉት አድባራት በዚሁ አካባቢ ነው የሚገኙት፡፡ ህዝብና አካባቡው አሁን ላለው መንግስት (ኢህአዴግ) ባለውለታ ናቸው ይባላል..
ደርግን ለመንቀል እንቅስቃሴ ሲደረግ አሮጌው፣ ቆንጆው፣ ውርጋጡ…  በዓል ነው፣ አዘቦት ነው ሳይል ወፍጮ ፈጭቶ፣ ጋግሮ፤ ስንቅ ቋጥሮ፣ ከዱር ያሉ ልጆች እንዳይርባቸው እንዳይጠማቸው አድርጎ ነው ለዛሬ ወግ ማዕረግ ያበቃቸው፡፡ አይደለም ህዝቡ የአካባቢው ተፈጥሮም ለእነሱ ባለውለታ ነው፡፡ ልጄዋ! ይሄ አካባቢማ “ራበኝ፣ ጠማኝ” ሳይል ነው የኖረ፡፡
 ደሞስ ካልሽስ… ከእኛ የወጡ አይደሉ ታጋዮችስ ብትይ፡፡ ጨቃኙ ደርግ እነሱን “ሸሽጋችኋል” ብሎ አስራ አንድ ጊዜ በጀት ደብድቦናል፡፡ ቀን በዱር ውሎ፣ ማታ  ወደ ከተማ መጥቶ፣ ለሊት ገበያ ወጥቶ… የዛሬዎችን አመራሮች አሳድጎበታል፡፡
እርስዎ ያኔ ምን ይሰሩ ነበር?
የደርግ ታጣቂ ሆኜ ሳገለግል ወያኔዎቹ ይዘው አስረውኝ ነበር፡፡ በጫካ በእስር ላይ ሳለሁ ልብስ ሰፊ ነበርኩ፤ ክላሽ መያዣ ሳይቀር ትጥቃቸውን እኔ ነበርኩ የምሰፋላቸው፡፡
ለተወሰነ ጊዜ አብሬያቸው እየተዟወርኩም፣ የትጥቅ ልብሳቸውን እሰፋ ነበር፡፡ በኋላ ሌሎችንም ልብስ መስፋት አስተምሬአቸዋለሁ፡፡
እስቲ የእነማንን ልብስ ሰፍተዋል?
ውው… የብዙዎቹን የብአዴን ልጆች የትጥቅ ልብስ እኔ ነበርኩ መትሬ የምሰፋላቸው፡፡ በስም ያልሽኝ እንደሁ አላስታውሳቸውም፡፡ ግን እጅግ ጥሩ አድርጌ ነበር የምሰፋላቸው፡፡ ሁለት ሌሎች ልብስ ለመስፋት ፍላጎት ያላቸውን ልጆች አሰልጥኜ የእኔን ስራ ይሰሩ ነበር፡፡  ያን ጊዜ የነበራቸውን ቁርጠኝነትና ጀግንነት ሳስበው ይደንቀኛል፡፡ ወንዱ ገበሬ መስሎ፣ ሴቲቱ እንቁላል የምትሸጥ አልባሌ ሆና ትመጣለች፡፡ የገበሬ ሚስት ወይም ልጅ ትሆናለች ብለን እናስባለን፡፡ አብረውን ይበሉ፣ ይጠጡ ነበር፡፡ ገብተው ምን ሰርተው እንደሚወጡ እንኳን አይታወቁም፡፡ ውስጥ ለውስጥ የልባቸውን ይሰራሉ… መቼም ጀግናዎች ናቸው፤ ብለው ብለው ደርግን ነቅለው ጣሉት፡፡
በደርግ ዘመን ሰቆጣን መንግስት አያስተዳድራትም ነበር ሲባል ሰምቻለሁ…
አዎ፡፡ እንደውም እነዚህም ሳይገቡ ደርግ መንግስት ሆኖ እየመራ፣ ከተማዋን ሌባ ገብቶ እንዳይሰርቃት፣ እኔን ጨምሮ አስራ ሁለት ሰዎች ተመርጠን እንጠብቃት ነበር፡፡ በወቅቱ እኔ ሰብሳቢ ነበርኩ፡፡ የሰቆጣ ህዝብ ደርግ በቀይ ሽብር ሁለትና ሶስት ጊዜ ከተማውን ስለፈጀው “እምቢ አልገዛም” ብሎ የኮበለለ ህዝብ ነው፡፡ ደርግ ከሰቆጣ የተባረረው ያኔ ነበር፡፡ ይሄ ህዝብ ፍቅሩ፣ መተሳሰቡና ትስስሩ ሁሉ የመጣው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ያለ መንግስትም ኖረን ቆይተን ይሄ መንግስት ሲመጣ አካባቢውን ተቆጣጠረው፡፡ ያው የወጣበት፣ የተወለደበት ስፍራ በመሆኑ፣ እየመራ መጣ፤ እኛም እልል ብለን ተቀበልነው፡፡
ያለመንግስት ስትኖሩ እንዴት ነበር ህይወታችሁን የምትመሩት?
