Saturday, 23 August 2014 11:01

በሁለት ሳምንት 11 ጋዜጠኞች ከአገር ለቀው መውጣታቸው - የዓለም ሪከርድ ነው

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(9 votes)

የዘንድሮው የጋዜጠኞች ስደት ለማስተባበል አይመችም!

በቅርቡ ፍትህ ሚኒስቴር በአምስት መፅሄቶችና በአንድ ጋዜጣ ባለቤቶችና አሳታሚዎች ላይ የመሰረተው ክስ ብዙ አላስደነገጠኝም፡፡ እኔን ብቻ ሳይሆን ብዙዎችን ያስደነገጠ አይመስለኝም፡፡ በተለይ በቅርቡ ኢቴቪ የሰራውን በግል ፕሬሱ ውልደትና ዕድገት ላይ የሚያጠነጥን ዶክመንተሪ የተመለከተ ፈፅሞ አይደነግጥም፡፡ (የክስ ቻርጅ ማለት እኮ ነው!) የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና ኢዜአ በግል መፅሄቶች ላይ አሰሩት የተባለው ጥናትም ተመሳሳይ ነው፡፡ (እነ ኢዜአ ላይ ጥናት ላካሂድ ነው!) በነገራችሁ ላይ በጥናቱ ከቀረበው ትንተና በጣም የማረከኝ “የኢኮኖሚውን ዕድገት የካዱ” የምትለዋ ነበረች፡፡ (ሁሉም ክደውታል እኮ!)
እናላችሁ… በመፅሄቶቹ መከሰስ ብዙ ሳልደነግጥ አገር ጥለው ተሰደዱ ሲባል ክው አልኩላችሁ፡፡ የ4ቱ ሲገርመኝ 7ቱ ተደገሙ፡፡ (እንዴት አያስደነግጥ!) እኔማ ቢቸግረኝ … “ስደት” ተፈርዶባቸው ይሆን እንዴ አልኩ - ለራሴ፡፡ በንጉሱ ዘመን “ግዞት” እንደሚባለው ዓይነት! (11 ጋዜጠኞች በሁለት ሳምንት መሰደድ እኮ… በኤርትራም ያልተያዘ አዲስ ሪከርድ ነው!)
እኔ ግን እኒህ ሁሉ ነገሮች ባይፈጠሩ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ (አንተ ማነህ? እንዳትሉኝ!) ክሱም፤ ስደቱም፤ እስሩም፣ ውዝግቡም… ወዘተ ማለቴ ነው፡፡ ሌላው ሁሉ ቢቀር ኢቴቪ ደጋግሞ ለሚወተውተን “የአገር ገፅታ ግንባታ” አሉታዊ እንጂ አዎንታዊ አስተዋፅኦ ወይም ተፅዕኖ የለውም እኮ (ልብ አድርጉ! ምኞቴን ነው የተነፈስኩት!)
ባለፈው ዓመት ከኤርትራ ቀጥሎ ጋዜጠኛ በማሰር ከዓለም 2ኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጠን ዓለም ዓቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (CPJ) ዘንድሮ ስንተኛ እንደሚለን አሰብኩና አንጀቴ አረረ፡፡ እኔ ኢህአዴግን ብሆን ምን እንደማደርግ ታውቃላችሁ? CPJ ሪፖርት እስኪያወጣ አልጠብቅም፡፡ ፈጥኜ የራሴን ሪፖርት አወጣለሁ፡፡ “11 ጋዜጠኞች ተሰደውብኛል” እላለሁ። (የዘንድሮው ለማስተባበልም አይመችማ!) እርግጠኛ ነኝ የCPJ ሪፖርት በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ የታሰሩትን 6 ጦማርያንና 3 ጋዜጠኞችንም ማካተቱ አይቀርም፡፡ (“በሙያቸው አይደለም” ሲባል አይሰማማ!) ከዚያም ጋዜጠኞች በማሰርና ለስደት በመዳረግ ኢትዮጵያን ከዓለም 1ኛ አድርጓት ቁጭ ይላል፡፡ ለነገሩ ዓምና ጋዜጠኞችን በማሰር ከዓለም ሁለተኛ የተባልነው “እውነት” ከሆነ፣ ዘንድሮ 1ኛነቱን ማንም አይነጥቀንም፡፡ (በCPJ የግምገማ መነፅር ማለቴ ነው!) ዓምና ጋዜጠኞችን በማሰርና በማሰደድ አንደኛ የወጣችውን ኤርትራን መብለጣችን አይቀርም (ኤርትራ ያሏትን ጋዜጠኞች ዓምና በእስርና በስደት ጨርሳለቻ!)
