Saturday, 23 August 2014 11:09

‘ቂፍ፣ ቂፍ ያሰኘሽ እንደ ቄብ ዶሮ…’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

                 እኔ የምለው…ይሄ የቡሄ ነገር… ክፈት በለው በሩን የጌታዬን ክፈት በለው በሩን የእመቤቴን ይባል የነበረው…‘ጌታዬ’ና ‘እመቤቴ’ የተባሉት ቃላት ምነዋ ‘ተሰረዙሳ! አሀ…ከዘንድሮ የእጅ አዙር “ጌታዬ”፣ “እመቤቴ” የበፊቱ እኮ ‘ግልጥና ግልጥ’ ነበራ! ስሙኝማ…የቃላት ነገር ካነሳን አይቀር…እንግዲህ የአዲስ ዓመት ዋዜማም አይደል! እናማ…ከወዲሁ የሆነ…አለ አይደል…በሆነ ጉዳይ ‘ፋና ወጊ’ ምናምን ነገር መሆን አምሮኛል፡፡ ታዲያላችሁ…የዘንድሮ የስብሰባ ቋንቋችን ለምን በአዳራሽና በቲቪ መስኮት ተወስኖ ቀረ የሚል ቁጭት ከዕለታት አንድ ቀን ሊያድርብኝ እንደሚችል ይታወቀኛል፡፡ እናማ…እዛ ሳንደርስ የዓመቱን አስተዋጽኦዬን ባደርግ ምን ይለኛል!…ልክ ነዋ…. እነኛን ቃላት ተጠቅሜ “አይ ላቭ ዩ ሞር ዛን አይ ካን ሴይ” ምናምን ብልስ! “እንትናዬ…ከእኔ ለመለየት መወሰንሽን የነገርሽኝ ዕለት የክርክርሽ አካሄድ ኋላ ቀርና የአፍራሽነት ባህሪይ የተጠናወተው ነበር፡፡

ያነሳሻቸውን ነጥቦች አንጻራዊ በሆነ መልኩ በከፊል ብቀበላቸውም የተንሸዋረረ እይታ እንዳለሽ ግን ሳልጠቅልሽ አላልፍም፡፡ እናማ…እኔን የማንገዋለል ሀሳብ የመጣልሽ ለነገሩ ልዩ ትኩረት ሰጥተሽ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር መክረሽበት ሳይሆን ከግንዛቤ እጥረትና ከልምድ ማነስ መሆን አለበት፡፡ ዙሪያሽን ያሉ የተሳሳተ መረጃ እየሰጡ ሰላምና መረጋጋትሽን የሚረብሹትን ሰዎች ማንነት በንቃት በመከታተል አፍራሽ ምክራቸውን መዋጋት ይኖርብሻል፡፡ እንደ እውነቱ ወሬ ከሚለቅም….ብር የሚለቅም ይሻልሻል ብለው የመከሩሽ ምክር ውሀ የሚያነሳ አይደለም፡፡ ያንቺን አመጡና ለእኔ ነገሩና የእኔን ወሰዱና ለአንቺ ነገሩና ተደላድለው ተኙ አለያዩንና ሲባል ሰምተሽ የለ…” ይሄ ደብዳቤ ገና ከጅምሩ ጠብ፣ ጠብ አለውሳ! “በእርግጥ…በእኔ በኩል አንዳንድ ችግሮች እንዳሉብኝ ግንዛቤ ወስጃለሁ፡፡ ትንሽ ትንሽ መጠጥ ቢጤ መቀማመሴ በቤታችን የመልካም አስተዳደር ሂደት እንቅፋቶች እንደፈጠሩ ይገባኛል፡፡

ግን ደግሞ እንደምታውቂው ዘንድሮ የሚመስሉኝን ሰዎች ሰብስቤ የጋራ ግንባር መፍጠር ካልቻልኩ የበይ ተመልካች ሆኜ መቅረቴ ነው፡፡ ትዝ ካለሽ አንቺን በእኛ ቱባ ሰውዬ የጠረጠርኩሽ ጊዜ ሁኔታውን ያጣሩልኝ የትምህርት ቤት ጓደኞቼና የሰፈር አብሮ አደጎቼ ሳይሆኑ የ‘ፉት’ ቤት ወዳጆቼ ነበሩ፡፡ የዘንድሮ ቅልቅል ደግሞ በዘመድ ጉባኤ ሳይሆን እንደምታውቂው በ‘ፉት’ ዙሪያ ነው፡፡ በአቅሜ አገር በቀሏን ብራንዲ ምናምን በመጠጣቴ የዘላቂ ግብ ችግር እንዳለብኝ መስሎ ሊታይሽ ይችላል፡፡ ሆኖም በእኔ በኩል እነኚህን መጠጦች የምጠጣው ለአገር በቀል ምርቶች ባለኝ ቀናኢነት ነው፡፡ ሆኖም ያመንኩባቸውን ችግሮች ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥቼ እየሠራሁ እገኛለሁ፡፡” ልክ ነዋ…ከተማዋን ሲያዩዋት ‘ፉት’ ማለት ‘የሚቀረፍ ችግር’ መሆኑ ቀርቷላ! እኔ የምለው ህዝቤ ከወሩ ውስጥ ሠላሳ ሰባት ቀን የሚጨልጠው ፈረንካው ከየትኛው ጫፍ ነው የሚቆረጠው! የምር… ግራ ግብት ብሎናል፡፡” (አጽንኦት የእኔ! ቂ…ቂ…ቂ…) “የአንቺን ፈጣን እሺታ ለማስገኘት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ነድፌ ለተግባራዊነታቸው እየተንቀሳቀስኩ ነው፡፡ ለዚህም በሌሎች ሰዎች ተሞክረው ውጤታማ የሆኑ ስትራቴጂዎችን እየፈተሽኩ ነው፡፡