ጤፍ ከበለሳ በአህያ ተጭኖ ይመጣና ሌሊት እንገበያያለን፡፡ በቅሎው አህያው ሁሉ የሚሸጠው ሌሊት ነበር፡፡ መቼም የጋማ ከብቱ ያኔ ውድ ነው፡፡ ነገር ግን የከብቱ ዋጋ በጣም የወደቀ ነበር፤ ለመሸጥ እንኳን ስለማያዋጣ አይሸጥም፡፡ የምግብ እጥረት የነበረ ቢሆንም የተገኘውን በልተን ጠጥተን እናድራለን፡፡ ህዝቡ ከዚያ የተነሳ ነው ፍቅሩና መተሳሰቡን ያጠነከረው፡፡
በትግል ወቅት አህያ ትልቅ ሚና እንደነበራት ይነገራል...
አዎ… አህያማ በትጥቅ ትግሉ ወቅት አንዷ ታጋይ በያት፡፡ በረሃ ለበረሃ ትጥቅና ስንቅ ተጭና አብራ የምትጓዝ ባለውለታ ነበረች እንጂ፡፡ በቅሎ ደግሞ ለተጋዳላዮች ወደ ከተማ ሲመጡ ትረዳቸዋለች፡፡ እኛም የአህያንና የበቅሎን ስራ ያህል ከጫካ ወደ ከተማ ሲመጡ ተቀብለን እናግዛቸዋለን፣ ከአሰቡት እናደርሳቸዋለን፡፡
ገበያ ሌሊት የምትገበዩት ለምን ነበር?
ቀን ቀንማ ደርግ በአየር እየደበደበን ተቸገርን፡፡ “የእስላም መንደር” የሚባል ስፍራ አለ፤ ምሽግ ነው፡፡ በየሰው መኖሪያ ቤትም ምሽግ ነበር፡፡ የምንውለው ምሽግ ውስጥ ተደብቀን ነው፡፡ ይህቺ ከተማ እኮ በደርግ ዘመን አስራ አንድ ጊዜ በአየር ተደብድባለች፡፡ በቀን ሁለት ሶስት ጊዜ የምትደበድብበትም ጊዜ ነበር፡፡ አየር በላያችን ላይ ሲያንቧርቅብን፣ በሰማዩ ላይ ዞረው ዞረው አስጨንቀውን እኮ ነው የሚመለሱት፡፡
የሻደይን በዓል ለማክበር ሰቆጣ ከተማ ስንገባ የመንግስት ባለስልጣናት ያለአንዳች ጠባቂ ሲዘዋወሩ አይተናቸዋል፡፡ ይሄ እንዴት ሊሆን ቻለ?
ያለጠባቂ!?..የምን ጠባቂ ነው ደሞ የሚያስፈልጋቸው? ይሄ ህዝብ መስሎኝ ለዚህ ያበቃቸው፡፡ ከማን ይሸሸጋሉ? እና ዛሬማ ደርግ ጠላታቸው ወድቆ አይደል፡፡ እንኳን ሰቆጣ ይቅርና መላ ኢትዮጵያን ቢዞሩ ማን ይነካቸዋል..እንደው ለደንቡ ካልሆነ በቀር፡፡ እኔ አሁን ሰላምታ የሰጠኋቸው እነ ካሣ ተክለ ብርሃን፣ ታደሰ ካሣ፣ መዝሙር ፈንቴ፣ የተስፋዬ ገብረ ኪዳን ልጆችም አሉ፡፡ ምኑን እቆጥርልሻለሁ ልጄ፡፡ ባህርዳር ያለው ተጋዳላይ ሁላ የሰቆጣ ልጅ እኮ ነው፤ ያኔ ሳይጎለብቱ ከትምህርት ቤት የወጡ ናቸው፡፡
ከተማዋ እንደ ውለታዋ አልተደረገላትም የሚል ቅሬታ ይሰማል …
በዚህ በዚህ እኛም አሁን ያለውን መንግስት እናማዋለን፡፡ ልጆቻችን የተሰውትም ተሰውተው፣ በህይወት ያሉትም ለዚህ ደረጃ መድረሳቸው እሰየው ነው፡፡ ዛሬ “ብአዴን”፣ ቀደም “ኢህዴን” በሚል የሚጠሩቱ ልጆቻችን፣ ያሰቡትን ትግል አድርገው እዚህ መድረሳቸው ቢያስደስተንም ይሄ ነው የማይባል ችግር ውስጥ ነው ያለነው፡፡ መንገድ ያለመኖሩ፣ ለልጆቻችን በቂ ትምህርት ቤትና የጤና ተቋም ባለማግኘታችን እጅግ ተከፍተናል፡፡ ወደ ገጠሩ ወጣ ብለሽ ብታይ ደግሞ ልጄ…  አንቺው እማኝ ትሆኛለሽ፡፡
እርግጥ ነው..መብራት፣ ባንክ ቤት፣ ውሃ፣ ወፍጮ፣ ስልክ አለ፡፡ ሆኖም አካባቢው የተረሳና የተጣለ በመሆኑ፣ ህዝቡ ዛሬ ዛሬ ከፍቶታል፡፡

Read 5041 times