እናም … እኔ ኢህአዴግን ብሆን ይሄ CPJ የተባለ “የጋዜጠኞች ተሟጋች ነኝ ባይ”፤ ሪፖርቱን ከማውጣቱ በፊት ቀድሜ በጋዜጠኞች አያያዝ ያለሁበትን አቋም እገልፅ ነበር፡፡ (ላስተባብል እኮ ነው!) የታሰሩትን የተሰደዱትን፣ የተከሰሱትን… በቁጥር፤ በፆታ፣ መድቤ ይፋ አደርገዋለሁ (ማን ይፈራል ሞት አሉ!) እርግጥ ነው ኑዛዜ ሊመስልብኝ ይችላል፡፡ (ይምሰላ!) ዋናው ነገር የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ነኝ ባዩን ድርጅት ኩም ማድረግ ነው፡፡ አያችሁ … CPJ እንደኛ አገር የጋዜጠኞች ማህበራት ነገሮችን በጥልቀት አይመረምርም፡፡ ለምሳሌ ብሎገሮች ምድባቸው ከጋዜጠኝነት እንዳልሆነ የሰማሁት ከኢትዮጵያ የጋዜጠኛ ማህበር ፕሬዚዳንት እንጂ ከCPJ አይደለም፡፡ (አያችሁ ልዩነት!)
እስካሁን የምመኘውን ተንፍሼአለሁ፡፡ አሁን ደግሞ የምፈልገውን ልተንፍስ፡፡ እኔ የምላችሁ ግን … “መንግስት ሆደ ሰፊ ነው” ሲባል አልነበረም እንዴ? (ሆደ ሰፊነቱ ለእኛ ነው ለጎረቤት አገር?) ግዴለም ሆደ ሰፊነቱም ይቅር… ግን እንደመንግስት ለግሉ ፕሬስ ማደግና ማበብ ምን አበረከተ? (“የኢቴቪ ዶክመንተሪስ?” እንዳትሉኝ!) ከክስ ቻርጅ በፊት የጋዜጠኝነት ስልጠና፣ የአቅም ግንባታ፣ የሙያ ክህሎት፣ ዎርክሾፕ እኮ ቢቀድም ስደትም እስርም ክስም ባልኖረ ነበር፡፡
ሰሞኑን አንድ ወዳጄ በሬዲዮ ሰማሁ ያለውን ባለ 5 ኮከብ ቅንጡ ወህኒ ቤት ታሪክ አጫወተኝ፡፡ ሌላ ስያሜ ጠፍቶለት ነው እንጂ እስር ቤት ለማለት አንኳን ይቸግራል፡፡ ወህኒ ቤቱ ያሉት መዝናኛዎች … ሲኒማ ቤቱ፣ የጂምናስቲክ ማዕከሉ፣ የመዋኛ ገንዳው፣ የቴኒስ ሜዳው … ግርም ድንቅ የሚሉ ናቸው፡፡ (ወዳጄ እንዳጫወተኝ እኮ ነው!) የወዳጄን ጨዋታ አብራን ስትሰማ የነበረችው የ10 ዓመት ልጁ ምን እንዳለች ታውቃላችሁ? “በእናትህ ባቢ.. እዛ አገር ሄደን እንታሰር” አይገርምም ለመታሰር የሚያስመኝ ወህኒ ቤት… ለነገሩ ለባለ 5 ኮከብ ወህኒ ቤት ባለ5 ኮከብ ወንጀለኛ ያስፈልጋል፡፡
ከባለ 5 ኮከብ ወህኒ ቤት በቀጥታ የምንሻገረው ወደ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጎራ ነው፡፡ እኔ የምላችሁ … የኢዴፓ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ሙሼ ሰሙ ራሳቸውን ከፖለቲካ ፓርቲ ማግለላቸውን እንዴት አያችሁት? (የጥሞና ጊዜ ፈልገው እኮ ነው!) እኔማ የእሳቸውን ዜና ባለፈው ሳምንት እዚሁ ጋዜጣ ላይ ሳነብ፣ ከዚህ ቀደም ራሳቸውን ከፓርቲ ፖለቲካ ያገለሉ ሰዎች በዓይነ ህሊናዬ ይመጡብኝ ጀመር፡፡ የኦፌዴኑ አቶ ቡልቻ … የመድረኩ አቶ ስዬ (የቀድሞው የህወሃት ታጋይና የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር) .. የአንድነቷ ወ/ት ብርቱካን (የሃርቫርድ ምሩቅ!) … የመኢአዱ ኢንጂነር ኃይሉ (ቆፍጣናው አዛውንት!)… የአንድነት ሊቀመንበር የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ (የቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት!) የኢዴፓው የቀድሞ መሪ አቶ ልደቱ (የሦስተኛ አማራጭ አቀንቃኝ!) ሌሎችም የዘነጋኋቸው ሳይኖሩ አይቀሩም፡፡ እኒህ ሁሉ በፈቃዳቸው የተገለሉ ናቸው፣ ከጦቢያ የፖለቲካ ንፍቀ ክበብ!
