Saturday, 16 August 2014 11:16

የአውሮፓ 5 ታላላቅ ሊጎች በ2014 - 15

Written by 
Rate this item
(4 votes)

     ብራዚል ካዘጋጀችው 20ኛው ዓለም ዋንጫ 1 ወር ካለፈ በኋላ የዓለም ስፖርት አፍቃሪ ትኩረት ወደ አምስቱ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ዞሮ ቆይቷል፡፡ አምስቱ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ፤ የስፔን ፕሪሚዬራ ሊጋ፤ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ፤ የጣሊያን ሴሪኤና የፈረንሳይ ሊግ 1 ሲሆኑ በሚቀጥሉት 9 ወራት በከፍተኛ ደረጃ ፉክክር ይደረግባቸዋል፡፡ ከሊጎቹ ከተከፈተ አንድ ሳምንት ያለፈው የፈረንሳይ ሊግ 1 ነው፡፡ ዛሬ እና ነገ  የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ሲጀመር፤ በሚቀጥለው ሳምንት  የስፔኑ ፕሪሚዬራ ሊጋና የጀርመኑ ቦንደስ ሊጋ እንዲሁም የጣሊያን ሴሪ ኤ ከሁለት ሳምንት በኋላ ይከፈታሉ፡፡
ዩሮ ቶፕ ፉት የተባለ የእግር ኳስ ድረገፅ በሊግና በአህጉራዊ ሻምፒዮናዎች  ያለውን የፉክክር ደረጃና ውጤት በማስላት  ለሊጎቹ ባወጣው ደረጃ የስፔኑ ፕሪሚዬራ ሊጋ በ5887 ነጥብ አንደኛ መሆኑን አመልክቷል፡፡ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በ5298 ነጥብ፤ የጣሊያኑ ሴሪ ኤ በ3428 ነጥብ እንዲሁም የጀርመን ቦንደስ ሊጋ በ3348 ነጥብ እስከ 4ኛ ደረጃ ተከታትለው ሲወስዱ፤ የፈረንሳዩ ሊግ 1 በ1877 ነጥብ አምስተኛነቱን 2520 ነጥብ ባስመዘገበው የፖርቱጋሉ ሊግ ተነጥቆ 6ኛ ነው፡፡
በሌላ በኩል ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አሃዛዊ እና ታሪካዊ መረጃዎች አሰባሳቢ ተቋም የሆነው አይኤፍኤችኤችኤስ በ2014 የዓለም ምርጥ የእግር ኳስ ሊጎች  ደረጃ ባወጣበት ወቅት በ1155 ነጥብ አንደኛ የሆነው የስፔኑ ፕሪሚዬራ ሊጋ ነው፡፡ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በ1128 ነጥብ፤ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ በ1056 ነጥብ እንዲሁም የጣሊያኑ ሴሪ ኤ በ927 ነጥብ እስከ 4ኛ ደረጃ ተከታትለው ሲወስዱ፤ የፈረንሳዩ ሊግ 1 በ796 ነጥብ በብራዚል እና በአርጀንቲና የሊግ ውድድሮች ተበልጦ 7ኛ ነው፡፡ ከዓለም ዋንጫ በኋላ የአውሮፓ ክለቦች   ለአዲሱ የ2014 — 15 የውድድር ዘመን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ሰንብተዋል፡፡ ላለፉት 6 ሳምንታት ደግሞ በክረምቱ የተጨዋቾች ዝውውር ገበያ ተሯሩጠዋል፡፡  በውድድር ዘመኑ  ተጠናክረው ለመቅረብ በተለይ በአምስቱ ትልልቅ የአውሮፓ ሊጎች የሚገኙ 25 ክለቦች በገበያው ንቁ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡ በ2014 15 የውድድር ዘመን የስፔን ላሊጋ ባርሴሎና ሪያል ማድሪድ ባሰባሰቧቸው ምርጥ ተጨዋቾች ትኩረት ቢያገኝም ከአምስት በላይ የእንግሊዝ ክለቦች በዝውውር ገበያው በርካታ ምርጥ ተጨዋቾችን በማስፈረም መጠናከራቸው ለፕሪሚዬር ሊጉ ሻምፒዮናነት ከባድ ፉክክር እንዲጠበቅ ምክንያት ሆኗል፡፡ ሁለቱ ሊጎች በክረምቱ የዝውውር መስኮት የነበራቸው ወጭ የገበያውን 63 በመቶውን የሸፈነ ነው፡፡ በአንፃሩ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ እና የጣሊያን ሴሪኤ ክለቦች ወጭያቸው በግማሽ ያነሰ ነበር፡፡
