Saturday, 23 August 2014 11:20

የመኢአድና የእነ አቶ ማሙሸት ውዝግብ ተባብሷል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

            የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና ከአራት ዓመት በፊት የዲሲፕሊን ጥሰት ፈፅማችኋል በሚል በቀድሞው የስራ አስፈፃሚ ከፓርቲው የተሰናበቱት የእነ አቶ ማሙሸት አማረ ውዝግብ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡
መኢአድ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ በጽ/ቤቱ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ እነ አቶ ማሙሸት የመኢአድ ህፈት ቤት ላይ ወረራ ፈጽመዋል ብሏል፡፡ በአቶ ማሙሸት የሚመሩ ጥቂት ግለሰቦች ነሐሴ 11 ማለዳ 12 ሰዓት ላይ ካሜራቸውን የፓርቲው ጽ/ቤት በር ላይ በጠመዱ የኢቴቪ ጋዜጠኞችንና ተሽከርካሪ በያዙ የደህንነት አባላት በመታገዝ ወረራ እንዳካሄዱ ፓርቲው ገልጿል፡፡
አቶ ማሙሸት አማረ በበኩላቸው፤ ፓርቲው የሚያወራውና እየሆነ ያለው ነገር ለየቅል መሆኑን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል። ለውዝግቡ መነሻ ነው የተባለው ጉዳይ እነ አቶ ማሙሸት በእርቅ ወደ ፓርቲው የመመለስ ፍላጎት ማሳየታቸውን ተከትሎ በተመረጡ ሽማግሌዎች ድርድር መካሄዱ እንደሆነ የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሃሪ በመግለጫው ተናግረዋል፡፡ “ምንም እንኳን በቀድሞው የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ በዲሲፕሊን ጥሰት ቢሰናበቱም ተፀፅተው በሽምግልና ከመጡ ለዴሞክራሲ ማበብ ሲባል ተቀብለናቸው ነበር” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ሽምግልናው በተካሄደብት ጊዜ ሽማግሌዎች በአምስቱም ማዕከላት ላለው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ጉዳይ ቀርቦ ከተወሰነ በኋላ ምላሽ ሊሰጣቸው ቀጠሮ መያዙ በመግለጫው ተብራርቷል፡፡ ቅዳሜ ነሐሴ 12 ስራ አስፈፃሚው ተሰብስቦ እሁድ እንደሚደወልላቸው ተነግሯቸው እንደነበር የገለፁት የፓርቲው አመራሮች፣ ቅዳሜ አብዛኞቹ ስራ አስፈፃሚዎች የመንግስት ሰራተኞች በመሆናቸው ስብሰባው እንዳልተካሄደ ተናግረዋል፡፡
እሁድ እለት ማለዳ መጥተው ፓርቲውን ከወረሩ በኋላ የፓርቲው ም/ፕሬዚዳንት አቶ እንድሪያስ ላይ ድብደባ ፈፅመውና ፀያፍ ስድብ ተሳድበው ከሰላማዊ ትግል በተቃራኒው የሆነ ነገር ፈፅመዋል ብሏል ፓርቲው፡፡
“ከአንድነት ጋር ለምናደርገው ውህደት ምርጫ ቦርድን በመደገፍ እንቅፋት የፈጠሩት እነ አቶ ማሙሸት ናቸው” ያሉት የፓርቲው ፕሬዚዳንት፤ በህወሃት ኢህአዴግ የሚመራው ምርጫ ቦርድ እነ ማሙሸትን እንደማጫወቻ ካርድ ተጠቅሞባቸዋል” ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
እነ አቶ ማሙሸት ለዚህ ፓርቲ ብዙ መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ ብዙ ታግለዋል ያሉት የፓርቲው ተቀዳሚ ም/ፕሬዚዳንት አቶ እንድሪያስ ኤፍ፤ ይህ ትግላቸውን ታሳቢ በማድረግ ለይቅርታ ከቀረቡ ደብዳቤ ፅፈው መመለስ ይችላሉ በሚል መኢአድ በሩን ክፍት በማድረጉ ለድብደባና ለወረራ ሆን ብለው ተዘጋጅተው በመምጣት ያሰቡትን ፈፅመዋል ብለዋል፡፡ ከተመረጡት ሽማግሌዎች አንዱ ዶ/ር በዛብህ ደምሴ በበኩላቸው፤ በሽምግልናው ተስማምተው ከሄዱ በኋላ እነ ማሙሸት እንዲህ አይነት ድርጊት ይፈፅማሉ ብለው እንዳላሰቡ ገልፀው፣ ጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ እስኪሰጥ መታገስ አቅቷቸው የሽፍታ ስራ በመስራታቸው ማዘናቸውን በመግለጫው አብራርተዋል፡፡
“ህወሃት ኢህአዴግ ፓርቲው ከአንድነት ጋር ተዋህዶ ለ2007 ምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ እንዳይሆን እነ ማሙሸትን ፓርቲውን እንዲያፈርሱ በማነሳሳትና የውስጥ ችግር ያለብን በማስመሰል እምነት እንድናጣ እያደረግን ነው” ያሉት አቶ አበባው፤ ይህ ህገ ወጥ ድርጊት በአስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን ብለዋል፡፡
አቶ ማሙሸት አማረ በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ የምርጫ ቦርድ፤ ተላላኪ ውህደት አደናቃፊ የተባልንበትን ሂደት ወደ ፍ/ቤት ወስደን በስም ማጥፋት “ክስ እንመሰርታለን” ያሉ ሲሆን “እርቅ ተፈፅሞ እሁድ እለት ከቀጠሩን በኋላ ዱላና ገጀራ የያዙ በፓርቲው ውስጥ አባል ያልሆኑ ከ20-25 የሚጠጉ ሰዎች ጽ/ቤት ግቢ ውስጥ ሆነው እንዳይገቡ እንደከለከሏቸው፣ የኢቴቪ ጋዜጠኞች፣ ፖሊስም ሆነ ደህንነት ይዘው እንዳልሄዱ አቶ ማሙሸት ገልፀዋል፡፡
“ውህደት አደናቃፊ ናችሁ ለተባልነው ጉዳይ ውህደቱ እንዲካሄድ ጀማሪዎቹ እኔና እስር ላይ የሚገኘው አንዷለም አራጌ ነን” ያሉት አቶ ማሙሸት፤ ውህደቱ የተሰናለከው ከ600 የጠቅላላ ጉባኤ አባላት 11ሺህ ያህሉ በጠቅላላ ጉባኤው ባለመሳተፉና ኮረም ባለመሙላቱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም ሰኔ 26 ቀን 2006 ዓ.ም ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ “ህጋዊ አይደላችሁም” ብሎ ደብዳቤ ፅፎላቸዋል ብለዋል፡፡ “ሁሉንም መንፈራገጥ ትተውና መኢአድ የውስጥ ችግሩ ተፈትቶ ትግላችንን ብንቀጥል ይሻላል” ሲሉ ተናግረዋል አቶ ማሙሸት፡፡

Read 3322 times