እርግጥ ነው አንዳንድ ከፖለቲካው ተገልለው እቤታቸው መቀመጥ ያለባቸው “ፖለቲከኞች” (በመጃጃት፣ ባለመብሰል፣ በስልጣን ሱሰኝነት፣ በእብሪተኝነት… ዝርዝሩ ብዙ ነው!) ችግሩ ግን ምን መሰላችሁ? እራሳቸው ካልፈለጉ በስተቀር ማንም ሊያገላቸው አይችልም፡፡ አንዳንዴ ምን እላለሁ መሰላችሁ? ምነው የኢህአዴግን የመተካካት ስልት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በኮረጁት! (አጉል ምኞት መሆኑ ይገባኛል!) በነገራችሁ ላይ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ከሞቱ በኋላ ኢህአዴግም መተካካትን አንስቶት አያውቅም እኮ። (ከእሳቸው እረፍት በኋላ የተተካካ አላየሁማ!) እርግጥ ነው… ብዙ የፓርቲው አባላት በመንግስት የኃላፊነት ቦታቸው ላይ በፈፀሙት ሙስና ወህኒ  ወርደዋል፡፡ (ወህኒ መውረድ ግን መተካካት አይደለም!)  
ሳልዘነጋው አንድ ወግ ላውጋችሁ፡፡ አንድ ባልደረባዬ ሁነኛ ጉዳይ ኖሮባት ወደ አንድ የመንግስት መ/ቤት ትሄዳለች - ሰሞኑን ነው፡፡ ለከሰዓት ይቀጥሯታል፡፡ ከሰዓት ተመልሳ ስትሄድ ግን “ለመለስ ሻማ ለማብራት ልንሄድ ነው” አሉና ጥለዋት ውልቅ አሉ፡፡ (የጠ/ሚኒስትሩን ሁለተኛ ሙት ዓመት ለመዘከር ነው!) መለስ ግን የትኛውን የሚመርጡ ይመስላችኋል? ሻማ እንዲበራላቸው ወይስ ሥራ በአግባቡ እንዲሰራ? (እኔ ከኢህአዴግ አላውቅም!)
ወደ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጎራ ልመልሳችሁ። ራሳቸውን ከፖለቲካ ፓርቲ ያገለሉ ፖለቲከኞችን ሳስብ ምን ይታየኛል መሰላችሁ? ተስፋ መቁረጥ! በአገራቸው… በፓርቲያቸው .. በኢህአዴግ… በስልጣን… በራሳቸው ወዘተ… ተስፋ የቆረጡ እየመሰለኝ እኔም ተስፋ እቆርጣለሁ፡፡ እኔ ግን ተስፋ ብቆርጥም መፃፍ አላቆምም። ሌላው ቢቀር ተስፋ ስለቆረጡ ፖለቲከኞች እፅፋለሁ፡፡ (ፖለቲከኞች እንጂ ፀሃፊዎች ተስፋ አይቆርጡም እኮ!) እኔ የምለው ግን ከኢህአዴጎች ውስጥ ራሳቸውን በራሳቸው ከፖለቲካ የሚያገሉ የሉም እንዴ? (አይፈቀድ ይሆናላ!)
