Print this page
Saturday, 16 August 2014 10:52

ከ“ጐጆ እቁብ” ጠንሳሽ ጋር የተደረገ ቃለምልልስ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

በቅርቡ የተመሰረተውና 100ሺ አባላት እንደሚኖሩት የተነገረለት
“ጐጆ እቁብ”፤ የአባላት ምዝገባ የጀመረ ሲሆን በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥም
12ሺ አባላት እንደተመዘገቡ የሃሳቡ ጠንሳሽና የድርጅቱ መስራች አቶ ናደው ጌታሁን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ የእቁቡ ባህሪና አሰራር ምን ይመስላል? ከባህላዊው ዕቁብ በምን ይለያል? የዕጣ አወጣጡ እንዴት ነው? የባንኮች ሚናስ ምንድነው? አባላት እንዴት ያምኑታል? እና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን ጋዜጠኛ አለማየሁ ለአቶ ናደው ጌታሁን አቅርቦላቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

“ጎጆ እቁብ” ሃሳቡ እንዴትና መቼ ተጠነሰሰ?
ከዚህ በፊት ማርኬቲንግ ላይ ብዙ ስራ እሰራ ነበር፡፡ በዚህ ስራ ውስጥ እያለሁ እንዴት ነው ብዙ ማህበረሰብ ጠቅመን ራሳችንን ተጠቃሚ የምናደርገው የሚለውን ስመራመር ነበር፡፡ ለረጅም አመታት በዚህ ሀሳብ ውስጥ ቆይቻለሁ፡፡ በወቅቱም የተለያዩ ፕሮፖዛሎችን ሰርቻለሁ፡፡ ዋነኛ ትኩረቴ የነበረው ባህላዊ የእቁብ ስርአታችን ላይ ነው። አሁን ያለውን እቁብ ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር ይቻላል የሚለው ሃሳብ ይበልጥ እየጎላ መጣ፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ሰፊ አቅምና የአስተዳደር ክህሎት ይጠይቃል፡፡ መጀመሪያ ያሰብነው ማን ነው ገንዘቡን የሚሰበስበው? የሚለውን ነው፡፡ ለዚህ ስራ ባንኮችን አመቻቸን፡፡ የመጀመሪያ ተመራጭ ያደረግነው ንግድ ባንክን ነው፡፡ ህጋዊ መሰረት የለውም ልንከፍት አንችልም የሚል ነገር መጣ፡፡ በኋላ ለባንኩ ሃላፊዎች በደንብ አስረዳኋቸው፡፡ ሃሳቤን ተቀበሉኝ እነሱ የእቁቡ ድልድይ ሆነው እንዲሰሩ አደረግናቸው፡፡ ይሄ “ብሬን ተበላሁ” ከሚለው አቤቱታና ሃሜት ነፃ ያደርገናል፡፡ በዚህ መሰረት እቁቡ ይፋ ተደረገ፡፡
እስቲ የእቁቡን ባህሪና አሰራር በዝርዝር ያስረዱን?
አንድ አባል በየወሩ 350 ብር ይከፍላል። በ90 ወር ወይም በ7 ዓመት ከ5 ወር 31,500 ብር ያጠራቅማል ማለት ነው፡፡ 350 ብር ከፍሎ መጀመሪያ የሚወጣው እጣ ተጋሪ ከሆነ በምርጫው ተሽከርካሪ፣ ቤት ወይም ሌሎች ንብረቶች ተገዝተው ይሰጡታል፡፡ ለምሳሌ መኪና ከወሰደ በመኪናው እየሰራ ይከፍላል፤ ቤትም ከደረሰው አከራይቶ ይከፍላል፡፡ እጣው የደረሰው ሰው 350 ብር መክፈል አቁሞ የንብረቱን ዋጋ ለ5 ወይም ለ6 ዓመት በየወሩ ይከፍላል፡፡ ሰርቶ ብሩን መመለስ እንደማለት ነው። ወለድ የለውም፤ የንብረቱን ዋጋ ብቻ ይከፍላል፡፡
እቁብተኛው መሃል ላይ እያቆመ (ቁጥሩ ቀንሶ) የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ቢቀሩስ እንዴት ይሆናል?
