Saturday, 16 August 2014 10:48

በአፍ የሚወሰዱ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎችና አጠቃቀማቸው

Written by 
Rate this item
(69 votes)

    የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች ሴቶች እርግዝናን ለመከላከል በየቀኑ የሚወስዷቸው የመድኃኒት ዓይነቶች ናቸው፡፡ እነዚህ መድኀኒቶች አንዳንድ ጊዜ “ኪኒን” ወይም በአፍ የሚወሰዱ የወሊድ መከላከያ ተብለው ይጠራሉ፡፡
የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች እንዴት እንደሚሰሩ ብዙ ሰዎችን ማደናገሩ የተለመደ ነው፡፡ የዚህን ሚስጥር የሚያቀለው የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች የሚፈበረኩት ከሰውነት ንጥረ ነገሮች (ሆርሞኖች) መሆኑ ነው፡፡ ሆርሞኖች በሰውነታችን ውስጥ የሚፈጠሩ ኬሚካሎች ሲሆኑ  የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻችን እንዴት እንደሚሰሩ የሚቆጣጠሩ ናቸው፡፡
የተወሰኑ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች ኢስትሮጂንና ፕሮጀስቲን /Estrogene and Progestin/ የተባሉ ሁለት ዓይነት ሆርሞኖችን ይይዛሉ፡፡ እነዚህ እንክብሎች ቅልቅል /Combination/ እንክብሎች ሲባሉ ሌሎች ደግሞ ከፕሮጀስቲን ብቻ የተሰሩ እንክብሎች ተብለው ይጠራሉ፡፡ አብዛኛዎቹ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብል ወሳጅ ሴቶች ቅልቅል እንክብሎችን ይወስዳሉ፡፡
በእንክብሎቹ ውስጥ የሚገኙት ሆርሞኖች፣ በአንድ በኩል የሴቷ እንቁላሎች ኦቫሪን (እንቁላል መፈጠሪያ ቦታ)  ለቀው ወጥተው ከወንድ ዘር ፍሬ ጋር ተገናኝተው እርግዝና እንዳይፈጠር /ከኦቫሪ እንዳይወጡ/ የሚያደርጉ ሲሆን በሌላ በኩል የማህፀን ጫፍ እንዲወፍር በማድረግ የወንድ የዘር ፍሬ ወደ እንቁላሎች ዘልቆ እንዳይገባ እንዲከላከል ያደርጋሉ፡፡
በአፍ የሚወሰዱ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች ጠቀሜታዎች
የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎችን መውሰድ ቀላል፤ ዘጠና በመቶ ያህል አስተማማኝና ተስማሚ ነው፡፡ የግብረ ስጋ ግንኙነት ለማድረግ ችግር ካለመፍጠሩም በላይ አንዳንድ ሴቶች በፈለጉ ጊዜ ወሲብ ለመፈፀም በመቻላቸው የወሲብ ህይወታቸውን እንደሚያሻሽልላቸው ይናገራሉ፡፡
የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች የሚያስገኙትን ተጨማሪ ጥቅሞች ለማግኘት ሲሉ ወሊድን መቆጣጠር የማይፈልጉ ሴቶች ጭምር እንክብሎቹን ይወስዳሉ፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱም ዓይነት የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች የወር አበባ በሚመጣበት ጊዜ የሚኖረውን ህመም ከማቅለላቸውም ሌላ የሚኖረውን ፈሳሽ እንዲቀንስ ያደርጋሉ፡፡
ቅልቅል እንክብሎች ተጨማሪ ጥቅሞች ይሰጣሉ
ብጉርን፣ የአጥንት መሳሳትን፣ ካንሰር ያልሆነ የጡት ማደግ፣ ከማህፀን ውጭ እርግዝናን፣ የማህፀን ካንሰርንና ሌሎች ኢንፌክሽኖችን እንዲሁም ከብረት ማዕድን ማነስ የሚመጣ የደም ማነስን በመከላከል በኩል ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ፡፡
እንክብሎችን እንዴት መውሰድ አለብን?
