Saturday, 23 August 2014 11:29

የእኛ ስብሰባ ችግር “አልኮል “ኮሌስትሮል እና “ፕሮቶኮል” ናቸው

Written by 
Rate this item
(4 votes)

- የኢራናውያን አባል
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ የሰርከስ ትርዒት ይታይ ነበር፡፡ ከሰርከሱ ጋራ አንድ ግዙፍ ሰው ታየ፡፡ የትርዒቱ አካል ነበር፡፡
ይህ ግዙፍ ሰው አንድ ብርቱካን ያወጣና እንደ ጉድ ይጨምቀዋል - እስከመጨረሻው እንጥፍጣፊ ጠብታ ጨመቀው፡፡ ጉድ ተባለ ተጨበጨበ!
ከዚያ የፕሮግራሙ መሪ፤
“ይህ ታላቅ፣ ጡንቸኛና ጠንካራ ሰው ከጨመቀው በላይ ጨምቆ አንዲት ጠብታ ብርቱካን ጭማቂ ሊያወጣ የሚችል ሰው ካለ ወደዚህ ይምጣ?!” ሲል ጠየቀ፡፡
ሁሉም ፈራ፡፡
ቀጠለ የፕሮግራሙ መሪ፤
“እሺ አንድ ተጨማሪ ነገር ላክል - አንዲት ቅንጣት ላወጣ ሽልማት እሰጣለሁ፡፡ አንድ ሺ ዶላር!” አለ ጮክ ብሎ፡፡
ብረት በማንሳት የሚታወቅ ጉልቤ መንዲስ ጡንቸኛ፤ ወደ መድረኩ እየተጐማለለ መጣ፡፡ ከፕሮግራም መሪው የተጨመቀውን ብርቱካን ተቀበለ፡፡
ከዚያ ባለ - በሌለ - ጉልበቱ እንደ ጉድ እየጨመቀ፤
“እንዴት እንደምፈጠርቀው አሁን ታያላችሁ!” አለና በሁለት መዳፉ ደፈጠጠው፡፡
ግን ምንም ጠብ አላለለትም፡፡
ቀጠለና አንድ ግንበኛ ጡንቻውን ወጣጥሮ፤
“ይሄን ይሄንማ ለእኛ ተዉልን!” አለና ከብረት አንሺው ተቀበለ፡፡
ደጋግሞ ጨመቀው፡፡ አለው! አለው! ላብ - በላብ ሆነ! “ተሸንፌአለሁ” አለና ወረደ፡፡
“ሌላ የሚሞክር አለ?”  አለ የፕሮግራም መሪው፡፡
“አትችሉም! ያልኳችሁ ለዚህ ነው”
ከህዝቡ መካከል አንድ አጭር፣ ሲባጎ የመሰለ ኮስማና ከወደኋላ ብድግ አለ፡፡
“እኔ ልሞክር?” አለ፡፡
አገር ሳቀ፡፡ መሪውማ ዕንባው እስኪፈስ ነው የሳቀው፡፡ ሁሉ ሰው የመገላመጥ ያህል እየተገላመጠ አየው፡፡
ቀጫጫው ሰውዬ ግን በኩራት ራሱን ቀና አድርጎ በህዝቡ መካከል ሰንጥቆ ወደ መድረኩ ወጣ፡፡
“አመረርክ እንዴ?” አለው የመድረኩ መሪ፡፡
“አሳምሬ!” አለ ቀጫጫው፡፡
ቀጫጫው ብርቱካኑን መጭመቅ ሲጀምር ሳቁ ቀስ በቀስ ጋብ አለ፡፡
የሚገርም ነገር ተከሰተ፡፡ ወለሉ ላይ ጠብ ጠብ ማለት ጀመረ ብርቱካኑ፡፡
የፕሮግራሙ መሪ እጅግ በጣም በመደነቅ፤ “እንዴት ይሄን ተዓምር ልትፈጥር ቻልክ? አንተ ለራስህ ከአፍ የወደቀች ፍሬ የምታክል?” ሲል ጠየቀው፡፡
ቀጫጫውም፤
“አይ ጌታዬ እኔ የሂሳብ ሰራተኛ - አካውንታንት ነኝ!” አለው፡፡
*         *           *
ጎበዝ! ባገራችን የመጨረሻዋን ነጠብጣብ ጭማቂ ሂሳብ የሚያሰላ ሰው ባገኘን እንዴት በታደልን ስንቱ በተጋለጠ!  
ጉልበት እውነትን አይበልጥም! እርግጥ ጊዜያዊ ጡንቻ ዘለዓለማዊ ሀቅን ይበልጥ የሚመስለን ጊዜ ይኖር ይሆናል፡፡ ግን የዓለምን ታሪክ መለስ ብሎ ማየት ትልቅ ትምህርት ይሆነናል፡፡ ናፖሊዮን ቦናፓርት፣ ሪቻርድ ባለ አምበሳ-ልቡ (The Lion – hearted) ታላቁ እስክንድር፣ ጁሊየስ ቄሣር፣ ጄንጂስ ካሃን … ሁሉም ታላላቅ ነበሩ፡፡ ሁሉም “ከሸክላነት ወደገደልነት” ተሸጋገሩ፡፡ ‘መኳንንትም ሲሻሩ ህዝብ ናቸው’ እንዲል አንጋረ ፈላስፋ። አንድን ህዝብ ለመምራት ታላቅነት በምንም መልኩ ሀቀኛ መለኪያ አይሆንም! ታላቅነት ከየት ይመነጫል? ቢባል አንድና አንድ መለኪያ ብቻ የለውምና! ታላቅ ነኝ ብሎ ዘለዓለማዊነት የተጎናጸፈ የለምና … They mistook longevity for immortality ይሏልና፡፡ ረዥም ዘመንን ከዘለዓለማዊነት ጋር ያምታቱታል ነው ነገሩ!  