ከአውሮፓ ሊጎች ሁለቱ የስፔን ክለቦች ባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ 190.2 ሚሊዮን ዶላር እና 146.3 ሚሊዮን ዶላር ከፍተኛውን ወጭ ያስመዘገቡ ናቸው፡፡ ቼልሲ 124.36  ፤ማን ዩናይትድ 97.62 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም የፈረንሳዩ ፒኤስጂ እና የስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድ እያንዳንዳቸው 78.20 ሚሊዮን ዶላር በላይ  ወጭ  እስከ አምስት ያለውን ተከታታይ ደረጃ አግኝተዋል፡፡በዝውውር ገበያው ውድ ሂሳብ የወጣው በባርሴሎና ሲሆን አወዛጋቢውን የኡራጋይ ተጨዋች ሊውስ ስዋሬዝ በ89.3 ሚሊዮን ዶላር ከሊቨርፑል ላይ የገዛበት ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ከፍተኛው ሂሳብ የተከፈለው በሪያል ማድሪድ ሲሆን ኮሎምቢያዊውን ጄምስ ሮድሪጌዝ ከፈረንሳዩ ክለብ ሞናኮ ለማስፈረም 88.2 ሚሊዮን ዶላር አውጥቷል፡፡ ቼልሲ ብራዚላዊውን ዴቭድ ሊውስ ለፈረንሳዩ ክለብ ፓሪስ ሴንትዠርመን የሸጠበት 54.57 ሚሊዮን ዶላር ሂሳብ ፤ አሁንም ቼልሲ ስፔናዊውን ዲያጎ ኮስታ ከአትሌቲኮ ማድሪድ በ41.9 ሚሊዮን ዶላር የገዛበት እንዲሁም አርሰናል ቺሊያዊውን አጥቂ አሌክሲ ሳንቼዝ ከባርሴሎና ለማዛወር የከፈለው 41.67 ሚሊዮን ዶላር ተከታታይ ደረጃ ይወስዳሉ፡፡
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዛሬ ሲጀመር  ሌስተር ሲቲ፤ በርንሌይ እና ኪውንስ ፓርክ ሬንጀርስ ሊጉን የተቀላቀሉ አዲስ ክለቦች ናቸው፡፡ በውድድር ዘመኑ ከሚጠበቁ ፍጥጫዎች ዋንኛው በአዲሱ የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሊውስ ቫንጋል እና በቼልሲው ጆሴ ሞውሪንሆ መካከል ለሻምፒዮናነት የሚደረገው እሰጥ አገባ የሞላበት ፉክክር ነው፡፡ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ጨምሮ በተለያዩ ሊጎች አራት ክለቦችን ለሊግ ሻምፒዮናነት ያበቁት ሆላንዳዊው ሊውስ ቫንጋል  የማንችስተር ዩናይትድን የሃያልነት ክብር ለመመለስ ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡
በዛሬዎቹ የመክፈቻ ጨዋታዎች ለዋንጫ ከሚፎካከሩት አምስቱ ክለቦች መካከል የሚጫወቱት ከሜዳው ውጭ ኪውፒአርን የሚገጥመው ቼልሲ እና በኦልድትራፎርድ ስዋንሴን የሚያስተናግደው ማንዩናይትድ ይሆናሉ፡፡ ሌሎቹ ትልልቅ ክለቦች በነገው እለት የመክፈቻ ግጥሚያቸውን ያደርጋሉ፡፡ ያለፈው ዓመት የፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮን ማንቸስተር ሲቲ የውድድር ዘመኑን የሚከፍተው ከሜዳው ውጭ ከኒውካስትል ዩናይትድ ጋር በሚያደርገው ፍልሚያ ነው፡፡ በሌላ በኩል ባለፈው የውድድር ዘመን የኤፍ ኤካፕ ዋንጫን ያነሳውና ከሳምንት በፊት የሊግ ካፕ ዋንጫን ማንቸስተር ሲቲን በመርታት የውድድር ዘመኑን በዋንጫ ድል የከፈተው አርሰናል በሜዳው ከክሪስታል ፓላስ ጋር ይጫወታል፡፡ በሌላ በኩል በታሪኩ ለ84ኛ ጊዜ በሚደረገው የስፔኑ ፕሪሚዬራ ሊጋ ከሚሳተፉ 20 ክለቦች ሰባቱ አዳዲስ አሰልጣኞች በመያዝ በውድድሩ ሲገቡ ባርሴሎና፤ ዲፖርቲቮ ላካሩኛ እና ሴልታ ቪጎ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ላሊጋው ከመጀመሩ አንድ ወር ቀደም ብሎ ማነጋገር የጀመረው ሊውስ ስዋሬዝ በባርሴሎና ክለብ የሚኖረው ሚና ነው፡፡ በክለቡ ባርሴሎና ከኔይማር እና ከሜሲ ጋር የሚጫወትበት አሰላለፍ እና ፉክክር ማነጋገሩን ቀጥሏል፡፡ ስዋሬዝ ንክሻውን ስላለመድገሙ በተነሱ ክርክሮችም ሰፊ ሽፋን ሲያገኝ ሰንብቷል፡፡

Read 3129 times