Saturday, 16 August 2014 11:15

እግር ኳስ የቢሊዬነሮች መናሐርያ ሆኗል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ባለፉት 10 ዓመታት በዓለም እግር ኳስ የቢሊዬነሮች ሚና እና የኢንቨስትመንት ድርሻ እያደገ መጥቷል፡፡ በተለይ በአውሮፓ አምስት ታላላቅ ሊጎች   በቢሊዬነሮች ሙሉ ለሙሉ በባለቤትነት በመያዛቸውና በከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ ኢንቨስት ስለተደረገባቸው  የፉክክር ደረጃቸውን ያሳደጉ ከ10 በላይ ክለቦች ናቸው፡፡ በአንፃሩ  የቢሊዬነሮች ኢንቨስትመንት ያለደረሰላቸው በርካታ የአውሮፓ  ክለቦች ምንም እንኳን በየሊጎቹ በቴሌቭዥን ስርጭት መብት እና በተያያዥ ንግዶች  ገቢያቸው ቢጠናከርም በዋንጫ ተፎካካሪነታቸው ያን ያህል እየተሳካላቸው አይደለም፡፡  በክለቦች ደረጃ በሚደረጉ የውስጥ ውድድሮች እና አህጉራዊ ሻምፒዮናዎች ላይ በሚገኝ ስኬት ቢሊዬነሮች ተማርከዋል፡፡ ወደ እግር ኳሱ የመሳባቸው ዋና ምክንያት ትርፋማነቱ  እንደሆነም ይገለፃል፡፡
ታዋቂው የቢዝነስ መፅሄት ፎርብስ በሰራው ጥናት  መሰረት በመላው ዓለም በእግር ኳስ ክለብ  ሙሉ ባለቤትነት እና የአክሲዮን ድርሻ ያላቸው ቢሊዬነሮች ከ50 በላይ ሆነዋል፡፡ እነዚህ ቢሊዬነሮች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የተሳካላቸው ሲሆኑ አሜሪካውያን ነጋዴዎች፤ ኤስያውያን  ቱጃሮች፤ የአረቡ ዓለም ንጉሳውያን ቤተሰብ አባላት፤ የራሽያ ቢሊየነሮች ዋና ዋናዎቹ  ናቸው፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ተወዳዳሪ ከሆኑ 20 ክለቦች መካከል 7 ያህሉ ከሌላ አገር በመጡ ቢሊዬነር ኢንቨስተሮች የተያዙ ናቸው፡፡  ባለፉት ሶስት እና አራት ዓመታት የቢሊዬነሮችን ትኩረት በመሳብ የስፔንና የፈረንሳይ ክለቦችም እየቀናቸው ናቸው፡፡
የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች በአፍሪካ፤በኤስያ በዓረቡ ዓለም እና በሰሜን አሜሪካ በሚያገኙት ትኩረት ቢሊዬነሮቹ  ይማረካሉ። ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በመላው ዓለም ለሚያንቀሳቅሱባቸው ኩባንያዎች የክለቦቹ ስኬት አስደናቂ የገፅታ ግንባታ ያስገኝላቸዋል። የእግር ኳስ ክለቦች እንደ አሰተማማኝ  ንብረት መታየታቸው ሌላው ጉልህ ጠቀሜታ ነው፡፡ በዓለም እግር ኳስ ክለቦች  አጠቃላይ የዋጋ ግምት በተሰራው ደረጃ  የስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ በ3.4 ቢሊዮን ዶላር ዋጋው በመተመን አንደኛ ደረጃ  ሲይዝ ባርሴሎና በ3.2 ቢሊዮን ዶላር ይከተለዋል፡፡  ማንችስተር ዩናይትድ በ3.17 ቢሊዮን ዶላር ሶስተኛ ደረጃ ሲያገኝ፤ ባየር ሙኒክ በ1.85 ቢሊዮን ዶላር፤ አርሰናል በ1.33 ቢሊዮን ዶላር፤ ቼልሲ በ901 ሚሊዮን ዶላር፤ ማንችስተር ሲቲ በ689 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ሊቨርፑል በ651 ሚሊዮን ዶላር አጠቃላይ የዋጋ ተመናቸው ተከታታይ ደረጃ አላቸው፡፡ እንደ ፎርብስ መፅሄት ጥናት በአጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው እስከ 20 ደረጃ የተሰጣቸው የእግር ኳስ ክለቦች አማካይ ተመን  968 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን ይህም ካለፈው የውድድር ዘመን በ26 በመቶ እድገት ማሳየቱን ጠቁሟል፡፡