ብዙ ሰው ሊያቋርጥ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ በየወሩ 1ሺህ ሰው ቢያቋርጥ እንኳ የመጀመሪያዎቹ ባለዕጣዎች በንብረታቸው እየሰሩ የብዙዎችን 350 ብር መክፈል ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ታክሲ የደረሰው 4ሺህ ብር በወር ሊከፍል ይችላል፡፡ ብዙዎች ባለንብረት በሆኑ ቁጥር የእቁቡ አቅም እየተጠናከረ ይሄዳል፡፡ ምክንያቱም ባገኙት ንብረት ሰርተው 350 ብር መክፈል ያቆሙና የንብረቱን ዋጋ በወር ተተምኖላቸው መክፈል ይጀምራሉ፡፡ ንብረቱ የ1 ሚሊዮን ብር እቃ ከሆነ፣ እንዴት ሰርቶ ያገኝበታል የሚለው ተሰልቶ እንዲከፍል ይደረጋል፡፡ እቁቡን የሚያፈጥነውም የመጀመሪያዎቹ ባለዕጣዎች ከፍተኛ ከፋይ መሆናቸው ነው፡፡ በመጀመሪያው 40 ሰዎች ባለዕድል ይሆናሉ፤ ቀጥሎ 45፣100፣200 እያለ ይሄዳል፡፡ ባለንብረቱ እየጨመረ ሲሄድ፣ የእቁቡ የገንዘብ መጠንና አቅም እየተጠናከረና እየበዛ ይሄዳል፡፡ እኛ 100 ሺህ ሰው ባለንብረት ስናደርግ ስራ ነው የፈጠርንለት ብለን እናምናለን፡፡
ንብረቱ የሚገዛው በባለዕጣው ፍላጎት ነው?
አዎ! ሰውየው በመረጠው ነው የሚገዛለት፡፡ ጎጆ እቁብ ሙሉ ክፍያውን ፈፅሞ ግለሰቡ መኪናም ሆነ ቤት የመረጠው ተገዝቶ ይሰጠዋል፡፡ ንብረቱን እየሰራበት እዳውን ይከፍላል፡፡ መኖሪያ ቤት ሲሆን ከጠቅላላ የቤቱ ዋጋ ላይ መጀመሪያ ባለዕጣው አንድ ሶስተኛውን ይከፍላል፤ ሁለት ሶስተኛውን በሂደት ይከፍላል፡፡
የእናንተ ሚና በዚህ መሃል ምንድን ነው?
የኛ ኃላፊነት ሂደቱን መቆጣጠር ነው፣ ድልድይ መሆን ነው፤
አንድ ባለዕድል በመጀመሪያው ዙር በወጣ ዕጣ የንብረት ተጋሪ ሆኖ ቢወሰርስ? ወይም ንብረቱን ሙሉ ለሙሉ ቢሸጥና ቢጠፋስ… እንዴት ትቆጣጠራላችሁ?
አንድ ሰው ባለዕድል ሲሆን ንብረቱን ዝም ብለን አንሰጥም፤ መኪና ከሆነ ሊብሬው ይያዛል፣ ሌላውም በተመሳሳይ መያዣ ይኖረዋል፡፡ እኛ የህግ ክፍል አለን፡፡ ውል የምንዋዋልበት፣ ንብረት እንዲገዙና ለባለዕድል እንዲሰጡ የሚያደርግ፡፡ በሱ በኩል ቁጥጥርና ክትትል ይደረጋል፡፡ ንብረቱ ሙሉ ኢንሹራንስ ይገባለታል፡፡ ንብረት በትኖ ይሸጣል የሚል ጥያቄ ይነሳል፤ ይህ እንዳይሆን ሚስጢራዊ በሆነ መልኩ መረጃዎች ይሰበሰባሉ፡፡ ለወደፊት የምንፈጥራቸው ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የማናጅመንት ዲፓርትመንቶች አሉ፡፡
የእቁቡ አባል በመሃል በሞት ቢለይስ?
መተዳደሪያ ደንቡ ላይ በግልፅ ተቀምጧል። ህጋዊ ወራሾቹ እንዲቀጥሉበት ይደረጋል፡፡ በፍርድ ቤት ስለወራሽነታቸው ይረጋገጥና ቀጥታ ይጀምራሉ።
የእናንተ ትርፍ ምንድን ነው?
