Saturday, 30 August 2014 10:48

የዋግኽምራ ህዝብ ምሬቱን ለመንግስት ባለስልጣናት ገለፀ

Written by 
Rate this item
(13 votes)
  • በ514 የዳስ እና የዛፍ ጥላዎች ትምህርት እየተሰጠ ነው
  • ከ20ሺህ በላይ ስራ አጥና መሬት አልባ ወጣቶች አሉ
  • ከግማሽ በላይ ህዝብ የትራኮማ ተጠቂ ነው

           ከኢህዴን/ብአዴን ዋና ዋና የጦር ማዘዣዎችና መንቀሳቀሻ አካባቢዎች መካከል አንዱ የነበረው የዋግኽምራ ዞን፤ በኢኮኖሚ እድገት ወደኋላ መቅረቱንና ድህነት አለመቃለሉን በመጥቀስ ከአስር አመታት በፊት ለቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ቅሬታ አቅርቦ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ሰሞኑን በድጋሚ ለፌደራልና ለክልል ባለስልጣናት ምሬቱን ገለጸ፡፡
ባለፈው ቅዳሜ በሰቆጣ ከተማ በተደረገ ውይይት ላይ ቅሬታቸውን ያቀረቡት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ዞኑ በአማራ ክልል ውስጥ ከሚገኙ አስር ዞኖች ጋር ሲነጻጸር፤ በድህነት፣ በጤና ጉድለትና በትምህርት ችግሮች ቀዳሚ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በትምህርት ጥራት ላይ  መጠነ ሰፊ ችግር እንዳለና በዞኑ በ514 ዳሶችና የዛፍ ጥላዎች ውስጥ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት እየተሰጠ እንደሚገኝ ነዋሪዎች ገልፀዋል፡፡ ሁለተኛ ደረጃ እና ከዛም በላይ ያሉ ትምህርት ቤቶች በአካባቢው ባለመኖራቸው 32 ሺ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ማቋረጣቸውንም አስረድተዋል፡፡
በዞኑ ከተሰሩት ሶስት ሆስፒታሎች አንዱ ብቻ አገልግሎት እንደሚሰጥ፣ ከሃያ ዘጠኝ የጤና ጣቢያዎች አስሩ ከደረጃ በታች በመሆናቸው እንደተዘጉ፤ ከተገነቡት 125  ጤና ኬላዎች  አስሩ ከደረጃ በታች ሆነው ሥራ እንዳቆሙ፣ 6 የግል ጤና ተቋማት ቢኖሩም ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንደማይሰጡ ነዋሪዎቹ ገልፀዋል፡፡ ከወሊድ ጋር በተያያዘ በሚከሰት  የእናቶች ሞት ዞኑ ከክልሉ በቀዳሚነት እንደሚጠቀስ፣ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ህዝብ  ለትራኮማ በሽታ የተጋለጠና በቤተሰብ አንድ ሰው ለዓይነ ስውርነት የተጋለጠ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡  
የዋግኽምራ ህዝብ ያደረገው የትግል ተጋድሎ ታሪክ የማይረሳ ቢሆንም፣ ከሌሎች ዞኖች ጋር ሲነፃፀር የልማት ተጠቃሚነቱ አነስተኛ ነው  ያሉት አንድ አስተያየት ሰጪ፤ ወደ ትግራይ ክልል ብንካለል ለውጥ እናገኝ ነበር፤ ምክንያቱም አላማጣና ራያና ቆቦ መንገድ ሲሰራ ለእኛም ይሰራልን ነበር ብለዋል፡፡
የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ለቀረቡት ቅሬታዎችና ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ በዞኑ የሚታዩ ችግሮች ተደራራቢ ከመሆናቸው አንፃር ችግሮቹን ከመሰረቱ መቅረፍ አዳጋች መሆኑን ገልፀው፣ ዞኑን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ መሰረት የሚጥሉ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ነዋሪዎች ያነሷቸው ችግሮች መኖራቸውን አምነው፣ ይሄም ሆኖ ግን በትምህርት፣ በጤናና በምግብ ልማት ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ ለውጥ እየታየ መሆኑንና የልማት ስታራቴጂውን ከግምት ማስገባት እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል፡፡ አካባቢው የቱሪስት መስህቦች ያሉት ቢሆንም በድህነት ምክንያት ዝቅ ያለና የተረሳ ዞን መሆኑን ያወሱት የአካባቢው ተወላጅና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ካሣ ተ/ብርሃን፤ “ከአካባቢው ተፈጥሮአዊ አቀማመጥ አንጻር ህዝቡ ድህነትን ለማሸነፍ የሚያደርገው ተጋድሎ ተጠቃሽ ነው፣ በትጥቅ ትግሉ ሁላችንም በእግራችን ስንማስን እናውቀዋለን፤ በዞኑ የሚሰሩና የሚኖሩ ህዝቦችን ጥረት አደንቃለሁ” ብለዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገድሉ አንዳርጋቸው በበኩላቸው፤ ከ5 አመታት በፊት በክልሉ ከሚኖረው 20 ሚ. ህዝብ 2.5 ሚ የሚሆነው የምግብ ዋስትና ያላረጋገጠ እንደነበር ጠቅሰው፤ በአሁኑ ጊዜ 1.4 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ በችግሩ ውስጥ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ ዋግኽምራ ዞንም በርከት ያለ ህዝብ በየዓመቱ ክረምት በመጣ ቁጥር ተረጂ እንደሚሆንና ዞኑ ስር የሰደደ የምግብ ዋስትና ችግር የሚታይበት በመሆኑ ሁልጊዜም አጀንዳ ሆኖ እንደቀጠለ ተናግረዋል፡፡
በዞኑ የመሰረተ ልማት ችግሮችን ለመቅረፍ 128 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የሰቆጣ ላሊበላ  መንገድ በ2007 ዓ.ም. ለመስራት መታቀዱን ጠቁመው፣ በዞኑ ያሉትን መጠነ ሰፊ ችግሮች ለመፍታት የአካባቢውን ተፈጥሮዊ አቀማመጥ ባገናዘበ መንገድ ህብረተሰቡና መንግስት በቅንጅት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ የስራ አጡን ቁጥር ከመቀነስ አኳያም የተደራጁ ስራ አጦችን በንብ፣ በማር እና በአሳ ምርት በማሰማራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል እንቅስቃሴ መጀመሩን አስገንዝበዋል፡፡
የእንስሳትና የአሣ ልማት ምርት፣ የቱሪዝም፣ የብረታ ብረትና ማዕድን መስኮች ላይ ትኩረት አድርጐ መስራት ለዞኑ የተፋጠነ ልማት ለማምጣት ተመራጭ አካሄድ እንደሆነም አቶ ገድሉ  ተናግረዋል፡፡

Read 7273 times