በዚህ በኩል የፈረንሳይ ተሞክሮ ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል በደረሰኝ ጥቆማ መሰረት ድረ ገጾችን እየፈተሽኩ መሆኔን ሳበስርሽ በደስታ ነው፡፡ “ስሚኝማ…አፍ አውጥተሽ አትናገሪ እንጂ እኔ ስጠረጥር ‘ነገርዬው’ ላይ ያለኝ ኋላ ቀርና ያረጀ ያፈጀ አተገባበር ያስከፋሽ ይመስለኛል፡፡ በመሆኑም የፈጠራ ክህሎቴን ተጠቅሜና አግባብነት ያላቸውን ቪዲዮዎች ተመልክቼ በአዲስ አቀራራብ ለመምጣት ተነሳሽነቱ እንዳለኝና ችግሩን በሂደት እንደምቀርፈው ስገልጽልሽ ስጋትሽን እንደሚያስወገደው እርግጠኛ ነኝ፡፡” እንትናዬ… የፌስቡክ ፍሬንዶችሽ ስንት ሺህ ደረሱ! ልክ ነዋ…እኔ እኮ የምለው ዕድሜ ልካቸውን በኖሩበት ሰፈር አምስት ወዳጅ የሌላቸው ሰዎች ዕድም ለፌስቡክ አምስት ሺ የፌስቡክ ወዳጆች አሏቸው፡፡ (ሀያ ከማትሞሉት የፌስቡክ ፍሬንዶቼ የተወሰናችሁ ሰሞኑን ስለምትቀነሱ ቅር እንዳይላችሁማ!) “እናልሽ…የእኔና የአንቺን ጉዳይ ከግብ ለማድረስ ራሴ በራሴ የተቀናጀ ርብርብ አደርጋለሁ፡፡

ታዲያልሸ… እኔ የሚሌኒየም ግብ የአሥር ዓመት ዕቅድ ምናምን እንደሌለኝ ልብ በይ፡፡ ይህ ደብዳቤ በደረሰሽ በማግስቱ ምሳ ሰዓት ላይ እትዬ ሁሉአገርሽ ፍርፍር ቤት እንገናኝ። እንደ ድሮ ‘እኔ እንጀራ ሳይሆን ጸጉሬን ነው ማፈርፈር የምፈልገው’ የምትዪውን ኋላ ቀር አስተሳሰብ ወደዛ አሸቀንጥሪ፡፡” ዐቢይ ነጥብ ማለት ይሄ ነው፡፡ ድጋሚ የሚጠይቅ ድጋሚ ሲጠየቅ እሺ ማለት አለበታ! “ሌላ ደግሞ በወር ሁለት ጊዜ የነበረው የክትፎ ፕሮግራም እንደሚሰረዝ እወቂ፡፡ ሁሉም ነገር በቁጠባ ሆኗል፡፡ አገሪቷ በሌላት ገንዘብ ያለችውን አብቃቅቶ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ቀበቶ ማጥበቅ ሲባል ሰምተሽ የለ! እኔም ቀበቶዬን አጥበቂያለሁ፡፡ ቀበቶዬን ማጥበቄ ምንም እንኳን ገንዘብ ባያመጣልኝ ሆዴ ውስጥ ክፍት የሆነውን ስፍራ ይቀንሰዋል፡፡ ይህም ማለት የወር ወጪዬ ላይ ሚዛን የሚደፋ ለውጥ ያስመዘግባል ማለት አይደል!” ሚዛን የሚደፋ ለውጥ ናፈቀንማ! “እንደገና የጋራ ግንባር በምንፈጥርበት ጊዜ ወጭሽንም ቀንሺልኝ፡፡