ከ350 ብሩ ላይ የአገልግሎት ተብሎ 50 ብር ይቀነሳል፡፡ ከ50 ብሩ ላይ መንግስት 30 በመቶ ይወስዳል፡፡ ከ5 ሚሊዮን ብር ላይ 1.5 ሚሊዮን ብር በየወሩ ያገኛል ማለት ነው፡፡ ቀሪውን አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በኮሚሽን መልክ ይከፋፈሉታል። የኛ ትርፍ ከ50 ብሩ ላይ 5 ብር አካባቢ ነው፡፡ መንግስት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ነው የምንለው። ምክንቱም አሁን ባለው ሁኔታ ለመንግስት በየወሩ 1.5 ሚሊዮን ብር ታክስ የሚያስገባ ተቋም ያለ አይመስለኝም፡፡ ከዚያም ሲያልፍ 100 ሺህ ሰዎች ባለንብረት ሆነው ከፍተኛ ታክስ ከፋይ እንዲሆኑ የሚያደርግ አሰራር ነው፡፡ ባንኮችም ተጠቃሚ ናቸው፡፡ እኛ ከንብረት አቅራቢዎች3 በመቶ ኮሚሽን እናገኛለን፡፡
ማሽነሪና ተሽከርካሪ አቅራቢ ኩባንያዎች ከናንተ ጋር በድንገት ውላቸውን ቢያቋርጡ ምን አማራጭ አላችሁ?
ለ90 ወር የሚያገለግል ስምምነት ከዋይኤችኤ ጋር ተፈራርመናል፡፡ እቃዎችን በጊዜ እና በተፈላጊው ሰዓት እንዲያቀርብ ነው ስምምነት የተፈራረምነው። እነዚህ ድርጅቶች ውላቸውን ያቋርጣሉ ማለት የማይታሰብ ነው፡፡ ለነሱም ገቢያቸው ነው፡፡
የተለየ የዋጋ ቅናሽ ያደርጉላችኋል?
ለህዝቡ መቀነስ አለባቸው፡፡ እንደምርጫው ሁሉ ዋጋ ላይ የሚደረገው ድርድርም በባለዕድለኛው እና በሻጩ ኩባንያ መካከል ይሆናል፡፡ እኛ ክፍያውን መፈፀም ነው ስራችን፡፡
ሰው እንዴት ነው እናንተን ሊያምን የሚችለው?
ጥያቄው… እኔ ነኝ አንተን ማመን ያለብኝ ወይንስ አንተ ነህ እኔን ማመን ያለብህ የሚለው ጥርት ብሎ መቀመጥ አለበት፡፡ እቁብን የሚዳኘው ህግ ነው፡፡ ለዚያ ተገቢው መተዳደርያ ደንብ አለ፤ ያንን ፈርሞ ይገባል፡፡ ባለንብረት ሲሆን ክፍያ አልተጠየቀም፤ ለወደፊት ሰርተህ ትከፍላለህ ነው የተባለው፡፡ ታዲያ ማን ነው መታመን ያለበትን? በግልፅ የምናገረው አንድ ሰው ውስጡ የተደበቀ መጥፎ አስተሳሰብና ባህሪውን ትቶ ነው ወደ ጎጆ መምጣት ያለበት። እሱ 350 ብር ሰጥቶ የ3 ሚሊየን ብር ንብረት ነው የሚረከበው፤ ስለዚህ መፍራት ያለብኝ እኔ ነኝ ማለት ነው፡፡ በመሃል ባንኮች እንዳሉበትም መርሳት አያስፈልግም፡፡
የተመዝጋቢው መረጃ የት ነው የሚቀመጠው?
አንድ ሰው አባል ሆኖ ሲመዘገብ ፎቶግራፍ፣ የተዋዋልንበት ውል ይኖራል፡፡ በጎጆ እቁብ ዌብሳይት ላይ የግለሰቡ መረጃ ይለቀቃል” እጣ አውጪው “ሲምቦል” ቢሮና እኛ ቢሮ ይቀመጣል፡፡ እንዲሁም ገንዘቡ ተቀማጭ የሚደረግበት ባንክ ጋም ይቀመጣል፡፡ ባንኩም ክፍያ የሚፈፅመው በዚያ መሰረት ነው፡፡ እኛ ከ50 ብሩ የአገልግሎት ተቆራጭ ውጪ ከገንዘቡ ጋር የምንነካካበት እድል የለንም፡፡
የባንክ ሂሳቡን ማን ነው ሊያንቀሳቅስ የሚችለው?
