Saturday, 23 August 2014 10:51

የምስራቅ አፍሪካ የእጅ ኳስ ሻምፒዮና ይካሄዳል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

                 የምስራቅ አፍሪካ የእጅ ኳስ ሻምፒዮና በኢትዮጵያ የወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በሚገኘው ዘመናዊ ጅምናዚዬም በነገው እለት ሊጀመር ነው። ውድድሩን ዓለምአቀፉ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን (IHF) የሚያዘጋጀው ሲሆን በአፍሪካ ደረጃ በዞን አምስት የሚገኙት ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ሱማሌና ሱዳን ይሳተፉበታል፡፡ አራቱ አገራት ‹‹ቻሌንጅ ትሮፊ›› በሚል ስያሜ ከነገ ጀምሮ እስከ ሳምንቱ አጋማሽ የሚካሄደው የምስራቅ አፍሪካ የእጅ ኳስ ሻምፒዮናው ላይ የሚካፈሉት በሁለቱም ፆታዎች ዕድሜያቸው ከ19 ዓመት በታች የሆኑ ስፖርተኞችን በማስመዝገብ ነው፡፡ በሁለቱም ፆታዎች ሻምፒዮን የሚሆኑት ብሄራዊ ቡድኖች የምስራቅ አፍሪካ ዞንን በመወከል በአፍሪካ የእጅ ኳስ ሻምፒዮና ላይ ተወዳዳሪ ይሆናሉ፡፡ በትንሿ ስታድዬም ዙሪያ እና በአራት ኪሎ የስፖርት ማዕከል ለሚገኙ የስፖርት አፍቃሪዎች ውድድሩ በሚካሄድባቸው ቀናት የትራንስፖርት አገልግሎት የተዘጋጀ ሲሆን ሻምፒዮናውን በወጣቶች ስፖርት አካዳሚው ጂምናዚያም በመገኘት በነፃ መከታተል እንደሚቻል ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኮማንደር ደመላሽ ካሳዬ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ውድድሩን ለማዘጋጀት የበቃችው በመወዳደርያ ስፍራ ጥራት ተቀባይነት በማግኘቷ ነው፡፡

የዞን ሻምፒዮናው የአገሪቱን መልካም ገጽታ የሚገነባ ይሆናል ያሉት ዶ/ር ኮማንደር ደመላሽ በሁለቱም ፆታዎች ያሉትን የኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድኖች በአፍሪካና በዓለም አቀፍ በየደረጃው የሚኖራቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ተስፋ ይጠልበታል ብለዋል፡፡ ዓለምአቀፉ የእጅ ኳስ ፌዴሬሸን ከውድድሩ በተያያዘ የዳኝነት እና የአሰልጣኝነት ኮርሶችን እንደሚያዘጋጅ የገለፁት የፌደሬሽኑ ሃላፊዎች በስልጠናው 26 ኢትዮጵያውያን እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ስፖርት ትኩረት አጥቶ መቆየቱን በጋዜጣዊ መግለጫው ያመለከቱት ዶ/ር ኮማንደር ደመላሽ ፤ የምስራቅ አፍሪካ ሻምፒዮናውን በማዘጋጀት ይህን ሁኔታ ለመቀየር አቅጣጫ መያዙን አስረድተው፤ ከአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽኖች ጋር ያለውን ግንኙነት የምናጠናክርባቸው ስራዎች ይከናወናሉ ብለዋል፡ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ወደፊትም በርካታ ውድድሮችን በማዘጋጀት ወጣቶች በእጅ ኳስ ስፖርት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ፍላጐት እንዳለውም አስታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ሃላፊ የሆኑትና በአፍሪካ ያሉ 10 አገራት በመወከል በኢንተርናሽናል እጅ ኳስ ዳኝነት በመስራት ብቸኛው የሆኑት አቶ ፈረደ ፍትሃነገስት የምስራቅ አፍሪካ ሻምፒዮናው መስተንግዶ ለስፖርቱ ከፍተኛ መነቃቃት የሚፈጥር ብለውታል፡፡ በሁለቱም ፆታዎች ያሉት የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ብሄራዊ ቡድኖች ከሐምሌ 22 ጀምሮ በአራት ኪሎ የስፖርት ማእከል የተሟላ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