በእግር ኳስ ስፖርት እየተጠናከረ የመጣው የቢሊዬነሮች ኢንቨስትመንት  በየሊጎቹ ለዋንጫ የሚፎካከሩ ክለቦችን አብዝቷል፡፡ የክለቦችን የተጨዋች ስብስብ በማጠናከር እና የዝውውር እና የደሞዝ ክፍያቸውን በማሳደግ ተጠቃሚ እያደረጋቸው ነው፡፡ የቢሊዬነሮቹ ኢንቨስትመንት  ጎን ለጎን አሉታዊ ተፅኖዎችን ማሳደሩም አልቀረም፡፡ በአውሮፓ አምስት ታላላቅ ሊጎች በቢሊዬነሮቹ በጀት የሚንቀሳቅሱ  ክለቦች ውስጥ ያሉ ተጨዋቾች፤ አሰልጣኞች እና ሌሎች ባለሙያዎች በየክለቦቻቸው ለረጅም ጊዜ በታማኝነት የሚያገለግሉበትን ሁኔታ ሲያቀዘቅዝባቸው፤ ደጋፊዎች በክለቦቻቸው ያላቸውን ሚናም በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ መሆኑ  ይተቻል፡፡  
አብራሞቪችና ሌሎች የሩስያ ቱጃሮች
በእግር ኳስ ክለብ ባለቤትነት  በጣም ስኬታማ የሚባሉትና በፈርቀዳጅነት የሚጠቀሱት ራሽያዊው ሮማን አብራሞቪች ናቸው። የነዳጅ ኩባንያ ባለቤት የሆኑት አብራሞቪች በቼልሲ ክለብ ባለቤትነት 12 ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡  በመጀመርያዎቹ 3 እና አራት አመታት ብዙም ባይሳካላቸውም ካለፉት 5 ዓመታት ወዲህ ግን የላቁ ክብሮችን  በማግኘት  ተክሰዋል፡፡
አብራሞቪች ቼልሲን  በባለቤትነት ከያዙት በኋላ የተገኙ ስኬቶች ገንዘብ ያመጣቸው እንጅ በተመጣጣኝ የፉክክር ደረጃ የተገኙ አይደለም በሚል በተደጋጋሚ ትችት ቀርቧል፡፡ የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ 3 የፕሪሚዬር ሊግ፤ አራት የኤፍኤ ካፕ፤ 2 የሊግ ካፕ እና በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮን በመሆን የሻምፒዮንስ ሊግ እና የዩሮፓ ሊግ የዋንጫ ክብሮችን  አግኝቷል፡፡  አብራሞቪች ክለቡን ከያዙት ግዜ ጀምሮ ከ1.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጭ አድርገውበታል፡፡ በየዝውውር መስኮቱ ወቅት በአማካይ 50 ሚሊዮን ዶላር በማውጣት ምርጥ ተጨዋች የሚገዛ ክለብ ሆኗል። አብራሞቪች ቼልሲን የገዙት በ334 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ አሁን ሊሸጡት ቢፈልጉ ክለቡ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያወጣል፡፡
ከአብራሞቪች በኋላ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የአውሮፓ ትልልቅ ሊጎች እና በአገራቸው ባሉ ክለቦችም ከ5 በላይ የራሽያ ቢሊዬነሮች  ኢንቨስት አድርገዋል፡፡ አንደኛው ቢሊዬነር በአርሰናል ክለብ ድርሻ ያላቸውና ክለቡ የሚመካበትን የኤምሬትስ ስታድዬም እንዲገነባ ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸው አሊሸር ኡስማኖቭ ናቸው፡፡ ሌላኛው ደግሞ የፈረንሳይ ክለብ የሆነውን