ሂሳቡ ዝግ ሆኖ ነው የሚቀመጠው፡፡ ነገር ግን ክፍያ እንዲፈጸም የሚያዙት ዳኛው አቶ ናደው ጌታሁን፣ ፀሐፊው ስነ ግርማ እንዲሁም የገንዘብና ሰነድ ያዥ ሹሙ ገዛኸኝ እርቄ ይሆናሉ፡፡ ከሶስቱ ውጪ ማንም አያንቀሳቅስም፡፡ ግልፅ እንዲሆን የምንፈልገው ሶስቱ ገንዘቡን ያንቀሳቅሳሉ ሲባል በራሳቸው ማውጣት አይችሉም፡፡ ማድረግ የሚችሉት፤ ለባለዕጣው ክፍያ ይፈፀምለት ብለው ለባንኩ ደብዳቤ መፃፍ ብቻ ነው፡፡ ባለዕጣውን የሚለየው ደግሞ ሌላ አካል ነው፡፡ እኛ ከ50 ብሩ ውጪ ከሌላው ገንዘብ ጋር አንገናኝም፡፡ በየወሩ ለማን ተከፈለ የሚለውንም አባላት መጠየቅ ያለባቸው ባንኮችን ይሆናል፡፡
አንድ ሰው በመሃል ቢያቋርጥ ገንዘቡ በስንት ጊዜ ውስጥ ተመላሽ ይሆናል?
የአገልግሎት በየወሩ 50 ብሩ ተቆርጦበት በ15 ቀን ውስጥ ይመለስለታል፡፡
እቁቡ  የእጣ ባህሪ አለውና ከብሄራዊ ሎተሪ ፍቃድ አግኝታችኋል?
ከብሄራዊ ሎተሪ ጋር ተነጋግረንበታል፡፡ ትምህርትም ሰጥቻቸዋለሁ፤ ፍቃድ ክፍሉንም አነጋግረናል፡፡ የእቁቡን እጣ በየወሩ አውጡልን ብዬ ጠይቄያቸዋለሁ ግን ፍቃድ ያስፈልጋችኋል አሉን፡፡ እንዴት ነው ለዚህ ፍቃድ የሚወጣው? ሎተሪ እድል ነው፣ ይሄ የወረፋ እጣ ነው፡፡ ከሎተሪ እድል ጋር አይገናኝም፡፡ በኋላ ላይ በኮምፒውተር በራሳችሁ ማውጣት ትችላላችሁ አሉን፡፡ በደብዳቤ አረጋግጡልን አልናቸው፤ እነሱም “እንዲህ ያለው የእጣ አወጣጥን የተመለከተ ጉዳይ በደንባችን ላይ የለም” ብለው በደብዳቤ አረጋገጠውልናል፤ ስለዚህ አይመለከታቸውም ማለት ነው፡፡
እቁቡ እውቅና ያለው ተቋም ነው?
እቁብ ተቋም ሊሆን አይችልም፡፡ ሰዎች በጋራ መግባባት በመተዳደሪያ ደንብ ተማምነው፤ ገንዘባቸውን ቁም ነገር ላይ የሚያውሉበት ነው፡፡ የኛም አሰራር እንደዚያ ነው፡፡
ምናልባት እቁቡ በሆነ ምክንያት ቢሰናከልስ ምንድን ነው የተቀመጠው አማራጭ?
መቶ በመቶ እንደማይሰናከል እርግጠኞች ነን። ቢሰናከል እንኳ እያንዳንዱን ገንዘብ ለባለቤቱ ተመላሽ ያደርጋል፡፡
የእውቅና ጉዳይስ እንዴት ነው አግኝታችኋል?
በመሰረቱ እውቅናችን መሬት የወረደው ውላችን ነው፡፡ የምንዳኘውም በዚህ መተዳደሪያ ደንብና ውል ነው፡፡ እንፈራረማለን፡፡ ውሉን ያፈረሰ በህግ ይጠየቃል መክሰስ የፈለገም በዚህ ደንብ መሰረት ሊጠይቅ ይችላል፡፡
የተመዝጋቢው ቁጥር ስንት ደረሰ?
በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ 12ሺህ ያህል ያለ ምንም የማስታወቂያ ስራ ልንመዘግብ ችለናል፡፡ አሁንም በከፍተኛ ደረጃ ምዝገባው ቀጥሏል፡፡
መቼ ነው የመጀመሪያው እጣ የሚወጣው?
100ሺህ አባላት እንደተመዘገቡ እናወጣለን የሚል እቅድ ነው የያዝነው፡፡ ነገር ግን 100 ሺህ ባይሞላም ማውጣታችን አይቀርም፡፡ በዚህ መሰረት እስከ መስከረም 16 የመጀመሪዎቹ ባለዕጣዎች ይለያሉ ብለን እናስባለን፡፡ 

Read 3508 times