አቶ ፈረደ ፍትሃነገስት ፤ በቻሌንጅ ትሮፊው ሁለቱም ብሔራዊ ቡድኖች የዞኑን ሻምፒዮንነት በማሳካት በአፍሪካ ደረጃ የመሳተፍ እድልን በማግኘት ውጤታማ ለመሆን እቅድ አለን ይላሉ። በሁለቱም ፆታዎች ያሉትን ብሔራዊ ቡድኖች ለማቋቋም ሰፊ ትኩረት በመስጠት ሠርተናል ያሉት የቴክኒክ ኃላፊው፣ ሻሸመኔ በተደረገው የፕሮጀክት ውድድር፣ በባህርዳር ለተደረገው የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎችና ለአዲስ አበባ በሚደረገው የክለቦች ሻምፒዮና ያሉ ስፖርተኞችና ለአዲስ አበባ በሚደረገው የክለቦች ሻምፒዮና ያሉ ስፖርተኞችን ተከታትለን ምልመላ አድርገናል ብለዋል፡፡ በመጀመሪያ ከሐምሌ 12-17 20 ከኦሮሚያ ከአማራ፣ ከትግራይ፣ ከጋምቤላ እና ከአዲስ አበባ “20 ስፖርተኞችን ለሴቶች ብሔራዊ ቡድን መልምለናል ያሉት አቶ ፈረደ፣ የጋምቤላ ክልል ምላሽ አለመስጠቱን ጠቁመው በተካሄደው ምርጫ የሴቶች ቡድኑ ከሐምሌ 17 ጀምሮ ተዘጋጅቷል፡፡ ለወንዶች ብሔራዊ ቡድን ደግሞ ከሐምሌ 17-20 ምርጫ መደረጉን የገለፁት የቴክኒኩ ኃላፊው ከአዲስ አበባ ክለቦች ከትግራይ፣ ከደቡብ፣ ከሶማልያና ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጡ ተጨዋቾች መርጠናል፣ ከኦሮሚያ ክልል የተመረጡ ተጨዋቾች መልስ አልሰጡንም የወንዶች ቡድኑ ከሐምሌ 22 ጀምሮ በአራት ኪሎ የስፖርት ማዕከል ልምምድ መስራቱንም ተናግረዋል፡፡ ሁለቱ የወንድና የሴት ብሔራዊ ቡድኖች አንድ ዋና አሰልጣኝና ሌሎች አራት ረዳት አሰልጣኞች ልምምድ ያሰሯቸዋል፡፡ ሁሉም አሰልጣኞች ከሻምፒዮናው በተያያዘ በሚዘጋጀው ስልጠና ተሳታፊ ሲሆን ከአራት ክልሎች ተወጣጥተው የተመረጡ በመሆናቸው በየክልላቸው ስፖርቱን እንዲያስፋፋ ይጠበቃል፡፡

የእጅ ኳስ ስፖርት የሚጀመረው ከ8 ዓመት ጀምሮ ነው ያሉት አቶ ፈረደ፤ በዚህ በኩል የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የሚያከናውናቸውን መሰረታዊ ተግባራት ለማነቃቃት በመክፈቻው ፕሮግራም ላይ በታዳጊ ህፃናት ስፖርተኞች ትርኢት እናቀርባለን ብለዋል፡፡ የእጅ ኳስ ስፖርትን ከ8-10 ላሉት ታዳጊዎች ስልጠና ለመጀመር ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው የሚሉት የቴክኒክ ኃላፊው አቶ ፈረደ፣ በምስራቅ አፍሪካ ሻምፒዮናው በታዳጊዎቹ ትርዒት ራዕያችንን በማንፀባረቅ በቀጣይ አገር አቀፍ ውድድር ለመጀመር ያለንን እቅድ እናስታውቃለን፡፡ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኮማንደር ደመላሽ ካሳዬ እንዳስረዱት ከምስራቅ አፍሪካ ሻምፒዮናው አዘጋጅነት በተያያዘ በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ፌደሬሽኖች ተጽእኖ ለመፍጠር ፍላጐት አለን ይላሉ፡፡ በተለያዩ የአመራርነት ስፍራዎች ለኢትዮጵያ የሚገባውን ቦታ የምንጠይቅ ይሆናልም ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ባሉት ብሄራዊ ቡድኖች ከአህጉራዊ ውድድሮች መጥፋት የለበትም ያሉት የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት፤ ከዞኑ ሻምፒዮና የተሳካ መስተንግዶ በኋላ በቅርብ ጊዜ ተግባራዊ ለማድረግ ትኩረት የሰጠነው በመላው አፍሪካ ጨዋታዎች የማጣሪያ ውድድር ለመግባት ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ስፖርቱን ለማስፋፋት በዩኒቨርስቲዎች፤ እና በትምህርት ቤቶች ሰፊ እንቅስቃሴዎች ለማድረግ ያቀደ ሲሆን፤ አገር አቀፍ ውድድሮችን በማጠናከር፤ በየክልሎቹ የክለቦችን ብዛት ለማሳደግ፤ በስፖርቱ ሊገኝ የሚችለውን የገቢ ምንጮች በማስፋት ለመስራት ፕሮጀክቶችን ቀርጿል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሲቋቋም በእጅ ኳስ ስፖርት ለመስራት ትኩረት አለመሰጠቱ የሚያሳስብ እንደነበር የሚገልፁት የፌደሬሽኑ ሃላፊዎች ሁኔታው ተገቢ አለመሆኑን በመግለፅ ጥያቄ አቅርበን ስልጠናው በአካዳሚው እንዲሰጥ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡ የእጅ ኳስ ስፖርት በት/ቤቶች፤ በዩኒቨርሲቲዎች፤ በክልሎች እና ክለቦች ሰፊ ተሳትፎ መኖሩን በማገናዘብ የወጣቶች ስፖርት አካዳሚው ለሰጠው አፋጣኝ ምላሽ አድናቆታቸውንም ገልፀዋል፡፡ በአዲስ አበባ እና በሌሎች ክልሎች የእጅ ኳስ ውድድሮችን የሚሳተፉ ክለቦች እየተመናመኑ መምጣታቸውን በተመለከተ በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጥያቄ የቀረበ ሲሆን የፌደሬሽኑ ሃላፊዎች በሰጡት ምላሽ ውድድሮችን በአገር አቀፍ ደረጃ ለማዘጋጀት ካሉት ፈተናዎች ጋር የተያያዘ ችግር እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን በፈለገበት መጠን እንዳይሠራ ዋንኛው ችግር የስፖንሰርሺፕ መንግስታዊ እና የግል ተቋማት በስፖርቱ ለውጥ እና እድገት ሊመጣ እንደሚችል አምነው ሰፊ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች እና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች በማዘጋጀት ፌዴሬሽኑ እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ስፖርተኞች በወቅታዊ የስልጠና ደረጃ እና ሳይንስ ከተሠራባቸው ዓለም አቀፍ ደረጃን የሚያሟሉ ፕሮፌሽኖች ይሆናሉ በማለት ለስፖርት አድማስ አስተያየት የሰጡት ደግሞ የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ዋና አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ሙሉጌታ ግርማ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ የእጅ ኳስ ስፖርት ሜዳዎች መጠናቸው 40 በ20 ሜትር እንደሆነ የገለፁት ዋና አሰልጣኙ ስፖርቱ ከፍተኛ ፍጥነት ቅልጥፍና የሚጠይቅ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