ሞናኮን በባለቤትነት የያዙት ዲምትሪ ራይቦሎቬሌቭ ናቸው፡፡ ሌሎቹ የራሽያ ቢሊዬነሮች በአገሮቻቸው ባሉ ክለቦችም አስደናቂ ኢንቨስትመንት አድርገዋል፡፡ የእንግሊዙ ክለብ ቼልሲ ባለቤት አብራሞቪች በራሽያ ያለውን ዜንት ፒትስበርግ በመደገፍ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በ2011 እኤአ  ከተመሰረተ 20 ዓመት የሚሆነው ወጣት ክለብ አንዚ ማክቻሃቻካላ ሌላ   ቢሊዬነር በመግዛት ወደ አህጉራዊ ውድድር አሳድገውታል፡፡
ሼክ መንሱንና የዓረቡ ዓለም ኢንቨስትመንት
የመካከለኛው ምስራቅ በተለይ በኳታር እና በዱባይ ያሉ የንጉሳውያን ቤተሰብ አባላት ካለፉት አምስት አመታት ወዲህ በአውሮፓ እግር ኳስ በስፋት ተሰማርተዋል፡፡ እነዚህ የአረቡ አለም ቢሊዬነሮች ክለቦችን በባለቤትነት በመያዝ ብቻ ሳይሆን በትልልቅ ኩባንያዎቻቸው የማልያ፤ የስታድዬም ግንባታ የስፖንሰርሺፕ ድጋፎችን በስፋት በመስጠት ጥቂት የማይባሉ ክለቦችን አጠናክረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአውሮፓ እግር ኳስ የመካከለኛው ምስራቅ አየር መንገዶች ከ20 የአውሮፓ ትልልቅ ክለቦች በሰባቱ ስፖንሰርሺፕ ሰጥተዋል፡፡ ኳታር ኤርላይንስ በባርሴሎና፤ ፍላይ ኤምሬትስ በሪያል ማድሪድ፤ በፒኤስጂ፤ በአርሰናል እና በኤሲ ሚላን፤ ኢትሃድ ኤርዌይስ በማንችስተር ሲቲ የማልያ ስፖንሰሮች  ናቸው። ከዓረቡ ዓለም የእግር ኳስ ኢንቨስትመንት አድራጊ ቢሊዬነሮች ግዙፍ ለውጥ የታየው በእንግሊዙ ክለብ ማንችስተር ሲቲ ነው። ማንችስተር ሲቲ የአቡዳቢ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለቤቶች በሆኑት የኳታር ንጉሳዊ ቤተሰብ ከ6 ዓመት በፊት ተይዟል፡፡ የአቡዳቢ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ያለው ሃብት እስከ  22 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ነው፡፡ የሚያስተዳድሩት ሼክ መንሱን ቢን ዛይድ  ሲቲን የገዙት በ321 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንታቸውም ነበር። ባለፉት 5 ዓመታት ክለቡን ለማጠናከር ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ፈሰስ አድርገዋል፡፡  ማንችስተር ሲቲ በአቡዳቢ ኢንቨስትመንት ግሩፕ መደገፍ ከጀመረ ወዲህ ከ44 ዓመት በኋላ የመጀመርያውን የፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮናነት ማግኘቱ እና ከዚያም ሁለተኛውን መድገሙ ይታወቃል፡፡ ባለፉት ሶስት አመታት ክለቡ በእንግሊዝ እና በአውሮፓ ደረጃ የላቀ ውጤት እና ተፎካካሪነት እንዲኖረው ማድረግ ተችሏል፡፡
በ2011 እኤአ ላይ ታዋቂውን ፓሪስ ሴንትዠርመን ባበለቤትነት የያዘው የኳታር ኢንቨስትመንት አውቶሪቲ ነው፡፡ ይህ ባለቤትነት ፒኤስጂን የፈረንሳይ አንደኛ ሃብታም ክለብ አድርጎታል፡፡ ክለቡ ከ20   ዓመታት በኋላ የሊግ ሻምዮን ለመሆን በቅቷል፡፡ ባለቤቶቹ ክለቡን ለማጠናከር በተጨዋቾች ግዢ ብቻ ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ አውጥቷል፡፡
