Print this page
Saturday, 23 August 2014 11:35

የኢትዮጵያ ቡና የኤክስፖርት ገቢ በ25 በመቶ እንደሚያድግ ይጠበቃል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አለማቀፍ የቡና ገበያንና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው

ኢትዮጵያ በመጪዎቹ አስራ ሁለት ወራት ለውጭ ገበያ ከምታቀርበው የቡና ምርት የምታገኘው ገቢ በ25 በመቶ እድገት ያሳያል ተብሎ እንደሚጠበቅ ብሉምበርግ ዘገበ፡፡
በቡና ምርትና በአቅራቢነት ከአለም ቀዳሚ በሆነችው ብራዚል በተከሰተው ድርቅ ምክንያት በአለም የቡና ገበያ ላይ የዋጋ ጭማሪ ይፈጠራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጸው ዘገባው፣ ኢትዮጵያም በተያዘው የፈረንጆች አመት ለውጭ ገበያ ከምታቀርበው የቡና ምርት 900 ሚሊዮን  ዶላር ያህል ገቢ ታገኛለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ዘገባው አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አለምሰገድ አሰፋን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ የአለም ገበያ የቡና አቅርቦት እጥረት የሚቀጥል ከሆነ በኢትዮጵያ የምርት ገበያ አማካይነት ለገበያ በሚቀርበው የአረቢካ ቡና ዋጋ ላይ በፓውንድ የ2 ዶላር ጭማሪ ሊገኝ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ እስካለፈው ሃምሌ ወር መጀመሪያ በነበሩት 12 ወራት ለውጭ ገበያ ካቀረበችው ቡና 719 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቷን ያስታወሰው ዘገባው፣ ይህም ከአንድ አመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር የ3 ነጥብ 7 በመቶ ብልጫ እንዳለው ጠቅሷል። በተመሳሳይ ጊዜ ለውጭ ገበያ ባቀረበችው የቡና ምርት መጠን ላይ የ4 ነጥብ 1 በመቶ ቅናሽ መታየቱንም አመልክቷል፡፡
በዚህ አመት በአገሪቱ 500 ሺህ ቶን ቡና ይመረታል ተብሎ እንደሚጠበቅና፣ ከዚህ ውስጥም ግማሽ ያህሉ ወደተለያዩ አገራት ገበያ የሚላክ እንደሚሆንም ዘገባው ጨምሮ ገልጧል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ከተለያዩ የአለም አገራት አዳዲስ የቡና ምርት ገዢዎችን ለመሳብና አገሪቱ በአለማቀፉ የቡና ገበያ ውስጥ ያላትን ድርሻ ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡ ወርልድ ቡሊቲን በበኩሉ፤ ከአፍሪካ ቀዳሚዋ የቡና አምራች የሆነችው ኢትዮጵያ ለአለም ገበያ የምታቀርበውን የቡና ምርት የንግድ ምልክት በማውጣት የበለጠ በገበያው ውስጥ ተወዳዳሪ ለማድረግ በአለማቀፍ ደረጃ ታዋቂ ከሆኑ ቡና ገዢ ኩባንያዎች ጋር እየሰራች መሆኗን ዘግቧል፡፡
ከኩባንያዎቹ ጋር የተጀመረው ስራ ህገወጥ የቡና ንግድንና አላግባብ የሚጣል የቡና ዋጋ ተመንን የመከላከል እንዲሁም የአገሪቱን የቡና የንግድ ምልክቶች በመጠቀም ትርፋማነትን የማሳደግ ዓላማ ያለው ነው ተብሏል፡፡
በአገሪቱ በቡና ልማት ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳትፎ የሚያደርጉ 15 ሚሊዮን ዜጎች እንዳሉ የጠቆመው ዘገባው፣ እነዚህ ዜጎች ከሽያጩ የሚያገኙት ገቢ ከ10 በመቶ በታች እንደሆነና የተቀረውን የሚወስዱት በአለማቀፍ ደረጃ የሚገኙ ነጋዴዎችና አከፋፋዮች መሆናቸውን ገልጧል፡፡
እስካሁን ድረስ 34 አገራት በደቡብና በምስራቅ ኢትዮጵያ የሚመረቱ የቡና ዝርያዎች መለያዎችንና የንግድ ምልክቶችን ተቀብለው ለገበያ እያቀረቡ እንደሚገኙ ገልጾ፣ በቀጣይም በአውስትራሊያና በብራዚል ተመሳሳይ ስራ ለመስራት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስረድቷል፡፡

Read 3851 times
Administrator

Latest from Administrator