እናላችሁ… በዕድሜ ገፋ ያሉት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በከንቱ ከሚለፉ ራሳቸውን ከፖለቲካው ማግለላቸው ለሁላችንም (ለእነሱም … ለእኛም… ለአገርም … ለዓለምም!) የሚበጅ ይመስለኛል፡፡ ለምን መሰላችሁ? አልሆነላቸውማ! (ሥልጣኑን ማለቴ ነው!) ከምሬ እኮ ነው … የአብዛኞቹ ተቃዋሚዎች ግብ ወይም ግብግብ  ኢህአዴግን ከስልጣን አውርዶ ስልጣን መያዝ ብቻ ነው፡፡ (ሥልጣንና ሥልጣን ብቻ!) ለእነሱ ህዝቡን የሥልጣን ባለቤት ማድረግ እኮ ይሄ ነው! ችግሩ ግን ይሄ በቅርቡ እውን የሚሆን አይመስልም፡፡ (ኢህአዴግም የዋዛ አይደለማ!) ተቃዋሚዎች (ያውም ቱባ ቱባዎቹ!) በ97 ምርጫ ህዝቡ የሰጣቸውን ዕድል ከኢህአዴግ ጋር ተባብረው እንዴት አፈር ድሜ እንዳስበሉት አይተነዋል፡፡ (“የወጋ ቢረሳ…” አሉ!) ግባቸው ሥልጣን ብቻ ነው ያልኩት እንደ ኢህአዴግ ልኮንናቸው ፈልጌ እንዳይመስላችሁ፡፡ (ምን ልጠቀም?) እውነት ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ይሄውላችሁ .. ተቃዋሚዎች (ሁሉም አልወጣኝም!)
በአገሪቱ ውስጥ ዲሞክራሲ እንዲሰፍንና እንዲፋፋ ቢፈልጉ ኖሮ ቤተመንግስት ብቻ ሳይሆን ፓርላማ መግባትም ያጓጓቸው ነበር፡፡ (ጉጉት ፓርላማ አያስገባም እንዳትሉኝ!) ኢህአዴግ በሚለው መንገድ ባይሆንም ዲሞክራሲ ሂደት መሆኑን ተረድተው በአንድ ዙር ምርጫ ሁሉም ነገር ካልተለወጠ ብለው አይፈጠሙም ነበር፡፡ በዚያ ላይ በየፓርቲው ውስጥ የምናየውና የምንሰማው ግጭትና ፍጭት፣ መናቆርና መቃቃር፣ መወጋገዝና ዱላ መማዘዝ… (ሰሞኑን በመኢአድ የተከሰተውን ልብ ይሏል!) ለዲሞክራሲና ለስልጡን የፖለቲካ ባህል ዝግጁ  አለመሆናቸውን ይጠቁመናል፡፡ ሰው እንዴት ዘመኑን አይመስልም? (21ኛውን ክ/ዘመን ማለቴ ነው!) እናላችሁ… በፖለቲካው ውስጥ ያረጁ ትያፈጁት ቦታ ሲለቁ… ገለል ሲሉ… ግሩም ነው (አይሉም እንጂ!) ነገር ግን እንደ እነ አቶ ሙሼ ሰሙ፣ ወይም ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ያሉት ከፖለቲካው ንፍቀ ክበብ መገለላቸው የሳሳውን የተቃዋሚ ጎራ ጭርሱኑ ኦና እንዳያደርገው ያሰጋል (ወላድ በድባብ ትሂድ እንዳትሉኝ!)
እኔ የምለው ግን… ይሄ ትግልን ዳር ሳያደርሱ  ትምህርቴ… ትዳሬ… ቤተሰቤ… የሚሉት ነገር አግባብ ነው እንዴ? (በትምህርት ሰበብ ስንቱ ሸወደን?!) እርግጠኛ ነኝ የአውራ ፓርቲ አባል ቢሆኑ ኖሮ ይሄ ሁሉ ሰበብ የለም ነበር፡፡ (በኢህአዴጎች አይተነዋላ!) የሆነ ሆኖ ግን ማስገደድ አንችልም፡፡ ራሳቸውን ከፖለቲካ ያገለሉትን ሁሉ “መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቸው” ብለናል! (ምርቃት ነው ተብሎ የለ!)

Read 2783 times