በፕሪሚዬር ሊግ የተማረኩት አሜሪካውያና ኤስያውያን
ቢያንስ በስድስት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች ላይ በባለቤት እና በአክሲዮን ድርሻ ያላቸው አሜሪካውያን ቢሊዬነሮች ናቸው፡፡ ሌርነር በአስቶንቪላ፤ የግሌዘር ቤተሰብ በማንችስተር ዩናይትድ፤ ስታን ክሮንኬ በአርሰናል፤ ኢሊስ ኾርት በሰንደር ላንድ ጆርጅ ኤሊት እና ቶም ሂክስ በሊቨርፑል ኢንቨስት ያደረጉ አሜሪካውያን ናቸው፡፡ የፉልሃምና የሰንደርላንድ ክለቦች ላይ ኢንቨስት ያደረጉ ሌሎች ሁለት  ቢሊዬነሮችም አሉ፡፡ አሜሪካውያኑ ከቤዝቦል እና ፉትቦል ክለቦች ባለቤትነት ወደ አትራፊው ፕሪሚዬር ሊግ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎታቸው አድጓል፡፡ በዋናነት በቲቪ ስርጭት ሊጉ በመላው ዓለም የሚያገኘው ሽፋን እና ተወዳጅነት በመማረካቸው ነው፡፡ ኤስያውያንም በአውሮፓ እግር ኳስ ኢንቨስትመንት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ በተለይ በደቡብ ኤስያ ባሉ አገራት ያሉ ቢሊዬነሮች በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ኢንቨስት እያደረጉ ናቸው፡፡  ኪውፒ አር፤ካርዲፍሲቲ፤ ሌስተርሲቲ በኤስያውያን ቢሊዬነሮች ባለቤትነት ተይዘዋል፡፡ ሲንጋፖራዊው ቢሊዬነር ፒተር ሊም የስፔኑን ክለብ ቫሌንሽያ በባለቤትነት የተቆጣጠሩት ባለፈው አመት ነው፡፡ ቢሊዬነሩ ቫሌንሽያን ሲረከቡ የራሳቸው እግር ኳስ ክለብ በባለቤትነት ለማስተዳደር የረጅም ግዜ ህልሜን አሳክቻለሁ ብለዋል፡፡
ክለቦች  ያሏቸው ቢሊዬነሮችና የሃብታቸው ደረጃ
በዓለም ታዋቂ የእግር ኳስ ክለብ ባለቤቶችና አክሲዮን ድርሻ ያላቸውን ባለሃብቶች ያላቸውን የሃብት ግምት በማስላት እስከ 20ኛ ደረጃ ያወጣላቸው “ዌልዝ ኤክስ” የተባለ የመረጃ ተቋም  ነው፡፡ እንደ ዌልዝ ኤክስ መረጃ  በተለይ በአውሮፓ ታላላቅ ሊጐችና በአሜሪካ ሜጀር ሶከር  ሊግ በሚወዳደሩ ክለቦች ሙሉ  ባለቤትነትና ከፍተኛ አክሲዮን ድርሻ  ያላቸው ቢሊዬነሮች ሃብት የተመዘገበላቸው ከፍተኛው 73 ዝቅተኛው 5 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ በአጠቃላይ የሃብታቸው ግምት ወደ 290 ቢሊዮን ዶላር ይጠጋል፡፡ ዌልዝ ኤክስ በክለብ ባለቤት ቢሊዬነሮች ላይ በሰራው ደረጃ መሰረት እስከ 20ኛ  11 የተለያዩ አገራት ዜጋ ቢሊዬነሮች ተካትተዋል፡፡ በአጠቃላይ የሃብታቸው ግምት ወደ 290 ቢሊዮን ዶላር ይጠጋል፡፡ ከ1 እስከ አምስት ደረጃ የሚሰጣቸው ቢሊዬነሮች የክለብ ባለቤቶች  የሚከተሉት ናቸው፡፡ ዌልዝ ኤክስ በሃብት ግምት እና መረጃ የታወቀ ተቀማጭነቱን በሲንጋፖር ያደረገና በአምስቱም አህጉራት የሚንቀሳቀሰ ተቋም ነው፡፡
1.ካርሎስ ስሊም
የሃብት ግምት — 73 ቢሊዮን ዶላር
በሶስት ክለቦች የአክሲዮን ድርሻ አላቸው ሁለቱ ፓችዋ እና ሌዎን የተባሉ የሜክሲኮ ክለቦች ሲሆኑ አንደኛው ደግሞ የስፔኑ ክለብ ሪያል ኦቪዬዶ ነው፡፡