የኢትዮጵያ ተጨዋቾችን በአሁኑ ጊዜ ያላቸውን ልዩ ብቃት በአሃዛዊ ስሌት ሲያስረዱም አንድ ምርጥ የእጅ ኳስ ስፖርተኛ 30 ሜትር በ4 ሰከንድ ከ1 ሚሊ ማይክሮ ሰኮንድ ይሸፍናል ብለው ብዙዎቹ ወንድ ተጨዋቾቻችን የተጠቀሰውን ርቀት በ4 ሰከንድ ከ30 ሚሊ ማይክሮ ሰኮንድ ይሮጡታል በዚህ አስገራሚ ብቃት ላይ ለ1 ዓመትና ሁለት ዓመት በትኩረት ከተሠራ ፕሮፌሽናል ደረጃ የሚበቁ ስፖርተኞችን በብዛት ማግኘት ይቻላል ብለዋል፡፡ በአውሮፓ ያሉ ፕሮፌሽናል የእጅ ኳስ ስፖርተኞች ተመሳሳይ ርቀትን በአማካይ በ4 ሰኮንድ 60 ሚሊ ማይክሮ ሰኮንድ የሚሸፍኑ በመሆናቸው ለኢትዮጵያውያን ስኬታማነት ማሳያ የሚሆን ነው ያሉት ኢንስትራክተሩ፤ በአውሮፓ የእጅ ኳስ ስፖርት በከፍተኛ ደረጃ በክለቦች ውድድር እንደሚደረግበት በማመልከት ኢትዮጵያውያን ፕሮፌሽናል የእጅ ኳስ ስፖርተኞች ለባርሴሎና፣ ለሪያልማድሪድ እና ለሌሎች የአውሮፓ ክለቦች ማብቃት ይችላል፤ ኬንያ ከ50 በላይ የእጅ ኳስ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች አፍርታለች በማለትም ማስረጃቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ኢንስትራክተር ሙሉጌታ ግርማ ኢትዮጵያ በእጅ ኳስ ስፖርት በአፍሪካ ሻምፒዮና፣ በኦሎምፒክ ውድድሮች ለማብቃት ከዞኑ ሻምፒዮና ከሚገኙ ተመክሮዎች ተነስቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ፡፡ ዋና አሰልጣኙ በሰጡት ምክር በመላው አገሪቱ ቁመታቸው ከ1.91 እስከ 2.08 ያላቸው ወጣቶችን በመፈለግ የሚሰራበት ፕሮጀክት በመቅረፅና የስልጠና ባለሙያዎችን በወቅታዊ እውቀትና የብቃት ደረጃ አሰባስቦ በመንቀሳቀስ በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ስኬታማ መሆን እንደሚቻል እምነቴ ነው ብለዋል፡፡

Read 2376 times