Saturday, 23 August 2014 11:39

የቻይና የማስታወቂያ ኢንዱስትሪ በአለም ገበያ 2ኛ ደረጃን ይዟል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አመታዊ የማስታወቂያ ገቢው 50 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል
ለስኬቱ የአንበሳውን ድርሻ የምትወስደው አንዲት ሴት ናት ተብሏል
ከአስርት አመታት በፊት በይዘትም ሆነ በአቀራረብ ጥራቱን ያልጠበቀና ደረቅ ፕሮፓጋንዳ የነበረው የቻይና የማስታወቂያ ዘርፍ፣ በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ በአመት 50 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ወደሚያስገኝ ዘመናዊ የማስታወቂያ ኢንዱስትሪነት መሸጋገሩንና፣ በዘንድሮው የዓለም የማስታወቂያ ገበያ ሁለተኛውን ደረጃ መያዙን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
የቻይና የማስታወቂያ ኢንዱስትሪ በአሁኑ ወቅት ከአውሮፓና ከሌሎች የአለም አገራት ታላላቅ የማስታወቂያ ኩባንያዎች ጋር ተፎካካሪ እንደሆነና በአትራፊነት የሚጠቀስ መሆኑን የጠቆመው ሲኤንኤን፣ ኢንዱስትሪው ከነበሩበት ችግሮች ተላቆ ዘመናዊ አደረጃጀትና አሰራር እንዲይዝ በማድረግ በኩል የአንበሳውን ድርሻ የምትወስደው ቻይናዊቷ የማስታወቂያ ባለሙያና ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሺናን ቹዋንግ እንደሆነች ገልጿል፡፡
በማስታወቂያው ዘርፍ ከ30 አመታት በላይ እንደቆየች የተነገረላት ቹዋንግ፤ በአሁኑ ወቅት በዘርፉ በአለማቀፍ ደረጃ ስማቸው ጎልቶ ከሚጠቀሱ የማስታወቂያ ድርጅቶች አንዱ የሆነውንና ትርፋማውን “ኦጊልቪ ኤንድ ማተር ግሬተር ቻይና” የተባለ የአገሪቱ ኩባንያ በዋና ስራ አስፈጻሚነት ከመምራት ባሻገር የቻይናን የማስታወቂያ ኢንዱስትሪ በአመት ከ50 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የሚያገኝበት ደረጃ ላይ ያደረሰች ብርቱ ሴት መሆኗን ዘገባው ይጠቁማል፡፡
ቹዋንግ በማስታወቂያው ዘርፍ በቆየችባቸው አመታት በአገር አቀፍ ደረጃ ተቋማዊና የአሰራር ለውጥ በመፍጠር ረገድ ሰፋፊ ስራዎችን አከናውናለች ያለው ዘገባው፤ አሁን ዋና በስራ አስፈጻሚነት በምትመራው ኩባንያ፤ አለማቀፍ የጥራት ደረጃዎችን የጠበቁ ማስታወቂያዎችን በመስራት ትልቅ ስኬት መጎናጸፍ መቻሏን አመልክቷል፡፡
ኩባንያው በቴክኖሎጂ የታገዙና ፈጠራ የታከለባቸውን አለማቀፍ የምርትና የአገልግሎት እንዲሁም የቅስቀሳ ማስታወቂያዎች በብዛት በመስራት ላይ እንደሚገኝ ጠቁሞ፣ ኩባንያው ለኮካ ኮላ በሰራው ማስታወቂያ የ “ኬንስ ግራንድ ፕሪክስ”ን ሽልማት ለመቀበል መብቃቱንም አስታውሷል፡፡

Read 1019 times