በአፍ የሚወሰድ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች በአንድ ማሸጊያ (Pack) ውስጥ በባለ 21፣28፣91 እንክብሎች ሊይዝ ይችላል፡፡ እነዚህን እንክብሎች ሃኪሙ ወይም የመድኀኒት ባለሙያው ባዘዘን መሰረት ብቻ መውሰድ አለብን፡፡ በትክክል ቀስቱ እንደሚያሳየንና በተጨማሪም በተጀመረው ሰዓት ብቻ ሁሌ ልንወስድ ይገባል፡፡ አብልጦ ወይም አሳንሶ መውሰድ አይቻልም፡፡ የማቅለሽለሽ ባህሪይ ስላላቸው ከወተት ወይም ከምግብ ጋር መውሰድ ይቻላል፡፡
በማሸጊያው ውስጥ 21 እንክብሎች የያዘ ከሆነ፣ በቀን 1 ፍሬ ለ21 ቀን፣ ከዚያ 7 ቀን ሳንወስድ ልክ ከ7 ቀን በኋላ አዲስ እንጀምራለን፡፡
በማሸጊው ውስጥ 28 ፍሬ ካለ፣ በቀን 1 ፍሬ ለ 28 ቀን በትክክል በቀስቱ መሰረት መውሰድ፤ ከዚያ አዲስ መጀመር፡፡
በማሸጊያው ውስት 91 ፍሬ ካለ፣ እስኪያልቅ አንድ ፍሬ ለ91 ቀን መውሰድ ያስፈልጋል፡፡
በአፍ የሚወሰዱ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች በሚወሰድበት ጊዜ የማስታወክ ወይም የማስቀመጥ ምልክት ካለ ለሃኪም በመደወል ወይም በአካል በመሄድ ማማከር ያስፈልጋል፡፡  ሃኪም ሳያማክሩ የወሊድ መከላከያ እንክብል በፍፁም ማቆም አይቻልም፡፡
የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች ከመውሰድ በፊት መደረግ የሚገባው ጥንቃቄ
ለእነዚህ እንክብሎች ወይም ለሌላ መድኃኒት የሰውነት መቆጣት (Allergic) ለሃኪም ወይም ለመድኀኒት ባለሙያ ካለ መንገር፡፡
ከዚህ በፊት የእግር ማበጥ፣ የሳንባ ወይም፣ የአይን ችግር ካለ ለሃኪም መንገር ያስፈልጋል፡፡
በቤተሰብ ውስጥ በጡት ካንሰር የተያዘ ካለ ሃኪሙን ማማከር አለብን፡፡
ነፍሰጡር ከሆኑ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብል በፍፁም መውሰድ የለብዎትም፡፡
የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብል ሲወስዱ መዘለል የለበትም፤ ከተዘለለ ለሃኪም ማሳወቅ ይገባል፡፡
የቀዶ ጥገና ህክምና ካለዎት ለሀኪም ወይም ለመድኀኒት ባለሙያ መንገር ይኖርብዎታል፡፡
የአመጋገብ ስርአት ጥንቃቄ
በሃኪም ካልተነገረ በስተቀር የተለመደው የአመጋገብ ሥርአት መቀጠል አለበት፡፡
የጎንዮሽ ጉዳቶች
የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች የሚወስዱ አንዳንድ ሴቶች ያልተፈለገ የጎንዮሽ ጉዳት ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ በርካታ ሴቶች ግን ትንሽ ወይም ምንም ችግር ሳያጋጥማቸው ከእንክብሎች ጋር ይላመዳሉ፡፡ በርካታዎቹ የሚያጋጥሙ ችግሮች በሁለት ወይም በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ይስተካከላሉ፡፡ ከሚያጋጥሙ ችግሮች ውስጥ በሁለት ተከታታይ የወር አበባ ጊዜያት መካከል የደም መፍሰስ፣ የጡት እብጠት፣ ማቅለሽለሽና ማስታወክ ይጠቀሳሉ፡፡
የማቅለሽለሽና የማስታወክ ችግሩን ለመቅረፍ እንክብሎቹን በምሽት ወይም በመኝታ ሰዓት መውሰድ ይመከራል፡፡ ይሁን እንጂ እንክብሎች አለመውሰድ አይመከርም፡፡ ምክንያቱም እንክብሎቹን ካልወሰዱ ለእርግዝና ያጋልጣልና ውስጥዎ እረፍት አይሰማውም፡፡ በተለይ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ችግሮች ካሉ ህክምና ከሚሰጥዎት ባለሙያ ጋር በግልጽ ይነጋገሩ፡፡
እድሜዎ 35 እና ከዚያ በላይ ከሆነ፣
ከመጠን በላይ ክብደት ካለዎት፣
በዘር የሚተላለፍ የደም መርጋት ችግር፣
የስኳር ህመም፣
ከፍተኛ የደም ግፊት፣
ከፍተኛ የስብ ክምችት፣
ረጅም የአልጋ ላይ እረፍት የሚፈልጉ ከሆነ እና ሲጋራ የሚያጨሱ ከሆነ … ከላይ ለተጠቀሱት ችግሮ የመጋለጥ እድልዎ ይጨምራል፡፡
እንክብሉ ሳይወሰድ ቢቀር ምን መደረግ አለበት?
