Saturday, 30 August 2014 10:54

“…ይቺን አገር የት ያደርሳት ይሆን!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…የዚህ ዓመት ‘ፍጥነት’ አይገርማችሁም! እንኳንም ተንደረደረ! ልክ ነዋ… ደስ የማይሉ  ነገሮች ‘ሚዛን የደፋበት’ ዓመት ነዋ! ‘ጦስ ጥምቡሳሳችንን’ ይዞ ይሂድማ!
ነገርዬው ምን መሰላችሁ… የሚያሳዝነው ደግሞ ለከርሞም ደመናው ስለመገለጡ እርግጠኛ ሆነን መናገር አለመቻላችን ነው፡፡ መሽቀንጠር ያለባቸው ትከሻችን ላይ የተከመሩ ችግሮች በዙብና!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ‘ባቡሩ’ ለከርሞ ሲመጣ እኛን “ጥርግርግር አድርጎ…” መውሰዱ ‘እንደተጠበቀ ሆኖ’ መጪው ዓመት የከፉ ነገሮቻችንን ጠራርጎ ሚሲሲፒ ወንዝ የሚከትልን ዓመት ይሁንልን ብለን እንመኝ! አሜን!
ታዲያላችሁ… ዙሪያችንን የከበበን የጥላቻ ጥልፍልፎሽ ይቺን አገር የት ሊያደርሳት ነው አያስብላችሁም! ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ…ዘንድሮ ለመጠላላት ምንም ‘ርስት መግፋት’ ‘ሚስት መንጠቅ’ ምናምን አያስፈልግም፡፡
እናማ…በማንነታችን፣በትውልድ ስፍራችን፣ በእነከሌ ዘመድነታችን…ምናምን በቀላሉ የምንጠላላበት ዘመን ነው፡፡ ሁሌ ሽክ በማለታችን፣ የደላን በመምሰላችን…ምናምን የምንጠላላበት ዘመን ነው፡፡ ‘ሳያልፍልን’ በመኖራችን፣ ሰባራ ሳንቲም የሌለን ‘መናጢ’ ድሆች በመሆናችን፣ ዕድል ፊቷን ያዞረችብን በመሆናችን…ምናምን የምንጠላላበት ዘመን ነው፡፡ታዲያላችሁ…ቀሺሙ ነገር ምን መሰላችሁ… ይህ የመጠላላት ‘የድንጋይ ዘመን’ ባህሪይ ወደ ትኩሱ ትውልድም መጋባቱ! በየስፖርቱ፣ በየሙዚቃው፣ በየትወናው… ምናምን ያለው የእርስ በእርስ መጠላላት የሚገርም ነው፡፡ እነኚህንና የመሳሰሉ ዘርፎችን የሞሉት የነገው ‘አገር ተረካቢ ትውልድ’ አባላት ናቸው፡፡ እናማ… መጪው ዓመት ጥላቻን “ጥርግርግ” አድርጎ ይወሰድልንማ!
ደግሞላችሁ…መናናቅ ይችን አገር የት ያደርሳት ይሆን የምንልበት ዘመን ላይ ነን፡፡ ለመናናቅም ቢሆን መስፈርቶቹ የግል ቁርሾ ምናምን አይደሉም፡፡ ወይም ገሚሶቻችን ‘ተባርከን’ ገሚሶቻችን ደግሞ ‘ተረግመን’ ወደዚች ዓለም ስለመጣን አይደለም፡፡ ወይም…አለ አይደል… “ተንቀህ ኖረህ ተንቀህ ይቺን ዓለም ተሰናበት…” ምናምን የሚል ግዝት ስላለብን አይደለም፡፡
የኢኮኖሚ አቋማችን ‘ከወለሉ በታች’ ስለሆነ ብቻ ‘እንናቃለን’፣ በምርጦች መሰባሰቢያ የቀለጡ መንደሮች አካባቢ ስለማንታይ ‘እንናቃለን’፣ የመጣንበት የዘር ግንድ ‘እንናቃለን’፣ በ‘ቦተሊካው’ በሚኖረን አመለካከት ‘እንናቃለን’፣ ሰዉ ሁሉ በየግል መኪናው ሲንፈላሰስ እኛ በዘጠኝና አሥራ አራት ቁጥር አውቶበሶች ተጠቅጥቀን ከቦታ ቦታ በመሄዳችን ‘እንናቃለን’፣ እንትናዬአችን ጸጉሯን የምትተኮሰው በየመንፈቁ በመሆኑ (ቂ…ቂ…ቂ…) ‘እንናቃለን’ በፈረንጅ አፍ “ሀው ኢዝ ዩ?”   “ኮንፊደንሻል ነኝ” ምናምን ማለት ባለመቻላችን ‘እንናቃለን’፡፡
እናላችሁ…መጪው ዓመት የመናናቅ ቫይረስን ጠራርጎ ይሂድልንማ!
እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ…ሁለት የናጠጡ ሀብታሞች ይፎካከራሉ አሉ፡፡ እናላችሁ…አንደኛው ምን ይላል… “እኔ ሚሊየነር ነኝ፡፡ አንተን ገዝቼ ልሸጥህ እችላለሁ፣” ይላል፡፡ ሁለተኛው ምን አለ መሰላችሁ…“እኔ ቢሊየነር ነኝ፡፡ አንተን ገዝቼ አስሬ አስቀምጥሀለሁ፡፡ መሸጥ አያስፈልገኝም!”
እናላችሁ…“አንተን ገዝቼ ውሻ ቤት አስሬ አስቀምጥሀለሁ…” ማለት የሚቃጣቸው ሰዎቸ እየበዙ ሲሄዱ ጥሩ ምልክት አይደለም፡፡  
ደግሞላችሁ…በሆነ ባልሆነው እርስ በእርስ መጠራጠር “ይቺን አገር የት ያደርሳት ይሆን!” የምንልበት ዘመን ላይ ነን፡፡ እናማ…አንዳችን ሌላኛችንን ለመጠርጠር ምንም ምክንያት አያስፈልገንም፡፡ እንዲህም ሆኖ እርስ በእርስ እንድንጠራጠር የሚያደርጉን ነገሮች አንድ መቶ አንድ ናቸው፡፡
መዝናኛ ስፍራ ላይ ሰዉ ሲያውካካ ብቻችንን ጥግ ይዘን በመቀመጣችን ‘እንጠረጠራለን’፣ እንደ ሌላው ሁሉ የትውልድ ቀዬአችን እዚህ ወይም እዛ ስፍራ በመሆኑ ‘እንጠረጠራለን’፣ አብረን ሻይና ጃምቦ ድራፍት በምንጠጣቸው ሰዎች ማንነት ‘እንጠረጠራለን’፣ በምናነባቸው የህትመት ውጤቶችና በምንከታተላቸው መገናኛ ብዙሀን ምንነት ‘እንጠረጠራለን’፣ ሌላው ከ‘ቅንጭላቱ’ አንድ ሁለት ብሎን በፈቃደኝነት አስወግዶ ‘ጨርቁን ሲጥል’ እኛ ግን “በገዛ እጄማ ጨርቄን አልጥልም…” በማለታችን ‘እንጠረጠራለን’፣ በምናደንቃቸው ወይም በማይመቹን ደራስያን፣ ገጣሚዎች፣ ተዋናዮች ምናምን ማንነት ‘እንጠረጠራለን’፣ የምናጨበጭብላቸው ‘ቦተሊከኞች’ (አሉ እንዴ!) እዚህ ወይም እዛኛው ቡድን ውስጥ በመሆናቸው ‘እንጠረጠራለን’፡፡  
እናላችሁ…ዘንድሮ አይደለም ባስ ያሉ ጉዳዮችን፣ የግል ጉዳዮችን ስናወራ እንኳን አንዳችን ሌላኛችንን በሆዳችን…አለ አይደል… “ሂድና የግሪክ ቱሪስት ብላ!” ምናምን እንባባላለን፡፡ ምን መሰላችሁ…የሚነገሩ የተለመዱ አባባሎች እንደየሰዉ  እየተከተፉና እየተከታታፉ “ጤና ይስጥልኝ!” ለመባባል እንኳን  አይመችም፡፡ ታዲያላችሁ…“ምን አግኝተህ ነው እንዲሀ ያማረብህ!” አይነት አባባል በፊት የወዳጅነት ጨዋታ ነበር፡፡ ተናጋሪም ሆነ አድማጭ ‘ተቀጥላ’ ትርጉም አይፈልጉለትም ነበር፡፡
ዘንድሮ ግን ታሪኩ ተለውጧል፡፡ “ምን አግኝተህ ነው ያማረብህ?” አይነት አባባል… መአት ነገር ሆኖ ሊመነዘር ይችላል፡፡ እናማ… እናንተ በወዳጅነት መንፈስ “ምን አግኝተህ ነው ያማረብህ?” ስትሉ…
“ስኳር ልሰሀል ወይ ማለቱ ነው እንዴ?”