ይሄ ጸጉር መደገሚያ ምናምን የምትይው ኋላ ቀርና እኔ ብቻ ማለት እንደሆነ ተረጂው። ሴቱ አንዴም መሠሪያ አጥቶ ጸጉር ሁሉ የብረት ድስት መፈግፈጊያ ሽቦ ሆኗል እሜቲት ድጋሚ ያስፈልግሻል። ለጸጉር መደገሚያ እንደምትዪው ሁሉ ምነዋ አንቺን ለሌላው ነገር ድጋሚ ስትጠይቂ ‘ድሮም መጥፎ ዕድሌ ነው’ እያልሽ የምታማርሪው!” የምናማርርባቸውን ነገሮች ይቀንስልንማ!” “እንግዲህ በመካከላችን ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ግማሽ መንገድ ድረስ ሄጃለሁ፡፡ እሺ ካልሽ መልካም፣ አሻፈረኝ ካልሽ ደግሞ መንገዱን ከፈለግሽ ጨርቅ ከፈለግሽ አቡጀዴ ያድርግልሽ፡፡” “እናማ…የእኔዋ እንትናዬ አንድ የማረጋግጥልሽ ነገር ቢኖር በምንም አይነት ወደዛ ለአምስት ሰዓት ቀጠሮ በዘጠኝ ሰዓት ትመጪበት ወደነበረው ጨለማ ዘመን ከእንግዲህ አንመለስም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በከተማዋ ልዩ ልዩ ክፍሎች እየተካሄደ ያለው የእንትናዬዎች ነጠቃ አላሳሰብኝም አልልም፡፡ አንቺ እንኳን የሚነጥቅሽ መጥቶ “ሊነጥቁኝ ለሚፈልጉ የወጣ የትብብር መልእክት!” የሚል ማስታወቂያ በኤፍ.ኤም. ብትለቂም አይገርምም፡፡

ለዚህ ነው ካለፈው ስርአት ኋላ ቀር አስተሳሰብሽ አላቅቄ ወደ ‘እንደዘመነችው’ አዲስ አበባ ላዘምንሽ እየጣርኩ ያለሁት፡፡” በወሬ ሳይሆን በአስተሳሰብ የምንዘምንበትን ጊዜ ያቅርብልንማ! “የሆነች የቅኔ መጽሐፍ ሳገላብጥ ያየሁትን ልንገርሽ። ምን ትላለች መሰላችሁ… ‘ቂፍ፣ ቂፍ ያሰኘሽ እንደ ቄብ ዶሮ፣ ለመከራ ለአሳርሽ ኖሮ፡፡’ አሪፍ አባባል አይደል! ‘ጦቢያ’ ውስጥ አሳርና መከራ ቅርብ ስለሆኑ ቂፍ ቂፍ አታብዥማ! ዘንድሮ እንዳንቺ በምኑም በምናምኑም እንደ ቄብ ዶሮ ‘ቂፍ፣ ቂፍ’ የሚያሰኘው ሰው በዝቷል፡፡ ችግሩ ግን ‘ቂፍ፣ ቂፉ’ ለአሳርና ለመከራ እንደሆነ አለማወቁ! “አሁን መጨረሻ ላስገነዝብሽ የምፈልገው አንድና አንድ ነገር ብቻ ነው፣ ይህ አሻፈረኝ የምትዪው ግትርነትሽ ከእንግዲህ እኔ ዘንድ ዋጋ አይኖረውም፡ ወይ አብረሽ ትጓዣላሽ ወይም ባቡሩ ትቶሽ ይሄዳል፡፡

(ይህ አባባል የሸገርን ቀላል ባቡር አይመለከትም፡፡)” ስሙኝማ…ይሄ ደብዳቤ በእስከሪፕቶ ሳይሆን በወይራ ሽመል የተጻፈ አይመስልም! ልክ ነዋ…አንዳንድ መግለጫዎችና ቃለ መጠይቆች በወይራ ሽመል የተጻፉ እየመሰሉን ተቸገርና! ስሙኝማ…የ“አይ ላቭ ዩ ሞር ዛን አይ ካን ሴይ” ደብዳቤ በዘመኑ ቋንቋ ለመተካት የመጣልኝን ሀሳብ ደግሜ እያሰብኩበት ነው፡፡ አሀ…የፍቅር ደብዳቤ ሳይሆን የጦርነት አዋጅ ምናምን መሰለብኛ! “የውቅያኖስ ጥልቀቱ፣ የፀሐይ ሙቀቱ፣ የጨረቃ ድምቀቱ…” የምትለው ለካስ አሪፍ ነበረችሳ! እንደ ቄብ ዶሮ… “ቂፍ፣ ቂፍ…” ከሚያሰኙ ነገሮች ይጠብቅንማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3374 times