ሜክሲኳዊ የቴሎኮም ኢንቨስተር ካርሎስ ስሊም 74 ዓመታቸው ሲሆን ከ2010 እኤአ ጀምሮ የዓለም ሃብታሞችን ደረጃ በየዓመቱ በአንደኝነት እየመሩ ናቸው፡፡ ግሩፖ ካርሶ በተባለ ግዙፍ ኩባንያቸው በቴሌኮም፤ በሪል ስቴት፤ በአየር መንገድ፤ በሚድያ፤ ቤክኖሎጂ እና በፋይናንስ ኢንቨስትመንታቸው በበርካታ የሜክሲኮ ኩባንያዎች ከፍተኛ ድርሻ አላቸው፡፡ በተለይ በ49 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል የሚንቀሳቀሰው አሜሪካ ሞቪል የላቲን አሜሪካ ግዙፉ የቴልኮም ኩባንያ ነው፡፡
2.አማንስዮ ኦርቴጋ
የሃብት ግምት 65.6 ቢሊዮን ዶላር
ክለብ ዲፖርቲቮ ላካሩኛ
ኢንድቴክስ ግሩፕ የተባለ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ኩባንያን በፕሬዝዳንትነት የሚያስተዳድሩት የ78 ዓመቱ አማንስዮ ኦርቴጋ በስፔን እና በዓለም አቀፍ የፋሽን ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ዝና ያላቸው በሃብታቸው ግምት በዓለም ሶስተኛ ዴጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ አመንስዮ ኦርቴጋ በዲፖርቲቮ ላካሩኛ ክለብ ባለቤትነት ለየት የሚያደርጋቸው እያንዳንዱን የክለቡ ጨዋታ ከክለቡ ቀንደኛ ደጋፊዎች ጋር በመመልከት ዝነኛ መሆናቸው ነው፡፡
3. አሊሸር ኡስማኖቭ
የሃብት ግምት 18.6
ክለብ አርሰናል
ራሽያዊው  በማእድን ቁፈራ እና በብረታብረት ኢንዱስትሪ በሚንቀሳቀስ ኩባንያቸው የናጠጡ ሃብታም ለመሆን የበቁ ናቸው። አሊሸር ኡስማኖቭ በታዋቂው ሲልከን ቫሊ ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ አላቸው፡፡ ኡስማኖቭ በ2007 እኤአ ላይ በሰሜን ለነድኑ ክለብ አርሰናል 17 በመቶ ድርሻ በመግዛት ክለቡን ሲደግፉት ቆይተዋል፡፡
4.ጆርጅ ሶሮስ
የሃብት ግምት 19.6 ቢሊዮን ዶላር
ክለብ ማንችስተር ዩናይትድ
አሜሪካዊ ነጋዴ ጆርጅ ሶሮስ በማንችስተር ዩናይትድ ክለብ 7.85 በመቶ ከፍተኛው የአክሲዮን ድርሻ አላቸው፡፡ በኦልድትራፎርዱ ክለብ ኢንቨስት ያደረጉት ሶሮስ ፈንድ ማኔጅመንት በተባለ ኩባንያቸው ነው፡፡
5. ፖል አለን
የሃብት ግምት 15 ቢሊዮን ዶላር
ክለብ ሲያትል ሳውንድረስ  
አሜሪካዊ ነጋዴ ፖል አለን ታላቁን የማይክሮሶፍት ኩባንያ ከመሰረቱ ባለሃብቶች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ህንዳዊው ላክሺም ሚታል በ15 ቢሊዮን ዶላር በኪውንስ ፓርክ ሬንጀርስ፤ ሪህና አኬሜቶቭ በ15 ቢሊዮን ዶላር በዩክሬን ሊግ በሚወዳደረው ሻካታር ዶንቴስክ፤ ፈረንሳዊው ፍራንኮይስ ሄነሪ ፒናልት በ14 ቢሊዮን ዶላር በሊግ 1 በሚወዳደረው ስታድ ዲ ሬኔስ፣ ራሽያዊው ሮማን አብራሞቪች በ12 ቢሊዮን ዶላር በቼልሲ እንዲሁም ጆን ፍሬድክሰን በ12 ቢሊዮን ዶላር በኖርዌይ ሊግ በሚወዳደረው ቫሌሬንጋ  ክለብ እስከ 10 ያለውን ደረጃ ወስደዋል፡፡  እስከ 20ኛ ባለው ደረጃ የሞናኮ ክለብ ባለቤት ራሽያዊው ዲምትሪ ራይቦሎቬሌቭ በ10 ቢሊዮን ዶላር ፤ የኤሲሚላን  ክለብ ባለቤት ሲልቭዮ በርልስኮኒ በ7 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም የማንችስተር ሲቲው ሼክ መንሱር ቢንዘየድ በ7 ቢሊዮን ዶላር ከ12 እስከ 15ኛ ደረጃ ሲሰጣቸው፤ በአርሰናል ክለብ 38 በመቶ ድርሻ ያላቸው አሜሪካዊ ቢሊዬነር ስታን ክሮንኬ በ4 ቢሊዮን ዶላር 19ኛ ደረጃ አላቸው፡፡


Read 2835 times