ከሞላ ጎደል እንክብል በመውሰድ ላይ ያሉ ሴቶች ሁሉ በአንድ ወቅት ይዘነጋሉ፡፡ እንክብሉን በየትክክለኛው ሰዓት መውሰድን በጥሩ ሁኔታ እንዲሰራ ያደርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ በሰዓቱ መውሰዱነ ቢዘነጉ ምን ማድረግ እንዳለብዎት ማወቅ ከማርገዝ ያድንዎታል፡፡
በሰዓቱ መውሰድ አይዘንጉ
ወዲያዉኑ እንዳስታወሱ እንክብሉን ይዋጡ
የሚቀጥለውን እንክብል በመደበኛ መዋጫ ጊዜው ይዋጡ
ሌሎች እንክብሎችን ቀደም ብለው ባስቀመጡት ፕሮግራም መሰረት መዋጥ ይቀጥሉ፡፡ የኋለኛውን እንክብል ከዋጡ እስከ 48 ሰዓት ያህል ተጨማሪ የወሊድ መከላከያ ዘዴን ጨምረው ይጠቀሙ፡፡ አንዳንዶቹ ተጨማሪ የወሊድ መከላከያ ዘዴዎች የወንድ ኮንዶም፣ የሴት ኮንዶምና ወይም ድንገተኛ የወሊድ የመከላከያ ናቸው፡፡ እንክብል መዋጥዎን ሳያስታውሱ ጥንቅቄ የጎደለው የግብረ ስጋ ግንኙነት አድርገው ከሆነ፣ ድንገተኛ የወሊድ መከላከያ መጠቀም እጅግ ተመራጭ የመከላከያ ዘዴ ነው፡፡
ምንም እንኳን ተጨማሪ የመካላከያ ዘዴዎችን ዘግይተው ቢጠቀሙም በርካታ ሴቶች እንክብል መዋጥ ሲዘነጉ መጠነኛ የደም መፍሰስ ያጋጥማቸዋል። አንዳንድ ሴቶች ሁለት እንክብሎችን በአንድ ቀን ሲወስዱ ሆዳቸውን ያማቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ማቅለሽለሹ ብዙ የሚቆይ ስላልሆነ አይጨነቁ።
አንዳንድ ጠቃሚ ምክሮች
እንክብሎችን በየቀኑ በተመሳሳይ ሰዓት መውሰድ ይበልጥ ውጤታማ ያደርጋል፡፡ ስለሆነም ሊያስታውሱት የሚችሉትን ጊዜ ለይተው ይምረጡ። ለዚህ እንዲረዳዎት ሁልጊዜ የሚያከናውኑትን ስራ መስሪያ ጊዜ፣ ለምሳሌ ጥርስዎን የሚቦርሹበት ወይም እራትዎን የሚመገቡበት ሰዓት ቢሆን ይመረጣል። በርካታ ሴቶች በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ወይም በሰዓታቸው ላይ የማስታወሻ ደውል ይሞላሉ፡፡
የታለፈ ወይም የተዘለለ የወር አበባ ማለት አርግዘዋል ማለት አይደለም፡፡ በተለይ የዘለሉት እንክብል ከሌለ፡፡ ምንም እንኳን የማርገዝ እድልዎ በጣም ዝቅተኛ ቢሆንም ለሁለት ተከታታይ ጊዜያት የወር አበባዎት ካልመጣ የእርግዝና ምርመራ ማድረግ ይገባዎታል፡፡
ስለወሊድ መቆጣጠሪያ አጠቃቀምም ሆነ ስለሚሰማዎት ችግር ህክምና ከሚሰጥዎት ባለሙያ ጋር በግልጽ ይነጋገሩ፡፡
መቼ መጀመር አለበት?
እርግዝናን ለመቆጣጠር ትክክለኛው መንገድ የወር አበባ በመጣ እስከ አምስተኛው ቀን መጀመር ነው፡፡ ሌላ የወሊድ መቆጣጠሪያ መቀየር ቢያስፈልግዎ አሁንም የወር አበባ ጊዜን መጠበቅ አይርሱ፡፡
የት መቀመጥ አለበት?
በሃኪም የታዘዘልዎት የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብል የጤና ባለሙያ ይቀመጥ ባልዎት ቦታ ማለትም እርጥበት በሌለው ደረቅ ቦታና ህፃናት በማይደርሱበት ሥፍራ ከሌላ መድኀኒት ጋር ሳይቀላቀል ቢቀመጥ ጥሩ ነው፡፡
ማጣቀሻ
www.acwww.nlm.nih.gov/medlneplus/druginfo/meds/a601050.html
www.plannedparenthood.org/healt
www.fad gov.com
የፅሁፉ አቅራቢ (የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና
ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን)     

Read 48333 times