Saturday, 30 August 2014 10:39

‘ስማርትቪስታ’ የተሰኘ ዘመናዊ የባንክ የክፍያ ስርዓት ሊዘረጋ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

       በአለማቀፍ ደረጃ ዘመናዊ የባንክ ክፍያ ስርዓቶችን በመዘርጋት የሚታወቀው ቢፒሲ ባንኪንግ ቴክኖሎጂስ የተባለ ኩባንያ፣ በኢትዮጵያ ‘ስማርትቪስታ’ የተሰኘ ዘመናዊ የባንክ ክፍያ ስርዓት ሊዘረጋ መሆኑን ባንክስ ቢዝነስ ሪቪው ድረ-ገጽ ትናንት ዘገበ፡፡የ “ስማርትቪስታ” የተባለውን የክፍያ ስርዓት የመዘርጋት ሃላፊነቱን በአገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ባንኮች በጋራ ከመሰረቱት የኢትዮጵያ ባንኮች ጥምረት የተረከበውና ተቀማጭነቱ በስዊዘርላንድ የሆነው ቢፒሲ ባንኪንግ ቴክኖሎጂስ፣ በአገሪቱ ሊዘረጋው ያቀደው የክፍያ ስርዓት ዘመናዊና ለአጠቃቀም ምቹ መሆኑ ተመራጭ እንዳደረገው ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ባንኮች ጥምረት አዲሱን የክፍያ ስርዓት ለመዘርጋት ያቀደው፣ ሁሉንም የአገሪቱ ባንኮች በአንድ የገንዘብ ዝውውር ማዕከል አማካይነት ለማስተሳሰርና ደንበኞች የተለያዩ የባንክ አገልግሎቶችን በኤቲኤም፣ በፖይንት ኦፍ ሴል ዲቫይስ፣ በሞባይልና በኢንተርኔት አማካይነት እንዲያገኙ ለማስቻል በማሰብ እንደሆነ ዘገባው አስረድቷል፡፡
ኩባንያው በቀጣይም “ስማርትቪስታ” በተሰኘው ዘመናዊ የክፍያ ስርዓት አማካይነት የአገሪቱ ባንኮች ቪዛ ካርድንና ማስተር ካርድን በመሳሰሉ የመክፈያ ካርድ አሰራሮች አለማቀፍ ክፍያዎችን መፈጸም የሚችሉበትን አሰራር እንደሚዘረጋ ተነግሯል፡፡
የቢፒሲ ባንኪንግ ቴክኖሎጂስ የአፍሪካ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ዳሪል በርግ፣ መሰል ፕሮጀክቶችን በመላው አለም በስኬታማ መንገድ በማከናወን የካበተ ልምድ ያለው ኩባንያው፣ በኢትዮጵያም የዘመኑ ቴክኖሎጂ የደረሰበትን ጠንካራና የተሻሻለ የክፍያ መሰረተ ልማት እንደሚዘረጋ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡  የኢትዮጵያ ባንኮች ጥምረት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ብዙነህ በቀለ በበኩላቸው፣ ጥምረቱ በባንኮች ውስጥ የሚከናወነውን የክፍያ አሰራር ሂደት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማገዝ በበለጠ ሁኔታ የተቀላጠፈ፣ ግልጽነት ያለውና ደህንነቱ የተጠበቀ የማድረግ ዓላማ ይዞ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
“በአገሪቱ ዘመናዊ የባንክ ክፍያ ስርዓት ለመዘርጋት የያዝነውን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ፣ በዘርፉ በአለማቀፍ ደረጃ የሚሰሩ ኩባንያዎችንና የክፍያ ስርዓቶችን የመገምገም ስራ በስፋት ከተከናወነ በኋላ፣ ወቅታዊውንና የወደፊቱን ዘርፈ-ብዙ ፍላጎታችንን የሚያሟላው “ስማርትቪስታ” በመሆኑ ልንመርጠው ችለናል” ብለዋል አቶ ብዙነህ፡ቢፒሲ ባንኪንግ ቴክኖሎጂስ በአሁኑ ወቅት በ45 የተለያዩ የአለም አገራት ለሚገኙ 126 ደንበኞቹ በዘርፉ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፣ የኢትዮጵያ ባንኮች ጥምረትም እ.ኤ.አ በ2011 በብሄራዊ ባንክና በአገሪቱ በሚገኙ ሁሉም ባንኮች ያቋቋሙትና ለፋይናንስ ተቋማት ብሄራዊ የክፍያ ስርዓት ለመዘርጋት ያለመ አክስዮን ማህበር መሆኑን አስታውቋል፡፡



Read 2347 times