“የጾምነው ነገር ቢበዛም
መፈሰኪያው ቀን አይቀርም!”
ይላል አንድ ፆመኛ ገጣሚ፡፡ ዕውነት ነው፡፡ እንደሶስተኛው ዓለም ባለ አገር፤ ከፍስኩ ፆሙ ይበዛል። ዲሞክራሲን ከፈሰከው የፆመው ይበዛል፡፡ ፍትህን ካየው ያላየው ይበዛል፡፡ ሀቅን ካገኘው የፆመው ይበረክታል። መልካም መስተዳድርን ከተጎናፀፈው የተራቆተው ይበዛል፡፡ ዞሮ ዞሮ መፆም ተለምዶ ፍስክን አርቆ ማየት ልክ እየመሰለ መጥቷል፡፡ መንገድ ከመጀመራችን በፊት የመንገዱን እርቀት እንመትር ቢባል የሚሰማ ጠፍቷል - ከሁሉም ወገን! አንዴ “እናሸንፋለን”፤ ካሉ “ተነጋግረን እንስማማለን” “እንደሰለጠነ ሰው ተቀራርበን እንፈታዋለን” ማለት እርም ሆኗል፡፡ ስለአገር ምን አገባን”፣ “ስለህዝብ ምን አስጨነቀን?” ማለት ወግና ልማድ የሆነ ይመስላል - በተግባር የለምና!
ዛሬም ከሼክስፔር ጋር፣ በፀጋዬ ገ/መድህን አንደበት፤
“ዛሬ ለወግ ያደረግሽው፣ ወይ ለነገ ይለምድብሻል
ልማድ ፊት እንዳሳዩት ነው፣ ወይ ይጠፋል ወይ ያጠፋል  
ከርሞም የሰለጠነ እንደሁ፣ ተፈጥሮ ይሆናል ይባላል” ማለት ተገደናል፡፡
የክረምቱን ሰዓት ስናስተውል፤
“ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት
ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት”
መባሉ ጊዜን አመላካች ብቻ ሳይሆን ያለፈ ድርጊትን አመላካችና ለንጋትና ለመስከረም ዝግጁ መሆንንም ጠቋሚ ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን እንደተምኔት ሳይሆን እንደተጨባጭ ነገር ማስተዋል ይገባናል፡፡ ፅንፍና ፅንፍ እየቆሙ፣ ማዶና ማዶ የጎሪጥ እየተያዩ፣ በደፈረሰ ልብ እያሰሉ፣ የምንመኘውን ዓይነት ለውጥ ማምጣት ከባድ ነው፡፡ ከቶውንም፤ በትንሹ የምንመኛቸውን ነገሮች እንኳ በእጃችን ማስገባት አዳጋች ይሆናል፡፡
የእንግሊዙ ፈላስፋ፣ መሪና ጠበቃ ፍራንሲስ ቤከን፤
“የምንፈልጋቸውና የምንጓጓላቸው ነገሮች ጥቂት፤ የምንፈራቸው ግን ብዙ ሲሆኑ፣ የአዕምሮ ደረጃችን ጎስቋላ ሆነ ማለት ነው” ይለናል፡፡
ግባችንን በውል ለመምጣት የእኛን መንገድ ብቻ “አንደኛ ነው!” የእነ እገሌ ውራ ነው” እያልን በአፈ ቀላጤዎቻችን ብናወራ ራስ-በራስ መሸነጋገል እንጂ ሁነኛ ፍሬ የሚያፈራ ጉዞ አይሆንም፡፡
ጆርጅ በርናርድ ሾው፣ አየርላንዳዊው ፀሐፌ-ተውኔትም “ሰው ነብርን ሲገል ስፖርት ነው ይለዋል፡፡ ነበር ግን ሰውን ሲገል ጭካኔ ነው ይባላል” ይለዋል፡፡ ዕይታችን “ወደ ገደለው” መሆኑ ነው፡፡
ምንጊዜም ሁሉም የየራሱን እንቅፋት መደርደሩ አይቀርም፡፡ በየዘመኑ የምናየው ነው፡፡ ዱሮ ቀኝ መንገደኞች፣ አምስተኛ ረድፈኞች፣ ፀረ-ህዝቦች፣ ሥርዓተ-አልበኞች፣ አስመሳዮች፣ አድርባዮች ወዘተ ይባል እንደነበር እናስታውሳለን፡፡  ይባል የነበረው በሀቅ ነው ወይ? ብሎ ጠይቆ አዎንታዊ ምላሽ ማግኘት ግን ዘበት ነው፡፡ ለሥልጣን መቆያነቱ ግን አያጠያይቅም፡፡ ኢራናውያን እንቅፋቶቻቸውን ሲደረድሩ በየዘመኑ የሚያቅን “የስብሰባ ጠላቶች - አልኮል፣ ኮሌስትሮል፣ ፕሮቶኮል፤ ናቸው” ይላሉ፡፡ እነዚህ እኛንም ሳይመለከቱን አይቀሩምና በጊዜ መጠንቀቅ ነው!!  

Read 5061 times