“በእሱ ቤት እኮ ከሰዎቹ ተጠጋህ ማለቱ ነው፡፡”
“እንግዲህ ያቺን የሆቴል ቤት ባለቤት ስለያዝኩ ገንዘብ አይቶ ገባ ሊል ነው፡፡”
“ሰው የማያውቀው የድብቅ ገቢ አለህ ሊል ፈልጎ ነው እንዴ!” ምናምን እየተባለ አንድ መቶ አንድ ሰበብ ሊሰጥ ይችላል፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ሁለትም ሦስትም ሆነው እየተዝናኑ ሳለ የተከፈተ ለስላሳ ወይም ቢራ ትቶ ወደ መጸዳጃ መሄድ እየቀረ ነው ይባላል፡፡ አሳላፊ ተስተናጋጁ አጠገብ ደርሶ እየታየ መጠጡን ካልከፈተው በስተቀር ከፍቶ ያመጣውን መጠጥ መጠጣት እየቀረ ነው አሉ፡፡ ምግብ ተመግበው ዘወር ካሉ በኋላ ተመልሶ መጥቶ መጉረስ እየቀረ ነው አሉ፡፡
 እናላችሁ…እርስ በእርስ የመጠራጠራችን ነገር አየደለም በ‘ሲኒየር ሲቲዘንስ’ አካባቢ…አለ አይደል… በወጣት የኪነጥበብና የስነ ጥበብ ሰዎች ዘንድ ሁሉ እየተስፋፋ ነው ይባላል፡፡ እናላችሁ…የምናየው ነገር ሁሉን “ይቺን አገር የት ያደርሳት ይሆን!” የሚያሰኙ እየሆኑ ተቸግረናል፡፡
መጪው ዓመት እርስ በእርሳችን በሆነ ባልሆነው የማንጠራጠርበት ዓመት ይሁንልንማ!
ታዲያላችሁ…“ኑሮ እንዴት ነው?” ምናምን ስንባል “አሸወይና ነው…” ምናምን አይነት አስተያየት የምንሰጥበትን ጊዜ ያቅርብልንማ!
እናማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ የአስተያየት ነገር ካነሳን አይቀር፣ ይቺን ስሙኝማ……አንዳንድ ‘ፈረንጅ’ ጎብኚ አስተያየት ሲሰጥ ልብ ብላችሁልኛል! ታዲያላችሁ…አገሪቱን እንደሚወድ ምናምን ይናገርና… “ለመሆኑ ስለ አገራችን የምታደንቀው ምንድነው?” ሲባል ምን ይላል መሰላችሁ… “ሴቶቻችሁ ቆንጆዎች ናቸው…” ብሎላችሁ እርፍ!
እኔ የምለው…‘ፈረንጅ’ እዚህ አገር ሲመጣ በአእምሮው ማሰቡን ትቶ ለሌላ አገልግሎት በተመደበለት (ቂ...ቂ…ቂ…) የሰውነት አካል ነው እንዴ የሚያስበው!
ይቺን ስሙኝማ…
አሰማራቸውና ከብቶቻችን ይብሉ፣
አሰማራቸውና በጎቻችን ይብሉ፣
አሰማራቸውና ከብቶቻችን ይብሉ፣
ያ ሣር አይደለም ወይ የምናየው ሁሉ፣
የሚሏት የጥንት አባባል አለች፡፡ መጪውን ዓመት የአሣር ከመሆን አንድዬ ይጠብቅልንማ!
እናማ…“…ይቺን አገር የት ያደርሳት ይሆን!” የሚያስብሉ ነገሮች የሚቀንሱበት ዓመት ይሁንልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!



Read 3171 times